Saturday, 21 October 2017 13:29

‹‹እመን እንጂ አትፍራ››

Written by  ደረጀ ኅብስቱ derejehibistu@gmail.com
Rate this item
(4 votes)

   ስምምነትን፣ አንድነትን፣ አለመፈረካከስን፣ አለመበጣጠስን፣ ማመንጨት የሚችል፤ እና የሁሉ ነገር አስገኝ ምክንያት መሆን የሚችል አንድ ፈጣሪ ብቻ ነው። እራሱ በራሱ ኅልው ሆኖ ለሌሎች የመኖር ምክንያት መሆን የሚችል ማለት ነው። ህይወት ላለው ፍጥረት በሙሉ ህይወት መሆን የሚችል:: የልዕለ ደስታ፣ የልዕለ እውቀት፣ የልዕለ ህልውና  ምንጭ መሆን የሚችል ፈጣሪ ነው። በውስጣችን ስምምነት፣ አንድነት፣ አለመፈረካከስና አለመበጣበጥ ሲኖር ኅልው የሆነውን ፈጣሪን እንመስላለን፡፡ ይሄ ደግሞ የመልካሞች መልካምነትን ያቀዳጀናል፡፡
ከዚህ በተቃራኒ በህላዌ የእርከን ደረጃ፣ ሽቅብ ወደ ዋናው የአስገኝዎች ሁሉ አስገኝ ወደ ሆነው፣ ወደ ልዕለ ደስታ ፣ ወደ ልዕለ እውነት መድረስ ካልቻልን፣ የህላዌ ጎደሎነት አለብን ማለት ነው። ስለዚህም ደካማነት ስንኩልነትና ክፉነት ይጠናወቱናል። ክፋት ማለት የህላዌ ጎዶሎነት ማለት ነው። አንድ ነገር ደግሞ የህላዌ ጎደሎነት ከአለው ምንምነት ውስጥ ነው ያለ ማለት ነው። በራሱ ምንም ነው። ስለዚህ ክፋት ማለት በህልውና መዋቅር ውስጥ ዝቃጩ ማለት ነው። የራሱ ጥላ የሚያስደነግጠው፣ ከቀልቡ የተጣላ፣ ፍርሃት ህልውና የሆነው የዲያብሎስ ቁራጭ ነው ክፉ ሰው።
ሁሌም መልካም ማድረግ ነው አንድን ሰው፣ ሰው ሆኖ በሰውነት ማሰሪያ  አንድ አድርጎ ይዞ እንዳይፈረካከስ የሚጠብቀው እንጂ፤ የክፋት ውጤቱ መፈረካከስ ነው፤ ልጋግን አለመሰብሰብ ፣ መዝረክረክ፣ በቁም መፍረስ። የፍጥረት ሁሉ ዝቃጭ መሆን፣ ሞተንም ቀብራችን የማያምር (ለትውልድ ሁሉ መሰደቢያ)፣ ተቀብረንም መሬት የማትቀበለን መሆን ማለት ነው፤ ክፉ መሆን ማለት። ይሄው ነው እንግዲህ ይደርስብናል ብለን የምንፈራው ክፋት፤ የክፋትን ምንነት አብጠርጥሮ ያሳየናል። ክፉዎች ክፋትን ቢያደርጉብኝ፤ እነሱን ለመበቀል ብዬ የክፋት ምግባር ሰለባ መሆን የለብኝም፤ ምነው ቢሉ፣ ክፋትን እየሰሩ በህሊና ጸጸት ከመንደድ ይልቅ የእነሱን ክፋት በስጋ መሸከም ይቀላልና ነው። ይደርስብናል ብለን የምንፈራው ክፋት ከስጋችን አልፎ ህሊናችንን የሚያቆስል አይደለምና፤ ክፋትን ከመስራት ይልቅ የክፋት ተቀባይ መሆን እጅግ ይሻላል፡፡ ‹‹unlike charges attract each other›› እንዲል ሳይንሱ፤ መልካምነትን በተከተልን ቁጥር ክፋትም ከዙሪያችን አይለይም፡፡ አቅሙ ደካማ ስለሆነ ግን ጊዜያዊ እንቅፋቶችን ከመፍጠር ያለፈ ሊጎዳን አይችልም፡፡
“በችጋር ቀጥቼ ባሪያ አድርጌ እልካቸዋለሁ” የምትለዋ መንፈስ፤ ዛሬም ቢሆን ስትፈራገጥ እያየናት ነው፤ ቀባሪዎቿ መሆናችንን ግን ታሪክ ይመሰክራል። ስንቱን ቀብረን ፈውስ እንደምናገኝ ግን እርሱ አንድዬ ይወቀው።
ክፋትን በመልካምነት ነጽቶ መዋጋት ያስፈልጋል፤ ክፋትን በክፋት መመከት አይቻልም። ተያይዞ ዝቃጭ መሆን ነውና ፍጻሜው። መልካሙ መንፈስ “ሰው” ያስነሳል፣ የዲያብሎስንም ሴራ ይበጣጥሳል፤ ምነው ቢሉ ክፉ ሆኖ ክፋትን ማስወገድ አይቻልምና፡፡ የሌብነት ትልቅ ትንሽ የለውም፤ ሌባ ያው ሌባ ነው፤ ሙሰኛም ያው ሙሰኛ ነው እንጂ ትንሽ ሙስና እና ትልቅ ሙስና የሚባል ነገር የለም። እንኳን ማስፈራሪያና እስር፤ መተትና አጋንንት የማያስፈሩት ብርቱ መንፈስ መታጠቅ ያስፈልገናል፤ እራስን ከመንፈስ እስረኝነት ነጻ ለማውጣት።
እርሱ መኪና እያሽከረከረ ጫማ በቀየረ ጓደኛው የሚቀናን ሰው ምን ይሉታል? የክፋት ዛር ውላጅ ካልሆነ በስተቀር። ህዝብ ከበላ ከጠጣ፣ ኑሮም ከተመቸው ሥልጣኔን ይጋፋኛል የሚል ፖለቲከኛንስ ምን ይሉታል? የክፋት አለቃ፣ የዲያብሎስ ደቀ መዝሙር ካልሆነ በስተቀር። መለያየትን፣ መፍረስን የሚሰብኩ ሁሉ ከህላዌ ህግጋት ውጭ የሆኑ፣ ባዶነት የተሞሉና ስንኩል ፍጡራን ናቸው። እራሳቸውን መሸከም የማይችሉ፣ በሌሎች መንፈስ ላይ ተንጠላጥለው እራሳቸውን ከፍ ከፍ በማድረግ ጊዜያዊ መጽናኛ የሚማጸኑ ናቸው፡፡ የህላዌ መዋቅራችንም የተለያየ ነውና ቀንተው ቢንጨረጨሩ አይደለም ሊገሉንም ቢሞክሩ አይቻላቸውም፡፡ የመልካሞች መልካምነትን የተቀዳጀ ሰው፣ ከፈጣሪ ጋር አንድ ሆኗልና አይፈረካከስም፣ አይበጣጠስም፣ ውስጡ ስምሙ ነው እንጂ መለያየትን አያውቅም፡፡
እድል፣ እጣ ፈንታ እንዳይገዛን በደገኝነትና  በንጽህና ማበብ ይኖርብናል። ወደ ታችኛው የህላዌ መዋቅር፣ ወደ ዝቃጭነት በወረድን ቁጥር ከልዕለ መልካምነት እርቀናልና የእጣ ፈንታ መጫወቻ እንሆናለን። የመንፈስ ልዕልና ያስፈልገናል። ሌባ ሆኖ ሌብነትን ማውገዝ አይቻልም። ጨቋኝ ሆኖ ስለ ጭቆና መታገል፣ ማውራት አይቻልም። ሰዎችን ከመመዘናችን በፊት በያዝነው ሚዛን እራሳችንን መመዘን አለብን። በመልካምነት ባደግን ቁጥር ከልዕለ ደስታ፣ ከፍጻሜ እውነት፣ ከአንድዬ ጋር አንድ እየሆንን እንመጣለን እና የክፋትን ሰንሰለት በጣጥሰን ደስተኞች እንሆናለን።
ባላዋቂዎችና በሰነፎች መገዛት የእድል የእጣ ፋንታ ጉዳይ አይደለም፤ ህላዌ ከሚጠይቀው ከፍታ ባለመድረሳችን ነው፡፡ ክፉዎች የነገሱብን ከክፉዎቹ የተለየ የህላዌ መዋቅር ላይ ባለመድረሳችን ነው። በህላዌ መዋቅር ላይ እራሳችንን በመልካምነት፣ በትህትና፣ በንጽህና፣ በጠንካራ ሰብዕና ብንጠብቀው፣ ክፉዎች የኛ ተገዥ ይሆናሉ እንጂ እኛ የክፉዎች ተገዥ ባልሆንን ነበር፡፡
ኢትዮጵያን የመሰለ ሃገርና ኢትዮጵያዊ ጨዋነት ባህል እያለን ‹‹ጠብ ያለሽ በዳቦ›› የምንለምን ይመስል፤ አንዴ ግራ ዘመም አንዴ ቀኝ ዘመም፤ የባእድ ሸክም ይዘን እንንገታገታለን። ማንኛውንም ዋሾ፣ አስመሳይ፣ ተንኮለኛን አሜን አሜን ማለት ሳይሆን ውሸቱን መግለጥ፣ አስመሳይነቱን ማሳበቅና ክፋቱን በመልካምነት መዋጋት ያስፈልገናል፤ ይገባናልም። ታሪክ የሚደልዘውን፣ ሴራ የሚሸርበውን  ማፋጠጥና ማስተማርም ያስፈልጋል። አለበለዚያ የፍጥረት ሁሉ እንቅርጣጭ፣ ነኳታ መሆን ነው ትርፉ። ያልተዘራንበትን አፈር፤ ያልበቀልንበትን አፈር፤ ያላበብንበትን አፈር፤ ያላፈራንበትን አፈር የኔ ነው ማለት ይቀናናል፡፡ በኢትዮጵያ ባህል አድገን ተምረን የአውሮጳና የእስያ አፈር ይናፍቀናል፤ የኔ ነውም እንለዋለን፡፡ ከራስ መጣላት ሲጀምር እንዲህ ነው፡፡ ከዚያማ ወደ ቁልቁለቱ መንደባለል ነው፡፡
መልካምነት ግን እራስን መጠበቅ ነው፤ የመልካምነት ዋጋውም በምናውቀውና በማናውቀው መንገድ ይከፍለናል፡፡ መሬት ስንቆፍር ድንገት የተቀበረ ሃብት ብናገኝ የእድል ጉዳይ ነው ልንል እንችላለን፤ ነገር ግን ጉድጓዱን እንድንቆፍር የሚያነሳሳን አንዳች መለኮታዊ ኃይል አለ። ይህ መለኮታዊ ኃይል ወደርሱ በመልካም ግብራችን በቀረብነው ቁጥር ደረጃ በደረጃ ተጠቃሚ የምንሆንባቸውን ሁነቶች ያመቻቻልና ነው። የመልካምነት መንፈስን ስንቀዳጅ ከቤታችን ሳንወጣ ዓለምን በሞላ በዐይነ ኅሊናችን መፈተሽና መበርበር እንችላለን። የኅላዌ ልዕልናችን ባደገ ቁጥር ወደ ፍጽምና እርከን እንደርሳለን፤ የዚህ ዓለም ግሳንግስና የሥጋ ሸክም ሁሉ እንደ ገለባ፣ እንደ እፉየ ገላ ብናኝ ይሆኑልናል፡፡ ‹‹እመን እንጂ አትፍራ›› ይላል ታላቁ መጽሐፍ፡፡

Read 2213 times