Saturday, 07 October 2017 15:09

የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የ4ኛ ዓመት ኢንጂነሪንግ ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲው ተመልሰዋል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

ለ4 ቀናት ከግቢው ውጭ ተንገላተዋል

  ከፈተና ጋር በተገናኘ ከዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ጋር ውዝግብ ውስጥ የገቡት የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የ4ኛ ዓመት የኢንጂነሪንግ ተማሪዎች፤ ዩኒቨርሲቲው “ውሳኔዬን ቀይሬያለሁ ተመለሱና ተማሩ” ማለቱን ተከትሎ ከ4 ቀናት እንግልት በኋላ ትናንት ወደ ዩኒቨርሲቲው መመለሳቸው ታውቋል፡፡  
ተማሪዎቹ የክረምት የእረፍት ጊዜያቸውን አጠናቀው ወደ ዩኒቨርሲቲው ሲመለሱ በቀጥታ የብቃት መለኪያ ፈተና ትወስዳላችሁ መባሉንና የውጤት አያያዙ ከቀድሞው መለወጡን በመቃወማቸው አለመግባባቱ መፈጠሩን ለአዲስ አድማስ የጠቆሙት ምንጮች፤ በዚህ ውዝግብ ለ3 ቀናት በግቢው ከቆዩ በኋላ ዩኒቨርሲቲው የምግብ አገልግሎት በማቋረጥ ግቢውን ለቀው እንዲወጡ ማሳሰቢያ መስጠቱንና ተማሪዎችም ማክሰኞ እለት ከግቢው መውጣታቸውን አስረድተዋል፡፡
ተማሪዎቹ በፀጥታ ኃይሎች ተገድደው ከግቢው መውጣታቸውን ተከትሎ፣ በሰአታት ልዩነት ውስጥ የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ባወጣው አዲስ መመሪያ ላይ ማሻሻያ ማድረጉን በመግለፅ፤ ተማሪዎቹ ወደ መደበኛ ትምህርታቸው እንዲመለሱ የሚገልፅ ማስታወቂያ ማውጣቱም ታውቋል፡፡
ይሁን እንጂ ከ1400 በላይ የሚሆኑት እነዚሁ የ4ኛ አመት የኢንጂነሪንግ ተማሪዎች፤ ዩኒቨርሲቲው አስተዳደር የማሻሻያ ውሳኔ በቂ አይደለም በሚል ለ4 ቀናት ከዩኒቨርሲቲው ውጪ በከተማዋ ተበትነው ለእንግልት ተዳርገው ቆይተዋል ተብሏል።
አብዛኞቹ ተማሪዎች በባህር ዳር ከተማ በሚገኙ የተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት ግቢና በወዳጅ ዘመዶቻቸው ቤት ተጠግተው መቆየታቸውን ምንጮች ለአዲስ አድማስ አስታውቀዋል፡፡ በዚህ ምክንያትም እስከ ትናንት ድረስ ተማሪዎቹ ለከፍተኛ ችግር ተዳርገው እንደነበር ያነጋገርናቸው ምንጮች አስረድተዋል፡፡
የተማሪዎቹ የተቃውሞ መነሻ የእረፍት ጊዜያቸውን አጠናቅቀው የ4ኛ አመት ትምህርታቸውን ለመቀጠል ወደ ዩኒቨርሲቲው ማምራታቸውን ተከትሎ፣ ከ5 ቀናት በኋላ “ሆልስቲክ” በመባል የሚታወቅ ከ26 የትምህርት አይነቶች የተውጣጣ የመመዘኛ ፈተና ትፈተናላችሁ መባሉ መሆኑን ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ተማሪዎች ለአዲስ አድማስ አስረድተዋል፡፡
“እኛ የመመዘኛ ፈተናውን ተፈትነን ወደ ቀጣዩ አመት ለማለፍ ችግር የለብንም” የሚሉት ተማሪዎቹ፤ “ጥያቄያችን በቂ የመዘጋጃ ጊዜ ይሰጠን፤ አሠራሩ አዲስ እንደመሆኑም ግንዛቤ ማግኘት አለብን የሚል ነው” ብለዋል፡፡ ሌላኛው የተማሪዎቹ ቅሬታ ከዚህ በፊት ከ “A” እስከ “F” በሚለካ የውጤት አሰጣጥ (ግሬዲንግ) ስርአት ውጤት ይገለጽላቸው የነበረው ሲሆን አሁን ግን “ከ50 በመቶ በታች ያመጣ ተማሪ ወዳቂ ነው” የሚል አዲስ መመዘኛ ተግባራዊ መደረጉንና በዚህም በርካታ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ እንደተደረጉ በመግለጽ አሠራሩን ተቃውመዋል። ይህ የመመዘኛ ስርአት በርካቶችን ከትምህርት ገበታ ውጪ ያደርገናል የሚል ስጋት ላይ መጣሉን ተማሪዎቹ አስታውቀዋል፡፡
በጉዳዩ ላይ ከትናንት በስቲያ ሐሙስ ምሽት ላይ ያነጋገርናቸው የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር ንጉስ ነብየሃብቱ፤ ተማሪዎቹ በተሻሻለው አሰራር መሰረት ለመፈተን ዝግጁ ነን ካሉ ወደ ግቢው መመለስ እንደሚችሉ ገልፀውልን የነበረ ሲሆን ተማሪዎቹ ትናንት ረፋድ ላይ ወደ ግቢው መመለስ መጀመራቸውም ታውቋል፡፡  
ዩኒቨርሲቲው ማሻሻያ ያደረገው ወደ ኢንተርንሺፕ መግቢያ ውጤት አያያዝ ላይ መሆኑን የጠቆሙት ዶ/ር ንጉስ ማለፊያ ነጥቡ 50 ተደርጎ የነበረው ወደ 40 ዝቅ እንዲል መደረጉን ጠቁመዋል። እንዲሁም የፈተና መስጫ ጊዜው ከ3 ሳምንት በማይበልጥበት ሁኔታ መራዘሙን አስታውቀዋል። ውጤት አያያዙም ቀድሞ ወደ ነበረው የግሬዲንግ አሰጣጥ (A-F) መመለሱንም ዶ/ር ንጉስ ለአዲስ አድማስ ጨምረው አስረድተዋል፡፡

Read 3456 times