Tuesday, 17 October 2017 11:05

የሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ፤ በዩኔስኮ የተመዘገበበት 50ኛ ዓመት!

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(3 votes)

 የሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ በተባበሩት መንግስታት የትምህርት የሳይንስና የባህል ተቋም (ዩኔስኮ) በዓለም ቅርስነት የተመዘገበበት 50ኛ ዓመት የወርቅ ኢዮቤልዩ በዓል ትላንት በሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ ጽ/ቤት ተከበረ፡፡
ፓርኩ በጥበቃ መጓደል፣ በደን መጨፍጨፍና በአካባቢው ህዝብ የታረሰ እንስሳትም እየተሰደዱ አደገኛ ሁኔታ ውስጥ መሆኑን የተመለከተው ዩኔስኮ፤ በአደጋ ላይ ነው በሚል መዝግቦት እንደነበረና ሁኔታዎች በአስቸኳይ ካልተስተካከሉ ሊሰርዘው እንደሚችል አስጠንቅቆ ነበር፡፡ በክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮና በአጋር አካላት ርብርብ ፓርኩ ወደነበረበት መመለሱን ካረጋገጠ በኋላ በሰኔ ወር 2009 ዓ.ም ከአደጋ ቀጠናነት መሰረዙም ተገልጿል፡፡
ፓርኩ በ1960ዎቹ በህዝብ ተከልሎ ሲጠበቅ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን እ.ኤ.አ በ1978 ዓ.ም በዩኔስኮ ተመዝግቦ የዓለም ቅርስ መሆኑና በተለይ በአገራችን በሰሜን ተራራ ብቻ የሚገኘው ዋልያ፣ ጭላዳ ዝንጀሮ፣ ቀበሮ ጉሬዛና በርካታ አዕዋፋትን የያዘው እንደ ውጬ፣ ዝግባ፣ ወይራና ዋንዛ የመሳሰሉ ዛፎችና በርካታ አይነት እፅዋት የሚገኝበት ሲሆን 138 ስኩየር ኪሎ ሜትር እንደሚሸፍን ይታወቃል። በአሁን ወቅት የሰሜን ጎንደር ዞን ዋና ከተማ ከሆነችው ደባርቅ ከተማ በ5 ኪ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው ሊማሊሞ ከተለያዩ የተፈጥሮ ውበቶቹ ጋር በፓርኩ ስር ተጠቃልሎ፣ የፓርኩ ስፋት ወደ 412 ስኩየር ኪሎ ሜትር ማደጉን የወረዳው ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊዎች ተናግረዋል፡፡ የፓርኩ 50ኛ አመት እና ከአደጋ ቀጠናነት የተሰረዘበት 3ኛ ወር በደባርቅ ከተማና በፓርኩ ፅ/ቤት፣ የዱር እንስሳት ጥበቃና ልማት ባለስልጣን፣ የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሀላፊዎች፣ ጋዜጠኞችና የክልሉ የስራ ሀላፊዎች በተገኙበት በሲምፖዚየም፣ በጉብኝትና በተለያዩ ስነ-ስርዓቶች በትላንትናው ዕለት መከበሩም ታውቋል፡፡

Read 2566 times