Saturday, 21 October 2017 12:45

አንበሳ ኢንተርናሽናል ባንክ ከታክስ በፊት 351 ሚ. ብር አተረፈ

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(0 votes)

 አንበሳ ኢንተርናሽናል ባንክ 13ኛ ዓመታዊ መደበኛና 5ኛ ድንገተኛ ጠቅላላ ጉባኤ ዛሬ በሸራተን አዲስ ሆቴል እያካሄደ ሲሆን በ2009 ዓ.ም ባደረገው እንቅስቃሴ ከታክስ በፊት 351 ሚሊዮን ብር ማትረፉን አስታውቋል፡፡
ባንኩ ለዝግጅት ክፍላችን በላከው መግለጫ፣ ትርፉን ለማግኘት 1.1 ቢሊዮን ብር መሰብሰቡን፣ ከዚህ ውስጥ ከብድር ወለድና ከዋስትና ኮሚሽን 71.6 በመቶ ድርሻ እንዳለው፣ ባንኩ ካስመዘገበው አጠቃላይ ትርፍ ውስጥ ለግብር 82.4 ሚሊዮን ብር ገቢ ማድረግ እንደሚጠበቅበት ገልጿል፡፡
ጠቅላላ ሀብቱ (እሴት) 10.97 ቢሊዮን መድረሱን የጠቆመው መግለጫው፤ ከአምናው ጋር ሲነፃፀር 35 በመቶ ወይም 1.87 ቢሊዮን ብር ጭማሪ ማሳየቱን፣ የተከፈለ ካፒታል 938.23 ሚሊዮን ብር፣ እንዲሁም ጠቅላላ ካፒታል ደግሞ 1.53 ቢሊዮን ብር መድረሱን አስታውቋል፡፡
በበጀት ዓመቱ በተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች ከ2.66 ቢሊዮን በላይ ብር ለአዲስ ተበዳሪ ደንበኞች ብድር የሰጠ ሲሆን ከ2.51 ቢሊዮን ብር በላይ ብድር መሰብሰቡን፣ ተደራሽነቱን ለማስፋት ባደረገው እንቅስቃሴ በመላ አገሪቱ 30 አዳዲስ ቅርንጫፎች በመክፈት የባንኩን ጠቅላላ ቅርንጫፎች 150 ማድረሱን፣ በሞባይልና በኤጀንት ባንኪግ 1,400 ወኪሎችን በመላ አገሪቱ መመልመሉን ገልጿል፡፡
የሄሎ ካሽ ደንበኞች ሂሳብ ከመቀበልና ከመክፈል ባለፈ፣ ለሞባይል ካርድ መሙላት፣ ለመዝናኛ፣ ለሲኒማ ቲኬት መቁረጥና ቦታ ማስያዝ፣ ለየብስ ትራንስፖርት፣ የባስ ቲኬት ለመቁረጥ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቲኬት ለመቁረጥ በአጠቃላይ ከ47ሺህ በላይ ለሆኑ ደንበኞች አገልግሎት በመስጠት ከ69 ሚሊዮን ብር በላይ ማንቀሳቀሱን አስታውቋል፡፡
ዲሊዮት የተባለ ዓለም አቀፍ ድርጅት ባደረገው ጥናት፤ አንበሳ ኢንተርናሽናል ባንክ “ለሰራተኞቹ ምቹ የሥራ ቦታ በመፍጠር” ለሁለተኛ ጊዜ 1ኛ ደረጃ ማዕረግ ማግኘቱን የጠቀሰ ሲሆን ባንኩ ከተመሰረተ 10 ዓመት እንደሞላው ታውቋል፡፡

Read 2860 times