Saturday, 21 October 2017 13:18

አንጋፋ ባለሥልጣናት ከኃላፊነታቸው የመልቀቅ አንደምታ?

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(4 votes)

“ኳሱ አሁንም በኢህአዴግ ሜዳ ላይ ነው ያለው”
               አቶ ሙላቱ ገመቹ (አንጋፋ ፖለቲከኛ)

    በኢህአዴግ የፖለቲካ ባህል የቱንም ያህል አስገዳጅ ሁኔታ ቢፈጠር ከፓርቲም ሆነ ከመንግስት ኃላፊነት በፈቃደኝነት መልቀቅ የተለመደ አይደለም፡፡ ለዚህም ነው ባለፈው ሰሞን የአፈጉባኤ አባዱላ ገመዳ አሁን ደግሞ የአቶ በረከት ስምኦን ከሥልጣን የመልቀቅ ጥያቄ በስፋት አነጋጋሪ የሆነው፡፡ በተለይ ደግሞ አገሪቱ በፖለቲካ ቀውስ በምትናጥበትና አለመረጋጋት ውስጥ ባለችበት ወቅት መሆኑ ብዙዎችን ሥጋት ውስጥ ከትቷቸዋል፡፡ በመቀጠልስ ከሥልጣን የመልቀቅ ጥያቄ የሚያቀርበው የኢህአዴግ አንጋፋ ባለሥልጣን ማን ይሆን? ባለሥልጣኖቹን ላለፉት 27 ዓመታት ከቆዩበት የመንግስት ኃላፊነታቸው ለመልቀቅ ያስወሰናቸው ምን የከፋ ሁኔታ ቢገጥማቸው ነው? ይሄ አገሪቱን ለሚመራት ኢህአዴግ ምን ተጽዕኖ አለው? በከፍተኛ የህዝብ ተቃውሞ ሲናጥና ጥልቅ ተሃድሶ ላይ መሆኑን ሲገልጽ ለነበረው መንግስትስ አንደምታው ምንድን ነው? የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ በዚህ ወቅታዊ አጀንዳ ዙሪያ አንጋፋ ፖለቲከኞችን አነጋግሮ ሃሳባቸውን እንደሚከተለው አጠናቅሮታል፡፡ ለፖለቲካዊ ችግሮች መፍትሄው ፖለቲካዊ ውይይት ነው፡፡

   የእነዚህ ሰዎች ስልጣን የመልቀቅ ጥያቄ አንድምታ፣ የሥርአቱ ጫፍ ላይ ደርሶ ለመውደቅ የመንገዳገድ ምልክት ነው፡፡ አንድ ሥርአት ይፈጠራል፣ ያድጋል፣ ይሞታል፡፡ ሁሉም ሂደት አለው፡፡ እነዚህ ሰዎችም በስልጣን ላይ ከ25 ዓመት በላይ ቆይተዋል፡፡ ለውጥ እናመጣለን ብለው ብዙ ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን የመጣው ነገር ያን ያህል ነው የሚል ትችትም ይቀርብባቸዋል፡፡ አሁን የጀመራችሁት ጉዞ ሊያዛልቃችሁ አይችልም የሚል ግፊትና ጫና ተበራክቶባቸዋል፡፡ የሚያሳዝነው ግን ይሄን ከሚሏቸው መካከል አንዳንዶቹ ታስረዋል፡፡ የእነሱ ግትርነት ሁኔታዎችን ከቀን ወደ ቀን እያበላሸ ከመሄድ የዘለለ አዎንታዊ ውጤት አላሳየም። ይሄን ውጤት የገመገሙ ሰዎች እንግዲህ በጊዜ እየተንሸራተቱ ያለ ይመስለኛል፡፡ መጨረሻው እየተቃረበ ስለሆነ ዝም ብለን ከምንቀመጥ ራሳችንን ከዚህ ማዕበል እናውጣ በሚል እሳቤ  እየለቀቁ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ከእንግዲህ ወዲህ አይሻሻልም የሚል ተስፋ መቁረጥ ይመስለኛል ይሄን እየፈጠረ ያለው፡፡
በሌላ በኩል፤ ህዝባቸውን ወክለው በተቀመጡበት የስልጣን ወንበር ላይ “ውጤት አላመጣንም” እያሉ ነው ያሉት፡፡ ይሄን ካሉ ደግሞ ህዝቡን መቀላቀል መፈለጋቸውና ራሳቸውን ከቡድኑ መለየታቸው የሚጠበቅ ነው፡፡ አንድ ሥርአት እየወደቀ ከሆነ ሥርአቱ ውስጥ መቆየት ዋጋ የለውም፡፡ ወደ ሌላ እቅድ መግባት የብልህ ፖለቲከኛ አካሄድ ነው፡፡ አሁን እነዚህ ሰዎች ወደ ሁለተኛው አማራጭና እቅድ እየገቡ ያሉ ነው የሚመስለኝ፡፡  
የእነዚህ ሰዎች ስልጣን መልቀቅ በራሱ በፓርቲው ውስጥ አደጋ ሊፈጥር ይችላል እንጂ በሀገር ላይ የሚፈጥረው ችግር የለም፡፡ ምክንያቱም አሁን ይህቺን ሀገር ከእነሱ ተረክቦ ለመምራት የተዘጋጀ የፖለቲካ ቡድን አለ፡፡ ህዝባችንም የሰላማዊ ለውጥ ፈላጊ ነው፡፡ በእርግጥ የሚመጣው የፖለቲካ ስልጣን በጉልበት መሆን የለበትም፡፡ በስምምነት የሚመጣ መንግስት፣ ይህቺን ሀገር ከውድቀት ሊታደጋት ይችላል፡፡ ለጊዜው ኳሱ አሁንም ያለው በኢህአዴግ ሜዳ ላይ ነው፡፡ እንደ ኢሰፓ መቀመቅ ከመውረድ ከወዲሁ ተቃዋሚዎችን አሰባስቦ፣ እንዴት ሀገሪቱን እንምራት? ምን እናድርግ ብሎ መምከር አለበት። ይሄን ካላደረገ፣ ራሱንም ሀገሪቱንም አደጋ ላይ ይጥላል፡፡ ሀገራዊ እርቅና ሰላም የሚፈጠርበት ሁኔታ በአስቸኳይ መመቻቸት አለበት፡፡ በጉልበት ከሆነ ግን ኢህአዴግም እየተመዘዘ በሂደት ማለቁ የማይቀር ይሆናል፡፡ ስለዚህ ብልህ ሆኖ የሽግግር መንግስት ማቋቋም አለበት፡፡  
-------------

                  “ኢህአዴግ የመፍረክረክ አደጋ ላይ እንዳለ የሚያሳይ ነው”
                    ወ/ሮ አረጋሽ አዳነ (አንጋፋ ፖለቲከኛ)

    ኢህአዴግ ችግር ውስጥ ያለ ድርጅት መሆኑ አሁን ብቻ ሳይሆን ቀደም ብሎም እየታየ የመጣ ነው፡፡ “በሃገሪቱ ባሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችና ቀውሶች ተጠያቂው እኔ ነኝ፤አመራሮቼ የፈጠሩት ችግር ነው” ብሎ ጥልቅ ተሃድሶ እያደረገ መሆኑን ገልጾ ነበር፡፡ እንደውም አንዱ ዋናው ተንቀሳቃሽ አቶ በረከት ስምኦን ነበሩ፡፡ “ስልጣናችንን ለግል ጥቅማችን እያዋልን ነው፤ያንን ካልታገልን አይሆንም፤ ያንን ለመታገል ቆርጠን ተነስተናል” ብለው ነበር፡፡ ግን ችግሩን እንፈታዋለን ያሉበት መንገድ ትክክለኛና ህዝቡ በሚፈልገው መንገድ አይደለም፡፡ በዚህ የተነሳ ችግሩ እየባሰ በመምጣቱና የሃገሪቱን መፃኢ እድል አስጊ ሁኔታ ላይ የሚጥል ደረጃ  ላይ በመድረሱ “ከደሙ ንጹህ ነኝ” ለማለት ያደረጉት ይመስለኛል፡፡
በሌሎች መንግስታት ታሪክ ውስጥ እንደምናየው፣ ችግር ሲያጋጥም የውስጠ ድርጅት መፍረክረክ ይመጣል፡፡ ስለዚህ የአቶ አባዱላም ሆነ የአቶ በረከት የስራ መልቀቅያ ማቅረብ፣ ኢህአዴግ ውስጡ የተረጋጋ እንዳልሆነ  ምልክት ነው፡፡ የመፍረክረክ አደጋ ላይ እንዳለ የሚያሳይ ነው፡፡
በሌላ በኩል እነዚህ ቁልፍ ሰዎች በአሁኑ ወቅት እንደዚህ ማድረጋቸው ተሃድሶ ያሉት ነገር አልሰምር ሲል እና ሁኔታው የማያምር ሆኖ ሲያዩት፣ በመጨረሻ ጥሎ በመውጣት ራስን የማዳን መንገድም ይመስለኛል፡፡ አሁን ማዕበሉ ይዟቸው እንዳይሄድ ተሃድሶ ያሉትን እየካዱ መሆን አለበት፡፡ እነዚህን አመራሮች ሲያጣ፣ ምንም ጥርጥር የለውም፣ ድርጅቱ ላይ የመዳከም ሁኔታ ይፈጥራል፡፡ በአባላት ላይም ተስፋ መቁረጥ ሊፈጥር ይችላል፡፡ በድርጅቱ ውስጥም አንድ ያለመሆን ችግር ያመጣል፡፡ ይህም በሃገር ላይ የራሱ ነፀብራቅ ይኖረዋል፡፡
አሁን ዋናው ጥያቄ፣ ሃገሪቱን ከዚህ ችግር እንዴት ነው ማውጣት የሚቻለው? የሚለው ነው። አንዱ መፍትሄ፣ ህዝቡና ምሁራን የሚሳተፉበት ፎረም፣ በራሱ በኢህአዴግ ጠሪነት ማካሄድ ነው። ግን ይሄን ለማድረግ ይደፍራል ወይ የሚለው ሌላ ጥያቄ ነው፡፡ ለዚህ ሰፊ ልቦና ይጠይቃል፡፡ ይሄ ካልሆነ ግን እነሱም መፍረሳቸው አይቀርም፣ ለሃገሪቱም ያሰጋታል፡፡

------------

                “ስልጣን መልቀቅ የተስፋ መቁረጥ ምልክት ነው”
                  ኢ/ር ይልቃል ጌትነት (ፖለቲከኛ)

    አሁን ባለንበት ሁኔታ ሕወኃት/ኢሕአዴግ ከባድ ችግር ውስጥ መሆኑ አያጠራጥርም፡፡ ነገር ግን ድርጅቱ ያለበትን የውስጣዊ ችግር የእድገት ደረጃ በጥሞና ለመረዳት፣ እያንዳንዱን ክንዋኔ በጥንቃቄ መመልከት ያስፈልጋል፡፡ የድርጅት ውስጣዊ ሽኩቻውንና ሀገራዊ ፋይዳውን ሚዛን ላይ አስቀምጦ ማየት ያስፈልጋል፡፡ ሕወኃት እጅግ ሚስጥራዊ ድርጅት መሆኑ ይታወቃል፡፡ ሀገሪቱን የመምራት ኃላፊነትም በእነሱ ትከሻ ላይ መውደቁን ጠንቅቀው ያውቃሉ፡፡ በዚህ ሁሉ ሀገራዊ ምስቅልቅል ውስጥ የአቶ በረከትን መልቀቂያ ይፋ ማድረግ ለምን አስፈለገ? ለዚህ ጥያቄ ለእውነት የቀረበ መልስ ለማግኘት ሁለት መላምቶችን ማቅረብ ይቻላል፡፡
አቶ በረከት የድርጅቱ ጭንቅላት እንደሆኑ ይታመናል፡፡ አቶ አባዱላ የይስሙላ ፓርላማም ቢሆን በዓለም አቀፍ ግንኙነት ደረጃ ሲታይ የነበሩበት ቦታ ትልቅ ገፅታ ነው፡፡ የእነዚህ ባለስልጣናት መልቀቅ ሕወኃት/ኢሕአዴግ በከፍተኛ ደረጃ ተዳክሞና ሁሉንም ነገር መቆጣጠር አቅቶት፣ ባለስልጣናቱ ተስፋ በመቁረጥና በመደናገጥ፣ ሀገራዊ ኃላፊነት መውሰድ የማይችሉበት ደረጃ ላይ በመድረሳቸው፣ በግላቸው እየወሰኑ ነው ማለት ነው፡፡ በመሆኑም ከዚህ በመነሳት ከፍተኛ ችግር መኖሩንና ለሀገራዊ የፖለቲካ ለውጥ መቃረባችንን መገመት ይቻላል፡፡
ሌላው በአሁኑ ሰዓት ኦህዴድ ከኃወሐት የበላይነት በብዙ መልኩ የማፈንገጥ አዝማሚያና በኦሮሚያ ክልል ከሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ኃይሎች ጋር አጀንዳ መጋራትና የዓላማ መደበላለቅ አለ ብሎ ሕወሐት ያምናል፡፡ የአባዱላ ገመዳ መልቀቅና የሰጡት ምክንያት የኦሮሞን ህዝብ ለማነሳሳትና አባዱላ የህዝባዊ እንቅስቃሴው ቀጥተኛ ያልሆነ መሪ /informal leader/ ለመሆን፣ በኦሮሞ ፖለቲከኞች የተቀነባበረ ነው በሚል ሕወኃት ይህንን የድርጅት ሽኩቻ ሚዛን ለማስጠበቅ፣ በህዝብ ዘንድ በተለይም በማህበራዊ ሚዲያው ያገኘውን የዜና ሽፋን መበረዝና በአባዱላ ምክንያት በኦሮሚያ ክልል የተፈጠረውን የፖለቲካ ትኩሳት ስለዚህም አቶ በረከት በተመሳሳይ ሁኔታ ከስራ እንዲለቁና የዜና ሽፋኑን እንዲቆጣጠሩ አድርጓል ብሎ መገመት ይቻላል፡፡ ይህንን ግምት የሚያጠናክረው ሕወኃት እጅግ ሚስጥራዊ ድርጅት ከመሆኑ አንፃር፣ አቶ በረከት ይሰሩበት የነበረው ቦታ ከህዝብ ገፅታ መራቁ ሲታይ፣ ዜናውን በአሁኑ ደረጃ ይፋ ሳያደርጉ በዝግታ መልቀቅ የሚችሉበት ሰፊ እድል ነበር፡፡ አቶ በረከትም በድርጅቱ ውስጥ ያላቸው ቦታ ከፍተኛና ሴራን ጠንቅቀው የሚያውቁ ከመሆናቸው አኳያ፣ በድርጅትም ሆነ በሀገራዊ ፖለቲካ የእሳቸው ከስልጣን መልቀቅ ዜና፣ ፋይዳው ከፍተኛ እንደሆነ ከዚህ አንፃር የሥልጣን መልቀቁ ታስቦና ታቅዶ የተደረገ ሊሆን እንደሚችል መገመት ይቻላል፡፡ በፖለቲካ ስራ ውስጥ አንድ ከባድ አደጋ ሲያጋጥም፣ ትኩረት ለማስለወጥና አቅጣጫን ለማስቀየር አዳዳዲስ ዜናዎች ፈጥሮ፣ ችግሩን ለመፍታት፣ ትንፋሽ የማግኛ ዘዴ አድርጎ መጠቀም የተለመደ ተግባር ነው፡፡
ለማጠቃለል፣ አሁን ያለው እውነታ በተራ ቁጥር 1 እንደተገለፀው ከሆነ፣ ሀገራችን በፈጣን የለውጥ ማዕበል ላይ ስለሆነች፣ ለውጥ ፈላጊ ኢትዮጵያውያን፣ በጥንቃቄና በአስቸኳይ ከባድ ሀገራዊ ስራዎችን መስራት ይጠበቅባቸዋል ማለት ነው፡፡ ነገር ግን ያለው እውነታ በተራ ቁጥር 2 ላይ እንደ ተገለፀው ከሆነ፣ የውስጥ የድርጅት ሽኩቻ ለትግሉ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ቢኖረውም ጊዜ የሚሰጥና በተረጋጋ ሁኔታ አስቦ ትግሉን ለመምራት የሚቻልበትን ዕድል ይፈጥራል የሚል እምነት አለኝ፡፡
(ከፌስቡክ ገፃቸው የተወሰደ)

----------

               “ከሥልጣን ለሚለቁት የማርያም መንገድ ልንሰጣቸው ይገባል”
                 አቶ አስራት ጣሴ (አንጋፋ ፖለቲከኛ)

    ኢህአዴግ ስልጣን ከያዘ ከረጅም አመታት በኋላ እነዚህ ወሳኝ ባለስልጣናት ከሃላፊነታቸው እንለቃለን ሲሉ በውስጡ የሴራ ፖለቲካ መኖሩ አያጠያይቅም፡፡ አንዳንድ ሰዎች የሁለቱን ባለስልጣናት እንለቃለን ማለት በጥርጣሬ ቢመለከቱት የሚያስገርም አይደለም፡፡ ህውሓት/ ኢህአዴግ እየፈረሰና እየወደቀ ባለበት በዚህ ሰአት፣ የእነዚህ ሰዎች ከኃላፊነት መልቀቅ ምናልባት በአንድ የሆነ መንገድ ከዚህ ፍርስራሽ ውስጥ ራስን እንደገና ለማዳንና ለመፍጠር የሚደረግ አካሄድ ነው ብሎ ማሰብም ይቻላል፡፡ ይሄ ሌላው የሴራ ፖለቲካ ትንተና ነው፡፡ የሴራ ፖለቲካ ትንተና አቅራቢዎች፤ ምናልባትም በእነዚህ ሁለት ቁልፍ ሰዎች የስራ መልቀቅ ተነሳስተው፣ ሌሎችም ተመሳሳይ እርምጃ ሊወስዱ ይችላሉ የሚልም ግምት ያስቀምጣሉ፡፡ በኔ በኩል ግን ይሄ ግምት ዋጋ የለውም ባይባልም ሚዛን የሚደፋ ሆኖ አላገኘሁትም፡፡
ኢህአዴግ ራሱን የአራት ፓርቲዎች ግንባር አድርጎ ነው የሚወስደው፡፡ ለኔ ግን ይሄ አይሠራም። ኢህአዴግ አሃዳዊ ነው፡፡ ህወኃት ነው በዋናነት የሚዘውረው፡፡ ይህን በምሣሌ ለማስረዳት፣ የቀድሞ የሃገሪቱ ፕሬዚደንት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ በሠጡት ቃለ ምልልስ፤ አባዱላ ገመዳ እስከ 1993 ዓ.ም ሜ/ጀነራል የነበሩ ወታደር ናቸው። ዶ/ር ነጋሶም፤ “የጀነራል ማዕረጉን የሠጠሁት እኔ ነኝ፤ አሁንም ለኔ ጀነራል ናቸው” ብለዋል፡፡ ማዕረጉን አንስተው ወደ ሲቪል የቀየሯቸውም ከህገ መንግስቱ አግባብ ውጪ መሆኑን አውስተዋል፡፡ ያንን ማዕረግ ያነሱት እንግዲህ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ናቸው፡፡ ታዲያ በምን መስፈርት ነው ኢህአዴግ አለ የሚባለው? ለእኔ ህውኃት ነው ወሣኙ፡፡ እኔ ከዚህ በኋላ አባዱላ ገመዳን ሜጀር ጀነራል ብዬ ነው የምጠራቸው፡፡ እሣቸውም ራሣቸውን ከዚህ በኋላ ሜጀር ጀነራል ብለው የሚጠሩ ይመስለኛል። ሜጀር ጀነራል አባዱላ ገመዳ፣ በኢህአዴግ ቤት የኖሩት በተሸናፊነት ስሜት ነው፡፡ በተቃራኒው አቶ በረከት ደግሞ በአሸናፊነትና በፈላጭ ቆራጭነት ስሜት ነው፡፡
ሁለቱም ዛሬ ላይ ለወሰዱት እርምጃ ያበቃቸው የጋራ ምክንያት እንዳለ ግን ይሰማኛል፡፡ ይህም የጋራ ምክንያት የአቶ መለስ ዜናዊ ሞት ነው፡፡ እኔ የሜጀር ጀነራል አባዱላን የሰሞኑን እርምጃ የማየው ከ1 ሺህ ሜትር እርምጃ፣ ገና አንዱን እንደተራመዱ አድርጌ ነው፡፡ ይህ እርምጃቸው የማይረባ ነው ብሎ ለመኮነንም ሆነ ለማወደስ አሁን ጊዜው አይደለም። አቶ በረከትም  የተሰሚነትና የፈላጭ ቆራጭነት ሚናቸው ቀስ በቀስ እየቀነሰና ጀንበራቸው እየጠለቀች በመምጣቷ ምክንያት ይሄን እርምጃ የወሰዱት ይመስለኛል፡፡ የሳቸው እርምጃም ከ2 ሺህ ሜትር እርምጃ አንድ ሜትር ብቻ  እንደመራመድ የሚታይ ነው፡፡ ገና 1999 ሜትር ይቀራቸዋል፡፡
ሁለቱም ሰዎች ከዚህ በፊት በህዝብና በአገር ላይ የፈፀሟቸውን ጥፋቶች ማመንና መቀበል ይጠበቅባቸዋል፡፡ ህዝብንና ሀገርን በተግባር ለመካስ የተዘጋጁ መሆን አለባቸው፡፡ ይሄን ስል ብዙ ሰው ቅር እንደሚሰኝ እገምታለሁ፤ ነገር ግን ኢትዮጵያ ሀገራችን ሀገራዊ ህልውናዋ አደጋ ውስጥ በወደቀበት በአሁኑ ወቅት፣ እኛ ሽማግሌዎች ማስተዋልን ጨምረን፣ አይናችን እያየ የፈረሱ ሀገራትን ሁኔታ በማጤን፣ በስርአቱ ውስጥ እያገለገሉ ያሉ ሌሎች ባለሥልጣናትም ተመሳሳይ መንገድ የሚከተሉበት ሰፊ እድል ሊከፈትላቸው ይገባል ባይ ነን፡፡
የማርያም መንገድ መኖሩን ልናሳያቸውና ልናስተምራቸው ይገባል፡፡ እርግጥ ነው ብዙ ሠው ተበድሏል፡፡ ግን አሁን ጊዜው የውግዘትና የመወነጃጀያ መሆን የለበትም፡፡ መጀመሪያ ሃገር ከመፍረስ መዳን አለባት፡፡ ልጆች የሚያድጉበት፣ ወጣቶች ሰርተው መለወጥ የሚችሉበት ሃገር ያስፈልገናል፡፡ ስለዚህ እኔ የእነዚህን ሰዎች መልቀቂያ ማስገባት፣ በበጎ ነው የምመለከተው፡፡ አሁን ሃገር ማዳን አለብን፡፡ በአስተዋይ ህሊና መጓዝ አለብን፡፡
ከእነዚህ ባለስልጣናት ጎን ለጎን ሁለት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎችም አሜሪካን ሃገር ሄደው ከድተዋል። ይሄ አንደምታው በህወኃት-ኢህአዴግ ውስጥ አንድነት መዳከሙንና የህወኃት የበላይነት ፈተና ውስጥ መግባቱን እንዲሁም ሌሎች ፓርቲዎች (ኦህዴድ፣ ብአዴን፣ ደኢህዴን) የራሳቸውን ህልውና የማስከበር የጥረት እርምጃ አድርጌም አየዋለሁ፡፡ የአቶ በረከት መልቀቅ፣ ለብአዴኖች አንድ መልካም አጋጣሚ የፈጠረ ይመስለኛ፡፡
 የሜጀር ጀነራል አባዱላ ደግሞ ለህዝቡም ሆነ ለክልሉ አመራር የልብ ልብ ሰጥቶ፣ ህውኃትን የሚገዳደሩበት ሃይል የሚያገኙ ይመስለኛል። የእነዚህ ሰዎች ከስልጣን መልቀቅ መንስኤው፣ የህዝብ ቁጣና እምቢተኛነት ነው፡፡ የህዝብን እምቢተኝነት አምነው መቀበላቸውን ነው የሚያሣየኝ፡፡

Read 3277 times