Print this page
Tuesday, 17 October 2017 10:36

ጥቁር ምላስ!

Written by  ኃይለይ ገብረእግዚአብሔር
Rate this item
(22 votes)

 አየኋት፡፡ ክው አልኩ፡፡ የተቆለለ በረዶ ውስጥ የተዘፈቅኩ ያህል ነበር የተሰማኝ፡፡ ምንም ብትበድለኝ ሰው አይደለች፡፡ ለዛውም ህልሜ ነበረች፡፡ አዎ ያኔ ስለ እሷ አልም ነበር - የእኔ እንድትሆን፡፡ አሁን እንደዚህ ሆና ሳያት ሰውነቴ ራደ - በድንጋጤ፡፡ ከጉልበቴ በታች ያለው አካሌ ተጎምዶ የተወሰደ ያህል ተሰማኝ፡፡ አየር ላይ እየተንሳፈፍኩ ያለሁ መሰለኝ፡፡ ከሚተራመሰው የሰው መንጋ ጩኸት መሐል የጓደኛዬ ድምፅ በትንሹም ቢሆን አይሎ ጆሮዬ ውስጥ ገባ - “ምን ሆነህ ነው? ” ሲል፡፡ አፌ የሚሰራም አይመስልም ነበር፡፡ ምላሴ በቦታዋ መኖሯ ያጠራጥር ነበር፡፡ ካየኋት ከአስር አመታት በላይ ቢሆንም፣ ቀዩ ፊቷ ወደ ከሰልማነት ቢቀየርም፣ ግማሽ ፊቷ ቢቃጠልም በግማሹ ፊቷና በአንድ አይኗ በደንብ ነበር ያስታወስኳት፡፡ ዓይኖቿ ልዩ ነበሩ - ያኔ፡፡ አፍዝ አደንግዝ የሚለው ቃል በብዛት ሲነገር የምሰማው እንደ አብዛኛው ሰው ፊልም ላይ ወይም ልብ ወለድ መጽሐፍ ሳነብ አልነበረም፡፡ ሰዎች ስለ ዐይኖቿ ሲያወሩ ነው በብዛት ስሰማው የነበረው። አሁን ግን… አሁን ከእነዚያ መለያዎቿ በቅጡ የሚታየኝ አንዱ ብቻ ነው፡፡ ወይስ በድንጋጤ ብዥ ብሎብኝ ይሆን? በሆነ!
“ታውቃታለህ?” አለኝ ጓደኛዬ በእጁ እየጎተተኝ።  ግማሽ አካሌ “ምን ማወቅ ብቻ” ያለ ይመስለኛል፡፡ እንደ ተሳቢ መኪና እየጎተተኝ ብዙም ስላልተሳካለት፣ እየገፋ መንገዱ አጠገብ ወደ ነበረ ካፌ አስገባኝ፡፡ ወንበር ስቦ ቁጭ እንድል ካደረገ በኋላ ትክ ብሎ ያየኝ ጀመር፡፡ መልስ እየፈለገ መሆኑን በግማሽ ልቦናዬ ተረድቻለሁ፡፡ ግን ደግሞ ያንን የተቃጠለ ፊት ካየሁ በኋላ መላ ሰውነቴ እንደተቃጠለ ሁሉ አልታዘዝ ብሎኛል፡፡ የልቤ ትርታ እንደ ማረጋገጫ ባይሆነኝ ኖሮ፣ ነፍሴ ናት እንጂ አካሌ በድን ሆኖ ሞቻለሁ ብዬ አምን ነበር፡፡
“እንካ እስቲ ውሃ ጠጣ” አለኝ ጓደኛዬ፡፡ በግዴታ ማለት ይቻላል፣ አንዴ ፉት አልኩለት፡፡ ደርቆ የነበረ ፊቴ ነፍስ የዘራ መሰለ፡፡ ይሄንን የተገነዘበው ጓደኛዬ፣ ጥያቄውን ደገመው፡፡
“የት ነው የምታውቃት?”
የት ነው የማውቃት? እንደ ሌሎች ጊዜያት ቢሆን ‘ጥሩ ጥያቄ ነው’ ብዬ ነበር በቀልድ መልክ የምጀምርለት፡፡ አሁን ግን ምላሴ ደርቋል፡፡ ፉት ያልኩት ውሃ እንኳን ሊያወረዛውና ወደተፈጠረበት ሙያው ሊመልሰው አልቻለም፡፡ ጥያቄው ግን ጭንቅላቴ ውስጥ ይዋልል ገባ፡፡
ከአስራ አራት አመታት በፊት ነው መሰለኝ። አዲስ ተከራዮች ሆነን ወደ አንድ ቤት ገባን - እኔና አጎቴ፡፡ አጎቴ ወንደላጤ ነበር፡፡ እኔ ደግሞ የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ፡፡ ግን የስድስተኛ ወይም ሰባተኛ ክፍል ተማሪ ነበር የምመስለው፡፡ ደቃቃነቴ ላይ አይነአፋርነቴ ተጨምሮበት ገና የመናገርን ሀሁ እያጠናሁ ያለሁ ነበር የምመስለው፡፡ አባቴ አንዳች ነገር ነው የሚያክለው፡፡ እናቴም ቁመተ መለሎ ናት፡፡ ታድያ የእኔ እንደዚህ ሆኖ መፈጠር ወላጆቼን ለሚያውቁ ሰዎች ሁሉ ትንግርት ነበር፡፡ ለወላጆቼም እንዲሁ፡፡ የመጨረሻ ልጅ ስለነበርኩ “ዘር አልቆባቸው ነው” እያሉ ሲቀልዱባቸው፣ እርር ድብን እያልኩ እሰማቸው ነበር፡፡ ወላጆቼ ግን ሌሎች ስድስት ወጠምሾችና ሶስት ውብ ሴቶች ስለነበሯቸው ስቀው ነበር የሚያልፉት፡፡
ትንሽ አደግ ስል ከአጎቴ ጋር መኖር ጀመርኩ። ዘጠነኛ ክፍል ስደርስ ወደ ትምህርት ቤት የሚቀርበኝን ቤት ተከራየን፡፡ እዚያው ግቢ መኖር ከጀመርን ከአንድ ሳምንት በኋላ ነበር ለመጀመርያ ጊዜ ያየኋት፡፡ የት ነበረች እስካሁን አልኩኝ። የት እንደነበረች እጠይቃታለሁ ብዬ ቀረብ ስል ዐይኖቿን አየኋችው፡፡ ወዲያው ጥያቄውን ረሳሁት። አዲስ ተከራዮች መሆናችንን ሳታውቅ አይቀርም። ለምንም ነገር ደንታ ያላት አትመስልም። በሚያሥቅና በማያሥቅ ትሥቃለች፡፡ ሌላ ልጅ ብትሆን እናደድና ከፊቷ እጠፋ ነበር፡፡ ይችኛዋ ግን ለምን እንደ ሆነ እንጃ (ለምን እንደሆነ የዚያን ቀን ማታውኑ ተገለጠኝ- እንዲሁ በቀላሉ) ሣቅዋ ጣፈጠኝ፡፡ ጥርሶችሽ በሜትር ተለክተው ነው እንዴ የተሰሩት? ልላት ከጀለኝ (በዚያን ወቅት ሳነበው ከነበረ ከመጽሐፍ ኮርጄ)፡፡ ዝም ብላ ትሥቃለች። ስትሥቅ ዐይኖቿን ትጨፍናለች። አሁን አጠፋች እላለሁ በውስጤ፡፡ እኒዚያን ከዋክብት የሚመስሉ ዐይኖች መጨፈን የለባትም፡፡ አይኖቿን ሳትጨፍን መሣቅን መለማመድ አለባት፡፡ አለበለዚያ ይሞጨሙጫሉ ብዬ አክላለሁ፡፡ ለረዥም ደቂቃ ስለምትሥቅ ለረዥም ደቂቃ ነበር የምትጨፍነው። በቃ አንድ ቀን እኔ አለማምዳታለሁ ብዬ ለራሴም ለእሷም ቃል ገባሁ፡፡
በዚያም በዚህም ብዬ ከእሷ ጋር ለመቀራረብ አንድ ወር ፈጀብኝ፡፡ በዛ? በቦታዬ ሆናችሁ ብታዩት እንደዛ አትሉም ነበር! ከምር! እሷን ለመቅረብ የተጠቀምኳቸውን ቴክኒኮች ብነግራችሁ በእርግጠኝነት ትኮርጇቸው ነበር፡፡ እናም ቀለሜዋ መሆኔን አጎቴ እንደነገራቸው ነገረችኝ፡፡ ተናደድኩ፡፡ ‘ሰርፕራይዝ’ ላደርጋት ነበር ያሰብኩት- የሚኒስትሪ ውጤቴን በማሳየት፡፡ አጎቴ ግን ለራሱ ጥቅም ሲል አከሸፈብኝ፡፡ በአከራዮቹ ተወዳኝነት ለማግኘት ሲል ዕቅዴን ሁሉ ፉርሽ አደረገው፡፡ ቤት ኪራይ የሚቀንሱለት መስሎት ነው! ይሁን በቃ ብዬ ስንተኛ ክፍል እንደሆነች ጠየቅኳት፡፡
“ውይ እኔ እንኳን ሰባተኛ ክፍል ነኝ” ብላ በሣቅ ተንከተከተች፡፡ አሁን ይሄ ያሥቃል? አልኩኝ። ይሁን እስቲ ትሣቅ፡፡ ዐይኖቿን ስትጨፍን ግን እሳቀቃለሁ፡፡
እውነቱን ለመናገር ለማያውቀን ሰው፣ እሷ ሳትሆን እኔ ነኝ ሰባተኛ ክፍል የምመስለው - ማለቴ በግዝፈት፡፡ ብቻ ምናለፋኝ ካላላችሁ በስተቀር ካላየሁ አላምንም ልትሉ ትችላላችሁ፡፡ እሷ ስጋ እንጂ አጥንት ያላት አትመስልም፡፡ እኔ ደግሞ አጥንት እንጂ ስጋ ያለኝ አልመስልም፡፡ እሷ ስትሥቅ ጉንጮቿ ሊፈነዱ የደረሱ ፊኛዎች ይመስላሉ፡፡ እኔ ስሥቅ ድግሞ ጉንጮቼ የተወጠረ የፍየል ቆዳ ይመስላሉ፡፡ የእሷ ዐይኖች ወደ ውጭ (ስትሥቅ ካልሆነ በስተቀር) ነው የሚለጠጡት፡፡ የእኔ ግን ወደ ውስጥ፡፡ አዘናችሁልኝ? ጎሽ!
እናም የእሷን አላውቅም፤ እኔ ግን ተያዝኩኝ፡፡ ድሮውኑስ ከእንደነዚህ ዓይነት ዐይኖችና ጥርሶች፣ ከእነዚህ ጉንጮች፣ ከዚህ ፍልቅልቅነት ማን ሊያመልጥ ይችላል? እንኳን እንደ እኔ ዓይነቱ ኮስማና (ይግረማችሁ አንድም ቀን ተርቤ አላውቅም) ቀርቶ፡፡ አውቃ ይሁን በግድየለሽነት ሳይገለጥልኝ አጠመደችኝ፡፡ ያልደነደነ ሰውነቴ በማይታይ፣ በማይጨበጥ፣ እፍ ብለው በማያጠፉት የእሳት ወላፈን ይለበለብ ጀመር፡፡ ሣቅዋ ያቃጥለኛል። ዐይኖቿን ስትጨፍናቸው ያንገበግበኛል፡፡ ግድየለሽነቷ ተስፋ ያስቆርጠኛል፡፡ አለማወቅዋ ያብሰከስከኛል፡፡ ከውስጤ የሚግተለተለው የአፍላ ጭስ፣ በአምስት ሜትር ከሚርቅ ክፍሏ ዘንድ ሊደርስ አልቻለም፡፡ ቅርብ ሳለች በምናቤ፣ ሚልክ ዌይ ጋላክሲ ድረስ እቃትታለሁ፡፡  
ታዲያ ሲብስብኝ (ማለቄ ነበር) አንድ ነገር አሰብኩ፡፡ ልነግራት ብል ሁሉንም ነገር እንደማበለሻሸው ለማወቅ ማለም ሳያስፈልግ፣ ማንም ሰው ሊፈታው የሚችል ነገር ነበር፡፡ እናም የሚሞከር አልነበረም፡፡ አፌ እንኳን ‘ወድጄሻለሁ’ ሊል ቀርቶ፣ አቶ ወዳጆ የሚባሉ ጎረቤታችንን ለመጥራት ራሱ ዳገት ነው የሚሆንበት፡፡ እሷን ካየሁ ወዲህ መውደድ፣ መወደድ፣ እወድሻለሁ….የሚሉ ቃላት በቀላሉ የማይደፈሩ እጅግ የተከበሩ ቃላት ሆነውብኛል፡፡ ያኛውን ቃልማ ተዉት፡፡ ሳስበው ራሱ ያስበረግገኛል፡፡
እናም እነዚህን አፌ ሊደፍራቸው ያልቻላቸውን ቃላት፣ በብዕሬ ልወራቸው ወሰንኩ፡፡ ብዕሬ (ያኔም ቢሆን) እንደ አፌ አይደለም፡፡ ተራራን መናድ፣ ጩኸትን ማስደንገጥ፣ ዝምታን መግፈፍ፣ ጨለማን ማስፈራራት፣ ሐሩርን መቋቋም፣ ትዕቢትን ማንበርከክ፣ ስንፍናን ማባረርና አላዋቂነትን መግለጥ ይችልበታል፡፡ ፍቅርንስ ምን ያደርገው ይሆን?
አራት ባለ መስመር ወረቀት በአንድ ብር ገዛሁ። አንድ ብሯን ከየት እንዳገኘሁ አትጠይቁኝ! ለ ፍ.. (ከንፈሬን አቃጠለኝ) የማይከፈል መስዋዕትነት የለም፡፡ የሚያውቀው ያውቀዋል! እናም ደጃፌን ዘግቼ ስሜቴን፣ ጭንቀቴን፣ ምኞቴን፣ ስቃዬን፣ ስካሬን ዘረገፍኳቸው፡፡ ለዛውም በሁለት እስክርቢቶዎች- ሰማያዊ እና ቀይ፡፡ ሚዛን የሚደፋውን በቀይ፣ እንቶ ፈንቶውንና መደዴውን በሰማያዊ፡፡ ቃላቶቹን የ25 ሳንቲም (በዚያን ጊዜ) ባለ መስመር ወረቀቶቹ ላይ በመስመር ዘራኋቸው። እንደ እህል ሺ ሆነው እንዲያፈሩ እየፀለይኩኝ፣ እንደ ወይራ ስር ልቧን ቆንጥጠው እንዲይዙት፣ መላ ሰውነቷን እንዲወሩት፣ ነፍሷን እንደ አደይ አበባ እንዲያፈኩት፣ ግድየለሽነቷን እንዲያተኑት፣ አለማወቅዋን እንዲመግቡት፣ መልሷን እንደ ማር እንዲያዋዉት ተስፋ አርግዤ አሰለፍኳቸው፡፡ የአራት ወራት ስሜቴን፣ ንዝረቴን፣ መቅበዝበዜን፣ የአራት ወር ጭንቀቴንና ቃንዛዬን እንደ ምንም ብዬ (አቤት ሲያስቸግር!) በአራት ገፅ አብቃቅቼ ጻፍኩላት፡፡ በክብር አጥፌ ሰጠኋት፡፡
“ምንድነው?” አለች፣ እየተፍለቀለቀች፡፡
“ብቻሽን ሆነሽ አንብቢው” ብያት ውልብ አልኩ፡፡ ከቤት ወጥቼ ጓደኛዬ ዘንድ አቀናሁ፡፡
መንገድ ላይ ሳለሁ ‘ምን ትል ይሆን?’ እያልኩ ስመራመር ነበር፡፡
‘እንዳየሁሽ መብረቅ የመታኝ ነው የመሰለኝ’ ስላት ምን ትል ይሆን?
‘ጥዋት ጥዋት ፀሐይ መሞቅ ምን ያደርግልሻል? ጥርሶችሽ አሉልሽ አይደል፡፡ እንኳን ላ’ንቺ ለእኔም ይበቃሉ’ የሚለውን ስታነብ ምን ትል ይሆን?
‘የእኔ ልብና የአንቺ ልብ ገመድ ሳያስፈልግ ከጥርሶችሽ በሚፈልቀው ብርሃን ተገናኝተዋል’ የሚለው  ጋ ስትደርስ ምን ይሰማት ይሆን?
‘ናላዬ ሲዞር በፊዚክስ ኬሚስትሪ
ለስጋዬ ስዳክር በታሪክ ጂኦሜትሪ
አንቺን አየሁና ተፈወሰች ነፍሴ
ሆነሽ ተገኝተሽ  የብቸኝነቴ  ዳማከሴ
በብርሃንሽ እፈካለሁ ቢደርቅም ምላሴ’ የሚለውን ስታነብ እንዴት ያደርጋት ይሆን?
‘ስንሳሳም ስሱ ከንፈሬ እና ወፍራሙ ከንፈርሽ እንዴት ይገጥሙ ይሆን?’ ስላት እንዴት ብላ ትሥቅ ይሆን እያልኩኝ። (ተዳፈርኩ አይደል? አበጀሁ!)
‘ስንጋባ አንድ ሳይሆን አስር ቀለበት ነው ምገዛልሽ’ (የቀለበትን ትርጉም አጥቼው አልነበረም- ትንሽ ልቅበጥ ብዬ እንጂ)  የሚለውን ስታይ ምን ትል ይሆን?
 ‘ስንገናኝ መጀመርያ የማለማምድሽ  ዐይንሽን ሳትጨፍኚ መሣቅን ነው’ ስላት ዐይኖቿን ጨፍና ሥቃ ይሆን?
‘ከአሁን ወዲያ ከአጠገቤ ሆነሽ አትርቂኝም
ከአሁን ወዲያ በህልሜ እንጂ በውኔ ጠርቼ አላጣሽም
ከአሁን ወዲያ ሳናግርሽ አልንተባተብም፣ ስትስሚኝ ምላሴ ትፈወሳለችና’ ስላት ስሜቷ ምን ያህል ግሎ ይሆን እያልኩኝ፡፡
እነዚህን ሁሉ እያሰላሰልኩ ጓደኛዬ ቤት ደረስኩ። ሲበዛ እጅግ ምስጢረኛ በመሆኔ ያደረግኩትን ለጓደኛዬ እንኳን አልነገርኩትም። ስንጫወት፣ ፊልም ስናይና ስናጠና ዋልን፡፡ ያበጠውን ስላፈነዳሁት ነው መሰለኝ ቅልል ብሎኝ ነበር የዋለው፡፡ ስለ መልሱ ቅንጣት ታህል እንኳን አልተጨነቅኩም፡፡ ምንም! አይገርምም? እንደዛ ለወራት ስማስን እንዳልነበረ አሁን ውስጤ እርጋታ ሰፈነበት፡፡ ፀጥ እረጭ! ነገሬን ከዳር ያደረስኩ መስሎ ተሰምቶኝ ይሁን? ብቻ እኔ እንጃ!
ጓደኛዬ ቤት እያጠናን ስላመሸን እዛው እራት በላን፡፡ ጥናታችንን ለመቀጠል በመስማማት እዚያው እንዳድር ተስማማን፡፡ ስወጣ ለአጎቴ ነግሬው ስለነበረና ከዚህ በፊትም ጓደኛዬ ቤት አድሬ ስለማውቅ ወደ ቤት መመለስ አላስፈለገኝም። የደብዳቤዬን ነገር ግን እርግፍ አድርጌ ረስቼዋለሁ። አይደል? ለእኔም ገርሞኛል፡፡ ‘ፈርተህ ነው’ ነው ያላችሁት? ሊሆን ይችላል፡፡ ዳሩ ግን በዚያን ሰአት በቅጡ አልተገለጠልኝም ነበር፡፡
ወደ ሁለት ሰአት ገደማ ሲሆን በሩ ሲንኳኳ ጓደኛዬ ሊከፍተው ወጣ፡፡ ጠርቶ ሰው ይፈልገሀል አለኝ። ወጣሁ፡፡ እኛ ግቢ የሚኖር ልጅ ነው፡፡ ‘ይሄን ነው እንዴ ሰው ያለው’ ብዬ እያሰብኩ ሰላም አልኩት። ልጁ እኩያዬ ነው፡፡ ወሬኛ ነገር በመሆኑ ብዙም አይመቸኝም፡፡ እሱ ግን አያውቅም፡፡
“አንተ ጉደኛ! ዛሬ ጉድህ ፈላ፣ የሰጠሃትን ደብዳቤ ለእናቷ ሰጠቻቸው” አለኝ፡፡
ምሽት ቢሆንም ለአፍታ ውስጤ የጨለመብኝ መሰለኝ፡፡ ልቤ ቀጥ ሳትል አትቀርም፡፡ ህሊናዬን እንዳልስት ሰጋሁ፡፡ በሩን ተደገፍኩት፡፡ ጓደኛዬ መጣ፡፡
“ ምንድነው?” ሲል ሰማሁት፡፡ ልጁ ነገረው፡፡
እጄን ይዞ ወደ ውስጥ አስገባኝ፡፡ ወሬኛው መልእክተኛ ስራውን አጠናቅቆ ተፈተለከ፡፡ ትንሽ እንደቆየን ከጓደኛዬ ጋር ማውራት ጀመርን፡፡ ሌላ ጊዜ ቢሆን አለቅስ ነበር፡፡ ዛሬ ግን አላለቀስኩም፡፡ እልህ ተናነቀኝ። የደም ሥሮቼ በብስጭት ተወጣጠሩ። ጥርሶቼን አጋጨኋቸው፡፡ መላ ሰውነቴ ላይ የነበረ ፀጉር የቆመ መሰለኝ፡፡ እንደ  ዳሞትራ ያገኘሁትን ሁሉ መንደፍ አሰኘኝ፡፡ በውስጤ ሲያብብ የነበረው ፍቅር፣ የጥላቻ ሰደድ ገባበት፡፡ ያከበርኩትን ቃል አራከስኩት። ተጠየፍኩት፡፡ ረገጥኩት፡፡ የተቀደሰው ዳቦት ባንዴ ከሰመ፡፡
ያን እለት ማታ እንደተለመደው አላጠናንም። ፊልም ስናይና ሴቶችን (ልጅቷን ጨምሮ) ስንኮንን አደርን። አላዋቂነቷን አብጠለጠለነው። ሞኝነቷን አፌዝንበት፡፡ የልቧን ደንዳናነት ከሰውነት ደረጃ ውጭ መደብነው፡፡ ጓደኛዬ ውፍረቷን አጋንኖ ጥላሸት ቀባት። (ታዲያ ለዚህ ካልሆነ ጓደኛ ለመቼ ነው!) ያደረብኝን ቅያሜ ለመግለፅ ሌላ የ25 ሳንቲም ወረቀት አይበቃም። ረገምኳት፡፡ እነዚያ የብርሃን ፍንጣቂ ያልኳቸው ዐይኖቿን፣ እነዚያ ከአልማዝ እኩል ያስተካከልኳቸው ጥርሶቿን፣ እነዚያ የእግዜር ፊኛዎች ያልኳቸው ጉንጮቿን፣ እነዚያ ሜሮን ብዬ ያነገስኳቿው ከንፈሮቿን ረገምኳቸው፡፡ ሣቋን የሞት ጥሪ መረዋ ብዬ ሰየምኩት፡፡ ፈገግታዋን በገሃነም ቋያ መሰልኩት፡፡
ጥዋት የግድ ወደ ቤት መሄድ ስለነበረብኝ እየተሸማቀቅኩ ሄድኩ፡፡በዳዴ የሚሄድ ህፃን ልጅ ሊቀድመኝ በሚችልበት ፍጥነት እየተራመድኩ - ጭራዬን ቆልፌ እየተብረከረኩ ደጃፉ ላይ ደረስኩ። የፈራሁት አልቀረም፡፡ እነሱ አንድ ለ ምናምን ተሰብስበው ሲጠብቁኝ ኖሯል፡፡ እናቷ፣ አጎቴ፣ ታላቅ ወንድሟ (በእድሜ አጎቴን ያክላል)፣ ታናሽ እህቷ፣ የጎረቤት ልጆች (ምናለበት ወደ ውጪ ቢያስወጥዋቸው)፣ አንድ ሌላ ተከራይ ሴት (ሌላ ጊዜ ወደ ሥራ አንግተው ነበረ የሚወጡት) ተሰብስበው ጠበቁኝ- በጠዋቱ የሳሩ ጤዛ እንኳን ሳይረግፍ፡፡ እሷ ግን የለችም፡፡ የት አባቷ ሄዳ ነው? ዙረታም!
ሊቀ መንበሯ እናትዋ ናቸው መሰለኝ ስሞታውን ዘረገፉት፡፡
“ልጆቼን ከቁምነገር አደርሳለሁ ብዬ ደፋ ቀና ስል፣ ከስራ ስራ ስቀያይር…” ሲሉ አንገቴን ደፋሁ። ምን እንደማደርግና ምን እንደምል ጨነቀኝ፡፡
“እንደ እኔ በስነ ሥርአት ይማራል ብዬ ነው እንጂ ከእኔ ጋር እንድትሆን ያመጣሁህ” አለ አጎቴ ደግሞ። ታዘብኩት፡፡ አሁን በለስ ቀንቶት እንጂ እሱ በስነ ሥርአት የተማረ አልነበረም፡፡ ከእሱ ጋር እንድኖር ወላጆቼን ያግባባቸውም ‘ፊልድ’ ሲወጣ ቤቱን እንድጠብቅለት ነበር፡፡
“ለመሆኑ ራስህ ነህ የጻፍከው? የማይታመን ነው! እኔ እንኳን እንደዚህ አድርጌ አልጽፍም” አለ ወንድሟ ደግሞ፡፡ ‘ነፈዝ! ትልቅ በሆነ መሰለህ እንዴ’ አልኩት በውስጤ፡፡
ሁሉም ወረዱብኝ፡፡ እናትየው በምሬትና በተግሳፅ፣ አጎቴ በማጥላላትና በማብጠልጠል፣ ወንድሟ በማስፈራራትና በመዛት፣ ማቲዎቹ በማውካካትና በማሾፍ፣ አሮጊቷ ደግሞ ከንፈር በመምጠጥና በትዝብት ተረባረቡብኝ፡፡ በቃላት በትር ነረቱኝ፣ በንቀት አለንጋ ገረፉኝ፡፡ በ እምጵ ድንጋይ ወገሩኝ። በፌዝ ቢላ ወጉኝ፡፡ በፉከራ ኮረንቲ አቃጠሉኝ። ሲደክማቸው አስፈራርተው ወደ ትምህርት ቤቴ እንዲሄድ አዘዙኝ፡፡ ቦርሳዬን አንጠልጥዬ ቁርስ ሳልበላ ውልብ ብዬ ወጣሁ፡፡
እሷን ግን ናቅኳት፡፡ ከማኩረፍም በላይ ጠላኋት። ረገምኳት፡፡ ከዚያ ወዲህ እንኳን ላናግራት ቀርቶ በቅጡ ተመልክቻትም አላውቅም። ከፊት ለፊት ስትመጣ ካየኋት መንገዴን እቀይራለሁ፡፡ አትሳሳቱ! ተጠይፌያት እንጂ ፈርቻት አልነበረም፡፡ መፍራትን ትቻለሁ፡፡ ደግሞ ለማን ብዬ፣ ለምን ብዬ ልፍራ! እንደዚያ ልቤ ውስጥ በቀላሉ እንዳላነገስኳት አሽቀንጥሬ ተፍቻታለሁ። አሁንም አትሳሳቱ! ወረተኛ ሆኜ አይደለም፡፡ እኔ ከወደድኩ ወደድኩ ነው፡፡ ከጠላሁ ድግሞ ጠላሁ፡፡ እኔ ለመጥላት እንጂ ለመውደድ ምክንያት አልደረድርም። ደግነቱ ከስድስት ወር በኋላ ቤት ቀየርን፡፡ (በሌላ ምክንያት ነው)
እንደዚያ ሌትና ቀን ስዘይርላት እንዳልነበረ አምርሬ ረገምኳት፡፡ ምላሴ ጠቆር ይላል፡፡ ግን እርግማኔ ይደርስባታል ብዬ አላሰበኩም፡፡ ብግነቴን ለማስተንፈስ እንጂ፡፡ አሁን  ግን… ከአስራ ምናምን አመታት በኋላ ግማሽ ፊቷ ተቃጥሎ፣ ግማሽ ፊቷ ተጨራምቶ፣ ፀጉሯ ባደፈ ሻሽ ተገንዞ፣ ግንባሯ ተቦድሶ፣ ኩርምት ብላ ስትለምን አየኋት፡፡ ልቤ በዳምጠው የተደፈጠጠ መሰለኝ፡፡
ቀና ብዬ ጓደኛዬን አየሁት፡፡ ዐይን ዐይኔን ያየኛል። ዐይኖቼ እንባ አቆሩ፡፡ ፊቴ በእንባ ታጠበ። ከንፈሬ ወደ ከሰልነት የተቀየረ መሰለኝ፡፡ ላንቃዬ ከትናጋዬ ጋር የተጣበቀ መሰለኝ፡፡ ጭንቅላቴ ውስጥ አንድ ድምፅ ድው ድው ይላል፡፡
ምን ሆና ይሆን? ምን ሆና ይሆን? ምን ሆና ይሆን? ምን ሆና ይሆን?
የአዘጋጁ ማስታወሻ፡- (ደራሲው “የልብ ሽበት” እና ሌሎችም መጽሐፍ አዘጋጅ ነው፡፡)

Read 5029 times