Tuesday, 17 October 2017 10:44

የመን በአለማችን ታሪክ እጅግ በከፋው የኮሌራ ወረርሽኝ ተጠቅታለች

Written by 
Rate this item
(2 votes)

ወረርሽኙ 815 ሺህ የመናውያንን አጥቅቷል፤ 2 ሺህ 156 ሰዎችን ገድሏል
   በእርስ በእርስ ጦርነት በደቀቀቺዋ የመን፣የተቀሰቀሰውና ባደረሰው ጥፋትም ሆነ በስርጭቱ ፍጥነት በአለማችን ታሪክ እጅግ የከፋው እንደሆነ
የተነገረለት የኮሌራ ወረርሽኝ፣ ከ815 ሺህ በላይ የአገሪቱን ዜጎች ማጥቃቱንና 2 ሺህ 156 ሰዎችን መግደሉን የአለም የጤና ድርጅት አስታውቋል፡፡
የኮሌራ ወረርሽኙ በፍጥነት በመዛመት ላይ እንደሚገኝ የጠቆመው ድርጅቱ፤ በመጪዎቹ ሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ ከአንድ ሚሊዮን በላይ
የአገሪቱን ዜጎች ያጠቃል ተብሎ እንደሚጠበቅና ከእነዚህም መካከል ከ600 ሺህ በላይ ያህሉ ህጻናት መሆናቸውን ከትናንት በስቲያ ባወጣው መግለጫ አመልክቷል፡፡ በየቀኑ 4 ሺህ ያህል የመናውያን በኮሌራ እንደሚጠቁ የገለጸው ድርጅቱ፣ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ተጠቂዎች እድሜያቸው ከ5 አመት በታች የሆኑ ህጻናት መሆናቸውን የጠቆመ ሲሆን ርሃብና የምግብ እጥረት ወረርሽኙን እያባባሱት እንደሚገኝና አለማቀፉ ማህበረሰብ አፋጣኝ ምላሽ ካልሰጠ በአገሪቱ የከፋ ጥፋት እንደሚከሰትም አስረድቷል፡፡ በአገሪቱ የተከሰተውን የከፋ የኮሌራ
ወረርሽን ለመግታት የሚደረገው ጥረት በቂ አለመሆኑን የጠቆመው ድርጅቱ፤ የጽዳት ሰራተኞች ደመወዛቸው ስላልተከፈላቸው የስራ ማቆም አድማ ማድረጋቸውን ተከትሎ፣ ቆሻሻዎች በየመንገዱ እየተጣሉ አስከፊ የጤና እክል እየፈጠሩ ነው ብሏል። ሰባ በመቶ የሚሆነው የአገሪቱ ህዝብ የንጹህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት እንደማያገኝ የዘገበው ዘ ጋርዲያን፤ የአገሪቱ መንግስት ካለፈው አመት አንስቶ ለህዝብ የጤና ተቋማት የሚሰጠውን የገንዘብ ድጋፍ ማቋረጡንና በርካታ የአገሪቱ ዶክተሮችና የሆስፒታል ሰራተኞች ደመወዛቸውን ካገኙ ከአንድ አመት በላይ እንዳለፋቸውም አስታውሷል፡፡

Read 2417 times