Saturday, 14 October 2017 15:31

‘ታዋቂነት’ እና ‘ልዩ ዙፋን’

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(9 votes)

 እንዴት  ሰነበታችሁሳ!
 ኧረ ይመኙሻል፣ ይመኙሻል7
አበበ ቢቂላ ያገባሻል
ጥላሁን ገሰሰ ይድርሻል
ተብሎ ነበር፣ የዛሬን አያድርገውና ያኔ … አትሌቶችም፣ ዘፋኞችም ፍራንክ በሌላቸው ዘመን።
ስሙኝማ…እንግዲሀ ጨዋታም አይደል… ‘ታዋቂነት’ እንደ ዘንድሮ የቀለለበት ጊዜ ነበር! ልክ እኮ ከ‘ተራው ህዝብ’ ብዛት ይልቅ የ‘ታዋቂ ሰዎች’ ብዛት የሚበልጥ ነው የሚመስለው፡፡ ታዋቂ ለመሆን የግድ “እንትን የተባለው ፊልም ላይ አስደናቂ ትወና” ማሳየት አያስፈልግም፡፡ የግድ “እንትን የተባለው ተከታታይ ድራማ ላይ ‘ሰናይ’ ገጸ ባህሪ” መጫወት አያስፈልግም፡፡
አይደለም ሌላ፣ ሌላውን… “እሱ ብልጥ ነው” የሚባል ታዋቂነት አለ እኮ! የምር…“አጅሬው እኮ፣ በብልጥነት ማንም አይስተካከለውም፣” ከተባለ የታዋቂነት ገበያውም ያን ያህል ይደራል፡፡ “ለምን እሱን አታናግረውም? ከፈለገ የመንግሥተ ሰማያትን በር ማስከፈት የሚችል ነው እኮ!” ይባላል፡፡ “እሷን በዘዴ ቅረባትና ይሄ ስንት ወር ተንገላታሁበት የምትለውን ነገር አንድ ቀን ሳታሳድር ነው የምትፈጽምልህ፣” ይባላል፡፡ (ታዲያ የጽድቅ ጉዳይ፣ የመንግሥተ ሰማያት ‘መግቢያ ነጥብ’ ማሟያ ምናምን ነገር ሳይሆን… ‘ኖ ፍሪ ላንች’ ነው፡፡)
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ለምሳሌ የበፊት ገጣሚያን ‘ታዋቂ’ ቢባሉ ባብዛኛው በስነጽሁፉ ቤተሰብ አካባቢ ነው፡፡ ያኔ… ‘የመጽሐፍ ምረቃ፣’ ‘የግጥም ምሽት’ የሚሏቸው ነገሮች ይሄን ያህል አልነበሩማ! ‘የግጥም ሲዲ/ቪሲዲ’ ብሎ ነገር የለማ! “ቀጥሎ ደግሞ ገጣሚ እከሊት አንድ ግጥም ታቀርብልናለች” የሚባለበት የበዓል ልዩ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ብሎ ነገር ይህን ያህል  የለማ! ‘ላይክ፣’ ‘ሼር፣’ ምናምን የምንባባልበት ፌስቡክ ብሎ ነገር፣ ትዊተር ኢንስታገራም ብሎ ነገር የለማ! እናማ…እንደ ዘንድሮ በምርኩዝ ዝላይ እንጨት ወደ ‘ታዋቂነት’ ለመዝለል የቀለለበት ጊዜ የለም፡፡ ‘እሰየው’ ነው፡፡
እናላችሁ…የበፊት ድምጻውያን ያው በየዓመቱ የእንቁጣጣሽ ዋዜማን እየጠበቁ ብቅ ከማለት ሌላ “የመጀመሪያ አልበሙን ባወጣ በስምንተኛ ወሩ ሁለተኛ አልበሙን አውጥቷል” ብሎ አድናቆት ምናምን የለማ! ደግሞላችሁ… “አዲሱን ሲንግሏን በኤፍ፡ኤሞች አልሰማህላትም?” ብሎ ነገር የለማ! “ዱባይ እየተመላለሰ በዘፈነው፣ አሜሪካ ሀበሻ ሬስቱራንቶች ውስጥ ዘፍኖ ባጠራቀመው ነው ጂ ፕላስ ስሪውን ገጭ ያደረገው፣” ብሎ ነገር የለማ!
ለነገሩ… አለ አይደል… ሰዎች ታዋቂ መሆናቸው ክፋት የለውም፡፡ በትወናውም ሆነ፣ በድርሰቱም ሆነ፣ በሙዚቃውም ሆነ በሌላው የሆነ ሰው ‘ታዋቂ’ ከሆነ ለስም የሚያበቃ ሥራ ሠርቷል ማለት ነው፡፡ ‘እሰዬው’ ነው፡፡ ችግሩ..ምን መሰላችሁ… አንዳንዶች ላይ ‘ታዋቂነት’ ከሚሉት ነገር ጋር ተዳብለው የሚመጡ ባህሪያት ናቸው፡፡ ‘ታዋቂ’ መሆንን ከሌላው ህብረተሰብ በሁሉም ነገር የበላይ መሆን አድርገው የሚቆጥሩ መኖራቸው ነው፡፡ በየሄዱበት ስፍራ ቀይ ምንጣፍ እንዲነጠፍላቸው የሚፈልጉ፣ ተራ በሚያዝበት ስፍራ እነሱ ብቅ ሲሉ በጸሀይ ሲንቃቃ የዋለው ህዝብ ሸሸት፣ ሸሸት ብሎ እነሱን እንዲያስቀድም የሚፈልጉ፣ አፍ አውጥተው ባይሉትም… አለ አይደል…እነሱ ባሉ ባገደሙ ቁጥር ሁሉም ሰው ሥራውን ትቶ እጅ እየነሳ “በአንተ መጀን!/በአንቺ መጀን!” አይነት አቀባበል እንዲያደርግላቸው የሚፈልጉ፡፡
ትንሽ ረዘም ያለ ጊዜ ሆኖታል፡፡ የሆነ ከቤት ባለቤትነት ጋር የተያያዙ አገልግሎቶች ይሰጡባቸዋል ከሚባሉት ስፍራዎች አንዱ ነው። ብዙዎቹ ባለጉዳዮች ደግሞ ተራ ጥበቃ ለቀናት ተመላልሰዋል፡፡
አንዲት ‘ታዋቂ’ የሆነች ልጅ ትመጣለች…ደጅ የተኮለኮለውን ሰው ከመጤፍ ሳትቆጥር ወረቀቶቿን እንደያዘች በቀጥታ ወደ አንድ ቢሮ ዘው ብላ ትገባለች፡፡ አለ አይደል…ልክ የሆነች ልዩ እንክብካቤ፣ የ‘ክላውድ ናይን’ መስተንግዶ መብቷ የሆነ ይመስል። ፋይሏን ተራ እንደሚያሲዙላት አይነት ነገር ይነግሯታል፡፡ በቻ እንዴት ተመናጨቀች! (“እንዴት፣ እንዴት እንዳደረጋት!” ላለማለት ነው፡፡ ‘እሷን የምታክል’ ታዋቂ መጥታ ቀጠሮ ማለት በዓለም ፍርድ ቤት ባያስጠይቅ ነው! (‘ታዋቂነቷ’ እኮ… አለ አይደል… መቶ ጣራ ሆኖ በቁጥር ብትመዘን፣ ወደ 19.6 ገደማ ብትሆን ነው!)
የምር እኮ ይገርማል…ለምንድነው ታዋቂ እንደሆኑ የሚሰማቸው ሰዎች ከሌላው የተለየ እንክብካቤ የሚያስፈልጋቸው የሚመስላቸው!  ለምንድነው ስንት ተገልጋይ ሲጉላላ በከረመበት እነሱ በፈለጉት ደቂቃ መጥተው ‘ዙፋኑ ላይ ካላስቀመጣችሁኝ’ አይነት ባህሪይ የሚያሳዩት! እንደውም…ሚጢጢም ትሁን፣ ገዘፍ ያለም ይሁን፣  ለ‘ታዋቂነት’ ያበቃቸውን ህዝብ አክብረው ማስቀደም ያለባቸው እነሱ አይደሉም እንዴ፡፡
ደግሞላችሁ…ታዋቂ ለመሆን መሞከር ክፋት የለውም፡፡ ችግሩ በባዶ ሜዳ፣ በወና ስታዲየም፣ ዝምብ በሌለበት አዳራሽ ራሳችንን ታዋቂ አድርገን የደመደምን ሰዎች መብዛታችን ነው፡፡ በዚህ ላይ እኛ ‘ቲፎዞነት’ ብንልም… ሞቅ ለማድረግ፣ ‘ሎቢዪንግ’ ምናምን የሚሏት ነገርም አለች፡፡
“የፊልም አክተሩን አሳደህ በለውን ታውቀው የለ!”
“አላውቀውም፡፡”
“እንዴት አታውቀውም! …እንትን ፊልም ላይ እንትን የተጫወተው!”
“ፊልሙን አይቸዋለሁ፡፡ ያልከውን ተዋናይ ግን አላውቀውም፡፡”
“ፊልሙ መሀል ላይ ዋናው አክተር የሚገባበት ሆቴል ውስጥ ሬሴፕሽን ሆኖ የሚሠራው እንኳን!”  (ቂ…ቂ…ቂ…)
ታዲያላችሁ…እሱዬው “ኧረ እባክህ፣ አትለኝም! እንዴት እድለኛ ነህ!” ምናምን እንዲባል ነበር የጠበቀው፡፡
“እንትና የሚባለውን ባለስልጣን ታውቀዋለህ?”
“ማነው እሱ?”
“ምን! እንዴት እሱን አታውቅም! አገር ሁሉ ያውቀው የለም እንዴ!”
“እሺ አገር ይወቀው..እኔ ግን አላውቀውም፡፡ ማነው እሱ?”
“ነገርኩህ፣ በጣም ታዋቂ ነው፡፡ በቀደም እንኳን ስለ እንትን መግለጫ ሲሰጥ የነበረው! የእንትን ድርጅት ሥራ አስኪያጅ እንኳን…”
“አላውቀውም አልኩህ! ግን መጀመሪያውኑ ለምን ጠየቅኸኝ?”
 “እኔ አውቀዋለሁ፡፡”
“እና!”
“እና ትለኛለህ እንዴ! እናማ አውቀዋለሁ ነው የምልህ! እንደውም አንድ ቀን እቤቴ ምሳ እጋብዝሀለሁ ብሎኛል፡፡”
እናማ… ‘ታዋቂ’ የሆነ ሰው ወይም በ‘ሎቢዪንግ’… አለ አይደል… ‘ታዋቂ እንዲሆን የተፈለገ’ ሰውን “አውቀዋለሁ” ማለቱም እንደ ዘንድሮ ቅልል ብሎ አያውቅም፡፡ እናማ… ይቺን “እከሌ የተባለውን ባለስልጣን አውቀዋለሁ፣” የምትለውን ካርድ እየመዘዝን የምንጫወት መአት ነን፡፡
የባለስልጣን ስም እየጠሩ “ዋ! ደውዬ ለእሱ እንዳልነገርው፣ ብታርፍ ይሻልሀል!” አይነት ነገር የሚሉ ሰዎች እንዳሉ ሀሉ ሰምተናል፡፡ (ዘንድሮ በኪነ ጥበቡ ይጠብቅን እንጂ ምን የማንሰማው ነገር አለ!)
አንዳንድ መዝናኛ ቦታዎች ስትሄዱ ችግር አለ፡ ጠምቷችሁ ከሆነ “ብቻ እኔ ሳላዝ የሆነ ታዋቂ ሰው እንዳይመጣ!” የሚል ጸሎት ምናምን ነገር ሊያስፈልጋችሁ ይችላል፡፡
እናማ…ወይም፣ ዘንድሮ መቼም የማይደረግ ነገር የለምና፣ ለ‘ታዋቂነት’ የሆነ የብቃት ማረጋገጫ መለኪያ ምናምን ነገር  እናውጣለት፡፡ የምር…ወደፊት እኮ በዚህ ሰሞን ‘ሎሬት’ ምናምን የተባሉትን  ሁሉ “ስማ እንትናን እኮ አውቀዋለሁ፣” መባባላችን ላይቀር ነው፡፡
“እሱን አወቅኸውና ወሬ ብለህ ታወራለህ!”
“አልሰማህም እንዴ! ሎሬት ተባለ እኮ!”
“ማነው ሎሬት ያለው?”
“ማንስ ቢለው… ዋናው ሎሬት መሆኑ ነው፡፡”
“እንደዛ ከሆነ እኔ አንዳንዴ ብቅ የምልበት ጠጅ ቤት እኛ ‘ፕሮፌሰር’ የምንላቸው የእድር ጥሩምባ ነፊ አሉ፡፡ ላስተዋውቅህ እንዴ!”  
ብቻ…‘ታዋቂዎች’ በዝተው የምናቀርባቸው ‘ልዩ ዙፋኖች’ እጥረት እንዳይገጥመን!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 5300 times