Saturday, 21 October 2017 12:50

“የቤት መሥሪያ ቦታችን ላይ ግንባታ ሲካሄድ ደረስንበት” - የወላይታ ሶዶ መምህራን “ችግሩን ከመምህራኑ ጋር በጋራ ሆነን እንፈታዋለን” - የሶዶ ከተማ ማዘጋጃ ቤት ሃላፊ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(9 votes)

 ከ400 በላይ የሚሆኑ የወላይታ ሶዶ ከተማ የአንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ መምህራን፤”መንግስት ለመኖሪያ ቤት መስሪያ በሚል ከ9 ወራት በፊት በሰጠን መሬት ላይ ግንባታ እየተካሄደበት ነው” ሲሉ ቅሬታቸውን ያቀረቡ ሲሆን የከተማ አስተዳደሩ በበኩሉ፤የመምህራኑን አቤቱታ ተከትሎ ግንባታውን ማገዱን ለማወቅ ተችሏል፡፡
በከተማዋ አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች የሚያስተምሩ መምህራን፣ በ25 ማህበራት በመደራጀት በነፍስ ወከፍ 110 ካሬ ሜትር የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ የተሠጣቸው ባለፈው አመት የካቲት ወር  ሲሆን በአቅም ማነስና ብድር በማጣት፣በመሬቱ ላይ ግንባታውን ሳይጀምሩ መቆየታቸውን ያስረዳሉ፡፡
ብድር በማፈላለግ ላይ ሳሉ በተሰጣቸው መሬት ላይ ሰሞኑን የቤት ግንባታዎች ተጀምረው መመልከታቸውን፣ ጉዳዩንም ሲያጣሩ፣ ለእነሱ በህጋዊ ሠነድ የተሰጣቸው መሬት ባላወቁት ሁኔታ  በከተማዋ ላሉ ሃኪሞችና ሌሎች ግለሰቦች መሰጠቱን መረዳታቸውን ጠቁመው፤ አቤቱታቸውን ከትናንት በስቲያ ሃሙስ ለከተማ አስተዳደሩ ማቅረባቸውን ተናገረዋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩም በቦታው ላይ የሚካሄዱ ግንባታዎች በአስቸኳይ እንዲቆሙ ትዕዛዝ ሰጥቶ፣  ሰነዶችን መርምሮ ጉዳዩን እንደሚያጣራ ተነግሮናል ያሉት የመምህራኑ የቤት ስራ ማህበራት ምክትል ሰብሳቢ መ/ር ፍቅሬ ሞሊሶ፤ “ሁኔታው በእጅጉ አስደንግጦናል” ብለዋል፡፡
መሬቱ የተሰጠን የሶዶ ከተማ ቤቶች ልማት የሥራ ሃላፊዎች ባሉበት ሚያዚያ 11 ቀን 2009 ዓ.ም ነው የሚሉት መምህራኑ፤”ግንባታው በቦታው ላይ መካሄዱን ያወቅነውም በአካባቢው ነዋሪዎች ጥቆማ ነው፤ እኛ በአቅም ማነስ በቦታው ላይ ግንባታ መጀመር አልቻልንም ነበር” ብለዋል፡፡
የሶዶ ከተማ ማዘጋጃ ቤት ሃላፊ አቶ ፍሬው ሻንካ በበኩላቸው፤ሁኔታውን መሬት ላይ ካለው በተጨማሪ ሠነዶችን በመመልከት ካጣራን በኋላ ምላሽ እንሰጣለን ሲሉ ለአዲስ አድማስ የገለፁ ሲሆን ችግሩን ከመምህራኑ ጋር በጋራ ሆነው እንደሚፈቱም አስታውቀዋል፡፡

Read 3117 times