Saturday, 07 October 2017 15:13

‹‹…ባለ ሙያው እውቀቱን ቢያደረጅ…ተቋማቱ ቢጠናከሩ…››

Written by 
Rate this item
(0 votes)

በኢትዮጵያ የግልም ሆነ የመንግስት… አንድም ሆስፒታል ደረጃውን መቶ በመቶ ባሙዋላ መልኩ የተደራጀ አይደለም፡፡
ባለፉት ሁለት ሳምንታት በወጣው እትም የህክምና ባለሙያዎች የህግ ተጠያቂነት በአለም አቀፍ ደረጃ ምን መልክ አለው? በአገራችንስ? የሚሉትን ነጥቦች ለንባብ ብለናል፡፡ በዚህ ዙሪያ የሚነሱ የመጨረሻ ሀሳቦችን ከህግ ከባለሙያው አቶ አበበ አሳመረ ማብራሪያ እናገኛለን። በኢትዮጵያ በሕክምና አገልግሎት አሰጣጥ በኩል የሚደርሱ ችግሮች ይህን ይመስላሉ የሚል ጥናት ባይኖርም የደረሱ ችግሮች ግን የሉም ማለት አይደለም።  ባለፉት ሁለት ሳምንታት የወጣውን እትም ያነበቡ የአንድ ቤተሰብ አባል በልጃቸው ላይ የደረሰውን ገጠመኝ በጽሁፍ ልከውልናል፡፡ እንደሚከተለው ነው፡፡  
‹…ሁኔታው ያጋጠመው በቅርብ ነው፡፡ ነሐሴ 2009/ ዓ/ም፡፡ ሕጻኑ በእድሜው 10/አመት ነው፡፡ ክስተቱ ሲያጋጥም ለእረፍት ከአያቱ ቤት ሰሚት ከሚባለው ስፍራ ነበረ፡፡ ከአባቱ እናት ጋር ሆኖ የፍልሰታን ጾም እየጾም ቁርባን ይቆርባል፡፡ አንድ ቀን ግን ያልታሰበ ሁኔታ ያጋጥ ማል፡፡ በድንገት ልጁ ታመምኩ አለ፡፡ ትኩሳት መድከም የመሳሰሉት ነገሮች ይታዩበታል፡፡ ቀረብ ወደሚለው ሐኪም ቤት ይወስዱታል፡፡ ከሐኪም ቤቱም የተገኘው መልስ የጨጉዋራ ሕመም መሆኑንና የሚመገበውን እና የማይመገበውን ምግብ ነግረው የጨጉዋራ መድሀኒት ይሰጡታል፡፡ ይህ ሕጻን እውን የጨጉዋራ በሽታ ያዘው? እንዴት? እየተባለ በቤተሰብ ውስጥ ሀሳቡ እየተንገዋለለ እሱም ህመሙ ምንም ሳይሻለው እንዲያውም እየባሰበት ሁለት ቀን አደረ፡፡ በሶስተኛው ቀን ግን ልጁ ምንም አይንቀሳቀስም፡፡ ዛለ፡፡ አይናገርም፡፡ ትኩሳቱ እጅግ ከፍ ብሎአል፡፡ እንደገና ወደሌላ ሐኪም ቤት ተወሰደ፡፡ የተገኘው መልስ እጅግ አስደንጋጭ ነበር። ትርፍ አንጀቱ በጊዜው ሕክምና ስላላገኘ ፈንድቶአል (rupture) አድርጎአል የሚባል ነበር፡፡ ቤተሰብ በሙሉ ተደናገጠ። ሐኪሞቹም እጅግ አዘኑ፡፡ ነገር ግን መሞቱ ካልቀረ ይከፈትና ይሞከር ተብሎ ከሁለት ሰአት በላይ የፈጀ ኦፕራሲዮን ተደርጎ አሁን ደህና ነው፡፡ ከመሞትም ተርፎአል፡፡ ለዚህ ጉዳይ ተጠያቂው ማነው? በሚል ሀሳቡን ለተለያዩ ሐኪሞች  አንስተን ነበር፡፡ የሐኪሞቹ መልስ ግን አስገራሚ ነበር፡፡
ግማሾቹ …በእርግጥ የጨጉዋራና የትርፍ አንጀት ሕመም ስሜት ይመሳሰላል፡፡ ለዚህም ነው ሐኪሙ ጨጉዋራ ነው ያለው አሉ፡፡
ሌሎቹ ደግሞ…ልጁ ሕጻን ስለሆነና በትክክል ስሜቱን መግለጽ ስለማይችል ሐኪሙ ሊሳሳት ይችላል፡፡ ይህ ደግሞ የሚያጋጥም ነገር ነው የሚል ነበር መልሳቸው፡፡
አልፎ አልፎ ግን አ..አ…ይ፡፡ ቢሆንም …ሐኪሙ  አስቀድሞ ከመወሰኑ በፊት መጠራጠርና በተገቢው መንገድ ምርመራ እንዲካሄድ ማድረግ ነበረበት ያሉም አሉ፡፡
እንግዲህ በእንዲህ ያለው አጋጣሚ እድል ካልቀናና ተገቢው ሐኪም ካልተገኘ የስንት ሰው ሕይወት እንደሚቀጠፍ መገመት ይቻላል፡፡ የህክምና ስህተት ማለት እንደሌሎች የስራ ዘርፎች ስህተት በቀላሉ ሊተካ ወይንም ሊታረም የማይችል የሰው ሕይወት ጉዳይ ነው። የአንድ ሰው ሕይወት ካለፈ በሌላ ሊተካ አይችልም። ሐኪሙ ቢከሰስ ቢወቀስ እንኩዋን ያ ያለፈ ሕይወት ሊመለስ አይችልም፡፡ አበቃ፡፡ ስለዚህ ይህ ነገር በደንብ ቢታሰብበት ጥሩ ይመስለኛል፡፡ የህክምና ባለ ሙያው በደንብ እውቀቱን ቢያደረጅ እንዲሁም አገልግሎት መስጫ ተቋማቱ በደንብ ቢጠናከሩ እና የአሰራር ዘዴያቸው ግልጽ እንዲሆን አስቀድሞ መሰራት ያለበት ነገር ቢሰራ ለአገልጋዩም ለተገልጋዩም ጠቀሜታው የጎላ ነው፡፡
የታማሚው አባት
አቶ አበበ አሳመረ እንደሚገልጹት በቅድሚያ የሙያ ኃላፊነት የሚባለውን ነገር ስንመለከት ማስረጃው ተቀባይነት አለው ወይ? ከየት ነው መምጣት ያለበት? ማንነው ይህንን ማስረጃ ለመስጠት በሕግ ስልጣን ያለው? …ወዘተ የሚል የማስረጃ ሕግ ስለሌለን ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን ክርክር እያየ ማስረጃ እየመዘነ ውሳኔ እየሰጠ ይገኛል፡፡ ወደፊት ግን መጀመር ያለበት አሰራር አለ፡፡ …ለምሳሌ በሌሎች አገሮች የሙያ ማህበራት አንዱ ሚናቸውና ኃላፊነታቸው የሙያ ኃላፊነት ላይ የሚወሰኑ ውሳኔዎችን ማስተቸት ነው፡፡ ይህም …
በስራ ላይ ያለው ሕግ የጎደለው ነገር ካለ እንዲመለከቱትና እንዲሻሻል ጥያቄ ለማቅረብ ይረዳል፡፡
የማህበር አባላትን በጉዳዩ ላይ ግንዛቤ እንዲያገኙና በአሰራራቸው እንዲጠነቀቁ እንዲሁም ትምህርት እንዲያገኙ ለማድረግ ይረዳል፡፡
ፍርድ ቤቶች በተመሳሳይ ጉዳይ የሚቀርብላቸውን የኃላፊነት መጉዋደል በሚመለከት ቀደም ብሎ የተሰራውን ስራ ወይንም የተወሰነውን ውሳኔ ሲያዩ የህጉን አተረጉዋጎም፣ የማስረጃ አሰባሰብ እንዲሁም እንዴት እንደተመዘነ በሚመለከት ሁሉ የተኬደበትን አሰራር ለማጤንና ለማገናዘብ እንዲረዳቸው ያግዛል፡፡
ከሕክምና አገልግሎት ጋር በተያያዘ የህግ ስራ ለሚሰሩ ማንኛቸውም አካላት ፣ለፖሊሲ አውጭዎች አሰራር ይረዳል፡፡
ከዚህ ውጭ ግን ልንመለከተው የሚገባን ነገር አለ ብለዋል አቶ አበበ፡፡ በሕክምና ሙያ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ዘርፎችም ላይ የመገናኛ ብዙሀን የሚያደርሱት የተጋነነ የመረጃ አሰጣጥ በሙያው የተሰማራውንም ሌላውንም ተገልጋይ እኩል የሚጎዳበት ሁኔታ ይስተዋላል፡፡ ለምሳሌ ያህል የሚከተለውን ገጠመኝ ላስታውስ ብለዋል የህግ ባለሙያው አቶ አበበ አሳመረ፡፡
‹…በአንድ ወቅት ከአንዲት ታካሚ ሆድ ውስጥ የፈሳሽ ማምጠጫው ፋሻ ወይንም ጎዝ ተረሳ፡፡ ወደህግ ሲቀርቡ ሶስቱም ሐኪሞች ጥፋተኛ ነን አሉ፡፡ ነገር ግን አለቃቸው በሰጠችው አስተያየት የባለሙያ እጥረት ፣የተቋማቱ የአደረጃጀት አለመሟላት የመሳሰ ሉት ሁሉ አብረው መታየት እንዳለባቸው ነው፡፡ አንድ ሐኪም መስራት ከሚገባው ሰአት በላይ እንዲሰራ ሲገደድ እንደሰው መድከምና መሳት ሊገጥመው ይችላል፡፡ ይህ ለምን ይደረጋል እንዳይባል …ታካሚው ቁጥሩ ከሐኪሙ በላይ ስለሆነ እና በወቅቱ ካልተሰራለት ሊሞት ስለሚችል ቢያንስ እንደምንም ይታይ የሚል ውሳኔም፣ ስምምነ ትም ተደርጎ ሐኪሙ በቅንነት እንዲያየው የተቻለው ሁሉ ይደረጋል፡፡ በዚህ መሀል አንድ ሐኪም አብዛኛውን ሰው አድኖ ግን አንድ ሰው ቢሞትበት ለፍርድ ከመቅረብ ባሻገርም በመገናኛ ብዙሀን በተጋነነ ሁኔታ ለህዝብ አቅርቦ ማሳጣት ሚዛኑን አያጣም ወይ? በሕግ ከሚችለው በላይ በከበደ መልኩ የሚዳኝና በመገናኛ ብዙሀኑም ብዙ የሚባል ከሆነ አንድ ሐኪም እኔ መስራት የሚገባኝ በቀን ይህን ያህል ታካሚ ማየት ብቻ ነው፡፡ ከዚህ በላይ አልችልም ብሎ ጋዋኑን አስቀምጦ ቢወጣ እስትሬቸር ላይ የሚሞተው ሰው ቁጥር ይጨምራል፡፡ የሚል ነበር፡፡
አቶ አበበ እንደሚሉት አንድ የህክምና አሰጣጥ ስህተት ተፈጠረ ሲባል ነገሩን ከብዙ አቅጣጫ መመልከትና መመርመር ይገባል፡፡ የትጋ ነው ስህተቱ የተፈጠረው? በባለሙያው ግድየለሽነት ወይንም የእውቀት ማነስ ነው? ወይንስ በተቋሙ የአሰራር ዘዴ መበላሸት ነው? …ወዘተ ይህንን ለማረጋገጥ የሰከነ አካሄድን ይጠይቃል፡፡ ካለበለዚያ ግን የህክምና ባለሙያው አስቀድሞውኑም ትምህርቱን ወይንም ሙያውን እንዳይመርጠው እስከማድረግ ድረስ የሚያደርስ የተሳሳተ አካሄድ ሊፈጠር ስለሚችል መጠንቀቅ ይፈልጋል፡፡ እንደ አቶ አበበ ማብራሪያ በኢትዮጵያ የግልም ሆነ የመንግስት አንድም ሆስፒታል ደረጃውን መቶ በመቶ ባሙዋላ መልኩ የተደራጀ አይደለም፡፡
በሌሎች አገሮች የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት በሕክምና ተቋማት አደረጃጀት አለመስተካከልም ይሁን በባለሙያው አሰራር ስህተት ምክንያት በሚፈጠሩ ስህተቶች የተነሳ በሕክምና ባለሙያውና በታካሚው መካከል የሚፈጠሩ ቅርበቶች ሊሻክሩ ይችላሉ፡፡ ሐኪሙም ሁልጊዜ ኃላፊነትን የሚያስብ ከሆነ በቀጥታ በትክክል ሊያድን የሚችለውን መድሀኒት ከማዘዝ ይልቅ መጠራጠርን በማብዛት በኃላፊነት ላለመጠየቅ ሲባል …ይህ ቢሆንስ…ይህ ባይሆንስ ስለሚል የተለያዩ ላቦራቶሪዎች ውጤት እንዲቀርብለት ማዘዝ የመሳሰሉትን እርምጃዎችን ሊወስድ ይችላል፡፡ ይህ አካሄድ ደግሞ ሕመምተኛው አፋጣኝ ውሳኔን እንዳያገኝ …እንዲሁም ለተለያዩ ወጪዎችም ሊዳረግ ይችላል፡፡
አቶ አበበ አሳመረ በማጠቃለያቸው የተናገሩት ‹‹…ሐኪሞች ሳይጨነቁና ሳይፈሩ በራስ በመተማመን የሚሰሩ ከሆነ ተገልጋዩም በደንብ ይጠቀማል፡፡ ስለሆነም በኃላፊነት የሚጠየቁ ባለሙያዎች የሚከፍሉት ካሳ የተጋነነ እና ሕይወትን የሚፈታተን መሆን የለበትም። ሆን ተብሎ የተፈጸመ ጥፋት ካልሆነ በቀር ወደወንጀል ኃላፊነት መውሰድም ባይኖር ጥሩ ነው፡፡ ባጠቃላይም ማህበራቱ ተጠናክረው ሌላው አለም እንደሚንቀሳቀሰው ቢንቀሳቀሱ እንዲሁም በዘርፉ የተለያዩ ጥናቶች ማለትም ከኢንሹራንስ ከሕግ አሰራር የመሳሰሉት ሁሉ መሰረት ተደርገው ጥናቶች ቢካሄዱ በቀጣይ ለሚኖረው አሰራር ይጠቅማል፡፡›› ብለዋል፡፡ 

Read 2023 times