Saturday, 14 October 2017 15:48

7ኛው ዙር የለዛ አድማጮች ሽልማት አሸናፊዎች

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(2 votes)

 ቴዲ አፍሮ በሁለት ዘርፎች አሸንፏል
                        አርቲስት ዘሪቱ ከበደ በ“ታዛ” ፊልም አሸንፋለች
                       
      በሸገር ኤፍኤም የሚተላለፈው “ለዛ” የሬዲዮ ፕሮግራም፣ 7ኛ ዙር የአድማጮች ሽልማት ከትላንት በስቲያ ምሽት በሂልተን ሆቴል በተካሄደው ስነ-ስርዓት ተጠናቀቀ፡፡ ድምፃዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) በምርጥ ነጠላ ዜማና በምርጥ አልበም ዘርፍ “ኢትዮጵያ” የተሰኘው አልበሙና የአልበሙ መጠሪያ ዘፈን አሸንፈዋል፡፡ ድምፃዊው በሥነስርዓቱ ላይ ባይገኝም በተወካዩ በኩል ሽልማቱን ተቀብሏል፡፡ በተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ ዘርፍ “ዘመን” ሲያሸንፍ፣ በምርጥ ሴት ተዋናይት፣ ዘርፍ አርቲስት ዘሪቱ ከበደ በ”ታዛ” ፊልም አሸናፊ ሆናለች፡፡ በምርጥ ወንድ ተዋናይ፣ አለምሰገድ ተስፋዬ “ያበደች ያራዳ ልጅ” በተሰኘው ፊልም ያሸነፈ ሲሆን በስራ ምክንያት ባይገኝም ሽልማቱን በተወካዩ በኩል ወስዷል፡፡
በምርጥ አዲስ ድምፃዊ ዘርፍ፣ በመጀመሪያው የኢትዮጵያ አይዶል ለውድድር ብቅ ብሎ ግርምትን ፈጥሮ የነበረው ትንሹ ዳዊት አለማየሁ አሸናፊ ሆኗል፡፡ በምርጥ የሙዚቃ ቪዲዮ ዘርፍ፣ የብስራት ሱራፌል “ወጣ ፍቅር” አሸንፎ፣ ድምፃዊው ከአርቲስት ፍቅር አዲስ ነቅአጥበብ እጅ ሽልማቱን ተቀብሏል፡፡
የአመቱ ምርጥ ፊልም በተሰኘው ዘርፍ “ታዛ” ፊልም ያሸነፈ ሲሆን ሽልማቱን የፊልሙ ቡድን በጋራ ተቀብለዋል፡፡ በህይወት ዘመን ተሸላሚነት የተመረጠው አንጋፋው የሙዚቃ ሊቅ ግርማ በየነ ሲሆን በሽልማት ስነ ስርዓቱ ላይ ባይገኝም ሽልማቱን ከባሕታ ገ/ህይወት እጅ ሲወስድ የሚያሳይ ቪዲዮ ለታዳሚው ቀርቧል፡፡ በምሽቱ ፕሮግራም በርካታ አንጋፋ ወጣት ድምፃዊያን፣ የሸገር ሬዲዮ ጋዜጠኞችና አመራሮች፣ እንዲሁም የመንግስት የስራ ኃላፊዎች የታደሙ ሲሆን የሸገር ኤፍኤም መስራች አንጋፋዋ ጋዜጠኛ መዓዛ ብሩ፣ እውቁ ገጣሚ ይልማ ገ/አብ፣ ተወዳጁ ድምፃዊ ዳዊት መለሰ፣ ሻለቃ ሀይሌ ገ/ስላሴ እና አርቲስት ሰለሞን ቦጋለ በሸላሚነት ተሳትፈዋል፡፡ለ7ኛ ዙር የተካሄደው የለዛ አድማጮች የሽልማት ሥነ-ስርዓት የተጠናቀቀ ሲሆን በቅርቡ በሞት ላጣናቸው አርቲስቶችም የህሊና ፀሎት ተደርጓል፡፡

Read 1603 times