Print this page
Saturday, 14 October 2017 15:38

የ21ኛው ክ/ዘመን 21ኛው የዓለም ዋንጫ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(3 votes)

    21ኛው የዓለም ዋንጫ 8 ወራት የቀሩት ሲሆን ማለፋቸውን ያረጋገጡት ብሄራዊ ቡድኖች አዘጋጇን ራሽያ ጨምሮ 23 ደርሰዋል፡፡  እነሱም ብራዚል፤ ኢራን፤ ጃፓን፤ ሜክሲኮ፤ ቤልጅዬም፤ ደቡብ ኮርያ፤ ሳውዲ አረቢያ፤ ጀርመን፤ እንግሊዝ፤ ስፔን፤ ናይጄርያ፤ ኮስታሪካ፤ ፖላንድ፤ ግብፅ፤ አይስላንድ፤ ሰርቢያ፤ ፈረንሳይ፤ ፖርቱጋል ፓናማ፤ ኡራጋይ፤ ኮሎምቢያ እና አርጀንቲ ና ናቸው፡፡ በመጭዎቹ ሁለት ወራት የዓለም ዋንጫ ማጣርያው በ6 ኮንፌደሬሽኖች በምድብ የመጨረሻ ጨዋታዎችና የጥሎ ማለፍ ትንቅንቆች
የሚቀጥል ሲሆን የቀሩት የተሳትፎ ኮታዎች 9 ናቸው፡፡ በዓለም ዋንጫ 12 ብሄራዊ ቡድኖችን ምታሳፍበት ኮታ ያላት የአውሮፓ አህጉር  በመወከል 9 አገራት ማለፋቸውን ሲያረጋግጡ  በቀረው የ3 ብሄራዊ ቡድኖች ኮታ 6 አገራት ነበጥሎ ማለፍ ማጣርያ ይተናነቃሉ። በጥሎ ማለፍ ማጣርያው  ስዊዘርላንድ፤ ሰሜን አየርላንድ፤ አየርላንድ፤ ዴንማርክ፤ ጣሊያን፤ ግሪክና ክሮሽያ የሚደለደሉ ይሆናል፡፡ አፍሪካ በዓለም ዋንጫ  በ5 ብሄራዊ ቡድኖች እንደምትወከል ሲታወቅ ግብፅ እና ናይጄርያ ብቻ ማለፋቸውን በማረጋገጣቸው በቀሩት የ3 ብሄራዊ ቡድኖች ኮታ ከየምድባቸው የማለፍ እድል ያላቸው ቱኒዚያ፤ ዲሪ ኮንጎ፤ አይቬሪኮስት፤ ሞሮኮ፤ ቡርኪናፋሶ፤ ሴኔጋል፤ ካሜሮን፤ ጋናና አልጄርያ ናቸው፡፡ ከደቡብ አሜሪካ ዞን ወደ የጥሎ ማለፍ ማጣርያ ያለፈችው ፔሩ ስትሆን የምትገናኘው ከኦስኒያዋ ኒውዝላንድ ጋር ይሆናል፡፡ ሌላው የጥሎ ማለፍ የዓለም ዋንጫ ማጣርያ ትንቅንቅ የኤስያን ዞን የምትወክለውን
አውስትራሊያ ከደቡብ አሜሪካዋ ሆንዱራስ የሚያገናኝ ነው፡፡በተያያዘ ዜና ያለፈውን 1 ወር በቆየው የ21ኛው የዓለም ዋንጫ የመጀመርያ የትኬት ሽያጭ መርሃ ግብር 3 ሚሊየን 496ሺ 204 ትኬቶችን
ለመግዛት ጥያቄ መቅረቡን ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር ፊፋ አስታውቋል፡፡ ትኬቶች ለመግዛት ጥያቄ ካቀረቡ የዓለም አገራት መካከከል 30 በመቶውን ድርሻ የአዘጋጇ አገር ስፖርትአፍቃሪዎች ራሽያውያን ቀዳሚ ሲሆኑ፤ ጀርመናዊያን፤ ብራዚላውያን፤ አርጀንቲናውያን ሜክሲኳዉያን፤
አሜሪካዊያን፤ ኮሎምቢያውያን፤ ግብፃውያን፤ ቻይናውያንና ፖላንዳዊያን በሞስኮው ሉዝንስኪ ስታድዬም ለሚስተናገዱት ለመክፈቻው ጨዋታ 150ሺ ለመዝጊያው 300ሺ ትኬቶች ለመግዛት ወረፋ መያዙንም ለማወቅ ተችሏል፡፡ ሁለተኛው የሽያጭ መርሃ ግብር ከሁለት በኋላ የሚቀጥል ነው፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ለ21ኛው የዓለም ዋንጫ በተካሄደው የምድብ ማጣርያ ክብደት በስድስቱም ኮንፌደሬሽኖች ታላላቅ ብሄራዊ ቡድኖችን የጣለ ሆኗል፡፡ ከአውሮፓ እነ ሆላንድ፤ ከደቡብ አሜሪካ እነ ቺሊ፤ ከአፍሪካ እነ ካሜሮንና እና ጋና  እንዲሁም ከሰሜንና መካከለኛውአሜሪካ አሜሪካ
የዓለም ዋንጫ ተሳትፎ ካልተሳካላቸው አገራት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ በተለይ ከ1990 እኤአ ጀምሮ  ሰሜንና መካከለኛውን አሜሪካ በመወከል  ለ7 ተከታታይ የዓለም ዋንጫ የቀረበችው  አሜሪካ ከ1986 ወዲህ ለመጀመርያ ጊዜ የዓለም ዋንጫ ተሳትፎ ሳይሳካላት ቀርቶ መውደቋ የሰሞኑ አበይት አጀንዳ ነበር፡፡ እንደ አሜሪካ ያሉ አገራት በዓለም ዋንጫ ተሳትፎ ባለማግኘታቸው እስከ 20 ሚሊዮን ዶላር የሚገመት ገቢ እንደሚያጡ መረጃዎችአውስተዋል።ፊፋ ለዓለም ዋንጫ ለሚያልፉ 32 ብሄራዊ ቡድኖች ለእያንዳንዳቸው ለምድብ ማጣርያ ተሳትፏቸው እና ለቅድመ ዝግጅታቸው 12.5 ሚሊዮን ዶላር እንደሚሰጥ የሚታወቅ ሲሆን፤ ከቅድመ የዓለም ዋንጫ የወዳጅነት ጨዋታዎች፤ ከቲቪ የስርጭት መብት፤ ከስፖንሰርሺፕ እና ከተለያዩ የንግድ እንቅስቃሴዎች ከ10 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ሊሆን ይችላል፡፡ የአሜሪካ መውደቅ  ከሌሎቹ አገራት ለየት የሚያደርገው በተለይ በፎክስ ጣቢያ ላይ የሚደርሰው ኪሳራ ሲሆን በ2015 እኤአ የሴቶች የዓለም ዋንጫን ከዚያም  እስከ ኳተሩ 22ኛው የዓለም ዋንጫ  በቀጥታ  ስርጭት
ለመስራት በ425 ሚሊዮን ዶላር ግዢ የፈፀመው ውልን አደጋ ላይ የሚጥልና የገባውን ስምምነት እንዳይሟሟቅ በማድረግ ለከፍተኛ ኪሳራ ስለሚዳርገው ነው፡፡ ፎክስ የ2018 የዓለም ዋንጫን በ350 ሰዓታት የቀጥታ እና ተያያዥ የስርጭት ሽፋኖች ለመዘገብ እስከ 200 ሚሊዮን ዶላር
በመክፈል በሰሜንና መካከለኛ አሜሪካ እንዲሁም በሌሎች የዓለም ክፍሎች ለመስራት አቅዶ ነበር፡፡ በዓለም ዋንጫ አሜሪካ ባለመሳተፏ ከፎክስ ኒውስ ባሻገር በስፖንሰርሺፕ እና በስታድዬም ተመልካች ብዛ ላይ ተፅእኖ እንደሚያሳርፍም ተገልጿል፡፡ በከፍተኛ እድገት ላይ የሚገኘው
የአሜሪካ ሜጀር ሶከር ሊግም  የሚቀዛቀዝሲሆን  በአሜሪካ ብሄራዊ ቡድን የትጥቅ ስፖንሰር ናይኪም ላይም ኪሳራ ሊያጋጥም ይችላል፡፡በሌላ በኩል በራሽያ በሚካሄደው 21ኛው የዓለም ዋንጫ ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማበር ፊፋ ለሽልማት ያቀረበው ገንዘብ ካለፉት ዓለም
ዋንጫዎች በ22 በመቶ እድገት እንደሚኖረው ታውቋል፡፡ በተለያዩ ደረጃዎች ለሚመዘገቡ ውጤቶች፤ ለተጨዋቾች ዋስትና እና ለክለቦች አስተዋፅኦ በሚታሰብ ድርሻ እስከ 700 ሚሊዮን ዶላር መቅረቡ ነው የተለጸው። በ21ኛው የዓለም ዋንጫ ሻምፒዮን የሚሆነው አገር 50 ሚሊዮን
ዶላር የሚበረከትለት ሲሆን፤ ለሁለተኛ 40 ሚሊዮን ዶላ ለ3ኛ 30 ሚሊዮን፤ ለአራተኛ 25 ሚሊዮን ዶላር ይታሰባል፡፡ በሩብ ፍፃሜ ለሚሰናበቱ

4 ቡድኖች 18 ሚሊዮን ዶላር በጥሎ ማለፍ ለሚሰናበቱ 8 ቡድኖች 12 ሚሊዮን ዶላር ሲታሰብላቸው በምድብ ማጣያ የሚሳተፉ 32 ቡድኖች 10

ሚሊዮን ዶላር እና ለዝግጅት 2 ሚሊዮን ዶላር በተጨማሪ ይሰጣቸዋል፡፡
በ2014 እኤአ ብራዚል ባስተናገደችው 20ኛ የዓለም ዋንጫ ላይ ፊፋ 4.8 ቢሊዮን ዶላር ገቢ አግኝቶ 2.7 ቢሊዮን ዶላር ወጭ በማረግ 2.1 ቢሊዮን ዶላር ንፁህ ትርፍ አጋብሷል፡፡ ከዚሁ ንፁህ ትርፍ የፊፋ አባል አገራት ድርሻ ሲኖራቸው ፊፋ በካዝናው ያስገባው እስከ 338 ሚሊዮን ዶላር ነበር፡፡ በገቢ ደረጃ 2.4 ቢሊዮን ዶላር ከቴሌቭዥ ስርጭት መብት፤ 1.5 ቢሊዮን ዶላር ከስፖሰርሺፕ 550 ሚሊዮን ዶላር ሲያገባ በወጭ ደረጃ ደግሞ ለሽልማት ገንዘብ እና ለክለቦች አስተዋፅኦ ክፍያ 576 ሚሊዮን ዶላር፤ ለቲቪ ፕሮዳክሽን 370 ሚሊዮን ዶላር፤ ለአዘጋጇ ብራዚል በተሰጠ ድጋፍ 100 ሚሊዮን ዶላር ተመዝግቦ ነበር፡፡ በ2014 እኤአ ብራዚል ባስተናገደችው 20ኛ የዓለም ዋንጫ ላይ ለተጨዋቾች ዋስትና 100 ሚሊዮን
ዶላር፤ ለክለቦች በሚከፈል የአስተዋፅኦ ድርሻ 70 ሚሊዮን ዶላር እንዲሁም በተለያዩ ደረጃዎች ለሚመዘገብ ውጤት በፊፋ የተበረከተው 576 ሚሊዮን ዶላር ነበር። በወቅቱ ሻምፒዮኗ ጀርመን 30 ሚሊዮን ዶላር ስታገኝ አርጀንቲና በሁለተኛ ደረጃ 25 ሚሊዮን ደርሷታል፡፡ፊፋ ከአጠቃላይ ገቢው በዓለም ዋንጫ የሚያስገባው 85 በመቶ ድርሻ ያለው ነው። በ2026 እኤአ ላይ የዓለም ዋንጫውን በ48 ብሄራዊ ቡድኖች ለማካሄድ ያሰበው ፊፋ ገቢው ከ6 ቢሊዮን ዶላር በላይ በማድረስ  ከ521 ሚሊዮን ፓውንድ በላይ ንፁህ ትርፍ የሚያገኝበትን እቅድ እየሰራበት

ነው፡፡

Read 3388 times