Sunday, 22 October 2017 00:00

መንግሥት ለህዝብ ጥያቄ አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጥ ኦፌኮ ጠየቀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(28 votes)

    መንግስት ለህዝብ ጥያቄዎች አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጥ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ የጠየቀ ሲሆን ህዝቡ በሰላማዊ ሰልፍ መብቱን ለመጠየቅ ሲንቀሳቀስ የሰው ህይወት እንዳይጠፋ፣ ንብረት እንዳይወድምና የህዝቦች አንድነትና አብሮነትን የሚሸረሽሩ ተግባራት ከመፈፀን እንዲቆጠብ ጥሪ አቅርቧል፡፡
በኦሮሚያ ክልል ሰሞኑን በታዩ ሰላማዊ ሰልፎቸ ላይ የታሰሩ ፖለቲከኞች ከእስር እንዲፈቱ፣ የዜጎች በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል ተዘዋውሮ የመኖርና የመስራት መብት ተጥሶ መፈናቀሎች መከተላቸውን የሚቃወሙ ጥያቄዎች መቅረባቸውን መረዳቱን የጠቀሰው ኦፌኮ፤ መንግስት ለእነዚህ የህዝቡ ጥያቄዎች አፋጣኝ ምላሽ በመስጠት፣ የታሰሩ ፖለቲከኞችን እንዲፈታ፣ መፈናቀል እንዲቆምና ለተፈናቀሉ ና ህይወታቸውን ላጤ ዜጎችም የንብረት ካሳና የደም ካሳ እንዲከፈላቸው ጠይቋል፡፡
“እስካሁን ድረስ ለህዝቡ ጥያቄዎች መንግስት ምንም ምላሽ አለመስጠቱን አረጋግጫለሁ” ያለው ፓርቲው፤ አንዱ ችግር ሌላ ችግር እየወለደ በመጨረሻም ወደማንወጣው አስፈሪ የቀውስ ደረጃ ላይ እንዳያደርሰን በእጅጉ ያሳስባል” ብሏል፡፡
በሰላማዊ ሰልፎቹ መሃል ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ሰዎች ህይወት ማለፉንና ንብረትም መውደሙን የጠቆሙት የፓርቲው አመራሮች፤ “የፓርቲያችን አርማም ያለ አግባብ በማይወክሉን ግለሰቦች በየሰልፎቹ ሲውለበለብ ነበር” ብለዋል። “ይሄ ጉዳይ ፓርቲውን እንደማይመለከት ህዝብ ይወቅልን” ሲሉ አመራሮቹ በመግለጫቸው አመልክተዋል፡፡

Read 3327 times