Saturday, 07 October 2017 15:10

የ2017 የኖቤል ተሸላሚዎች ይፋ እየተደረጉ ነው

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

የኖቤል የሽልማት ተቋም የ2017 የኖቤል አሸናፊዎችን ዝርዝር ከያዝነው ሳምንት መጀመሪያ አንስቶ ይፋ በማድረግ ላይ ሲሆን፣ እስካሁንም የፊዚክስ፣ የኬሚስትሪ፣ የህክምና እና የስነጽሁፍ ዘርፍ ተሸላሚዎች ታውቀዋል፡፡
ተቋሙ ባለፈው ሰኞ ይፋ ባደረገው ቀዳሚው የዓመቱ የኖቤል የህክምና ዘርፍ ተሸላሚዎች ዝርዝር፣ ሰርካዲያን ሪትም በተባለ የዘርፉ ምርምር የላቀ ፈጠራ ያበረከቱት ሶስቱ አሜሪካውያን ተመራማሪዎች፡-  ጄፍሪ ሲ ሃል፣ ማይክል ሮስባሽ እና ማይክል ደብሊው ያንግ አሸናፊዎች መሆናቸውን አስታውቋል፡፡
ማክሰኞ ዕለት ይፋ የተደረገው የፊዚክስ ዘርፍ ተሸላሚዎች ዝርዝር በበኩሉ፡- ሌዘር ኢንተርፌርኖሜትር ግራቬቲሽናል ዌቭ በተባለው የፊዚክስ መስክ የላቀ የምርምር ውጤት ያበረከቱት ጀርመናዊው ሬነር ዌስ እና አሜሪካውያኑ ተመራማሪዎች ባሪ ሲ ባሪሽ እና ኪፕስ ኤስ ትሮን የዘርፉ አሸናፊዎች እንደሆኑ አስታውቋል፡፡
ሬነር ዌስ የ1 ሚሊዮን ዶላር ሽልማቱን ግማሽ ሲወስድ፣ ሌሎቹ ሁለት ተመራማሪዎች ቀሪውን ገንዘብ እኩል እንደሚካፈሉ ተቋሙ አስታውቋል፡፡
የዓመቱ የኖቤል የኬሚስትሪ ዘርፍ ተሸላሚዎችን ባለፈው ረቡዕ ይፋ ያደረገው ዘ ሮያል ስዊድሽ አካዳሚ ኦፍ ሳይንስስ፣ እጅግ ረቂቅ የሆኑ ደቂቀ አካላትን በከፍተኛ ሁኔታ አጉልቶ የሚያሳይ ማይክሮስኮፕ የፈጠሩትና የባዮ ኬሚስትሪ መስክ ምርምርን ወደላቀ ደረጃ ያሳደገ ነው የተባለለት የዚህ የፈጠራ ውጤት ባለቤቶች የሆኑት ስዊዘርላንዳዊው ጃክ ዶቼት፣ እንግሊዛዊው ሪቻርድ ሄንደርሰን እና አሜሪካዊው ጆኣኪም ፍራንክ የዘርፉ አሸናፊዎች መሆናቸውን አስታውቋል፡፡  
“ዘ ሪሜንስ ኦፍ ዘ ዴይ” እና “ኔቨር ሌት ሚ ጎ” በሚሉት ተወዳጅ ልቦለድ መጽሐፍቱ የሚታወቀው እንግሊዛዊው ደራሲ ኢካዙኦ ሺጉሮ፤ 830 ሺህ የእንግሊዝ ፓውንድ የሚያስገኘው የዘንድሮ የኖቤል የስነ ጽሁፍ ዘርፍ ተሸላሚ መሆኑን ተቋሙ ከትናንት በስቲያ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
እ.ኤ.አ በ1954 በጃፓኗ ናጋሳኪ የተወለደው ደራሲው፣በረቀቀና ጥልቅ ስሜትን በሚጭር አጻጻፉ ዓለማቀፍ ዝናን እንዳተረፈ ያስታወቀው ተቋሙ፤ ሁለቱ ተወዳጅ ስራዎቹ በፊልም መልክ ተሰርተው ለእይታ መብቃታቸውን ተከትሎም ዝናው የበለጠ በዓለም ዙሪያ መናኘቱን አመልክቷል።
የአልፍሬድ ኖቤል መታሰቢያ የሆነው የኢኮኖሚክስ ዘርፍ የ2017 ተሸላሚ በበኩሉ፤ ከነገ በስቲያ ስቶክሆልም ውስጥ በሚከናወን ስነስርዓት በይፋ እንደሚገለጽ ይጠበቃል፡፡

Read 3683 times