Sunday, 22 October 2017 00:00

በኦሮሚያ ከተሞች በቀጠለው ተቃውሞ የ4 ሰዎች ህይወት ጠፍቷል

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(80 votes)

   • በሰላማዊ ሰልፍ ላይ የተገደሉ ዜጎች ጉዳይ በገለልተኛ አካል እንዲጣራ ተጠይቋል
   • “ሰልፎችን ወደ ሁከት የለወጡ በቁጥጥር ስር እየዋሉ ነው” የኦሮሚያ ክልል

      በኦሮሚያ የተለያዩ ከተሞች በቀጠለው ተቃውሞ፤ የ4 ሰዎች ህይወት መጥፋቱ የተገለጸ ሲሆን በአዲስ አበባ የአሜሪካ ኤምባሲ ባወጣው መግለጫ፣ሰላማዊ ሰልፎች በሁከትና በሞት መጠናቀቃቸው በእጅጉ እንዳሳዘነው ጠቅሶ፣ በሰላማዊ ሰልፍ መሃል የተገደሉ ዜጎች ጉዳይ በገለልተኛና ተዓማኒነት ባለው አካል እንዲጣራ  ጠይቋል፡፡
ባለፈው ሳምንት አጋማሽ አንስቶ የተጀመረው ተቃውሞና ሰላማዊ ሰልፍ፤ በሞጆ፣ በሙከጡሪ፣ በፊቼ፣ በገብረ ጉራቻ፣ በደገምና በጅማ እስከ ትላንት በስቲያ ሐሙስ (ጥቅምት 9 ቀን 2010 ዓ.ም) ቀጥሎ መሰንበቱን የጠቆሙት ምንጮች፤በሰልፎቹ ላይ የፌደራል መንግስቱን የሚያወግዙና የኦሮሚያ- ሶማሌ ግጭትን የሚያብጠለጥሉ መፈክሮች መሰማታቸውን ተናግረዋል፡፡  
ከሁሉም ጠንከር ብሎ የታየው በገብረ ጉራቻ ከተማ ባለፈው ረቡዕ የተደረገው ተቃውሞ መሆኑን የዘገበው ቢቢሲ፤ተቃውሞውን ተከትሎም የ3 ሰዎች ህይወት ማለፉን ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ኃላፊዎች ማረጋገጡን ጠቅሷል፡፡ በሙከጡሪ ከተማ በተደረገው የተቃውሞ ሰልፍ ላይም የአንድ ወጣት ህይወት ማለፉ የተገለፀ ሲሆን በርካታ ተሽከርካሪዎችና መኖሪያ ቤቶች በእሳት መቃጠላቸውም ተጠቁሟል፡፡  
በሰሜን ሸዋ ዞን የደገም ወረዳ ነዋሪ፣ተቃውሞ ሰልፎቹን አስመልክቶ ለቪኦኤ በሰጡት አስተያየት፤ “በተቃውሞው ህዝቡ የሚጠይቀው የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ጥያቄ ነው” ብለዋል፡፡ በአብዛኞቹ ከተሞች በተደረጉት ተቃውሞዎች ላይ ከሶማሌ ክልል ለተፈናቀሉ ዜጎች እርዳታ የማሰባሰብ ሥራዎች ሲከናወኑ እንደነበርም  ምንጮች ተናግረዋል፡፡  
 የመንግስት ኮሚኒኬሽን ኃላፊ ሚኒስትር ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ፣ በጉዳዩ ላይ ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ፤ እነዚህ በኦሮሚያ ክልል የሚደረጉ ሰልፎች በአንድ በኩል ለተፈናቀሉ ሰዎች ገቢ እንሰበስባለን በሚል በሌላ በኩል ደግሞ የተቃውሞ ድምፅ ለማሰማት የሚደረጉ መሆናቸው እንደሚታወቅ ተናግረዋል፡፡ ማንኛውም ሰው ህጉ በሚፈቅደው መሰረት፣ሃሳቡን የመግለፅ መብት አለው ያሉት ዶ/ር ነገሪ፤በዚህ መሃል ጉዳት የሚያደርሱትን መንግስት በቸልታ እንደማያልፋቸውና ከህግ ተጠያቂነት እንደማያመልጡ አስታውቀዋል፡፡
“ሰላማዊ ሰልፍ ሁከትና ንብረት ማቃጠልን አያካትትም፤የማይወክለንን ባንዲራ ይዘው እየወጡ ጉዳት የሚያደርሱ አካላት አሉ” ብለዋል - ሚኒስትሩ፡፡
ክልሉ እንዳይረጋጋ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን በመለየት የክልሉ መንግስት እርምጃ እንደሚወስድ መታወቅ አለበት ያሉት ዶ/ር ነገሪ፤ “ለተፈናቃሉ ወገኖች የሚደረግ ድጋፍ በግርግር ሳይሆን በሰላማዊ መንገድ ነው የሚከናወነው፣ከዚህ ካለፈ ህግን ለማስከበር መንግስት ስራውን ይሰራል” ሲሉ አስጠንቅቀዋል፡፡  
በአዲስ አበባ የአሜሪካ ኤምባሲ ባወጣው መግለጫ፤በሰላማዊ ሰልፍ ላይ የተገደሉ ዜጎች ጉዳይ በገለልተኛና ተአማኒነት ባለው አካል እንዲጣራ  ጠይቋል፡፡ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሀሳቡን ሰላማዊ በሆነ መንገድ መግለፅ እንዲቀጥል አሜሪካ እንደምታበረታታ ያስታወቀው ኤምባሲው፤ የመንግስት ኃላፊዎችም ሰላማዊ የሀሳብ መግለጫ መንገዶችን ከመገደብ እንዲታቀቡ መክሯል፡፡ ኤምባሲው አክሎም፤ለኢትዮጵያውያን ወሳኝ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ገንቢ፣ሰላማዊና ሁሉን አቀፍ አገራዊ ውይይት ይደረግ ዘንድም ያበረታታል ብሏል - በመግለጫው፡፡  
የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ በበኩላቸው፤ በክልሉ አንዳንድ ወረዳዎችና ከተሞች በተካሄዱ ሰልፎች ላይ ሁከት እንዲፈጠር ያደረጉ አካላትን የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን በቁጥጥር ስር እያዋለ ነው” ብለዋል።
በክልሉ ፖሊስ ቁጥጥር ስር እየዋሉ ያሉትም በሰልፎቹ ላይ የሰው ህይወት እንዲጠፋ ያደረጉ፣ ንብረት እንዲወድምና በህዝቦች መካከል ግጭት እንዲፈጠር ያደረጉ መሆናቸውን አቶ አዲሱ አስታውቀዋል፡፡
በክልሉ የተለያዩ ከተሞች እየተደረጉ ያሉ ሰልፎችን ማን እንዳዘጋጃቸው፣ የሰልፉ አላማ ምንድን ነው? ሰልፎቹን ወደ ግርግር የለወጡ አካላትን ማን አሰማራ? በህግ የተከለከሉ ባንዲራዎችንና አርማዎችን ማን አዘጋጀ? ማን ለሰልፈኞች አከፋፈለ? የሚሉ ጉዳዮችንም በፖሊስ ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን አቶ አዲሱ አስታውቀዋል፡፡

Read 10030 times