Print this page
Saturday, 21 October 2017 13:12

የአፍሪካ ክለቦች፤ ሊጎችና አዝጋሚው የእግር ኳስ ገበያ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(1 Vote)

በአፍሪካ እግር ኳስ በ50 አገራት ከፍተኛ የሊግ ውድድሮች  ከተመሰረቱ 50 እና ከዚያም በላይ ዓመታት ባስቆጠሩ በርካታ ክለቦች የሚካሄዱ ቢሆንም በአዝጋሚ የእግር ኳስ ገበያ የሚዳክሩ ናቸው፡፡ በገቢያቸው የተቀዛቀዙና ትርፋማ ያልሆኑት የአፍሪካ ሊጎች በሰሜን አሜሪካ፤ በኤሽያና በደቡብ አሜሪካ የሚካሄዱትን በሚስተካከከል ደረጃ አለመገኘታቸው ለብዙ የስፖርት ባለሙያዎች የሚያስቆጭ አጀን ሆኖባቸዋል፡፡ በአፍሪካ  የህዝብ ብዛት 1 ቢሊዮን መድረሱ፤ እግር ኳስ ስፖርት በተወዳጅነት የሚስተካከለው ማጣቱ፤ ተሰጥኦ ያላቸው ታዳጊ ተጨዋቾች እንደመብዛታቸው… እግር ኳስ በከፍተኛ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ  መካሄድ ነበረበት፡፡ የአፍሪካ ሊጎች በስፖንሰርሺፕ ገቢያቸው የተጠናከሩ አይደሉም፡፡ የእግር ኳስ ፌደሬሽኖች በየሊጎቹ ከፍተኛ የገቢ ምንጮች ዙርያ ምቹ እድሎችን በመፍጠር የማይንቀሳቀሱ ናቸው፡፡  በሊግ ውድድሮች ላይ ጣልቃ በመግባት፤ የስፖንሰርሺፕ እና ስፖርታዊ ንግዶችን በማያበረታቱ የአስተዳደር ስራዎች በመጠመድ ፌዴሬሽኖች ለሚፈለገው ለውጥ እንቅፋት እንደሆኑ ቀጥለዋል፡፡ በእግር ኳስ በተለይ በሊግ ደረጃ ለሚወዳደሩ ክለቦች ዋንኛ የገቢ ምንጮች የቴሌቭዥን ስርጭት  መብት፤ የሽልማት ገንዘብ እና ስፖንሰርሺፕ፤ የስታድዬም ትኬት ሽያጭ ገቢ እና የማልያና ሌሎች የስፖርት ቁሶች ንግዶች ናቸው፡፡ በአፍሪካ የሚንቀሳቀሱ ክለቦች የገቢ ምንጮቻቸውን ለማሳደግ በደጋፊዎች አያያዝ እና በስታድዬም ገቢ፤ በስፖንሰርሺፕ እና የስፖርት ንግዶች እንዲሁም በቴሌቭዥን ስርጭትና የሽያጭ መብት ፕሮፌሽናል የአስተዳደር አቅጣጫዎችን በመከተል መስራት ይኖርባቸዋል፡፡ በተለይ በአህጉሪቱ ክለቦች ፕሮፌሽናል የንግድ እና የእድገት አቅጣጫዎችን ለመከተል እንቅፋት የሆነባቸው ብዙዎቹ በመንግስት ባለቤትነት ስር በመውደቃቸው ሲሆን ከዚሁ አይነት አስተዳደር ወጥተው በባለሃብቶች፤ በባለአክሲዮኖች ድርሻ፤ በደጋፊዎች ኢንቨስትመንት በሚጠናከሩበት ዘመናዊ ስርዓት መግባት አለባቸው፡፡
በአፍሪካ የክለብ እግር ኳስ በስታድዬም የትኬት ሽያጭ ትርፍ ለማግኘት የሚያዳግት ነው፡፡ በዓለም ዙርያ ከክለቦች ዋንኛ የገቢ ምንጮች ከፍተኛውን ድርሻ የሚወስደው የስታድዬም ትኬት ሽያጭ የሚገኘው ገቢ እንደሆነ ቢታወቅም በአፍሪካ ግን ይህን ማሳካት የሚከብድ ሆኖ ቆይቷል፡፡ በአንድ አጋጣሚ ሱፕር ስፖርት እንደዘገበው በአፍሪካ በአንድ የጨዋታቀን ትልቁ ገቢ ሆኖ የተመዘገበው በደቡብ አፍሪካ አብሳ ፕሪሚዬር ሊግ በ1 ጨዋታ በአማካይ የሚገኘው 8ሺ ዶላር ገቢ ነው፡፡ በአፍሪካ እንኳንስ መደበኛ የአገር ውስጥ የሊግ ውድድሮች ይቅርና የየአገራቱ ትልልቅ ክለቦች በአህጉራዊ ደረጃ በሻምፒዮንስ ሊግ እና በኮንፌደሬሽን ካፕ በሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ስታድዬሞች ብዙ ተመልካች የማያገኙ ናቸው፡፡ አንዳንድ የስፖርት ትንታኔዎች ይህን የስታድዬም ድርቅ ከ280 ሚሊዮን በላይ አፍሪካውያን በአውሮፓ ታላላቅ ሊጎች ከሚሰጡት ትኩረት ጋር ያያይዙታል፡፡ የአፍሪካ ሊጎች የውድድር ዘመናት እና የጨዋታ መርሃ ግብሮች ከአውሮፓ ሊጎች ጋር በተመሳሳይ ወቅት ተደራርበው መካሄዳቸው የስታድዬም ተመልካች ማሳጣቱን በመጥቀስ ነው፡፡
በአፍሪካ የክለብ እግር ኳስ ሌላው አዝጋሚ ሁኔታ ከቴሌቭዥን ስርጭት እና ከሽያጭ መብት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ በዓለም እግር ኳስ የብሮድካስት ኩባንያዎች ከፍተኛ ባለድርሻ አካል እንደሆኑ ቢታወቅም የአፍሪካ ክለቦች በውስጥ የሊግ ውድድሮቻቸው እና በአፍሪካ ደረጃ ከቴሌቭዥን ስርጭት እና ሽያጭ መብት ጋር በተያያዘ ለሚገኙ ገቢዎች ትኩረት ባለመስጠታቸው በስፖርቱ እድገት ላይ እንቅፋት ፈጥሮባቸዋል፡፡ የብሮድካስት ኩባንያዎች ከእግር ኳስ ሊጎች ጋር ሲተሳሰሩ ጨዋታዎች በቀጥታ የቴሌቭዥን ስርጭት ሽፋን በማግኘት ተደራሽነታቸው ይጨምራል፤ በስፖንሰርሺፕ የሚገኙ ውሎች ተጠናክረው ገቢዎች ይጨምራሉ፤ የተጨዋቾች፤ የክለቦችና የስፖንሰሮቻቸው ብራንድ በተሻለ ደረጃ ይተዋወቃሉ፡፡ የብሮድካስት ጣቢያዎች ከሊጎች ጋር በአጋርነት ለመስራት ሲዋዋሉ በቴሌቭዥን ስርጭት እና የሽያጭ መብት የግዢ ውል ፈፅመው ሲሆን ይህ ገቢም ለሊግ ተወዳዳሪ ክለቦች በእኩልነት የሚካፈል በመሆኑ በስፖርቱ ያለውን የመዋዕለንዋይ እንቅስቃሴ ያሟሙቀዋል፡፡ ስፖርት አድማስ  በኢትዮጵያ የክለብ እግር ኳስ መኖር ያለበትን የፕሮፌሽናሊዝም አቅጣጫ ለማነቃቃት እነዚህን ጠቃሚ መረጃዎች ከተለያዩ ምንጮች በማሰባሰብ አቅርቧቸዋል፡፡
የአፍሪካ ሊጎችና ስፖንሰርሺፕ
በአፍሪካ የክለብ እግር ኳስ በተለይ በከፍተኛ የሊግ ውድድሮች የስፖንሰርሺፕ ገቢ ቀዝቃዛ ነው፡፡ እንደ አውሮፓ ታላላቅ ሊጎች ባይሆን እንኳን የአፍሪካ የእግር ኳስ ሊጎች በስፖንሰርሺፕ እና በተለያዩ የስፖርት ንግዶች ከሰሜን አሜሪካ እና ከኤሽያ አህጉራት ጋር መስተካከል አለመቻላቸው የሚያስደንቅ ነው፡፡ በአፍሪካ ክለቦች እና የሊግ ውድድሮቻቸው ዙርያ በሚሰራጩ የተለያዩ ትንታኔዎች እና ዘገባዎች በፕሮፌሽናል የሊግ አስተዳደራቸው፤ በስፖንሰርሺፕ እንቅስቃሴ በመጠናከራቸው፤ በቴሌቭዥን ስርጭት እና በተሻሉ የገቢ ምንጮች በመደራጀታቸው የሚጠቀሱት የሰሜን፤ ምዕራብ እና ደቡብ አፍሪካ አገራት  ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ ከምትገኝበት የምስራቅ አፍሪካ ዞን በእግር ኳስ ሊጋቸው ፕሮፌሽናል አደረጃጀት፤ አህጉራዊ ውጤታማነት ከቅርብ ዓመት ወዲህ መሻሻል ያሳዩት ሊጎች በሱዳን፤ ኬንያ እና ታንዛኒያ የሚካሄዱት ናቸው፡፡ በ3ቱ አገራት የሊግ ውድድሮች በሊጉ አብይ የስያሜ ስፖንሰር፤ በቴሌቭዥን ስርጭት እና በማልያ እና ልዩ ልዩ የስፖንሰርሺፕ እና የንግድ እንቅስቃሴዎች ያሉት ጅማሮዎች በኢትዮጵያ አለመሞከራቸው የሚያስቆጭ ነው፡፡
በደቡብ አፍሪካ ከፍተኛው የክለቦች ውድድር አብሳ ፕሪሚዬር ሊግ የተባለው ነው፡፡ ይህ ሊግ በቲቪ ስርጭት ፤ ከአብይ ስፖንሰር በሚያገኘው ገቢ፤ በክለብ ባለቤት ባለሃብቶች ብዛት፤ በከፍተኛ የተጨዋቾች ስብስብ የዋጋ ተመንና የደሞዝ ክፍያ ከአፍሪካ ሊጎች ግንባር ቀደም ሆኖ የሚጠቀስ ነው፡፡ አብሳ በደቡብ አፍሪካ አገራት የሚንቀሳቀስ ግዙፍ ባንክ ሲሆን በሊጉ አብይ ስፖንሰርነት  ስያሜውን በመውሰዱ ለአምስት የውድድር ዘመናት የከፈለው 61 ሚሊዮን ዶላር ነበር፡፡ በአፍሪካ ትልቁ የሆነው የብሮድካስት ኩባንያ ዲኤስቲቪ ደግሞ በሱፕር ስፖርት የሊጉን ጨዋታዎች በቀጥታ ስርጭት ለማስተላለፍ በየዓመቱ 1.95 ሚሊዮን ዶላር ይከፍላል፡፡
የግብፁ ፕሪሚዬር ሊግ ከ2005 እኤአ ጀምሮ በቴሌኮም ኩባንያ ኢስሳላት ስፖንሰር ተደርጎ ነበር፡፡ የቱኒዚያው ሊግ ፕሮፊሲዮናሌ 1 በይፋ የስፖንሰርሺፕ የተገለፀ ባይሆንም ከበርካታ የአፍሪካ አገራት ተጨዋቾችን በማስፈረም የአገሪቱ ክለቦች ከመታወቃቸውም በላይ በየስታድዬሞች ለደጋፊዎችእና ለስፖንሰሮች የተመቸ አሰራር በመኖሩ ተምሳሌት ሆኖ የሚጠቀስ ነው፡፡ የጋናው ፕሪሚዬር ሊግ ከ2008 ጀምሮ ለአምስት አመታት በናይጄርያዊ ባለቤትነት በተያዘ የምእራብ አፍሪካ ትልቁ የቴሌኮም ኩባንያ ግሎባኮም አብይ ስፖንሰርነት ሲካሄድ እስከ 23 ሚሊዮን ዶላር ክፍያ ተፈፅሞበት ነበር፡፡ ከዚህ በታች የቀረበው በአፍሪካ የክለብ እግር ኳስ የየአገራቱ ሊጎች በአብይ እና የስያሜ ስፖንሰርሺፕ ያላቸውን የገቢ ደረጃና ቅደም ተከተል ነው፡፡
1. ደቡብ አፍሪካ አብሳ ፕሪሚዬርሺፕ- 17 million USD$
2. ናይጄርያ ግሎ ሊግ USD$4 million
3. ጋና ፈርስት ካፒታል ሊግ USD$2 million
4. ታንዛኒያ USD$ 2million
5. ሞሮኮ ቦቶላ ሊግ USD$1.8 million
6 ካሜሮን ኤምቲኤን ሊግ USD$1.4 million
7. ቦትስዋና ቢ ሞባይል ሊግ USD$1.4 million
8. ዚምባቡዌ ካስትል ሊግ USD$1.2 million
9. አይቬሪኮስት ፕሪሚዬር ሊግ USD$1 million
10. ኬንያ ታስከር ሊግ USD$ 645,000
11. ዲ.ሪፖብሊክ ኮንጎ ፕሪሚዬር ሊግ USD$ 523,000
12. ማላዊ ሊግ USD$ 454,000
13. ማሊ ኦሬንጅ ሊግ USD$450,000
14. ስዋዚላንድ ፕሪሚዬር ሊግ USD$ 140,000
15. ዛቢያ ኤምቲኤን ሊግ USD$ 83,000
የአፍሪካ ክለቦችና ባለሃብቶች
ቬንቹር አፍሪካ የተባለ መፅሄት ከዓመት በፊት ‹‹ሃብታም የእግር ኳስ ክለብ ባለቤቶች በአፍሪካ›› በሚል ርእስ በአፍሪካ እግር ኳስ ኢንቨስት ያደረጉ ሚሊዬነሮችን ያስተዋወቀበት ዘገባ አቅርቦ ነበር፡፡ በዚሁ ዘገባ ላይ በአፍሪካ የክለብ እግር ኳስ  በባለቤትነት ብዙ ኢንቨስተሮች የሚገኙት በደቡብ አፍሪካው አብሳ ፕሪሚዬር ሊግ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡  በአፍሪካ  የእግር ኳስ ክለብ ባለቤቶች ከሆኑ ባለሃብቶች በግንባር ቀደምነት የሚጠቀሱት የደቡብ አፍሪካው ክለብ ሜመሎዲ ሰንዳውንስ ባለቤት ፓትሪስ ሞትሶፔ ናቸው፡፡ በፕላቲኒዬም እና በወርቅ ማዕድኖች ላይ የሚሰራው ‹‹አፍሪካን ሬንቦው ሚኒራልስ›› ኩባንያ መስራች እና ዋና ስራ አስኪያጅ የሆኑት ፓትሪስ ከ2.9 ቢሊዮን ዶላር በላይ ሃብት እንዳላቸው ይገመታል፡፡ በሁለተኛ ደረጃ የሚጠቀሱት በደቡብ አፍሪካው አንጋፋ ክለብ ካይዘርቺፍ ዩናይትድ 40 በመቶ ድርሻ ያላቸው ካይዘር ሞቱንግ ሲሆኑ በ1970 እኤአ ላይ ክለቡን የመሰረቱ ናቸው፡፡ ባላቸው የሃብት መጠን ከአፍሪካ ሃብታም የክለብ ባለቤቶች በ3ኛ ደረጃ የሚጠቀሱት ነጋዴ እና ፖለቲከኛ የሆኑት የዲ. ሪፕብሊክ ኮንጎው ክለብ ቲፒ  ማዜምቤ ዋይስ ቻፑዌ ናቸው፡፡ የዲ.ሪ. ኮንጎዋ ካታንጋ ግዛት አገረ ገዢ የሆኑት ዋይስ ቻፑዌ 60 ሚሊዮን ዶላር ኢንቨስት አድርገዋል፡፡ በመጨረሻም በአፍሪካ ከሚገኙ ሃብታም የእግር ኳስ ክለብ ባለቤቶች የሚጠቀሱት በደቡብ አፍሪካው ክለብ ኦርላንዶ ፓይሬትስ ከ1980 እኤአ ጀምሮ በፀሃፊነት ተነስተው እስከ ከፍተኛው ባለድርሻ ለመሆን የበቁት ኤርቪን ኮሆዛ ናቸው፡፡ በኦርላንዶ ፓይሬትስ ክለብ ባለቤትነታቸው ከ10 ሚሊዮን ዶላር በላይ ኢንቨስት ያደረጉት ኤርቪን ኮሆዛ በ2010 እኤአ ደቡብ አፍሪካ  19ኛው የዓለም ዋንጫን ስታስተናግድ ከፍተኛ ሚና ነበራቸው፡፡
የአፍሪካ ክለቦች፤ሊጎችና ቴሌቭዥን
በአፍሪካ አግር ኳስ ከቴሌቭዥን ስርጭት እና የሽያጭ መብት በተያያዘ የተሻሉ ሁኔታዎች የሚስተዋሉት በደቡብ እና በሰሜን አፍሪካ ነው፡፡ የደቡብ አፍሪካው የብሮድካስት ኩባንያ ዲኤስቲቪ በታዋቂው የሱፕር ስፖርትቻናል ለደቡብ አፍሪካ፤ ኬንያ፤ አንጓላ፤ዛምቢያ እና ናይጄርያ ለሚካሄዱ ሊጎች ሽፋን ይሰጣል፡፡ ሱፕር ስፖርት ከደቡብ አፍሪካው አብሳ ፕሪሚዬር ሊግ ጋር በቴሌቭዥን ስርጭት እና የሽያጭ መብት ለ5 ዓመታት ሲዋዋል በ134 ሚሊዮን ዶላር ሲሆን፤ ለናይጄርያ ለአምስት አመት 34 ሚሊዮን ዶላር እንዲሁም ለዛምቢያ በተመሳሳይ የውድድር ዘመናት  እስከ 5 ሚሊዮን ዶላር ክፍያ በመፈፀም ነው፡፡ ዚምባቡዌ፤ ኬንያ፤ አንጎላ፤ ጋና እና አቬሪኮስት ከቴሌቭዥን ስርጭት እና ከሽያጭ መብት በተያያዘ በየዓመቱ ከሱፕር ስፖርት 1 ሚሊዮን ዶላር እየተከፈላቸው በእግር ኳስ ሊጋቸው ሰርተዋል፡፡ በነገራችን ላይ የጋና ፕሪሚዬር ሊግ በአሁኑ ወቅት ኦፕቲመም ሚዲያ ፕራይም በተባለ ተቋም የሊጉ ጨዋታዎች በቴሌቭዥን የቀጥታ ስርጭት እና የተደራጁ ዘገባዎች የሚሰሩለት ሲሆን በየዓመቱ 90ሺ ዶላር በሚከፈልበት የስፖንሰር ውል ነው፡፡ በሌላ በኩል የግብፅ ሊግ በአፍሪካ ልዩ የሚያደርገው በስታድዬም የትኬት ገቢ እና በቲቪ ስርጭት ከፍተኛ ሽፋን የሚያገኝ በመሆኑ ነው፡፡ የግብፅ  ብሄራዊ የቴሌቭዥን ጣቢያ እና ሌሎች የአገሪቱ ቻናሎች የሊጉን ጨዋታዎች በቀጥታ ስርጭት የሚያስተላልፉ ሲሆን ይህም የሊጉን ገቢ በዓመት እስከ 1.3 ሚሊዮን ዶላር ያደርገዋል፡፡
የአፍሪካ ክለቦችና የተጨዋቾች ደሞዝ፤  ስደት
በአፍሪካ የክለብ እግር ኳስ ከፍተኛ ደሞዝ ለተጨዋቾች የሚከፍሉት  በሰሜን፤ ምእራብ እና ደቡብ አፍሪካ የሚካሄዱ ሊጎች  ናቸው፡፡ በአልጀርያው ሊግ ፕሮፌስዮናሌ 1 በሚወዳደር ክለብ የሚሰለፍ ተጨዋች በአማካይ  በሳምንት 1334 ፓውንድ በዓመት 69375 ፓውንድ ደሞዝ ስለሚያገኝ ሊጉን ከፍተኛ ክፍያ በመፈፀም በአፍሪካ የአንደኝነቱን ደረጃ ያሰጠዋል፡፡  የደቡብ አፍሪካ አብሳ ፕሪሚዬር ሊግ  በሳምንት 647 ፓውንድ  በዓመት 33659 ፓውንድ እንዲሁም የናይጀርያው ግሎ ፕሪሚዬር ሊግ  በሳምንት 130 ፓውንድ  በዓመት 6776 ፓውንድ ለአንድ ተጨዋች በአማካይ በመክፈል በሁለተኛ እና በሶስተኛ ደረጃዎች ይከተላሉ፡፡
የአፍሪካ የእግር ኳስ ክለቦች በገቢ አለመጠናከራቸው፤ የየሊጎቹ ትርፋማነት መቀዛቀዙ ለአገሪቱ ታዳጊ እና ወጣት የእግር ኳስ ትውልድ ስደት ምክንያት እንደሆነም ይገለፃል፡፡ በየአገራቱ በሚገኙ አካዳሚዎች በሚያፈሯቸው ታዳጊዎች እና የእግር ኳስ ትውልዶች ስደት ላይ አዝጋሚው የአፍሪካ የእግር ኳስ ገበያ በተዘዋዋሪ ብዙ ተፅእኖዎችን ፈጥሯል፡፡ የየአገሮቻቸው ክለቦች በሚከፍሏቸው ደሞዞች አነስተኛነት ወደተሻሉት የአውሮፓ ታላላቅ ሊጎች መሄድ ያልቻሉ የአፍሪካ ታዳጊዎች ስደታቸው ወደ መካከለኛው ምስራቅ በተለይ ኳታር እና ዱባይ ወይንም ወደ ኤሽያ በተለይ ወደ ቻይና ሆኗል፡፡ በዓለም አቀፉ የፕሮፌሽናል እግር ኳስ ተጨዋቾች ማህበር ፊፍፕሮ በ2016 በፕሮፌሽናል እግር ኳስ ያለውን የተጨዋቾች የስራ ሁኔታ በዳሰሰበት ዓለም አቀፍ የቅጥር ሪፖርት፤ በአፍሪካ የእግር ኳስ ሊጎች በወር ከ1ሺ ዶላር በታች የሚያገኙ ተጨዋቾች 73.2 በመቶ እንደሆነ ከአፍሪካ ክለቦች 55 በመቶው ለተጨዋቾች ደሞዝ በወቅቱ እንደማይከፍሉ እና 15 በመቶ የሚሆኑት የአፍሪካ ክለቦች ተጨዋቾች ከክለባቸው የፈረሙት ኮንትራት እንደሌለ ማረጋገጥ ተችሏል፡፡  ባንድ ወቅት ከዓለም እግር ኳስ የዝውውር ገበያ ላይ በማተኮር በተሰራጨ መረጃ ለመረዳት እንደሚቻለው በመላው ዓለም በተለያዩ አገራት ሊጎች የተሰማሩ አፍሪካውያን ተጨዋቾች ብዛት ከ4515 በላይ ነው፡፡ 596 ከናይጄርያ፤ 397 ከሴኔጋል፤ 370 ከኮትዲቯር 336 ከካሜሮን፤ 365 ከጋና ተሰድደው በዓለም እግር ኳስ የተሰራጩ ሲሆን ሞሮኮ፤ ኬፕቬርዴ ፤ ዲ.ሪፖብሊክ ኮንጎ፤ ማሊ፤ አልጄርያ እና ጊኒ ቢሳዎ ቢያንስ እያንዳንዳቸው ከ100 በላይ ተጨዋቾችን በስደት አጥተዋል፡፡
የአፍሪካ ክለቦች የሃብት ደረጃ
Source: Database.com #MSM
አልሃሊ ግብፅ 17.18 ሚሊዮን ዩሮ
ኤስፔራንስ ዴ ቱኒስ ቱኒዚያ 17.17
ክለብ አፍሪካን ቱኒዚያ12.83
ኤትዋል ደ ሳህል ቱኒዚያ 11.53
ሜመሎዲ ሰንዳንስ ደቡብ አፍሪካ - 11.18
ካይዘር ቺፍ ደቡብ አፍሪካ  10.15
ዛማሌክ ግብፅ 9.4
ዋይዳድ ካዛብላንካ ሞሮኮ 9.38
ኤኤስ ሴቲፍ አልጄርያ 9.3
ራጃ ካዛብላንካ ሞሮኮ 8.9
ኦርላንዶ ፓይሬትስ ደቡብ አፍሪካ 8.78
ዩኤስኤም አልጀር አልጄርያ 8.53
የአፍሪካ ክለቦች በተጨዋቾች ስብስብ የዋጋ ተመን  
(Source: TransferMarkt)
አል አሃሊ - ግብፅ - 19.25 ሚ. ዩሮ
ኤስፔራንስ - ቱኒዝያ - 12.75
ክለብ አፍሪካን - ቱኒዝያ - 11.8
ካይዘር ቺፍ - ደቡብ አፍሪካ - 10 .48
ሜመሎዲ ሰንዳውንስ - ደቡብ አፍሪካ - 10.35
ዛማሌክ - ግብኝ - 10.3
ዩ ኤስ ኤም አልጀርስ - አልጀርያ - 9.65
ኢ.ኤስ ሴቲፍ - ቱኒዝያ - 8.6
ራጃ ካዛብላንካ - ሞሮኮ - 8.13
ቲፒ ማዜምቤ - ዲ.ሪፕብሊክ ኮንጎ -7.3
የአፍሪካ ክለቦች በአህጉራዊ ውድድሮች ውጤታማነት ደረጃ (Source: rssf)
የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን ከ2 የውድድር ዘመናት በፊት ባለፉት አምስት ዓመታት በአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ እና ኮንፌደሬሽን ካፕ ክለቦች ያስመዘገቡትን ውጤት በመንተራስ ለአገራት  ያወጣው ደረጃ ነበር፡፡ ቱኒዚያ በ96 ነጥብ መሪነቱን ስትይዝ፤ ግብፅ በ87፤ ናይጄርያ በ75፤ ሱዳን በ54፤ ዲ. ሪፖብሊክ ኮንጎ በ46፤ አልጄርያ በ27፤ ሞሮኮ በ20፤ ካሜሮን በ19፤ ኮትዲቯር በ18፤ አንጓላ በ18 እንዲሁም ዚምባቡዌ በ12 ነጥብ እስከ 10ኛ ደረጃ ተቀምጠዋል፡፡አርኤስኤስኤፍ በሰራው የአፍሪካ ክለቦች በአህጉራዊ ውድድሮች ያላቸው ውጤታማነት ደረጃ ከዚህ በታች የቀረበው ነው፡፡
አልአሃሊ - ግብፅ - 20 ዋንጫዎች
ዛማሌክ - ግብፅ - 11 ዋንጫዎች
ቲፒ ማዜምዜ - ዲ.ሪፕብሊክ ኮንጎ - 10 ዋንጫዎች
ራጃ ካዛብላካ -ሞሮኮ - 6 ዋንጫዎች
ካኖን ያውንዴ - ካሜሮን - 4 ዋንጫዎች
 
የአፍሪካ ክለቦች ደረጃ  በ2017
 (Source: footballdatabase)
በ2017 እ.ኤ.አ ላይ የአፍሪካ ክለቦች በአህጉራዊ እና በአገር ውስጥ ውድድሮች ያስመዘገቡትን ውጤት በመንተራስ በfootballdatabase የክለቦች ደረጃ ደግሞ የሚከተለው ነው፡፡ ከአንድ እስከ 10 ባለው ደረጃ የሰሜን አፍሪካ ክለቦች በብዛት ተወክለዋል፡፡ የሱዳኖቹ አልሜሪክና አልሂላል ምስራቅ አፍሪካን፤ የደቡብ አፍሪካው ሜመሎዲ ሰንዳውንስ ከደቡብ አፍሪካ የዲ.ሪ ኮንጎዎቹ ቲፒ ማዜምቤ እና ኤኤስ ቪታ ከመካከለኛው አፍሪካ ይገኙበታል፡፡ የምዕራብ አፍሪካ አገራት ክለቦች በደረጃ ሰንጠረዡ ላይ በብዛት የሚገኙት ከ10ኛ በኋላ እስከ 50ኛ ባሉ ደረጃዎች ነው፡፡
ኤስፔራንስ ዴ.ቱኒስ - ቱኒዚያ - 1620 ነጥብ
ኤትዋል ደሳህል - ቱኒዚያ - 1611
አልአሃሊ - ግብፅ - 1609
ቲፒ ማዜምቤ - ዲ . ሪፐብሊክ ኮንጎ - 1590
አልሜሪክ - ሱዳን - 1554
ኤስ ቪታ ክለብ - ዲ. ሪፐብሊክ ኮንጎ - 1548
አልሂላል ኦምዱርማን - ሱዳን - 1544
ዋይዳድ ካዛብላንካ - ሞሮኮ -1535
ሜሞለዲ ሰንዳውንስ - ደቡብ አፍሪካ - 1525
ኤ ኤስ ሴፋክስዮን - ቱኒዚያ - 1516

Read 2995 times