Saturday, 14 October 2017 15:29

“የላቀ ጥራት፣... አያሸልምም! ያስቀጣል!... ማምረት ያስጠቃል!”

Written by  ዮሃንስ . ሰ.
Rate this item
(6 votes)

 • በጥራት ደረጃው፣... ወረድ ያለ ቡና፣... በኪሎ ከ100 እስከ 150 ብር እየተሸጠ
                          • በጥራት የላቀ፣ በዓለም ደረጃ ተመራጭ የሆነ ቡና ግን፣ በኪሎ 3 ዶላር! 80 ብር!
                          • ይሄ የስነምግባርና የፍትህ ጉድለት... የመንግስት ብቻ አይደለም!
                          • እንዳሰኛቸው መንገድ በመዝጋትና ንግድን በማሰናከል፣... አምራቾችን ማክሰርስ?
                          • “የላቀ ጥራት ያስቀጣል? ማምረት ያስጠቃል? እኔ የለሁበትም!” የሚል ማን ነው?
                                  
     የተዛባ የዶላር ምንዛሬ፣ ያለማስተካከያ ከዓመት ዓመት ይዞ መቀጠል፣ ችግርን ከማራዘምና እየደራረቡ ከማባባስ ውጭ ጥቅም አላስገኘም። የኤክስፖርት እድገት ከነአካቴው የጠፋው ለምን ሆነና?
የዶላር ምንዛሬ በፍጥነት መዛባት የጀመረው፣ በ2003 ዓ.ም ነው - ቅጥ ባጣ  ሳቢያ። በገንዘብ ሕትመት ምክንያት ነው፣ በዚያው ዓመት የብር አቅም በጣም የወረደው። ይህንን ተከትለው የሚመጡ አይቀሬ መዘዞችን ለማስቀረት መሞከር፣ በከንቱ መላላጥ እንደሆነም፣ ያኔውኑ ማወቅ ይቻል ነበር። ለማወቅ አለመፈለግና አይንን መጨፈን፣ ለውጥ አላመጣም።
በገንዘብ ሕትመት ምክንያት... የብር አቅም ከረከሰ በኋላ፣ በሸቀጦች ላይ የዋጋ ንረት መከሰቱ አይቀሬ ነው። የዶላር ዋጋም እንዲሁ! በአዋጅና በዋጋ ቁጥጥር አማካኝነት፣... የዋጋ ንረትን ለማስቀረት መሞከር፣ ለጊዜው የሚያዋጣ ይመስል እንደሆነ እንጂ፣ አያዛልቅም። እንዲያም ሆኖ ተሞክሯል። ችግርን ከማባባስ የዘለለ ፋይዳ አላስገኘም እንጂ።
በቃ! መንስኤውን ታቅፈን፣ ከመዘዙ መሸሽና ማምለጥ አንችልም። ብር ሲረክስ፣...  ለሸቀጦች የምንከፍለው ብር ይንራል። ያው፣ (ዶላርም እንደ ብር በገፍ ካልታተመና ካልረከሰ በቀር)፣... ለዶላር የምንከፍለው ብርም በዚያው መጠን እንደሚንር ምን ያከራክራል? የሸቀጦች ዋጋ እንዳይንር፣ በዋጋ ቁጥጥር ለመከላከልና ደፍጥጦ ለማቆየት መሞከር ጉዳት እንጂ ጥቅም እንደሌለው፣ ከ2003 ዓ.ም ወዲህ በተግባር አይተን የለ! ልክ እንደዚያው፤ የዶላር ምንዛሬንም በቁጥጥር ለመደፍጠጥ መሞከርም ውሎ አድሮ ተጨማሪ ችግሮችን እንደሚያስከትል ግልፅ ነው - ማየት ለሚፈልግ ሰው። እየጎተተ የሚያመጣቸው “ችግሮች” በጣም ግልፅ ከመሆንም ያልፋሉ እንጂ። ገበያውን በማሳከር፣ “አስቂኝ የኮሜዲ መድረክ” እንዲሆን ያደርጉታል። ለምሳሌ....
ጥራት ያለው ተመራጭ ምርት በአነስተኛ ዋጋ፣... ገለባ የበዛበት የወረደ ምርት ደግሞ ከፍ ባለ ዋጋ እየተሸጠ እንደሆነ ብትሰሙ...
አዎ፣ የሰማችሁትን ነገር ለማመን ብትቸገሩ አይገርምም። እንዲህ አይነቱ “የዞረበት የስካር ዓለም”፣ በኮሜዲ መድረክ እንጂ፣ እንዴት በእውን ይፈጠራል?...
ነገርዬው፣ በምናብ የተፈጠረ ልብወለድ ዓለም ከሆነ፣ አስቂኝ ኮሜዲ ሊሆን ይችላል። እንዲህ አይነት የተሳከረ ዓለም በእውን ከተፈጠረ ግን፣... ኮሜዲነቱ ይቀርና የትራጄዲ ትዕይንት ይሆናል - የሰዎችን ኑሮ የሚያናጋና ለኪሳራ የሚዳርግ፣ የአገሬውን ገበያ የሚያሳክርና ኢኮኖሚውን የሚያቃውስ ትራጄዲ።
ጥራት ያለው ተመራጭ ምርት በአነስተኛ ዋጋ፣ ገለባ የበዛበት የወረደ ምርት ደግሞ ከፍ ባለ ዋጋ እየተሸጠ እንደሆነ መስማት ሳይሆን ማየት ከፈለጋችሁ፣... የቡናን ዋጋ ተመልከቱ። ይሄ ሚስጥር አይደለም። በግላጭ የሚታይ የእለት ተእለት ኑሮ ነው።
ለገበያ የሚቀርብ ቡና፣ እንደ ሌሎቹ የእርሻ ምርቶች፣ በጥራት ደረጃና በዋጋ እንደሚለያይ ታውቃላችሁ። በአዲስ አበባ ሱቆች ውስጥ፣ በጥራት ደረጃ የሚለያዩ የቡና አይነቶችን ታገኛላችሁ  - በኪሎ ከመቶ ብር እስከ 150 ብር ሂሳብ።
ለውጭ ገበያ የሚቀርበው ቡና ደግሞ፣... ባለሙያዎች እንደሚሉት... በጥራት ደረጃቸው ከሌሎቹ በጣም የላቁ ናቸው።... በጣም የላቁ። ዋጋቸውም፣... የዚያኑ ያህል ከፍ ቢል፣ ከ150 ብር በላይ ብቻ ሳይሆን፣ ከሁለት መቶ ብርም በላይ ሊያልፍ ይችላል?
እንግዲህ፣ በጥራት ደረጃው እንደነገሩ ወረድ ያለ ቡና በማቅረብ በኪሎ፣ ከመቶ እስከ 150 ብር የምታገኙ ከሆነ፤... በጥራት ደረጃው የላቀ፣... በዓለም ደረጃ ተመራጭ የሆነ ቡና በማቅረብስ ስንት ታገኛላችሁ?
በኪሎ 3 ዶላር!
ዶላሩ እጃችሁ ውስጥ አይገባም። መንግስት፣ በብር መንዝሮ ይሰጣችኋል። ባለፈው ሳምንት በነበረው የምንዛሬ ሂሳብ ሲሰላ፣ ስንት ይሆናል?
70 ብር ለአንድ ኪሎ!
ይሄ፣ “የምናብ ዓለም” አይደለም። የእውኑ ዓለም የየእለቱ ክስተት ነው።  
ጥራቱ የወረደ ቡና ግን፣ በኪሎ ከ100 ብር በላይ... ከ120 ብር በላይ... ከ150 ብር በላይ እየተሸጠ እንደሆነ በእውን ታውቃላችሁ።
በዓለም ተመራጭ የሆነና በጥራት ደረጃው የላቀ ቡና፣ በኪሎ 70 ብር?
በጥራት የላቀ ምርት ይዛችሁ፣ በአነስተኛ ዋጋ ከመሸጥና ወደ ውጭ ከመላክ፣ እዚሁ አገር ውስጥ፣... በጣም በጣም አነሰ ቢባል ከ150 ብር በላይ መሸጥስ?
አይቻልም። ክልክል ነው። ገበያ ውስጥ ለመሸጥ ብትሞክሩ፣ እንደ ዘራፊ፣ እንደ ሌባ የሚያስቆጥር “ወንጀል” የሰራችሁ ያህል ትታሰራላችሁ።
በጥራት የላቀ ምርት፣ ለመከራ ይዳርጋል። በግማሽ ዋጋ የመሸጥ ኪሳራን ያስከትላል።
ጥራቱ የወረደ ምርት ደግሞ፣ ነፃነትን ያስገኛል፤ በፈለጋችሁ ገበያ ውስጥ፣ በገበያው ዋጋ መሸጥ ትችላላችሁ። ጥሩ ዋጋም ያስገኛል - ለአንድ ኪሎ ከ100 ብር እስከ 150 ብር።
በጥራት ደረጃው የላቀና በዓለም ገበያ ተመራጭ የሆነ ቡና ከያዛችሁ ግን፣ የገበያ ዋጋ ትከለከላላችሁ። በወረደ ዋጋ የመሸጥ ግዴታ ይጫንባችኋል - ከ80 ብር በታች በሆነ ሂሳብ። ከቅጣት በምን ይለያል?
የላቀ ጥራት፣ የላቀ ጥቅም ማግኘት በተገባው ነበር። በግዴታ ሳይሆን፣ በነፃ ገበያ! ገበያተኞችን በማስገደድ ሳይሆን፣ የምርቱን ጥራት በማሳየት፣ የተሻለ ዋጋ ለማግኘት የመሞከር ነፃነት ብቻ ነው የሚያስፈልገው፤ የሚገባውም።
ወረድ ያለ ጥራት ደግሞ፣ በዚያው መጠን ዝቅ ያለ ዋጋ!
የነፃ ገበያ በረከት፣ እንዲህ እጥፍ ድርብ ነው። የላቀ ጥራት፣... የላቀ ጥቅም እንዲያገኝ ሰፊ እድል ይፈጥራል - ነፃ ገበያ። ይሄ ነው፣ ትክክለኛው የሞራል “ፍትህ” ትርጉም። ይሄ እውን የሚሆነው፣ የእያንዳንዱን ሰው ነፃነት በሚያከብር መንገድ መሆኑ ደግሞ፣ የሕግ “ፍትህ” ብለን ልንሰይመው እንችላለን።
በተቃራኒው፣ የላቀ ጥራት፣... ለጉዳትና ለቅጣት የሚዳርግ ሆነ። በአነስተኛ ዋጋ የመሸጥ ግዴታን... ቅጣትን ያስከትላል። ነፃነትን ያሳጣል፤ እንደወንጀለኛ ያስቆጥራል።
እና ምን ይሻላል? ይሄ ሁሉ ጣጣ መዳን የሚቻለው፣... “በወረደ ጥራት” ነው!
እንዲህ አይነት “የዞረበት ዓለም” የተፈጠረው፣ በውጭ ምንዛሬ ቁጥጥር አማካኝነት ነው... በተለይ ደግሞ፣ በገንዘብ ሕትመት ሳቢያ ብር እየረከሰ ሲሄድና፣ የዶላር ምንዛሬ እንዳይስተካከል ተደፍጥጦ ሲቆይ!
ሰሞኑን፣ የዶላር ምንዛሬ ላይ የታየው ለውጥ፣ በመጠኑም ቢሆን፣ ችግሩን ለማቀለል ያግዛል።
በጥራት ደረጃው የላቀ፣... በዓለም ደረጃ ተመራጭ የሆነ ቡና በማቅረብ፣ በ3 ዶላር ሂሳብ... ማለትም 80 ብር ለማግኘት ተቻለ ማለት ነው። ከ70 ብር ወደ 80 ብር! ይሻላል። ግን፣ የወርቅ፣ የሰሊጥ፣ የእንሰሳት፣ የአበባ... አምራቾችና ነጋዴዎች ላይም ተመሳሳይ ነው። የላቀ ጥራት... መከራ ነው! ይህንን መከራ ለማስወገድ... ቢያንስ ቢያንስ ለማቃለል አለመሞከር፣ የሞራልና የሕግ ፍትህን እንደአልባሌ ከመጣል አይለይም። በላቀ ጥራት፣ ለውጭ ገበያ የሚሸጡ ሰዎች ባይበራከቱ፣ የኤክስፖርት ገቢ ባለፉት አምስት ዓመታት ባያድግ፣ እዚያው ባለበት ቢደነዝዝ፣... ጭራሽ ወደ ታች ቢንሸራተት፣... አለምክንያት አይደለም።    
የላቀ ጥራት... መከራ እንዲሆን አድርገናላ! ይህንን መከራ ለማስወገድ... ቢያንስ ቢያንስ ለማቃለል ብንሞክር፣ የሞራልና የሕግ ፍትህን የማክበር ጅምር፤... የኢኮኖሚ ውጤቱም የተሻለ ይሆንልናል።

Read 3888 times