Saturday, 21 October 2017 12:51

ኢህአዴግ በህዝብ ያለውን ቅቡልነት፣ በህዝበ ውሳኔ እንዲያረጋግጥ ተጠየቀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(14 votes)

 የሀገሪቱ የፖለቲካ ችግር ከዕለት ወደ ዕለት እየተባባሰ መምጣቱንና ለሀገሪቱ ቀጣይ ህልውናም አስጊ ደረጃ ላይ መድረሱን የጠቆመው የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ (ኢራፓ)፤ ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ በህዝብ ያለውን አመኔታና ቅቡልነት ህዝበ ውሳኔ በማካሄድ እንዲያረጋግጥ ጠይቋል፡፡
ፓርቲው በወቅታዊ የአቋም መግለጫው፣ የሀገሪቱን የፖለቲካ ችግሮች ከስር መሰረታቸው ሲገመግም መሰንበቱን ጠቁሞ፤ በ2007 ዓ.ም የተካሄደውን ሀገር አቀፍ ምርጫ ተከትሎ አሸናፊነቱ የታወጀው ኢህአዴግ የመሰረተው መንግስት ላይ ውሎ ሳያድር ተቃውሞ ማየሉ፣ በሀገሪቱ ጤናማ ያልሆነ የፖለቲካ አካሄድ እንዳለ ያመላክታል ብሏል።
“በአሁኑ ወቅት ከሚታዩት ህዝባዊ ተቃውሞዎችና ግጭቶች አንጻር፣እንደ ሀገርና ህዝብ ህልውናችንን አስጠብቀን ለመሄድ አጠራጣሪ ሆኗል” ያለው ፓርቲው፤ ሁሉንም ወገኖች ያካተተ የብሄራዊ መግባባት መድረክም በአስቸኳይ መፈጠር እንዳለበት አሳስቧል፡፡  
ከ2007 ምርጫ ማግስት ጀምሮ በሃገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ተቀስቅሶ እስካሁን መብረድ ያልቻለውን ተቃውሞ በቅጡ መመርመር ያሻል የሚለው ኢራፓ፤ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት አባላት በመራጮቻቸው አመኔታ በሚያጡበት ወቅት ስለሚወሰድ እርምጃ የወጣውን አዋጅ 88/1989 ዓ.ም በመጥቀስም፡- መራጩ ህዝብ በአሁኑ ወቅት በኢህአዴግ ላይ ያለውን አመኔታ ለመለካት ህዝበ ውሣኔ በአስቸኳይ እንዲካሄድ ጠይቋል፡፡ ፓርቲው ይህን ጥያቄውንም አግባብ ላለው አካል ያለመታከት እንደሚያቀርብ አስታውቋል፡፡
መንግስት ለፖለቲካ የጋራ ውይይት፣ለሃገራዊ መግባባትና ብሄራዊ እርቅ ራሱን እንዲያዘጋጅ የተለያዩ አካላት ምክር እንዲለግሱ የጠየቀው ፓርቲው፤ የኢህአዴግ አመራሮች ስልጣናቸውንና ሃላፊነታቸውን በገዛ ፍቃዳቸው በመልቀቅም ለለውጥ ተፅእኖ እየፈጠሩ መሆኑን በአድናቆት እንደሚመለከተው አስታውቋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በመላ አገሪቱ በህብረተሰቡ መሃል ጥቃቅን ልዩነቶችን አግዝፎ በማቅረብ፣ ክስተታዊ ግጭቶችን ቋሚ ቁርሾዎች በማስመሰል፣ የመቀራረቢያና የመወያያ መንገዶችን በማዳፈን እንዲሁም ተፈጥሯዊ የብሄር፣ የቋንቋ፣ የባህልና ሃይማኖት ልዩነትን በማራገብ፣ ወደ እርስ በእርስ ግጭት የማሸጋገር አዝማሚያ መኖሩን የጠቆመው ኢራፓ፤ ይህ ድርጊት ሊወገዝ የሚገባው ነው ብሏል፡፡
ህዝቡም እነዚህን ልዩነቶች ወደ ጎን አድርጎ፣ ለሃገር አንድነትና ህልውና በጋራ እንዲቆም፣ መንግስትም የለውጥ እርምጃዎችን ህዝቡን በሚያረካ  መልኩ እንዲወስድ ፓርቲው ጥሪውን አስተላልፏል፡፡

Read 6077 times