Saturday, 07 October 2017 15:15

በ30ኛው የዓለም ኮከብ አትሌት ሽልማት አልማዝ አያና እጩ ናት

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማህበር ለ2010 የዓለም ኮከብ አትሌቶች ምርጫ በሁለቱም ፆታዎች 10 እጩዎችን ሰሞኑን ይፋ ሲያደርግ በውድድር ዘመኑ በ10ሺ ሜትር የዓለም ሻምፒዮን ለመሆን የበቃችውና በ2016 የዓለም ኮከብ አትሌት የነበረችው  አልማዝ አያና በሴቶች ምድብ ከአስሩ እጩዎች አንዷ ሆናለች፡፡
አይኤኤኤፍ ሰሞኑን በሁለቱም ፆታዎች ይፋ ያደረገውን የእጩዎች ዝርዝር ከ6 አህጉራት በተውጣጡ የዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ኤክስፐርቶች ፓናል መምረጡን ያስታወቀ ሲሆን በውድድር ዘመኑ በለንደኑ 16ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና እና በዳይመንድ ሊግ ውድድድሮች ለተመዘገቡ ውጤቶች ትኩረት እንደሰጠ ለመረዳት ይቻላል፡፡
በሴቶች ምድብ ከተያዙት አስር አጩዎች አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያዊቷ አልማዝ አያና በቅርቡ በኢቢሲ የስፖርት ሽልማት የዓመቱ ምርጥ ሴት አትሌት ተብላ እንደተሸለመች የሚታወስ ሲሆን በአይኤኤኤፍ ማህበር የ2017 የአለም ምርጥ አትሌት ምርጫ በእጩነት የቀረበችው በ16ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ በ10ሺ ሜትር የወርቅ ሜዳልያ እንዲሁም በ5ሺ ሜትር የብር ሜዳልያ በመጎናፀፏ፤ እንዲሁም በርቀቱ የዓመቱን ፈጣን ሰዓት 30፡16.62 በሆነ ጊዜ በማመዝገቧ ነው፡፡ ዋና ተፎካካሪዎቿ ይሆናሉ ተብለው የተጠበቁት በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ በየስፖርት መደባቸው የወርቅ ሜዳልያዎች ያገኙትና የዳይመንድሊግ ሻምፒዮኖቹ ናቸው፡፡
በተለይ በውድድር ዘመኑ በ5ሺ ሜትር የዓመቱን ፈጣን ሰዓት ያስመዘገበችና በምንም ውድድር ያልተሸነፈችው፤ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የወርቅ ሜዳልያ እንዲሁም የዳይመንድ ሊግ አሸናፊዋ ሄለን ኦቡሪ ከአልማዝ አያና የኮከብ አትሌትነቱን ክብር ለመንጠቅ ከፍተኛ ግምት ሲሰጣት፤ የደቡብ አፍሪካዋ ካስተር ሴማንያ በ800 ሜትር በውድድር ዘመኑ ባለመሸነፍ፤ የዓለም ሻምፒዮን ሆኖ የወርቅ ሜዳልያ በመውሰድ እና የዳይመንድ ሊግ ዋንጫን በማንሳት እንዲሁም በ1500 ሜትር በዓለም ሻምፒዮና ተጨማሪ የነሐስ ሜዳልያ በመውሰድ ነው፡፡
በከፍታ ዝላይ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና እና የዳይመንድ ሊግ ድርብ አሸናፊ ማሪያ ላሳኢታካኔ፤ በ100 ሜትር መሰናክል የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና እና የዳይመንድ ሊግ ድርብ አሸናፊ አውስትራሊያዊቷ ሳሊ ፓርሰን፤ በዲስከስ ውርወራ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና እና የዳይመንድ ሊግ ድርብ አሸናፊ የክሮሽያዋ ሳንድራ ፔርኮቪች፤ በዝርዘመት ዝላይ የዓለም ሻምፒዮን የሆነችው አሜሪካዊቷ ብሪትኔ ሪስ፤ በምርኩዝ ዝላይ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና እና የዳይመንድ ሊግ ድርብ አሸናፊ ግሪካዊቷ ኤካቴሪን ስቴካንዲ፤ በሄፕታተሎን የዓለም ሻምፒዮን የሆነችው ቤልጅማዊቷ ናፊ ሳቱ እንዲሁም በመዶሻ ውርወራ የሚስተካከላት ያጣችው ፖላንዳዊቷ አንቲታ ዋልደርሽዚያክ ሌሎቹ ተፎካካሪዎች ናቸው፡፡በሌላ በኩል በወንዶች ምድብ በ2017 የዓለም ኮከብ አትሌቶች ምርጫ ላይ ከቀረቡት አስር እጩዎች መካከል የአምና አሸናፊ ዩሲያ ቦልት አለመካተቱ ብዙዎችን አስገርሟል፡፡ ዩሴያን ቦልት የሩጫ ዘመኑን ያበቃ በዚሁ የውድድር ዘመን ሲሆን በ16ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ በ100 ሜትር የነሐስ ሜዳልያ ማግኘቱ ብቻ እንደ ትልቅ ውጤት ቢጠቀስ ነው፡፡በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ10ሺ ሜትር የወርቅ ሜዳልያ፤ በ5ሺ ሜትር የብር ሜዳልያ ያገኘውና የዳይመንድ ሊግ ያሸነፈው እንግሊዛዊው ሞፋራህ የማሸነፍ እድል ሊኖረው ይችላል፡፡ በከፍታ ዝላይ ሙታዝ ኢሳ ከኳታር፤ በመዶሻ ውርወራ ፓል ፋጄክ ከፖላንድ፤ በምርኩዝ ዝላይ ሳም ኬንድሪክስ ከአሜሪካ፤ በ1500 ሜትር ኤልያህ ማንጎኒ ከኬንያ፤ በርዘመት ዝላይ ሉቮ ማናዮናጋ ከደቡብ አፍሪካ፤ በ110 መሰናክል ኦማር ኤምሲሎይድ ከጃማይካ፤ በስሉስ ዝላይ ክሪስትያን ቴይለር አከሜሪካ፤ በ400 ሜትር ዋይደን ቫን ኒኪሪክ ከደቡብ አፍሪካ እንዲሁም በጦር ውርወራ ጆሃነስ ቬተር ከጀርመን ሌሎቹ እጩ ተፎካካሪዎች ናቸው፡፡
ዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማህበር በድረገፁ እንዳመለከተው ከ6 ሳምንታት በኋላ በ2017 ኮከብ አትሌትነት የሚመረጡ አሸናፊዎችን ለመሸለም በመጀመርያ በሚቀጥሉት 9 ቀናት አስሩን እጩዎች ወደ 3 እጩዎች ለመለየት በሶስት የዓለም አትሌቲክስ ባለድረሻ አካላት ድምጽ ይሰበሰባል። የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ማህበር ምክር ቤት 50 በመቶ እንዲሁም የአይኤኤኤፍ ቤተሰቦች የሚባሉት አባል ፌዴሬሽኖችና የተለያዩ ኮሚቴዎች አባላት 25 በመቶ የድምፅ ምርሻ በመያ የሚሰጡትን ድምፅ በኢሜል የሚያቀርቡ ሲሆን የዓለም አትሌቲክስ አድናቂዎች እና የአትሌቶች ደጋፊዎች ደግሞ በቀሪው 25 በመቶ የድምፅ ድርሻ በአይኤኤኤፍ ድረገፅ www.iaaf.org እንዲሁም ለእያንዳንዱ አስር እጩዎች በአይኤኤኤፍ ዎርልድ አትሌቲክስ ክለብ www.facebook.com/WorldAthleticsClub/ በተከፈቱ የኢንተርኔት ማህበረሰብ ገፆች ላይ በመስጠት ይሳተፉበታል።  በሶሻል ሚዲያዎቹ ላይ በፌስቡክ የየእጩዎቹን ልዩ ገፅ ላይክ በማድረግ በትዊተር ገፅ መልሶ ሪቲዊት በማድረግ ድምፅ ይሰጣል ማለት ነው፡፡
ባለፈው ዓመት በተካሄደው 29ኛው የአይ.ኤ.ኤ.ኤፍ የዓለም ኮከብ አትሌት ሽልማት ኢትዮጵያዊቷ አትሌት አልማዝ አያና በሴቶች ምድብ ማሸነፏ የሚታወስ ሲሆን  በሽልማቱ ታሪክ 6ኛውን ክብር ለኢትዮጵያ  ያስገኘችበት ነበር። በ1998 እኤአ ኃይሌ ገብረስላሴ፤ በ2004እና በ2005 እኤአ ለሁለት ተከታታይ ጊዚያት ቀነኒሳ በቀለ፤ በ2007 እኤአ መሰረት ደፋር እንዲሁም በ2015 እኤአ ገንዘቤ ዲባባ የዓለም ኮከብ አትሌት የተባሉ የኢትዮጵያ አትሌቶች ናቸው፡፡ አልማዝ አያና በ30ኛው የዓለም ኮከብ አትሌት ሽልማት በድጋሚ ከተመረጠች በሽልማቱ ታሪክ ሁለት ጊዜ ያሸነፈች  ብቸኛዋ ሴት እንዲሁም 7ኛዋ ኢትዮጵያዊ አትሌት ትሆናለች፡፡
በ2016 የአይኤኤኤፍ የዓለም ኮከብ አትሌት ምርጫ ላይ በሴቶች ምድብ አልማዝ አያና ያሸነፈችው በ31ኛው ኦሎምፒያድ በ10ሺ ሜትር የወርቅ ሜዳልያ ስትጎናፀፍ የዓለም እና የኦሎምፒክ ሪከርድ በማስመዝገቧ፤  በተጨማሪ በ5ሺ ሜትር የነሐስ ሜዳልያ በማግኘቷ እንዲሁም  በ2016 የአይኤኤኤፍ ዳይመንድ ሊግ ደግሞ በ3ሺ እና 5ሺ ሜትር 4 ውድድሮች አድርጋ በሰበሰበችው 50 ነጥብ የዳይመንድ ሊግ ዋንጫ እና የ43ሺ ዶላር ተሸላሚ ለመሆንም በመብቃቷ ነበር፡፡

Read 2103 times