Tuesday, 17 October 2017 10:46

የጎንደር ራስ ግንብ ሙዚየም ሰኞ ይመረቃል

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

  በ16ኛው ክ/ዘመን ከፋሲለደስ ቤተመንግስት ወጣ ብሎ የተሰራውና ከራስ ቢትወደድ እስከ ራስ ሚካኤል ስሁል ድረስ የነበሩት ከ14 በላይ ራሶች መኖሪያ የነበረው ራስ ግንብ በሙዚየምነት ተደራጅቶ የፊታችን ሰኞ ይመረቃል፡፡ ራስ ግንብ የጎንደር እህት ከተማ በሆነችው ቬንሰን ከተማ ሙሉ ወጭው ተሸፍኖ የቀደመ ማንነቱን ሳይለቅ፣ ሙሉ እድሳት ተደርጎለት፣ በ2006 ዓ.ም መመረቁ የሚታወስ ሲሆን ላለፉት ሶስት አመታት ግንቡን ሙዚየም ሊያሰኙ የሚችሉ በርካታ ቁሳቁሶች ሲሰበሰቡ መቆየታቸውን ባለፈው ሳምንት ሙዚየሙን ሲጎበኙ ለነበሩ ጋዜጠኞች ተገልጿል። ሙዚየሙ በአሁኑ ወቅት በተለይ አፄ ኃይለስላሴ ዋና መኖሪያ አድርገውት በነበረበት ጊዜ የነበረውን የእቴጌ  መነን የመኝታ፣ የመዋቢያ፣ የመታጠቢያና የመኝታ አልጋ፣ ጨምሮ የጃንሆይ አልጋ በክር ጥልፍና በስዕል የተሰራ ምስል፣ የመመገቢያ ጠረጴዛና ወንበሮች፣ ብራና መፅሀፍት ይዟል፡፡
በደርግ ግዜ ቦታው ወጣቶች እየታፈሱ የሚታጎሩበትና የሚገረፉበት ቦታ ሆኖ እንደነበር የገለፁት የሙዚየሙ ሃላፊዎች፤ ይህን የሚያሳይ ስዕልም ተስሎ በሙዚየሙ ውስጥ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ ግንቡ በጣሊያን ወረራ ጊዜ ጣሊያኖች መኖሪያ አድርገውት የነበረ ሲሆን ሲወጡ ትተውት የወጡት በርካታ በጣሊያንኛና በእንግሊዝኛ የተፃፉ መፅሀፍቶችን የያዘ የመፅሀፍ መደርደሪያም ይገኝበታል፡፡
በሙዚየሙ መግቢያ ላይ የትኞቹ ራሶች ምን ምን ይጠቀሙ እንደነበር፣ የትኛውን ክፍል ለምን ተግባር ይጠቀሙበት እንደነበር የሚገልፅ ጽሑፍ በብራና መልክ ተዘጋጅቶ በአማርኛ፣ በእንግሊዝኛና በሌሎችም ቋንቋዎች ተፅፎ፣ አስጎብኚዎች ለጎብኚዎች ገለፃ እንደሚያደርጉበት የጠቆሙት ኃላፊዎቹ፤ በዛን ወቅት ከአያት ቅድመአያት የተወረሱ የነገስታቱ ቁሳቁሶች ያሏቸው የከተማው ነዋሪዎች እንዳሉና ለሙዚየሙ በሽያጭ፣ በውሰትም ሆነ በግዢ እንዲሰጡ ጥያቄ መቅረቡንና ወደፊትም ብዙም ባይሆን የተወሰኑ እቃዎች ይገኛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ኃላፊዎቹ ገልፀዋል፡፡ ግንቡ ከነገ በስቲያ የክልሉ የባህልና ቱሪዝም ኃላፊዎች፣ የጎንደር ከተማ አስተዳደር ኃላፊዎችና በቱሪዝም ላይ የተሰማሩ ድርጅቶች እንዲሁም ግለሰቦች በተገኙበት እንደሚመረቅ ተገልጿል፡፡

Read 1225 times