Tuesday, 17 October 2017 10:38

የምንዛሪ ለውጡና አንደምታው?!

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ ለፓርላማው እና ለፌዴሬሽን ምክር ቤት የመክፈቻ ንግግር ባደረጉበት ወቅት የመንግስት የአመቱ የትኩረት አቅጣጫዎች ብለው ከጠቆሙት መካከል የውጭ ምንዛሬ ተመንን የማሳደግ ጉዳይ አንዱ ነበር፡፡ የፕሬዚዳንቱን ንግግር ተከትሎም ብሄራዊ ባንክ በሰጠው መግለጫ፤ የብር የምንዛሪ ተመን በ15 በመቶ መቀነሱን አስታውቋል፡፡ በዚህም መሠረት፤ በ23.88 ይመነዘር የነበረው አንድ ዶላር ወደ 26.96 ብር ከፍ እንዲል ተደርጓል፡፡ የምንዛሪ ለውጡ ያስፈለገበት ዋነኛ ምክንያት እየተዳከመ የመጣውን የወጪ ንግድ ለማበረታታት ነው ተብሏል፡፡ ለመሆኑ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ምን ይላሉ? ጥቅምና ጉዳቱ ምንድን ነው? የተፈለገውን ውጤትስ ያመጣ ይሆን? የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ሁለት የኢኮኖሚ ባለሙያዎችን አነጋግሮ ትንታኔያቸውን እንደሚከተለው አጠናቅሮታል፡፡

                  “ተጎጂው ሸማቹ ህብረተሰብ ነው”
                      አቶ ሞሼ ሰሙ (የኢኮኖሚ ባለሙያ)

     የውጭ ምንዛሬ በ15 በመቶ የመጨመሩ አንድምታው ምንድን ነው?
በመጀመሪያ ማየት ያለብን መጨመሩ ለምን አስፈለገ የሚለውን ነው፡፡ በመንግስት በኩል የሚቀመጡ ምክንያቶች አሉ፡፡ አንደኛው ምክንያት፣ የውጭ ምንዛሬ አቅርቦት በሚፈለገው ደረጃ እያደገ አይደለም፤ ከጊዜ ወደ ጊዜ በጣም እየተዳከመ ስለመጣ፣ ይሄን ወደተሻለ ደረጃ ለማምጣት የብርን የመግዛት አቅም በመቀነስ ለውጪ የሚቀርበው ምርት በሌላ ሀገር ገበያ ላይ ተወዳዳሪ እንዲሆን ያስፈልጋል በሚል ስሌት ነው፡፡ በዚህም ወደ ውጪ ሸቀጥ ልከን የምናገኘው የውጪ ምንዛሬ ይጨምራል፡፡ የኤክስፖርት መጠኑም ይጨምራል፡፡ ይሄ እንግዲህ በውስጡ ሁለት ነገር አለው፡፡ አንደኛ ዋጋ ሲቀነስ ዋጋ በመቀነሱ ምክንያት የሚገኘው የዶላሩ መጠን ይቀንሳል፡፡ ይህ ሊሆን የሚችለው ምርት በከፍተኛ መጠን ወደ ውጪ ሄዶ ይሸጣል ከሚል ስሌት ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ከውጪ ተገዝተው የሚገቡ እቃዎች (ገቢ ንግድ) ከመጠን በላይ እየጨመረ ስለሆነ (የክሬዲት ዴፊሲት) የንግድ ሚዛኑ ልዩነቱ እየጨመረ መጥቷል፡፡ በ2015 የነበረው አሃዛዊ መረጃ የሚያሳየው የ3.2 ቢሊዮን ዶላር የውጪ ንግድ ሲፈፀም፣ 15.6 ቢሊዮን ዶላር አካባቢ ደግሞ ወደ ሀገር ውስጥ ያስገባንበት መጠን ነው፡፡ ይሄ ልዩነቱ በጣም ከፍተኛ መሆኑ ያሳያል። ይሄን ማጥበብ ያስፈልጋል፡፡ ለማጥበብ ደግሞ መንግስት የተከተለው መንገድ ኤክስፖርትን በማበረታታት፣ ከፍተኛ ገቢ ማግኘት የሚል መርህን ነው፡፡ መንግስት ይሄን አቋም ለመውሰድ አስገድዶኛል ያላቸው መሰረታዊ መነሻዎች እነዚህ ናቸው፡፡ በአንድ በኩል መንግስት በውጪ ምንዛሬ የተገኙ ትልልቅ ብድሮችን የመክፈል አቅሙም በከፍተኛ ሁኔታ ፈተና ውስጥ እየወደቀ ነው። ያንን የመክፈል አቅም ለማጠናከር በውጪ - ገቢ ንግድ መሃከል ያለውን ሰፊ ልዩነት ማጥበብ አለብኝ፤ ልዩነቱን ካጠበብኩ የመክፈል አቅሜ ይጨምራል የሚል እምነት አለው፡፡ ነገር ግን የተደረገው የምንዛሬ ለውጥ የጤናማ ኢኮኖሚ ምልክት አይደለም፡፡
በምንዛሬ ተመኑ መጨመር በእርግጥ መንግስት ያሰበውን  ሊያሳካ ይችላል?
በመጀመሪያ ደረጃ የብርን የመግዛት አቅም በዚህ ደረጃ መቀነስ፣ የመጀመሪያ ተጠቂ የሚያደርገው ሸማቹን ማህበረሰብ ነው፡፡ አብዛኛው የምንጠቀመው ከውጪ የሚገባ ነው። ስለዚህ ደሞዛቸው መሻሻል የማያሳይ ዜጎች፣ የመጀመሪያዎቹ የችግሩ ሰለባ ይሆናሉ፤ የመግዛት አቅማቸው ይዳከማል፡፡ ኢኮኖሚውን ወደ ግሽበት ከሚወስዱት አንደኛው የነዳጅ ዋጋ መጨመር ነው። የነዳጅ ዋጋ መናር ደግሞ በሌሎች ሸቀጦች ላይም የዋጋ ጭማሪ ያመጣል፡፡ ሌላው ደግሞ የጉልበት ዋጋ መጨመር ነው፡፡ ሶስተኛው ደግሞ ኢትዮጵያ በሃገር ውስጥ ምርት ፍላጎትን ማሟላት ያልቻለችባቸው እንደ ስኳር፣ ስንዴ፣ ዘይት የመሳሰሉት  በብር ዋጋ ማጣት ምክንያት ዋጋቸው ይጨምራል፡፡ በአጭሩ ወደ ሁለት አሃዝ ጨምሮ በነበረው የሸቀጦች የዋጋ ግሽበት ላይ የበለጠ ይሄ ተደማሪ ነው የሚሆነው፡፡
በ2010 እ.ኤ.አ በ17 በመቶ የተጨመረው የውጭ ምንዛሬ ያስከተለው የዋጋ ግሽበት ወደ 40 በመቶ የሚጠጋ ነበር፡፡ የአሁኑ የ15 በመቶ ጭማሪ ደግሞ የሚያስከትለውን ወደፊት የምናየው ይሆናል። ስለዚህ የምንዛሬ ተመን ጭማሬም በመጀመሪያ የሚያስከትለው ችግር የዋጋ ግሽበት ነው፡፡ ይሄ ደግሞ ተያያዥና ተቀጣጣይነት ያለው ነው የሚሆነው፡፡ የጉልበት ዋጋ ጨመረ ማለት ምርት ላይ ጭማሪ ይከተላል ማለት ነው፡፡ ትራንስፖርት ጨመረ ማለት ሁሉም ሸቀጥ ጨመረ ማለት ነው፡፡ ይሄ ቀጥተኛ ተፅዕኖው ነው፡፡
የብር የመግዛት አቅም መቀነስ ተጠቂ ሊሆኑ የሚችሉ ሌሎች አካላት እነማን ናቸው?
ሁለተኛ ተጠቂ ሊሆኑ የሚችሉት በባንክ ተቀማጭ ገንዘብ ያላቸው ሰዎች ናቸው፡፡ ተቀማጭ ገንዘብ ያላቸው ሰዎች ደግሞ በተግባር ኢንቨስተሮች ናቸው፡፡ በልማት ወይም በኢንቨስትመንት ላይ ሳያውሉ ባንክ ውስጥ ያስቀመጡት ወለድ እናገኝበታለን ከሚል ስሌትም ነው። እነዚህ ሰዎች ያስቀመጡት ገንዘብ ትናንትና እና ዛሬ ዋጋው የተለያየ ሆኗል፡፡ የትናንት መቶ ብር ዛሬ 85 ብር ሆኗል፡፡ ትናንት የመቶ ብር እቃ፣ ዛሬ 115 ብር ነው የሚሆነው፡፡ ስለዚህ የእነዚህ ሰዎች ገንዘብ የመግዛት አቅሙ ስለሚዳከም ተጎጂዎች ናቸው። የመጀመሪያ ቀጥተኛ ተጎጂ የሚሆነው አብዛኛው ማህበረሰብ ወይም 80 በመቶ የሚሆነው ነው። በባንክ ብር ያስቀመጡት ከእነዚህ አንፃር ትንሽ ናቸው ማለት ይቻላል፡፡
የሚፈጠረው ጉዳት መንግስት አገኘዋለሁ ከሚለው ውጤት አንፃር እንዴት ይመዘናል?
ኢትዮጵያ 89 በመቶ የውጪ ንግዷ የግብርና ምርት ነው፡፡ የግብር ምርት በባህሪው ከምርቱ መብዛት አንፃር ገበያ ላይ የመገዛት እድሉ የተለጠጠ ወይም ሰፊ አይደለም፡፡ ለምሳሌ የኤሌክትሮኒስ እቃ በማንኛውም ጊዜ የመገዛት እድሉ ሰፊ ነው፡፡ የግብርና ምርቶች ግን ይሄ አይነቱ እድል የላቸውም። የተለየ ፍላጎት የሚታይባቸው አይደሉም፤ የግብርና ምርቶች በባህሪያቸው፡፡ ፈላጊያቸው ተመሳሳይና ወጥ ነው፡፡ ለዚህ ተብሎ የውጪ ምንዛሬ መጨመሩ፣ ኤክስፖርት በሚደረገው መጠን ላይ በሚፈለገው ደረጃ አይጨምርም፡፡ እንደውም የገንዘብ የመግዛት አቅም በመቀነሱ፣ ወደ ሀገር ቤት የሚገባው ሸቀጥ ዋጋ ይንራል፡፡ ስለዚህ በግብርና ምርት ላይ ተመስርቶ ኤክስፖርትን አበረታታለሁ፣ ኤክስፖርትን ለማበረታታት ደግሞ በቀጥታ ዋጋ እቀንሳለሁ የሚለው ፖሊሲ፣ በሌሎች ፖሊሲዎችና በሌላ የፊዚካል ፖሊሲ ካልተደገፈ ብቻውን የትም አያደርስም፡፡
ለምሳሌ ቡናውን እዚሁ ፈጭቶ እሴት ጨምሮ፣ ኤክስፖርት የሚደረግበት መንገድ ካልተፈጠረ በስተቀር በሚፈለገው ደረጃ የሚፈለገው የውጪ ምንዛሬ አይገኝም፡፡ ይሄ አንዱ ያልታየ ችግር ነው። በሁለተኛነት የሀገር ውስጥ አምራቾች፣ ከውጪ የሚገባ ሸቀጥን የሚተካ ምርት እንዲያመርቱ ነው የሚፈለገው፤ ነገር ግን እነዚህ አምራቾች 90 በመቶ የሚሆኑት ኢትዮጵያ ውስጥ ያለ የተፈጥሮ ሀብትን አውጥተው ወደ ምርት የሚለውጡ አይደሉም፡፡ አምራቾቹ ራሳቸው ከ20 እስከ 40 በመቶ ጥሬ እቃ ከውጪ ነው የሚያስገቡት፡፡ እነዚህ ሰዎች አሁን በውድ ዋጋ ከውጪ ጥሬ እቃ አምጥተው፣ ምርት በማምረት ተወዳዳሪ መሆን የሚያስችል አቅም አይኖራቸውም፡፡ እንዲሁም በሀገር ውስጥ ያለው የምርት ግብአት ዋጋ ስለሚጨምርባቸው ሌላ ንረት ይከተላል፡፡ ስለዚህ እነዚህ ሰዎች ሁለት ጭማሪ ይዘው ነው ሊሰሩ የሚገደዱትና በመጨረሻም ወደ ተጠቃሚ ምርታቸውን የሚያወርዱት፤ ስለዚህ አሁንም የተሻለ ዋጋ የሚኖረው እዚህ ከሚመረተው ይልቅ ከውጪ በሚመጣው እቃ ላይ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት የሚፈለገውን ግብ ለመምታት በጣም ያዳግተዋል፡፡ ሌላው ደግሞ የሀገር ውስጥ ምርትን የኤክስፖርት ተወዳዳሪ እናደርጋለን የሚለው ነው፡፡ አምራቹ ግን የመብራት ችግር፣ የጉልበት ዋጋ ንረት አለ፤ በሚገባ 8 ሰዓት የሚሰራ ጉልበት በበቂ ሁኔታ አይገኝም፤ የታክስ ስርአቱ፣ የትራንስፖርት ስርአቱ፣ ወደብ የለም-- ወዘተ፡፡ እነዚህን ሁሉ ተሸክመው ነው አምራቾች ወደብ ካላቸው፣ አስተማማኝ መሰረተ ልማት ከተሟላላቸው የሌላ ሀገር ነጋዴዎች ጋር  እንወዳደራለን እየተባለ ያለው። ይሄ እንዴት ያዋጣል? ለቻይናዎች ይሄ ቀላል ሊሆን ይችላል። ለኢትዮጵያ ግን ይሄ አስቸጋሪ አካሄድ ነው፡፡ ስለዚህ ይሄ የምንዛሬ ለውጥ በመደረጉ ይገኛሉ ተብለው የተሰሉት አዎንታዊ ውጤቶች አይገኙም ማለት ይቻላል። የሚብሰው ህዝቡ የሚሸከመው ችግር ነው፡፡ በረጅም ጊዜ ውስጥ ምንም አዎንታዊ ውጤት የለውም፤ በአጭር ጊዜም ብናስበው የሚያስከትለው ማህበራዊ ቀውስ ይብሳል፡፡ ግሽበትና አለመረጋጋትን ነው የሚያመጣው፡፡
እርግጥ ነው መንግስት የውጭ ምንዛሬ እጥረት አለበት፣ ብድር ለመክፈል ተቸግሯል፡፡ ከዚህ አንፃር የዓለም ባንክ፣ ይሄን የዋጋ ማስተካከያ ካደረጉ ብድር ሊሰጣቸው ተስማምተው ሊሆን ይችላል ማስተካከያውን ያደረጉት የሚል ግምት አለኝ። አሁን እያንዳንዱ ደሞዝተኛ፣ የደሞዙ የመግዛት አቅም በ15 በመቶ ቀንሷል፡፡ በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ውስጥ በአገር ውስጥ አቅርቦት ላይ በቂ ስራ ባልተሰራበት ሁኔታ፣ ከውጭ የሚመጣውንም ጨምሮ ማናር ብዙ ችግር ይፈጥራል፡፡
መንግስት ማድረግ የነበረበት ምንድነው?
እኔ የሚመስለኝ ገበሬዎች ኤክስፖርትን የሚመጥን ምርት እንዲያመርቱ ማድረግ ነው አንዱ። አሁን ግን ዝም ብሎ ነው ምንዛሬው ላይ ለውጥ የተደረገው፡፡ በባለሙያዎች ቋንቋ እንዲህ አይነቱ እርምጃ ከውጥረትና ከጭንቀት የመጣ እርምጃ ነው የሚባለው፡፡ ምክንያቱም ወጥ የሆነ የፖሊሲ አቅጣጫ የተከተለ አይደለም፡፡ አስቀድሞ ተከታታይ ስራዎች ቢሠሩ ኖሮ፣ እንዲህ ያለ ድንገተኛ እርምጃ አይወሰድም ነበር፡፡
በግልፅ ለመናገር፣ አሁን በዚህ ምንዛሬ ለውጥ የተነሳ የአባይ ግድብ የግንባታ ዋጋ በእጅጉ ሊንር ይችላል፡፡ ምክንያቱም በርካታ በውጭ ምንዛሬ የሚገቡ እቃዎች ነው የሚያስፈልጉት፤ ይሄ ኋላ ላይ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታውንም ጥያቄ ላይ ይጥለዋል። ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ የሌለው ታሪካዊ ግድብ ከመስራት አያልፍም ማለት ነው፡፡ ይሄ ቀላል ነገር አይደለም፡፡

----------------------

                          “የምንዛሬ ለውጡ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል”
                                ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ በርሄ (የኢኮኖሚ ባለሙያ)

    የምንዛሬ ለውጡ  ምን ውጤት  ያመጣል?
ከዚህ በፊትም በፈረንጆች 2010 የ22 በመቶ ጭማሪ ተደርጎ ነበር፡፡ በወቅቱ እንደውም አይኤምኤፍ ጠይቆ ሳይሆን መንግስት በራሱ ነበር ያደረገው፡፡ ዋናው ምክንያት ኤክስፖርት ለመጨመርና የውጭ ምንዛሬ እንዲገኝ ለማስቻል የሚል ነው፡፡ አሁን ኤክስፖርት እያደረግን ያለነው ቡና እና ሰሊጥ ነው፡፡ ከእነዚህ ምርቶች የሚገኘው ምንዛሬ መጠን ከፍ ሊል ይችላል የሚል ስሌት ነው ያለው፡፡ ሌላው ወደ አረብ ሀገራት የሚሄዱ የቤት ሰራተኞች፣ በኢትዮጵያ ምንዛሬ የተሻለ ገንዘብ እንዲያገኙ ይረዳቸዋል ከሚል ይመስላል፡፡ በሌላ በኩል የጥቁር ገበያ የዶላር ምንዛሬን ለመግደልም ይሆናል፡፡ ነገር ግን ይሄ ብዙም አያዋጣም፤ ጥቁር ገበያውም ሊጨምር ይችላል፡፡ ዋናው ጉዳይ ግን በባንኮች ውስጥ በርካታ የውጭ ምንዛሬ እንዲኖር ለማድረግና የምንዛሬ እጥረቱን በመቅረፍ ከውጭ የሚመጡ ጥሬ እቃዎችን ለማስገባት ይጠቅም ይሆናል፡፡
በዚህ ሳቢያ የሚፈጠሩ ችግሮችና አዎንታዊ ውጤቶች ምንድን ናቸው?
አንዱ ትልቁ ችግር፣ አሁን ወደ ሀገር ውስጥ በዋናነት የምናስገባው ነዳጅ ነው፡፡ ሌላው የቢራ ብቅል ነው፣ የምግብ ግብአትና ማዳበሪያም፣ አልባሳትም ከውጭ ይመጣሉ፡፡ እነዚህ ሁሉ በከፍተኛ መጠን ዋጋቸው እየጨመረ ነው የሚሄደው፤ ስለዚህ ቋሚ ገቢ ባላቸው በተለይ በመንግስት ሠራተኞችና በጡረታ በተገለሉ አዛውንቶች ላይ ከፍተኛ ጫና ነው የሚፈጠረው። በሁለተኛ ደረጃ ነዳጅ ከጨመረ ሁሉም ነገር ይጨምራል፡፡ እርግጥ ነው ብዙ አጥንተውበት ያደረጉት ይመስላል፡፡ በዚያው ልክ አበዳሪዎችም ከፍተኛ ብድር ይሰጡናል፡፡ እኔ ግን ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ነው የታየኝ፡፡ ጉዳቱ ከፍተኛ ነው፡፡ አሁን ነጋዴው ሁሉ እቃውን ቆልፎ አቆይቶ በአዲሱ ዋጋ መሸጥ ነው የሚፈልገው፡፡ ይሄ ደግሞ ሌላ ቀውስ ነው የሚፈጥረው፡፡ በአንድ ጊዜ 15 በመቶ የብር መግዛት አቅምን መቀነስ ከፍተኛ ቀውስ ሊያስከትል ይችላል፡፡ የኤክስፖርት መጠንን የመጨመሩ ጉዳይ ደግሞ በጊዜው የምናየው ነው የሚሆነው፡፡
በዜጎች ላይ የሚያስከትለው ቀጥተኛ አሉታዊ ተጽዕኖ ምንድነው?
የቤት ኪራይ፣ በአጠቃላይ የሸቀጦች ዋጋ፣ የመጠለያ፣ ምግብና አልባሳት ዋጋ ይንራል፡፡ ስለዚህ ሁኔታው በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ ገበያውን ትልቅ ቀውስ ውስጥ ይከተዋል፡፡ እርግጥ እስካሁን መጠነኛ ማስተካከያዎች ሲደረጉ ቆይተዋል፡፡ እነዚያ ግን ጉዳታቸው ዝቅተኛ ነበር፡፡ በአንድ ጊዜ 15 በመቶ ጨመረ ሲባል ግን ቀውሱ ቀላል አይደለም። በየጊዜው 5፣ 3፣ 2 በመቶ እየጨመሩ ቢሄዱ ነበር መልካም የሚሆነው፡፡
መንግስት ሊወስደው የሚችለው ሌላ የተሻለ አማራጭ ነበር?
አንዱ ከውጭ  የሚገቡ ሸቀጦችን በሃገር ውስጥ ምርቶች የመተካት አማራጭ ነው፡፡ ለምሳሌ ስኳር ፋብሪካዎች ይሠራሉ ተብሎ እስካሁን ተግባራዊ ባለመሆናቸው ስኳር ከውጭ እያስገባን ነው፡፡ ስንዴም፣ ዘይትም፣ ማዳበሪያና ሌሎችንም በሀገር ውስጥ ምርት መተካት ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ ትልቁ የውጪ ምንዛሬ የምናወጣበት የቢራ ገብስ ነው። የቢራ ገብስ ምርትን በሀገር ውስጥ በማስፋፋት ሙሉ ለሙሉ ከውጭ አለማስገባት አንዱ አማራጭ ነው፡፡ መሬትና ውሃ እያለን ይሄን መስራት ለምን አቃተን? ይሄ ነው ወሳኙ ጉዳይ፡፡ የውጪ ምንዛሬ የሚፈልጉ ትልልቅ ፕሮጀክቶችንም በቅደም ተከተል መስራት ያስፈልጋል፡፡

Read 3665 times