Saturday, 07 October 2017 14:59

ሞያተኛው ቀብር አስፈፃሚ

Written by  መሐመድ ኢድሪስ
Rate this item
(14 votes)

አንድሬ ጁድ በሩ ሲከፈትለት ከአሳንሰሩ ወጥቶ ወደ ኮሪደሩ አመራ፡፡ ወደዚህ ሆስፒታል ከዚህ በፊት መጥቶ አያውቅም፡፡ ጭንቅላተ ትልቁና ጉጭማው አንድሬ፤ ግራጫማ ካኪ ሱሪና አላባሹን ጃኬት ነበር የለበሰው፡፡ የዘወትር አለባበሱ እንደዚህ ነው፡፡ ኑሮው ከሙታን ጋር ስለሆነ አለባበሱ ከቀብር አፈር ጋር መመሳሰል እንዳለበት፤ ለምን እንደዚህ እንደሚለብስ ለሚጠይቁት ሁሉ ፈገግ እያለ የሚሰጠው ምክንያት  ነው፡፡ ፈገግታው ከፊቱ የማይጠፋው አንድሬ፣ በሰሜን ለንደን ውስጥ ለሰላሳ አመታት የቀብር አስፈፃሚ ሆኖ ሲሰራ አንድም ቀን ደንበኞቹን አስከፍቶ አያውቅም፡፡
አንድ ጊዜ ልጅዋ የሞተባት እናት ቢሮው ድረስ መጥታ እያለቀሰች፤ “ልጄ መሞቱን አላምንም፣ አሁንም ውድ እናቱን ፈልጎ ከሞት የሚነቃ ይመስለኛል፡፡ አሁን እዚያ ሳጥን ውስጥ ሆኖ ቢነቃ ምን ይውጠዋል? አንድ ነገር አድርግ አንድሬ!” ስትለው ጮሌውና ትሁቱ አንድሬ ፈገግ ብሎ፣ “አይጨነቁ ማዳም፤ ስራዬ ሙታንን በሰላም ወደ ፈጣሪ መሸኘት ነው፡፡ ያላለቀ ስራ ወይም ፍላጎት ካላቸው፣ ነፍሳቸው ወደ ሰማይ አትወጣም፡፡ እዚሁ ምድር ላይ ስለምትቅበዘበዝ “ጎስት” ሆነው ይቀራሉ” አላቸው፡፡
“ጎስት!? ያንተ ያለህ አንድ ሺህ ፓውንድ እከፍላለሁ፡፡ አንተ የፈጣሪ ሰው ነህ፤ አንድሬ ልጄን አሳርፍልኝ” አለች ሴትየዋ አይንዋ ፈጥጦ፡፡
“ደህና ብለዋል ማዳም፤ገንዘቡን ይዘው ከሰአት በኋላ ይምጡ”
ሴትየዋ ከሰአት በኋላ ስትመጣ፣ አንድሬ የሟቹ የሬሳ ሳጥን መዝጊያ ስር በወርቃማ ፍሬማ የለበጠውን፣ እጅዋን ዘርግታ የቆመችውን የድንግል ማርያም ምስል አሳያት፡፡
“ልጅዎ ከሞት ቢነሳ መጀመርያ የሚያየው እመቤቴን ስለሆነ፣ የእስዋ ፀጋና ሰላም ወደ ፈጣሪ ይወስደዋል!”
ሴትየዋ በደስታ ፊቷ በርቶ፤ “አሁን ገና ልቤ አረፈ፡፡ እናቴን የያዘ ምን ይሆናል!” አለችና የአገልግሎቱን አንድ ሺህ ፓውንድ፣ መቶ ፓውንድ ደግሞ ጉርሻ ጨምራ ለአንድሬ ሰጠችው፡፡
ይህ የሆነው ከብዙ አመታት በፊት ሲሆን በቀጣዮቹ አመታት ሞያተኛው ቀብር አስፈፃሚ፣ የደንበኞቹን ፍላጎት እያረካና ዳጎስ ያለ ገንዘብ እያስከፈለ መጦርያውን አካብቷል፡፡ ጠቀም ያለ ገንዘብ ይከፈለው እንጂ አልችለውም የሚለው ነገር የለውም፡፡ እድሜ ልኩን ወንደላጤ ሆኖ የሞተው ልጃቸው ሚስት ባለማግባቱ ልባቸው በሃዘን ለተሰበረው እናት፣ መቃብሩ በወጣት ቆንጆ ልጃገረድ እንክብካቤ ሲደረግለት አሳይቷቸው፣ ዳጎስ ያለ ገንዘብ ተቀብሏቸዋል፡፡ ልጃገረዲቱ መቃብሩን ስትጠርግ፣ አበቦች ስትተክልና ስትንከባከብ ነው እናትየው ያዩት፡፡ የልጃቸው ሚስት መሆንዋ ነው፡፡
አንድሬ በሆስፒታሉ ኮሪደር ውስጥ እየተራመደ፣ በራሱ ችሎታ እየተገረመ ነበር፡፡ በመላው ለንደን ውስጥ ተወዳዳሪ የሌለው ቀብር አስፈፃሚ ለመሆን የበቃው፣ በሶስት ምክንያቶች ነው፡፡ የመጀመርያው ምክንያት ሞያውን ማክበሩ ነው፡፡ ሁለተኛው ምንም ይሁን ምንም የደንበኞቹን ፍላጎት ማሟላት መቻሉ፡፡ ሶስተኛውና ዋነኛው ግን እሱ እራሱ ነው፡፡ እሱና የሱ ጭንቅላት፡፡ የሱ ጭንቅላት በመጠን ብቻ አይደለም የገዘፈው፡፡ በማሰብ ሃይሉም ጭምር እንጂ፡፡ ትሁት፣ ፈገግታ የማይለየው፣ ሞያውን አክባሪ፣ የደንበኞቹን የልብ ትርታ የሚያውቅና ለችግራቸው ከሰማይ በታች መፍትሄውን አፈላልጎ የሚሰጥ ሊሆን የቻለው በጭንቅላቱ ነው፡፡ በዚህ ምድር ላይ ማንም በጭንቅላት አይበልጠኝም ሲል አሰበ፤ ኮሪደሩ ላይ እየተራመደ፡፡
የፈለገው የበር ቁጥር ዘጠኝን ነበር፡፡ እዚያ በመኪና አደጋ ግጭት መጠነኛ ጉዳት ደርሶበት የተኛ ወንድሙ አለ፡፡ ይሄ ዘሎ ያልጠገበ ወንድሙ፣ በጣም ቢወደውም አሁን አሁን ተስፋ እያስቆረጠው መጥቷል፡፡ የእሱ ሐሳብ የሱን ፈለግ ተከትሎ፣ እንደሱ እገሌ እንዲባል ነበር፡፡ ወንድሙ ግን እንደሱ ከሙታን ጋር መኖር የፈለገ አይመስልም፡፡ ከአቅሙ በላይ ከሆኑ ሰዎች ጋር እየገጠመ፣ ያለ ችሎታው፣ ደራሲ መሆን ይፈልጋል፡፡ ስራውም እንደ ሃብታም ደራሲያን ጓደኞቹ፤ ያልሆነ ፍልስፍና መፈላሰፍ፣ ቀኑን በሙሉ ውስኪ መጠጣትና ሴቶችን ማማገጥ ብቻ ሆኖዋል፡፡
አንድሬ የበር ቁጥር ዘጠኝን እየፈለገ፣ ኮሪደሩ ላይ ሲራመድ ቆየና ድንገት ቆመ፡፡ ክፍሉን አግኝቶታል፡፡ በሩን ከፈተና ወደ ውስጥ ገባ፡፡ ክፍሉ ውስጥ ሁለት አልጋዎች ናቸው ያሉት፡፡ አንደኛው ታናሽ ወንድሙ የተኛበት ሲሆን ሁለተኛው ቤተሰቦቹና ሀኪሞቹ የከበቡት ሌላ በሽተኛ የተኛበት ነበር፡፡ አንድሬ ሰላምታ ሰጠና በቀጥታ ወደ ወንድሙ አመራ፡፡ ወዲያው ወንድሙ ላይ ማንቧረቅ ጀመረ፡፡
“አንተ የማትረባ! እንደለመድከው ዊስኪህን ገልብጠህ ስትነዳ ከቆመ ስልክ እንጨት ጋር ተጋጨህ?! ጭንቅላት እንደሌለህ እንኳን የታወቀ ነው፡፡ አይን ግን የለህም ? እንዴት ስልክ እንጨትን የሚያክል ነገር ማየት ያቅተሃል?” አለ፤ አልጋው ላይ እየተቀመጠ፡፡
“ምን ይደረግ!? ፈጣሪ ያመጣው ነው” አለ ወንድሙ።
“አንቡላህን እየተጋትክ ፈጣሪ ፈጣሪ ትላለህ፡፡ ፈጣሪ ምን ያድርግህ? አፍህን ዘግተህ አይኖችህን ከፍተህ ማሽከርከር የነበረብህ አንተ ነህ፡፡ ዳሩ ምን ዋጋ አለው፡፡ ከዚያ ሐሚልተን ከሚሉት እብድ ደራሲ ጋር ያለህን ጉዳይ ካላቆምክ የሚጠብቅህ ሞት ብቻ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ምን እንማደርግልህ ታውቃለህ፤ የሬሳ ሳጥንህ ውስጥ አንድ ካርቶን ዊስኪ ከትቼ፣ ግብአተ ቀብርህን ማስፈፀም ብቻ ነው፡፡ መቼም አንተ እዚያም ሳያምርህ አይቀርም” አለ አንድሬ በምጸት፡፡
“ሐሚልተን ከኔ ጋር አልነበረም”
“ባይኖር አይገርመኝም፡፡ አንድ አጭር ልቦለድ ፅፎ፣ ሃምሳ ሺህ ፓውንድ የሚከፈለው ሰው ነው። እንዳንተ ስራ ፈት አይደለም፡፡ እብደቱ ከእውቀቱ ጋር ነው፤ መሃይም እብድ አይመቸኝም”
“ደህና አሁን ነገሩ አልፏል፡፡ የቀኝ ትከሻው ላይ ቀላል ቁስል ነበር፤ ቁስሉን ሰፍተን አስፈላጊውን ህክምና አድርገንለታል፤ አሁን መውጣት ይችላል” አለች አንዲት ነጭ ጋዋን የለበሰች ወጣት ነርስ፣ አጠገባቸው ቆማ፡፡
ወንድሙ የሆስፒታሉን ፒጃማ አውልቆ ልብሱን ሲለባብስ፣ የአንድሬ ትኩረት ክፍሉ ጥግ ያለው፣ ሁለተኛው አልጋ ላይ አርፎ ነበር፡፡ አልጋው ላይ የተኛው በሽተኛ፣ እራሱን የሳተ ሲሆን ሁለት ነጭ ጋዋን የለበሱ ነርሶችና ሌሎች ሁለት ሰዎች ከበውታል፡፡ ከሃኪሞቹ ውጭ ካሉት ሁለት ሰዎች አንዱ ሰማያዊ ሙሉ ልብስ የለበሰ ወጣት ሲሆን ሁለተኛዋ ቀጠን ብላ ረዘም ያለች ወጣት ሴት ነበረች። አንድሬ፤ ሴትየዋ የበሽተኛው ሚስት፣ወጣቱ ደግሞ ጓደኛው ሊሆን እንደሚችል ገምቷል፡፡
አንድሬ፤ ወደ በሽተኛው አልጋ ተጠጋ፡፡ ምንም ሳይናገር እጁን የበሽተኛው ግንባር ላይ ጫነ፡፡ ሃኪሞቹና ሰዎቹ በመደነቅ ያዩታል፡፡ እጁን ከሰውየው ግንባር አነሳና፣ አንሶላውን ገልጦ እግሮቹ ላይ አሳረፈ፡፡ አሁንም ሁሉም ሰው በመገረም እያየው ነው፡፡ ትንሽ ቆይቶ እጁን ከበሽተኛው እግር ላይ አነሳና፣ እንደ ጉድ ወደሚመለከተው ወጣት ወንድ ጆሮ ጠጋ ብሎ፣ “በሁለት ደቂቃ ውስጥ ይሞታል፤ ቀብር አስፈፃሚ ከፈለጉ አንድሬ ጁድ እባላለሁ” አለውና፣ ከኪሱ ካርድ አውጥቶ ሰጠው። ሰውየው በመገረም አፍጥጦ ተመለከተው፡፡
አንድሬና ወንድሙ ከክፍሉ ወጥተው ወደ አሣንሠሩ ሲያመሩ የኡኡታ ድምጽ ሰሙ፡፡ በሽተኛው እንደሞተ የገባው የአንድሬ ወንድም፤
“እንዴት አወቅህ?” ሲል ጠየቀው
“ሞያተኛ ነኝ፡፡ ከሙታን ጋር ለሰላሳ ዓመታት ያህል ቆይቻለሁ፡፡ እግሩ ቀዝቅዞ ነበር፡፡” አለው አንድሬ፡፡
አንድሬ ቢሮው ገብቶ፣ አንዳንድ ስራዎችን ሲሰራ አረፈደ፡፡ ከሰአት በኋላ ትንሽ እረፍት ወስዶ ቡናውን እየጠጣ እያለ የቢሮው በር ተንኳኳ፡፡ የገባው ሰው ቀጠን ብሎ ረዘም ያለ፣ ቡናማ ሰብር ያለው የጣልያን ሱፍ የለበሰ፣ ቡናማ ህብር ያለው ባርኔጣ ያደረገ ሲሆን ሮሌክስ ሰአት አስሮአል። አንድሬ ይሄ ሽቅርቅር ሰው ማን እንደሆነና ምን እንደሚፈልግ ለማወቅ ጓግቶ፣ የተለመደ ፈገግታውን እያሳየው፣ እንዲቀመጥ ጋበዘው፡፡ ሰውዬው እግሩን አነባብሮ ተቀመጠ፡፡
አንድሬ ሰውየውን በጥንቃቄ አጠናው፡፡ ፊቱ ከጥርብ ድንጋይ የተሰራ ይመስላል፡፡ የጉንጩና የግንባሩ እጥፋቶች ብዙ ያሳለፈ እንደሆነ ይመሰክራሉ፡፡ ቀጥ ያለ አፍንጫና ሰርስረው የሚያዩ አይኖች አሉት፡፡ አንድሬ አይኖቹን ሲመለከት ሰውየው የዋዛ እንዳልሆነና ብልህ እንደሆነ ስለተረዳ፣ ከዚህ በፊት የዋህ ደንበኞቹን የሚያስተናግድበት ብልጠት እሱ ላይ እንደማይሰራ ገብቶታል፡፡
“ምን ነበር?” ጠየቀ አንድሬ
“ሞያተኛ ቀብር አስፈፃሚ እንደሆንክ ሰምቻለሁ። እንድትረዳኝ እፈልጋለሁ” አለ፡፡
ሰውየው ወፍራም ሲሆን ገደብ የሌለው በራስ መተማመን ይታይበታል፡፡
“ሟች ማን ነው?” ጠየቀ አንድሬ
“እኔ ነኝ!”
አንድሬ ሰውየው እሱ ላይ ሊያላግጥ እንደመጣ አሰበና ብስጭት አለ፡፡ ሆኖም ፈገግታው ከፊቱ አልጠፋም፡፡ ህይወት ብዙ አስተምራዋለች፡፡ ስሜታዊ ሳይሆን ሰውየውን ማስጨረስ እንዳለበት ወሰነ፡፡
“መች ነው የሞትከው?”
“እስካሁን አልሞትኩም፡፡ ወደፊት ነው የምሞተው፡፡”
“ይቅርታ ስምህን ሚስተር?”
“ቢን ሃሚልተን እባላለሁ፡፡ ደራሲ ነኝ፡፡”
አንድሬ  አልተገረመም፡፡ ዝነኛው ደራሲ ቢን ሃሚልተን፣ የሱን ወንድም ጨምሮ የብዙ ሚልዮን ሰዎችን ቀልብ የገዛ ሲሆን ስለ ችሎታው ማንም ባይከራከርም ወፈፍ እንደሚያደርገው ግን ሁሉም ሰው የሚያወራለት ነው፡፡
“አልገባኝም?” አለ አንድሬ
“ላይገባህ ይችላል፤ ላስረዳህ እሞክራለሁ” አለ ሰውየው፡፡
“ቀጥል”
“እስከዛሬ ከፃፍኳቸው ታሪኮች የተለየ ታሪክ ያለው አጭር ልቦለድ መፃፍ ጀምርያለሁ፡፡ እንዴት እንደምትረከው ግን አላውቅም፡፡ ዋናው ነገር ታሪኩን መተረክ ነው፡፡ የኔም ህይወት ታሪኩ ውስጥ አለ፡፡ እና ታሪኩን ስመለከት አንድ ችግር እንዳለ ተረዳሁ” አለ ቢን ሃሚልተን፤ የአንድሬን አይኖች ትኩር ብሎ እያየ፡፡
“ችግሩ ምንድነው?”
“ከልክ ያለፍ የአልኮልና የኮኬይን ተጠቃሚ ነኝ። ሱሱን ደግሞ ማቆም አልቻልኩም፡፡ በዚህ የተነሳ ከዚህ በፊት ለሃያ አራት ሰዓታት እራሴን ስቼ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ አንድ ነገር ተረዳሁ፡፡ በማንኛው ጊዜ ልሞት እንደምችል፡፡ ሞትን አልፈራም፡፡ ነፍሴ የምትሄደው ወደ ፈጣሪ ነው፡፡ የምፈራው ስጋዬ ቀባሪ አጥቶ እንዳይበሰብስ ነው፡፡ ይህ ስጋ መሽተት የለበትም፡፡ ነፍሴ ከስጋዬ በወጣችበት ቅፅበት አስክሬኔ ታጥቦ፣ ተገንዞና ተገቢው የፀሎት ስርአት ተደርጎለት እንዲቀበር እፈልጋለሁ፤ ይህን ማድረግ የምትችለው ሞያተኛ ቀብር አስፈፃሚ አንተ ስለሆንክ ካንተ ጋር አንድ ኮንትራት ለመፈራረም ፈልጌ ነው”
“ምን አይነት ኮንትራት?”
ሐሚልተን ከደረት ኪሱ ውስጥ ረብጣ ፓውንድ አወጣና ጠረጴዛው ላይ አስቀመጠ፡፡
“ይሄ ምንድነው?” ጠየቀ አንድሬ፡፡
“አስር ሺህ ፓውንድ ነው፡፡ ለስራ ማስኪያጃ ይሆነናል፡፡ እንደ ኮንትራቱ ቀብድ ልታየውም ትችላለህ”
“ኮንትራቱ ምንድነው?” ጠየቀ አንድሬ፤ ልቡ እየመታ፣ ቀብዱ ብቻ አስር ሺህ ፓውንድ የሆነ ኮንትራት ምን ሊሆን እንደሚችል እየገመተ፡፡
“ኮንትራቱ እኔ በሞትኩኝ በሃያ አራት ሰዓት ውስጥ አስፈላጊውን ስርአት ፈፅመህ፣ አስከሬኔን እንድትቀብር ነው፡፡ ይህንን ስታደርግ ካለኝ የባንክ ሂሳብ አንድ መቶ ሺህ ፓውንድ ትወስዳለህ”
አንድሬ አይኑን ጨፍኖ በጥሞና ማሰብ ጀመረ። አሁን ነገሩ አጓጉል ቀልድ እንዳልሆነ ገብቶታል። በሰላሳ ዓመታት ሞያዊ ህይወቱ እንደዚህ አይነት ውል ተዋውሎ አያውቅም፡፡ ይህ ስጋዬ መበስበስ የለበትም የሚል ሽቅርቅር፣ ቀላል ሰው እንዳልሆነ አውቋል፡፡ እሱም እራሱ ቀላል ሰው እንዳልሆነ የሚያውቀው አንድሬ፤ ከእኔና ከሱ ማን ያሸንፍ ይሆን? ሲል አሰበና፣ ነገሩን በጥልቀት ለማወቅ ጥያቄ መደርደሩን ቀጠለ፡፡
“ቤተሰብ የለህም? ሊቀብርህ የሚችል ማለቴ ነው”
“የለኝም”
“አግብተሃል?
“አዎ፡፡ ግን ሚስቴ አለሌ ነች፡፡ ከውሽሞችዋ ጋር ከመንዘላዘል በስተቀር ይህንን ሃላፊነት የምትወጣ አይደለችም” አለ ሃሚልተን፤ ከኪሱ የዊስኪ መያዣ ቆርቆሮ አውጥቶ አንዴ እየተጎነጨ፡፡
“ታድያ ለምን አትፈታትም?”
“ይሄም የምፅፈው ታሪክ ውስጥ ያለ እንቆቅልሽ ነው፡፡ እንደነገርኩህ ዋናው ነገር ታሪኩ እንዴት እንደሚሄድ ነው፡፡”
“ማለት?”
“እንደምትዘሙት አውቃለሁ፡፡ ነገር ግን ማስረጃ የለኝም፡፡ ያለ ማስረጃ ብፈታት ደግሞ ካለኝ ሃምሳ ሚሊዮን ፓውንድ ውስጥ ግማሹን ትወስዳለች፡፡”
“እሺ እኔ በውሉ መሰረት ስራዬን ስጨርስ ገንዘቡን ማን ይሰጠኛል?”
“የኔ የግል ደብተር፣ የህግ ጠበቃዬና ሂሳቤ የተቀመጠበት ባንክ ስራ አስኪያጅ ያሉበት ኮሚቴ ይቋቋምና ገንዘቡ በኔ ኑዛዜ መሠረት ይሰጥሃል፡፡ ሃኪሙ አስከሬኑ በወቅቱ መቀበሩን የማያረጋግጥ፣ ጠበቃው ደግሞ ህጋዊ ስራዎችን የሚያቀላጥፍ፣ የባንኩ ስራ አስኪያጅ ደግሞ ክፍያውን የሚፈፅም ሲሆን ኮንትራቱ በፍርድ ቤት ይፀናል፡፡”
“መሞት አለመሞትህን፣ እንዴት አውቃለሁ ሚስተር ሃሚልተን?”
“ቀላል ነው፡፡ በየቀኑ ሶስት ጊዜ ስልክ ትደውልልኛለህ፡፡ ቢያንስ አንዱን አንስቼ ካንተ ጋር መነጋገር አለብኝ፡፡ ይህ ካልሆነ ችግር አለ ማለት ነው፡፡ የቤቴን አድራሻና ቁልፍ ስለምሰጥህ ፈጥነህ መጥተህ ስራህን መስራት ነው፡፡”
አንድሬ ለደቂቃ ያህል አቀርቅሮ ሲያስብ ቆየና ቀና አለ፡፡ ትኩር ብሎ የሃሚልተንን አይኖች ማየት ጀመረ፡፡ ለሴኮንዶች ተፋጠጡ፡፡ የሃሚልተን አይኖች የሚሰበሩ አልነበሩም፡፡ አንድሬ አይኖቹን ሰበረና በረጅሙ ተነፈሰ፡፡ እነዚያ አይኖች የሚረጩት ጨረርና ሃይል፣ ፍርሃትና ደስ የማይል ስሜት የሚፈጥር ነበር፡፡
“ተስማምቻለሁ፡፡ ነገ ያልካቸው ሰዎች በተገኙበት በፍርድ ቤት ውሉን እንፈፅማለን፡፡” አለ አንድሬ፤ እጁን ለሰላምታ እየዘረጋ፡፡ ሁለቱም ተጨባበጡና ቢን ሃሚልተን ተነስቶ ወደ በሩ አመራ፡፡
“ሚስተር ሃሚልተን” አለ አንድሬ፤ ሃሚልተን በሩን ከፍቶ ሊወጣ ሲል፡፡
“ወንድሜ፣ ጓደኛህ እንደሆነ አውቃለሁ፡፡ ቤትህም ቤቱ እንደሆነ፡፡ ስለዚህ ከውሉ ባሻገር ላንተ የተለየ ቀረቤታ እንዳለኝ ልነግርህ ፈልጌ ነው” አለ አንድሬ ፈገግ ብሎ፡፡
ሃሚልተን የምጸት ፈገግታ ፈገግ አለና፤ “እንደነገርኩህ ዋናው ነገር ታሪኩ ነው፡፡ ታሪኩ እንዴት እንደሚሄድ--” አለና በሩን ከፍቶ ወጣ፡፡
በቀጣዩ ቀን ኮንትራቱ ተፈረመ፡፡ አንድሬ የቤቱን አድራሻና ቁልፍ ከወሰደ ሶስት ወራት አለፉ። በየቀኑ ሶስት ጊዜ እየደወለ የሃሚልተንን ደህንነት ማረጋገጥ የአንድሬ ስራ ሆነ፡፡ ስራው  በጣም አሰልቺ እየሆነበት መጣ፡፡ በየቀኑ ስራዬ ብሎ ሰዓት ሳያዛንፍ፣ ሶስት ጊዜ መደወል አድካሚ ስራ ሆነበት። ሐሚልተን ከአሁን በኋላ ሰባ አመታት ቢኖር፣ ለሰባ አመታት ያህል አይምሮው ሳያርፍ በየቀኑ ሶስት ጊዜ መደወልና የቅንጡው ደራሲን ደህንነት ማረጋገጥ እንዳለበት ሲረዳ፣ የሐሚልተን ጠባቂ ባርያ እንደሆነ ተሰማውና አምርሮ ጠላው፡፡ ድሮም ቢሆን ቀልቡ አይወደውም ነበርና፣ ሞቶ አንድ መቶ ሺህ ፓውንድ ለመውሰድ በጉጉት ተናጠ፡፡
ሌላው ችግር ውሉን ማፍረስ አለመቻሉ ነው። ምክንያቱም ውሉን ካፈረሰ፣ ውሉን ላከበረው ሐሚልተን ሃያ ሺህ ፓውንድ የመስጠት ግዴታ አለበት፡፡ ይሄ ደግሞ እድሜ ልኩን የቋጠረውን ጥሪቱን ያራቁትበታል፡፡ ሌላው ውሉን የማያፈርስበት ምክንያት ደግሞ ሐሚልተን ቢሞት የሚያፍሰው መቶ ሺህ ፓውንድ፡፡ መቶ ሺህ ፓውንድ ሳይሰራ እድሜ ልኩን አንቀባሮ የሚያኖረው ገንዘብ ነው፡፡ ስለዚህ መፍትሄው አንድ ብቻ ነው፡፡ የሐሚልተን መሞት፡፡ ሐሚልተን ግን የሚሞት አይነት ሰው አልሆነም፡፡ ድምፁን በስልክ ሲሰማው ከአሁን በኋላ ገና ለመቶ ዓመታት የሚኖር ነው የሚመስለው፡፡
አንድ ቀን ምሽት ግን ነገሩ ተቀየረ፡፡ አንድሬ ደጋግሞ ቢደውልም ሐሚልተን ስልኩን አላነሳም። ጊዜው ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ሲሆን በዚያ ሰዓት ሊተኛ እንደማይችል የታወቀ ነው፡፡ በዚያ ላይ ቀንም ሲደውልለት አላነሳም ነበር፡፡ በአንድሬ ልብ ውስጥ ተስፋ እንደገና አንሰራራ፡፡ አጅሬ ሐሚልተን አልቆለታል ማለት ነው፡፡
አንድሬ ሲዝናናበት ከነበረው ግሮሰሪ ወጥቶ፣ መኪናውን እያበረረ፣ ወደ ኦክስፎርድ ጎዳና አመራ፡፡ አሁን ምን ማድረግ እንዳለበት ያውቃል። አስፈላጊውን ዝግጅት ካጠናቀቀ በኋላ በነጋታው የሐሚልተንን አስከሬን በኬንሳል ግሪን የመቃብር ስፍራ ግብአተ መሬቱን ይፈጽምለታል፡፡ ይህንን የሚያደርገው ከሐሚልተን የግል ሐኪም፣ ጠበቃና ከባንክ ቤቱ ስራ አስኪያጅ ፊት ሲሆን ከዚያ በውሉ መሰረት አንድ መቶ ሺህ ፓውንድ መቀበል፡፡ ልቡ ጮቤ እየረገጠ፣ የመኪናውን ፍጥነት ጨመረ፡፡
ቤቱ እንደደረሰ በሩን በቁልፍ ከፍቶ ወደ ሳሎኑ አመራ፡፡ ማንም የለም፡፡ መኝታ ቤቱን ከፍቶ ቃኘ፡፡ አሁንም ምንም አላገኘም፡፡ የመታጠቢያ ቤቱን በር ከፍቶ ሲገባ፣ ባየው ነገር ደሙ ሲቀዘቅዝ ይታወቀው ነበር፡፡ ሐሚልተን የመታጠቢያ ገንዳው ውስጥ የተኩረፈረፈ የሳሙና አረፋ ባለው ሙቅ ውሃ ውስጥ በእጁ ዊስኪ በበረዶ የተሞላ ብርጭቆ ይዞ ተንጋሎዋል፡፡ የተለኮሰ ሲጋራ የገንዳው ጠርዝ ላይ በተቀመጠ መተርኮሻ ላይ እየጨሰ ነው፡፡ አንድሬ አሁን ትዕግስቱ ተሟጠጠ፡፡
“ለምንድነው ስልኩን ያላነሳኸው?” ሲል ጠየቀ በብሽቀት፡፡
“ሞያተኛ መሆንህን ለማረጋገጥ ነው” አለ ሐሚልተን በተቀዛቀዘ ስሜት፤ “አሁን ስራህን በደንብ መስራት እንደምትችል አስመስክረሃል፡፡ እንደነገርኩህ ዋናው ነገር ታሪኩ እንዴት እንደሚጓዝ ነው፡፡ ይሄ ክስተት የታሪኩ አንድ አካል ነው---”
አንድሬ የተለመደ ፈገግታውን እያሳየ፤ “አሃ.. ገባኝ፡፡ መልካም የስራ ምሽት” አለና በሩን ዘግቶ ወጣ። የዘጋው ግን በሩን ብቻ አልነበረም። የሐሚልተንን ፋይል ጭምር እንጂ፡፡ ከአሁን በኋላ አይታገስም፡፡ ወደ ቤቱ ሲሄድ ሐሚልተንን ለማስወገድ ወሰነ፡፡
በቀጣዩ ቀን ምሽት ላይ አንድሬ የፊት ጭንብሉን አጥልቆ፣ ጓንቱን አድርጎ፣ ሽጉጡን አቀባብሎ ወደ ሐሚልተን ቤት አመራ፡፡ በሩን በቁልፍ ከፈተና ኮቴውን እንዳይሰማ በጥንቃቄ እየተራመደ፣ ወደ ሳሎኑ አመራ፡፡ ማንም ሰው አልነበረም፡፡ የመኝታ ቤቱን በር ከፍቶ ሲገባ አየው፡፡ አልጋው ላይ ተንጋሎ በአንሶላ ተሸፍኖ ተኝቷል፡፡ ወደ አልጋው ተጠጋና ትራሱን አነሳ፡፡ ወዲያው በትራሱ አፈነው። ተንፈራፈረ፡፡ አንድሬ ትራሱን አጥብቆ ጫነበት። ነፍሱ እስክትወጣ ድረስ ተንፈራፈረና ፀጥ አለ፡፡ አንድሬም ድምፁን አጥፍቶ በገባበት እግሩ ወጣና ወደ መውጭያው በር ሲያቀና፣ የመታጠቢያ ቤቱ በር ተከፈተና አንዲት የለሊት ልብስ የለበሰች ሴት ወጣች፡፡ ገና ስታየው ጩኸትዋን አስነካችው። አንድሬ ሁለት ጊዜ ተኩሶ መሬቱ ላይ ዘረራት፡፡ አሁን ስራው ተጠናቋል፡፡ ምንም የተወው ፍንጭም የለም፡፡ በፍጥነት ከቤቱ ወጣና መኪናውን አስነስቶ ተሰወረ፡፡
ሶስት ቀናት አለፉ፡፡ ወንድሙ ግን ቤት ተመልሶ አልመጣም፡፡ ቢደውልለትም ስልክ አያነሳም፡፡ ወደየጓደኞቹ እየደወለ ደብዛውን ሊያገኝ ሞከረ፡፡ አየሁት የሚል ሰው ግን አልተገኘም፡፡ በአራተኛው ቀን የቢሮው በር ተንኳኳ፡፡ “ይግቡ” አለ አንድሬ። በሩ ተከፍቶ የገባውን ሰው ሲመለከት፣ አንድሬ በድንጋጤ አይኑ ተጎልጉሎ ሊወጣ ደረሰ፡፡ ቢን ሐሚልተን ሙሉ ጥቁር ሱፍ፣ ነጭ ሸሚዝ ለብሶ፣ ቀይ ከረባት አስሯል፡፡ ተደላድሎ ወንበሩ ላይ ተቀመጠ፡፡
“ባለፉት አራት ቀናት ስልክ አልደወልክም። ስራህን በትክክል አልሰራህም፡፡ ስለዚህ ውሉን ለማፍረስ ነው የመጣሁት” አለ የምፀት ፈገግታ ፊቱ ላይ እየታየ፡፡
አንድሬ እስከዛሬ “ጎስት” አይቶ አያውቅም፡፡ አሁን ግን በትክክል ፃእረ ሞት እያየ እንደሆነ አሰበና የገዛ ምራቁ አነቀው፡፡
“ያልደወልኩበት ምክንያት..” ሊናገር ጀመረና አንጠልጥሎ ተወው፡፡
“አውቃለሁ” አለ ሐሚልተን ዘና ብሎ፤ “ያን ቀን ገንዳው ውስጥ እየታጠብኩ የመጣህ ቀን ፊትህ ላይ ያነበብኩት በነጋታው ልትገድለኝ እንደምትመጣ ነበር፡፡ ደራሲ ስለሆንኩ ገፀ ባህርያትን ማንበብ እችላለሁ፡፡ ስለዚህ ስራ እንዳለኝና ለሶስት ቀናት እንደማልመጣ ለሚስቴ ነግሬ ጓደኞቼ ቤት ሰነበትኩ።
ይህ ሲሆን አመንዝራም ውሽማዋ ከሆነው ወንድምህ ጋር ስትዳራ እንደምትሰነብት አውቃለሁ። ይሄን ግዜ ነው ገዳዩ የሚመጣው፡፡” አለው ሰርፀው በሚያዩት አይኖቹ ትኩር ብሎ እያየው፡፡
አንድሬ ልቡ እንደ ነጋሪት መጎሰም ጀመረ፡፡ “ወን--ድ--ሜ--” ተንተባተበ፡፡ “አዎ ወንድምህ! እንደነገርኩህ ዋናው ነገር ታሪኩ እንዴት እንደሚሄድ ነው፡፡ ብፈታት ኖሮ ግማሽ ሐብቴን የምትካፈለው አመንዝራዋና ውሽማዋ ተወግደዋል፡፡ ይህ በመሆኑ ሃያ አምስት ሚሊዮን ፓውንድ ሳተርፍ፣ ሁለቱ ጠላቶቼ ደግሞ ከትናንት ወዲያ ፖሊስ ቀብሯቸዋል። ወንጀሉ በተፈፀመበት ወቅት ቤቴ እንዳልነበርኩና አብርያቸው እንደነበርኩ ሰዎች ምስክርነት ስለሰጡ ፖሊስ በነፃ ለቆኛል፡፡ አሁን ሚስቴን የሚያማግጥ ባላንጣና ንብረቴን የምትካፈለኝ ቀበኛ አመንዝራ በህይወቴ ውስጥ የሉም፡፡ ‹ፐርፌክት ስቶሪ›” አለ ሐሚልተን፡፡
አሁን አንድሬ ሁሉም ነገር ወለል ብሎ ታየው። አፍኖ የገደለው ለካ የሐሚልተን አልጋ ላይ ተኝቶ የነበረውን የገዛ ወንድሙን ነው፡፡ መቶ ሺህ ፓውንድ ለመውሰድ ከመጓጓቱ የተነሳ አንሶላውን ገልጦ እንኳን ፊቱን ለማየት አልሞከረም፡፡ ሚስቲቱም ብትሆን በሐሚልተን የማትፈለግ ስትሆን በሱ ሽጉጥ ለዘላለም አሸልባለች፡፡ አሁን ሐሚልተን የሚባለው ሰይጣን፣ በሱ ህይወት ታሪኩን እየፃፈ እንደሆነ ተረዳ፡፡ ሁሉም ሰው የሱ ገፀ ባህሪ ነበር። የሱ ገፀ ባህሪ፣ መቶ ሺህ ፓውንድ የሚከፈለው ቅጥር ነፍሰ ገዳይ ነው፡፡ አሁን ግን ሐሚልተን ውሉን ሊያፈርስ ነው፡፡ ስለዚህ ገዳዩ ቤሳ ቤስቲን አያገኝም፡፡ ደራሲው ምንም ገንዘብ ሳያወጣና በፖሊስ የመጠርጠር አደጋ ሳያገኘው፣ ጠላቶቹን ፈጅቶና አፋጅቶ ጨርሶዋቸዋል፡፡ ሰዎች ስለዚህ ሐሚልተን የሚባል ደራሲ የሚያወሩት ነገር አሁን ገባው፡፡
“እውነትህን ነው፡፡ ‹ፐርፌክት ስቶሪ›” አለ አንድሬ፤ ድምፁ እየተንቀጠቀጠ፡፡ ሻንጣውን ሸክፎ ገንዘቡን ይዞ ከአገር ለመውጣት እያሰበ ነበር፡፡
“እንደነገርኩህ ዋናው ነገር ታሪኩ ነው፡፡ ስለዚህ ከዚህ በላይ ፍፁም አደርገዋለሁ፡፡ ታሪኩ የተዋጣለት አጭር ልብ ወለድ እንዲሆን ሁለት ነገሮች መጨመር አለባቸው” አለ ሐሚልተን ትኩር ብሎ አንድሬን እየተመለከተ፡፡
“ምንና ምን?” አለ አንድሬ፤ እንባ እያነቀው፡፡
“ደራሲው፤ ገዳዩ ገፀ ባህሪ ለዋናው ገፀ ባህሪ የሰራለትን ውለታ ስለሚያስታውስ እንዲያዝ አይፈልግም፡፡ ነገር ግን ከመያዝ ሊያድነው አይችልም፡፡ ታሪኩ የተዋጣለት አጭር ልቦለድ እንዲሆን ገዳዩ መያዝ አለበት፡፡ ጥቁር ሱፍና ጥቁር መነፅር የሚያደርጉት የስኮትላንድ ያርድ ኢንስፔክተሮች ከገዳዩ ጋር እህል ውሃ መቀማመሳቸው አይቀርም፡፡ ዋናው ገፀ ባህሪ ቢሞት፣ መቶ ሺህ ፓውንድ የሚወስደውና የቤቱ በር ቁልፍ በእጁ ያለው በእንግሊዝ አገር ውስጥ አንድ ሰው ብቻ ነው፡፡ ይሄ መረጃ ለኢንስፔክተሮቹ የቢንጎ እጣ ነው፡፡ ይሄ ነጥብ ታሪኩ ላይ ቢጨመር ታሪኩ ምን ሊሆን እንደሚችል አስበው?!” አለ ሐሚልተን የምፀት ፈገግታ ፊቱ ላይ እየታየ፡፡
“ሁለተኛው ነጥብስ ምንድነው?” አለ አንድሬ ሆዱን ባር ባር እያለው፡፡ ቀዝቃዛ ላብ በጀርባው እየወረደ ነበር፡፡
“ሁለተኛው ነጥብ የታሪኩ መቋጫ ነው። ዋናው ገፀ ባህሪ አመንዝራም ሚስቱ ሞታለች። ልትወስድበት ያሰበችው ሃያ አምስት ሚሊዮን ፓውንድም ተርፎዋል፡፡ ገዳዩም ይያዛል፡፡ ስለዚህ አሁን ስለማረፍያው ማሰብ አለበት፡፡ በማንኛውም ሰአት ሊሞት ስለሚችል የቀብሩን ነገር ማስተካከል አለበት፡፡ ስለዚህ ካርል ሂዩስተን ከተባለ ሰው ጋር አዲስ ውል ይፈራረማል፡፡ ይህ የታሪኩ መቋጫ ሲሆን ዋናው ገፀ ባህሪ ሁሉንም ነገር አስተካክሎ ጨረሰ ማለት ነው” አለ ሐሚልተን፤ከኪሱ የዊስኪ መያዣ ቆርቆሮ አውጥቶ አንዴ ከተጎነጨ በኋላ፡፡
“ማነው ካርል ሂዩስተን?”
“ሞያተኛ ቀብር አስፈፃሚ ነው፡፡” አለ፤ ሐሚልተን ፊቱ ላይ የምፀት ፈገግታ እየታየ፡፡
የአዘጋጁ ማስታወሻ፡- የታሪኩ መቼትና የገጸባህርያቱ ስሞች የፈረንጅ ቢሆኑም ድርሰቱ ሙሉ ለሙሉ ወጥ ልብወለድ መሆኑን ደራሲው ለዝግጅት ክፍላችን አረጋግጦልናል፡፡ ደራሲውን በአንባቢያን ስም ከልብ ልናመሰግነው እንወዳለን፡፡

Read 4754 times