Tuesday, 17 October 2017 10:49

የጥጥ ምርትን ከ12 እጥፍ በላይ በማሳደግ ከአፍሪካ ቀዳሚ የመሆን ትልም

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(0 votes)

  በአሁኑ ወቅት 138 ሺህ ቶንስ የሆነውን የጥጥ ምርት በ15 ዓመት ውስጥ በ2025 በ12 እጥፍ በማሳደግ ከ2 ሚሊዮን ተኩል በላይ በማድረስ ኢትዮጵያን ከአፍሪካ ቀዳሚ ጥጥ አምራች የሚያደርግ ብሔራዊ ስትራቴጂ ይፋ ሆነ፡፡
“ብሔራዊ የጥጥ ልማት ስትራቴጂ” የተሰኘው ሰነድ ከትናንት በስቲያ በኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል በተደረገው ጉባኤ፤ በጥጥ በጨርቃጨርቅና አልባሳት ዘርፍ የተሰማሩ አምራቾችና ባለድርሻ አካላት፣ በስትራቴጂው ይዘትና ትግበራ ላይ የተወያዩ ሲሆን ስትራቴጂው፣ የጥጥ ምርትና ምርታማነትን በማሻሻል፣ በአጭር ጊዜና በፍጥነት የጥጥ ምርትን መጠን በማሳደግ፣ ኢትዮጵያን ከአፍሪካ ቀዳሚ እንደሚያደርግ ተገልጿል፡፡
ስትራቴጂው ስድስት ክፍሎች ያሉት እንደሆነ የገለጹት የኢንዱስትሪ ሚ/ር ዴኤታ ዶ/ር መብረሃቱ መለሰ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፤ በፍጥነት ወደ ተግባር መገባት ያለበት፣ አሁን ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮች እየገቡ ያሉት ትልልቅ ኩባንያዎች ጥሬ እቃውን ከውጭ አገር እያመጡ ሰፍተው እየላኩ ስለሆነ፣ ጥሬ ዕቃውን በአገር ውስጥ ማቅረብ ስላለብን ነው ብለዋል፡፡
ስትራቴጂው የመንግሥት ወይም የኢንዱስትሪ ሚ/ር ብቻ ሳይሆን የግሉን ዘርፍ ጨምሮ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት (ከእርሻው እስከ ዓለም አቀፍ ገበያ) የሚሳተፉበት ስለሆነ ተዋናዮች ተቀናጅተው በጋራ የሚሰሩበት፣ ሀገራዊ ስትራቴጂ እንደሆነ ዶ/ር መብረሃቱ ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ በጥጥ ምርት ግብአት (መሬት፣ ውሃ፣ የአየር ንብረት፣ …) የታደለች ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶችና ብሄራዊ ስትራቴጂ ስላልነበራት “ነጭ - ወርቅ” በሚባለው የጥጥ ዘርፍ እስካሁን ተጠቃሚ አልሆነችም ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ በዘርፉ በሚታዩ ችግሮችና መወሰድ ባለባቸው መፍትሄዎች ከባለድርሻ አካላት ጋር በጎንደር፣ በሐዋሳና በአፋር ውይይት አድርገን ባገኘነው ግብአት፤ ይህንን ብሔራዊ የጥጥ ልማት ስትራቴጂ ቀርፀናል፡፡ የግል ባለሀብቶች ወደ እርሻው እንዲገቡ እንፈልጋለን፡፡ ሰፋፊ የኢንዱስትሪ ፓርኮችም በቦሌ ለሚ፣ በሀዋሳ፣ በመቀሌና በኮምቦልቻ ተከፍተው፣ ለጥጥ እርሻ ተስማሚ የሆነ የ3 ሚሊዮን ሔክታር መሬት ኮሪደር ተለይቷል፡፡ መሠረት ልማት ተዘርግቷል፣ የገንዘብ ብድር ይሰጣል፣… ስለዚህ ባለሀብቶች ወደ ዘርፉ ገብተው ማልማት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡
የጥጥ፣ የጨርቃ ጨርቅና የአልባሳት ዘርፍ በርካታ የሰው ኃይል ስለሚጠቅም ለብዙ ዜጎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥሩ ጠቅሰው፤ አይካ ብቻውን ከስምንት ሺህ በላይ ሠራተኞች ቀጥሮ እያሠራ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ዘርፍ በሁለተኛው የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ውስጥ ከፍተኛ ትኩረት ከተሰጣቸው ዘርፎች ውስጥ አንዱ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን መንግሥት፣ ከዘርፉ ሁነኛ ኢንቨስትመንት ለመሳብና ከ2008-2012 ከወጪ ንግድ እስከ አንድ ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት አቅዶ እየሠራ መሆኑ ታውቋል።
ስትራቴጂው በፍጥነት በእርሻውና በምርታማነቱ ላይ እንደሚያተኩር የጠቀሱት ሚ/ር ዴኤታው፤ ዘርፉን ለማሻሻልና ለማሟላት የሚያስፈልጉ የተለያዩ ደንቦች መመሪያዎችና ማበረታቻዎች እንደሚኖሩት፣ ግብርናው፣ ኢንዱስትሪውና የንግድ ዘርፉ፣… የሚሳተፉበት ስለሆነ እነዚህ አካላት በጋራ ተቀናጅተው የሚሠሩበት ተቋማዊ አደረጃጀት፣ አምራቾች ፀረ-አረምና ፀረ- ተባይ ኬሚካሎች ስለሚጠቀሙ፣ በአካባቢው ምህዳር ላይ ጉዳት እንዳይደርስ የአጠቃቀምና የአያያዝ መመሪያ ይዘጋጃል፡፡ ከሁሉም በላይ ጥጥ፣ ዓለም አቀፍ ምርት ስለሆነ የዋጋ መዋዠቅ እንዳያጋጥም፣ በዓለም ላይ ከሌሎች አምራቾች ጋር ተወዳድሮ እንዲሸጥ የጥራት ደረጃው አስተማማኝ መሆን ስላለበት፣ በዚህ ላይ አተኩረን መሥራት ይጠበቅብናል ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡
ዘርፉ-ግዙፍ ኢንቨስትመንት በመሳብ ላይ ቢሆንም ዘለቄታዊ ዕድገቱን የሚጎትቱ ማነቆዎች እየተፈታተኑት እንደሆነ የተጠቀሰ ሲሆን ለአገር ውስጥ የጨርቃጨርቅ ፋብሪካዎች ፍጆታ የሚውል ተፈላጊውን የጥራት መስፈርት የሚያሟላ የጥጥ አቅርቦት እጥረት፣ የዋጋ መዋዠቅን መቋቋም የሚያስችል የግብይትና የግብአት አቅርቦት ሥርዓት ያለመኖር፣ ለጥጥ አምራቾች የሚሰጠው ሁሉን አቀፍ ድጋፍና ክትትል አገልግሎት አናሳነት፣ አምራቾች ከጥጥ መዳመጫ ድርጅቶች ጋር ያላቸው ደካማ ትስስር፣… ጥቂቶቹ መሆናቸው ተጠቅሷል፡፡

------------------------------------------

Read 1110 times