Saturday, 07 October 2017 14:55

ተርጓሚ ሕይወት ታደሰን አንብቧት!

Written by 
Rate this item
(5 votes)

ተርጓሚ ሕይወት ታደሰ፤ የሐማ ቱማን The Case of the Socialist Witchdoctor “የሶሻሊስቱ ጠንቋይ ጉዳይ” በሚል ወደ አማርኛ የተረጎመች ሲሆን የሕይወት ተፈራን Mine to Win ደግሞ “ኃሰሳ” በማለት ወደ አማርኛ መልሳዋለች፡፡ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በህግ ሙያ በመጀመሪያ ድግሪ የተመረቀችው ሕይወት ታደሰ፤ እንዴት ወደ ትርጉም ሥራ ልትገባ ቻለች? የተርጓሚነት ተሞክሮዋስ ምን ይመስላል? ”አንደምታ” ከተሰኘው ድረገፅ ላይ ያገኘነውን ቃለምልልስ ለጋዜጣ እንዲመች አድርገን እንዲህ አቅርበነዋል፡፡ ከልጅነት እስከ ዕውቀት --- ትናገራለች፡፡ ወደፊት ልትስራ ያቀደቻቸውንም እንዲሁ፡፡የህግ ምሩቋን ተርጓሚ ሕይወት ታደሰን እነሆ፡፡ አንብቧት፡፡


እስቲ በልጅነትሽ ከመጻህፍት ጋር ባለሽ ትውውቅ ጨዋታችንን እንጀምር ---
በልጅነቴ መጀመሪያ ላይ ያነበብኳቸው የልጆች መጻሕፍት አልነበሩም። በስምንት ወይም በዘጠኝ አመቴ ያነበብኩትን የመጀመሪያ መጽሐፍ (“ግርዶሽ” በሲሳይ ንጉሡ) ጨምሮ በዚያን ጊዜ አካባቢና ከዚያ በኋላ ሁሉ ይታተሙ የነበሩትን ያካትታል። ቤታችን ውስጥ በርካታ ልብወለድ፣ የታሪክና ጥቂት የሚባሉ ከዚህ ውጪ የሆኑ መጻሕፍት ነበሩ። ልብወለዶቹ የሀገር ውስጥ ወጥ ስራዎች፣ ብዛት ያላቸው ትርጉሞችና ጥቂት በእንግሊዘኛ የተጻፉ ናቸው። በሀገራችን ታሪክ ዙሪያ በተለያየ ጊዜ የተጻፉ መጻህፍትም ቤት ውስጥ ነበሩ። እንዲሁም በይዘታቸው ለየት ያሉ በዚያ እድሜዬ የሚገርሙኝ አንዳንድ መጻሕፍት ነበሩበት፡፡ በቤት ውስጥ የህክምና እርዳታ አሰጣጥ ላይ የሚያተኩር ወደል የእንግሊዘኛ መጽሐፍና ‘ባሃኡላህና አዲሱ ዘመን’ የሚል አንድ ደቃቃ መጽሐፍ ለአብነት ያህል ትዝ ይሉኛል። በትምህርት ቤት ደግሞ እንደው ለይስሙላ በክፍል ውስጥ ይሰጡ የነበሩ እንደ ‘እጅ ስራ’ ያሉ የትምህርት ክፍለ ጊዜዎች ላይ የልጆች መጻሕፍትን የምታነብልን ታሪክ የምትባል መምህርት ነበረች። ለኔ ባለውለታዬ ናት። ‘የተኛችው ቆንጆ፣ ሲንደሬላ፣ አንድ ሺህ አንድ ሌሊት፣ ቲሙርና ቡድኑ ወዘተ’ በሙሉ መኖራቸውን ያወቅሁት በእሷ ምክንያት ነው። ብዙዎቹ እነዚህ መጻሕፍት ትርጉሞች ናቸው። ከትምህርት ቤት ተመልሼ ማታ ማታ እነዚያን ታሪኮች ለእህቶቼና ለእናቴ ስተርክ አመሻለሁ። ሳላስብበት ትረካን (story telling) ወደድኩ።
ቤት ውስጥ የነበሩትን ልብወለዶች በተለይ ትርጉሞቹን በሙሉ አንብቤያቸዋለሁ። ኢንተርኔት፣ ጉግል የመሳሰለውን በማላውቅበት፣ ለአቅመ የብእር ጓደኛ ባልበቃሁበት እድሜ ላይ ስለነበር ያነበብኳቸው፣ በርካታ አስደናቂ ዓለማትን ለምናቤ ከፍተዋል። ከ1983 ወዲህ ደግሞ ከዚያ በፊት ያለፈውን የአስራ ሰባት አመት ታሪክ በተለያየ አኳኋን የሚዘክሩ መጻሕፍት መጡና ቀልቤን ማረኩት። ከዚህ በኋላም እናቴ የBritish Council ቤተመጻሕፍት የአባልነት መታወቂያ አወጣችና፣ የተለያዩ የእንግሊዘኛ መጻሕፍትን አስነበበችኝ፡፡ አባቴም የእንግሊዝ ሥነጽሑፍ ቁንጮ ደራሲያንን ዘመን ተሻጋሪ ሥራዎች፣ ለታዳጊ ወጣቶች እንዲሆኑ አጠር ተደርገው የተዘጋጁትን፣ ከፍ ስንልም እንደዚያው ጠንከር ያሉ መጻሕፍትን ገዝቶ ያስነብበን ነበር።
የንባብ ባህሉ በትምህርት ቤትም ቀጠለ ወይስ ---?
እስከ ስምንተኛ ክፍል በተማርኩበት የገዳመ ሲታውያን ማርያም ጽዮን ትምህርት ቤት (Cistercian Monastery Mariam Tsion School) የማስታውሰው፣ የተለመደው የአማርኛ ቋንቋችንን የማዳበሪያ ተግባራት ይሰጡን እንደነበረ ነው፤ ግጥም መጻፍ፣ ክርክር ማድረግ የመሳሰሉት። ሰባተኛና ስምንተኛ ክፍል ላይ ግን የአማርኛ መምህራችን ከዚህ በላይ ገፍቶ ያተጋን ነበር። ተውኔት ደርሰንና አዘጋጅተን፣ በክፍል ውስጥ ስናቀርብ አስታውሳለሁ። በአማርኛ ሥነጽሑፍ ውስጥ እስካሁንም የሚጠቀሱ አውራ ደራስያንና ስራዎቻቸው ላይ ሂሳዊ ንባብ እንዲሁም ግምገማዎችንም እንድናካሂድ ያደርገን ነበር። በዚህ መልኩ መምህራችን (አቶ ታሪኩ)፤ የአማርኛ ሥነጽሑፍን እንደው ዝም ብሎ ማንበብ ብቻ ሳይሆን ማጣጣምንም አስተምሮናል።የሁለተኛ ደረጃ ትምህርትን በተከታተልኩበት ሰላም የሕጻናት መንደር ትምህርት ቤት ደግሞ መደበኛ የመማሪያ መጽሐፉ ከሚጠቁመው በተጨማሪ ለማትሪክ የበለጠ ዝግጁ ያደርጋል ብለው ያሰቡትን ይዘት አክለው የሚያስተምሩን ሁለት የአማርኛ መምህራን ነበሩ። ስለዚህ ከተማርነው ይዘት ፈሊጣዊ አነጋገሩ፣ ቅኔው፣ ምሳሌያዊ አነጋገሩና ይህን የመሳሰለው ይበዛ ነበር። እና ደግሞ ቁጥር የለሽ (መምህራኑ ‘ጥሬ’ የአማርኛ ቃላት የሚሏቸው) በተለምዶ በሚነገረው አማርኛችን ውስጥ እምብዛም የማንገለገልባቸው አስገራሚ ቃላትን አጥንተናል።
ድራማና ጭውውት ደርሶ አዘጋጅቶ መተወን፣ በክፍል ውስጥ ብቻ  ሳይሆን፣ በክፍሎች መካከል በውድድር መልክ የሚካሄድና፣ በየማለዳው ቀኑን በጸሎት በምንጀምርበት አዳራሽ (ቻፕል) ውስጥ ለተማሪዎችና ወላጆች በሚቀርቡ ዝግጅቶችም ላይ የምንሳተፍበት ሁኔታ ነበር።
እንዴት ነው ሕግን ለማጥናት የወሰንሽው?
ወፍራም እንጀራ ያወጣል፣ ያስተማምናል ስለተባልኩና፣ የተባልኩትን ስለሰማሁ! ጉጉት፣ ጥያቄ፣ ቀጥታ ንግግርና ትንሽ ድፍረት የምታሳይ፣ በትምህርት ቤት ደህና ውጤት ያላት ታዳጊ ስትሆን ጸሐፊ ወይም ተዋናይት መሆን ትችላለች ብሎ  የሚመኝልህ ብዙ ሰው አይኖርም፤ ነገረ ፈጅ እንጂ! ዩኒቨርሲቲ ስገባ  ምን ማጥናት እንዳለብኝ ብዙዎችን ሳማክር ተመሳሳይ ምላሽ ስላገኘሁ፣ ይህንኑ በመከተል ሕግን መረጥኩ። 
በአገራችን በሕግ ሙያ የተመረቁ  በርካታ የኪነጥበብ ዝንባሌ ያላቸው ሰዎች አሉ፡፡ የተለየ ምክንያት ያለው ይመስልሻል?
እውነት ነው። ሕግ ተምረው የኪነጥበብ ዝንባሌ  ያላቸው ምሩቃን ጥቂት አይደሉም። በተለይ ከመነሻው ትንሽም ቢሆን ኪነጥበባዊ ፍላጎት (interest) የነበራቸው ሰዎች ከሆኑ። ምክንያቱ ምን እንደሆነ ሳስብ የሚከተለው ይታየኛል፤ በተለይ በራሴው ልምድ ከተገነዘብኩት በመነሳት። አንደኛ የሕግ ትምህርት የቋንቋና የግንዛቤ ክህሎትን ይሞርዳል ብዬ አስባለሁ። የሕግ ትምህርት የግድ ከባድ አይደለም፤ ግን እጅግ ሰፊ ነው። የሚነበበው ብዙ ነው፣ የሚተነተነው ብዙ ነው፣ የሚጻፈው ብዙ ነው። የምታነባቸው መጻሕፍት አይነትና ብዛት ቋንቋህና እውቀት አዘል ግንዛቤህ ላይ አይነተኛ ተጽዕኖ  አላቸው። በትምህርት እንዲሁም በስራ ወቅት እንድታዘጋጃቸው የሚጠበቁብህ የጽሑፍ አይነቶች የመተንተን፣ የማሰናሰልና የማስረዳት ክህሎትህ ላይ እንዲሁ ተጽዕኖ አላቸው።
ሁለተኛ ሕግ ራሱ ሁሉን ጠለቅ (pervasive) ባሕሪይ አለው። ሕግ የማይመለከተው ወይም የማይገዛው የሕይወታችን ክፍል የለም። ሕግ የሚባለው ምን እንደሆነና እንደምን እንደመጣ ለመረዳት መጀመሪያ ላይ የፍልስፍና ትምህርት፣ በመቀጠል የሕግ ፍልስፍና ትምህርት ስትወስድ ዘላለማዊ የሚባሉትን የሰው ልጅ ኀሠሣዎች ገረፍ አድርገህ ታልፋለህ። ከዚያ በኋላ በሕግ ግምትና  በሕግ አተያይ ሰው ከመሆን አንስቶ፣ የግለሰብን ሕይወትና ከግለሰብ፣ ከማህበረሰብና  ከመንግስት ጋር የሚኖር መስተጋብር፣ የሀገር እና የአለም አቀፍ ህብረተሰብን መስተጋብር፣ በየፈርጁ የሚፈትሹ ሃሳቦችን፣ የሚገዙ መርሆችን ታያለህ። በአጭሩ ሕግ መቼ ተፀነስክ ከሚለው የማህፀን ውስጥ ሀቅ ጀምሮ ቤትህን፣ ምድርን፣ ባህርን፣ አየርንና አሁን ደግሞ ‘ቨርቹዋል’ የምንለውንም አለም እንዲሁም እዚህ ሁሉ ውስጥ ያለውን ክንውን ይቃኛል። ኪነትስ? በአንዳች አይነት መልኩ ይህንኑ አታደርግም?
የኔ ፍላጎት ሥነጽሑፍና ቴአትር ስለነበር፣ አባቴ አበበ ባልቻን ምሳሌ አድርጎ፣ ሕግ ትምህርት ቤት እንድገባ አሳመነኝ። እኔ አብዛኛዎቹን አመታት ክፍል ውስጥ ግጥም እየጻፍኩ አሳለፍኳቸው። ቴዎድሮስ ሞሲሳ ዘፈን ሲያወጣ፣ ጓደኞቼ ‘የሒዊ መጨረሻ’ ብለው ለወራት ተዝናኑብኝ።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ  የነበረው ኪነጥበባዊ ድባብ ምን ይመስል ነበር?
አአዩ በነበርኩበት ጊዜ፣ እኔና ጓደኞቼ እንሳተፍበት የነበረው የባህል ማእከሉን የግጥም ምሽት ነበር። በሳምንት አንድ ቀን የሚጽፉ ልጆች ግጥሞቻቸውንና ወጎቻቸውን የሚያካፍሉበት መድረክ ነው። በወቅቱ የነበረው የመብራት መጥፋት ወረፋ እንኳን ሳያግደው በመማሪያ  ክፍሎች ውስጥ በሻማ  ብርሃን ይከናወን ነበር። በ1993 በዩኒቨርሲቲው ውስጥ በተነሳው ግርግር ምክንያት ተቋረጠ። ከዚያ  በኋላም ተማሪዎች በቡድን ተሰባስበው መገኘት ስለተከለከሉ የሥነጽሁፍ ምሽቱን ማስቀጠል አልተቻለም። ለወትሮውም ቢሆን ከሚቀርቡት ጽሁፎች ውስጥ ጥቂት የማይባሉት ይዘታቸው ፖለቲካዊ እንደሆነ  የታወቀ  ነውና። በ1993 የትምህርት ዘመን የሁለተኛውን ሴሚስተር ተምሮ ላለመጨረስና ፈተና ላለመውሰድ የወሰኑት መደበኛ ተማሪዎች በሙሉ ለአንድ አመት በትምህር  ገበታ ላይ እንዳይገኙ ተደርገው ተቀጡ። በመሆኑም በ1994 እንኳን እንደወትሮው የደመቀ የሥነጽሁፍ ምሽት ሊካሄድ፣ በግቢው ውስጥ የቀሩት እኛ የሕግ ትምህርት ቤት ተማሪዎችና በዚሁ አመት የገቡ አዲስ ተማሪዎች ብቻ ነበሩ። ምናልባት በሌሎች መርሃ ግብሮች የሚማሩ ተማሪዎችም ነበሩ ይሆናል፣ በትክክል አላስታውስም። የማስታውሰው እንደ ድንጋይ የሚካበደውን ጭርታ ብቻ ነው።
በ1995 ተማሪዎች ከተመለሱና  ነገሮች ከተረጋጉ በኋላ ግን እኔና የክፍል ጓደኛዬ የሆነው ይርጋ ገላው (ገጣሚና ደራሲ)፣ የተቋረጠው መድረክ መቀጠል እንዳለበት ስላሰብን፣ በወቅቱ ወደ ነበሩት የዩኒቨርሲቲው ምክትል ፕሬዚደንቶችና ሌሎችም የሚመለከታቸው አካላት በመሄድ የግጥም ምሽቱ በድጋሚ እንዲጀመር ጠየቅን። ግልጽና  ከፍተኛ  ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶን ተፈቀደ። መድረኩም በሌሎች እገዛ እንደገና ጀመረ። ልጆች አሁንም ፖለቲካዊ አመለካከታቸውን በስራዎቻቸው መግለጽ አላቆሙም ነበርና ከባህል ማእከሉ ተቆጣጣሪዎች ተግሳጽና ምክር፣ አንዳንዴም የ‘እባካችሁ ሁላችንንም እንዳታሳስሩን’ ልመናን አስተናግደናል።
ከባህል ማእከል ባለፈ ደግሞ ተለቅ ያሉ የሥነጽሁፍ መድረኮችን ከሌሎችም ጓደኞቻችን ጋር በመሆን እናዘጋጅ ነበር። በተለመደው በሳምንት አንዴ  በሚዘጋጀው መድረክ ከሌሎቹ ካምፓሶች የሚመጡት ተማሪዎች ቁጥር እምብዛም ስላልነበረ፣ አልፎ አልፎ እያዘጋጀን ቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ፋኩልቲ አዳራሽ የምናቀርበው መድረክ እነዚህንና ሌሎችንም ይስብ ነበር። በስድስት ኪሎና አካባቢው በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ከይርጋ ጋር እየተዘዋወርን፣ ትምህርት ቤቶቹ ከተማሪዎቻቸው መካከል መርጠው በእኛ ዝግጅት ላይ ግጥም የሚያነቡ ታዳጊዎችን እንዲልኩልን ስንጠይቅ ሁሉ አስታውሳለሁ።
እኔና ጓደኞቼ እንደሌሎች ብዙዎች ከግጥም ምሽቱ በኋላ የምናዘወትረው ልማድ ነበረን። ተያይዘን ‘አሴ ቤት’ ወይም ‘ማዘር ቤት’ እንሄዳለን። በዚያም ምሽቱን መድረክ ላይ በቀረቡት ስራዎች መንስዔነት የተለያዩ ሃሳቦች ተነስተው ይንሸራሸራሉ። በመሆኑም በተለያዩ ርእሰ ሃሳቦች ላይ በልዩ ሁኔታ ስምም የሆንነውና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተቀራረብን የመጣን ልጆች አንዲት ማኅበር መሰረትን። ማህበሯም በተማሪዎች ዲን ጽ/ቤት እውቅና አግኝታ፣  በግቢው ውስጥ አንዳንድ ዝግጅቶችን በማከናወን መንቀሳቀስ ጀመረች። አላማዋ ለተማሪዎች/ለወጣቶች በሃገር በቀል ባህሎችና ማንነት፣ በአፍሪካዊ ማንነትና ትልሞች እና በመሳሰሉ ጉዳዮች ላይ ግንዛቤ ለመፍጠር ነበር። የክዋሜ ንክሩማ ልጅ ጋማል ንክሩማ ተገኝቶ ለተማሪዎች ንግግር ያደረገበት በማህበሯ የተዘጋጀው መድረክ ከማይረሱኝ አንዱ ነው። በኋላ ላይ የመስራቾች የመመረቂያ ጊዜ እየተቃረበ ሲመጣ፣ ማኅበሯን ከግቢ ውጪ እንደ ድርጅት የማስመዝገብ ሃሳብ መጣ፤ ተመዘገበችም። ከጊዜ በኋላ ነባር መስራቾች በተለያየ የግል ምክንያት ብንጎድልም፣ ከመካከላችን ጎበዛዝትና ምርጦች የሆኑት ግን ይዘዋት፣ ደግፈዋት ቀጥለዋል፤ ዛሬም ድረስ እየሰራች ነው።
የሐማ ቱማን “The Case of the Socialist Witchdoctor” እና የሕይወት ተፈራን “Mine to Win” እንዴት ለመተርጐም ወሰንሽ?
“The Case of the Socialist Witchdoctor” (“የሶሻሊስቱ ጠንቋይ ጉዳይ”) ጋር የተገናኘሁት በአጋጣሚ ነው። መጽሐፉ በሀገር ውስጥ እንደ ልብ የማይገኝ በመሆኑ ፎቶ ኮፒውን አግኝታ ያነበበች ጓደኛዬ፣ ደጋግማ ስላነሳችብኝ ተውሺያት አነበብኩት። የመጀመሪያውን ክፍል ሙሉ በሙሉ ሳልጨርሰው ለመተርጎም ወሰንኩ፡፡ እንደ ሀገር እንደ ህዝብ ስለራሳችን ያልተቀበልናቸውና ዘወትር ሸፋፍነን የምናልፋቸውን አስቀያሚ ገጽታዎቻችን እንዲሁም እርስ በእርስ የተደራረስነው ግፍ፣ የተገበርነውን ክፋት እያዋዛ ሆጭ አድርጎ ማሳየቱን ወደድኩት። ሰው ሁሉ እንዲያነበው ፈለግሁ። ስለዚህ ልተረጉመው ወሰንኩ። የደራሲውን አድራሻ ከጉግል ላይ አፈላልጌ ፍቃዱን ጠየቅኩት። የተቀረው፣ … እንደሆነው ነው።
በሌላ በኩል “Mine to Win” ደግሞ፣ ሕይወት ተፈራ ለማስተርጎም ፈልጋ ወዳጅ ጓደኞቿን ተርጓሚ እንዲጠቁሟት ስትጠይቅ፣ የኔ ስም በሁለት ወገን ይደርሳታል። “የሶሻሊስቱ ጠንቋይ ጉዳይ”ን ትርጉም ብዙ ሰው ወዶት ስለነበር ነው እኔን መጠቆማቸው። ነገር ግን ሕይወት ሶስት ሰዎችን ለማወዳደር ነበር የፈለገችው። በተለይም ደግሞ “የሶሻሊስቱ ጠንቋይ ጉዳይ”ን አላነበበችውም ነበርና፣ ለመጀመሪያ ጊዜ በስልክ ስንነጋገር፣ ይህንኑ ገልጻ ከ“Mine to Win” አንድ ምእራፍ ብቻ ሰጥታኝ፣ ከሌሎች ሁለት ሰዎች ጋር እንደምታወዳድረኝ ነገረችኝ። ተወዳደርኩ። ዳኞች እኛ ተወዳዳሪዎች ያላውቅናቸው ሰዎች ናቸው፤ እራሷም አልዳኘችም።
ከጥቂት ጊዜ በኋላ፣ የመጽሐፉ ታሪክ የሚያጠነጥንበትን መቼትና  ሁኔታ የሚመጥን ረቂቅ በማቅረቤ እኔ እንዳለፍኩ ተነገረኝና ስራውን ጀመርኩ። በእርግጥ ሙሉ የትርጉም ስራውን ከመጀመሬ በፊት የእንግሊዝኛውን መጽሐፍ ሳነበው ከዋናው ገጸ ባሕሪይ ከተውኔ (ተዋነይ) ጋር ልባዊ ቁርኝት መፍጠር ያስቻሉኝን በርካታ ነገሮች አገኘሁና፣ ተወዳድሬ እንዳገኘሁት ስራ ሳይሆን ፈልጌ፣ ጠይቄ  የተረጎምኩት ያህል አቅሜ የቻለውን ሁሉ ለማድረግ በቂ ውስጣዊ ግፊት ነበረኝ።
ከእነዚህ ሥራዎች በፊት የትርጉም ልምድ ነበረሽ?
ከዚህ በፊት የነበረኝ የትርጉም ልምድ በአብዛኛው ግጥሞችን መተርጎም ነበረ። ሙሉ ስራ ሳይሆን፣ እንዲሁ እዚህም እዚያም ሳነባቸው የወደድኳቸውንና  ስሜቴን የነኩትን አንዳንድ ግጥሞች ተርጉሜያለሁ። “የሶሻሊስቱ ጠንቋይ ጉዳይ”ን ተርጉሜ ስጨርስ ጉዳዩ ለራሴውም ጥያቄ ሆነብኝ። አንብቤው እዚያው ለመተርጎም የወሰንኩበትን ቁርጠኝነት ከየት አመጣሁት? እስካሁን ለምን ሙሉ ስራ ለመስራት አልተነሳሁም ነበር? እና የመሳሰሉት ጥያቄዎች ውስጤ ይመላለሱ ነበር። ይህን ጊዜ ነው ለመጀመሪያ  ጊዜ ትርጉም የሞከርኩበት አጋጣሚ ታልሞ  እንደተረሳ  ህልም ትውስ ያለኝ። አምስተኛ  ክፍል ነበር። I am Legend የተባለውን የሪቻርድ ማቴሰን መጽሐፍ ቤት ውስጥ አግኝቼ አንብቤዋለሁ፤ እንግዲህ በአምስተኛ ክፍል እንግሊዘኛ ምን ያህል ገብቶኝ እንደሆነ አሁን በዝርዝር መግለጽ አልችልም። የማስታውሰው ግን አንዲት ጓደኛዬን “እንተርጉመው” ብያት በጠራራ ፀሐይ ይዘነው ሜዳ ላይ ቁጭ ብለን እንደሞከርን ነው። እንደሚጠበቀው አንድ አረፍተ ነገር እንኳን አልተሳካልንም።
ሥነጽሑፍን በተመለከተ፣ ግጥም እጽፍ ነበር፤ አብዛኛዎቹ በዩኒቨርሲቲ ቆይታዬ የተጻፉና ባህል ማእከል የቀረቡ ናቸው። ገጣሚ እንዳልሆንኩ የገባኝ ለታ ግን መጻፍ ተውኩ። ባለፈው አስራ ሁለት አመት ውስጥ፣ እጅግ በጣም ስሜቴን የነኩት ነገሮች ገጥመውኝ፣ አንድ ሶስት ግጥም ሳልጽፍ አልቀረሁም። ፌስቡክ ላይ ተለጥፈዋል። ድሮ የሞካከርኳቸው አጫጭር ልቦለዶችም ነበሩኝ።
ብዙ ጊዜ የምትጠቀሚው የትርጉም ስልት ምን ዓይነት  ነው?
ስለ ትርጉም ስልቴ ለማብራራት “ኀሠሣ” ላይ የአርትኦት ስራ የሰራው ይኩኖአምላክ መዝገቡ በአንድ ወቅት ያለኝን ላካፍል። ስለ “ኀሠሣ” አንዳንድ ነገር ለመነጋገር እኔና  ሕይወት ተፈራ አግኝተነው ነው። “የሶሻሊስቱ ጠንቋይ ጉዳይ”ን ቀድሞ አንብቦት ነበረና ስለ ትርጉም ስልቴ የሚያስበውን እንደሚከተለው አጫወተኝ። ወደ እኛ ከመምጣቱ በፊት የሚነበብ ነገር ሲያገላብጥ፣ አንድ ሰው ስለ ተርጓሚዎች በጣልያንኛ የተናገረውን ነገር አግኝቷል። ሰውየው “Traduttore traditore” ነው መሰለኝ ያለው። Translator, traitor ለማለት ነው በእንግሊዘኛ፤ “ተርጓሚ ከሃዲ ነው” እንደማለት።
ማለትም አንድ ሰው የትርጉም ስራ ሲሰራ የሚከናወን የፈጠራ ስራ አለ፣ ምንም ያህል እናት/ምንጭ ስራውን ተቀራርቦ ሊተረጉም ቢሞክር እንኳን፣ የቋንቋ ብቃት፣ የራሱ አመለካከትና ንቃተ ህሊና፣ የራሱ ባህልና ስነልቦና የመሳሰሉት ነገሮችን ይጨምርበታል። ስለዚህ ትርጉሙ ዋናውን ሊመስል አይችልም። ተርጓሚው የራሱን አረዳድ ነው የሚጽፈው፤ በመሆኑም ከሃዲ ነው። ዋናው ባለስራ ወይም ዋናው ስራ ላይ የሚፈጽመው ክህደት አለ የሚል ነገር አጫወተኝና፣ “አንቺ ግን ከሃዲ አይደለሽም” አለኝ በስተመጨረሻ። ትክክል ነው፤ እናት ጽሑፉ የግድ መጨመርን ወይም መቀነስን ካልጠየቀ በስተቀር (ለሚተረጎምበት ቋንቋ አንባቢዎችን ስምም ለማድረግ ሲባል) እንደተጻፈው መተርጎምን እመርጣለሁ። ይህንን ስልት አስቤበት መርጬው አይደለም። እስከዛሬ  ትርጉም ስሞክር ልቦናዬ  የመራኝ በዚያ  መንገድ ስለነበረ፣ መጠቀም የቀጠልኩበት ስልት ነው።
ዕለታዊ አሰራሬ ጠዋት ራሴን ከማስደሰት ይጀምራል። ቁርስ፣ ቡና በትልቅ ኩባያ፣ ትንሽ ፌስቡክ። ከዚያ ስራ፣ ምሳ፣ ለኻያ ደቂቃ ማሸለብ፣ ተነስቶ ስራ መቀጠል፣ ከምሽቱ አንድ ሰዓት ላይ ስራ አቁሞ ሌሎች የሚያስደስቱኝን ነገሮች ማድረግ። በሌሎች የስራ ወይም የማህበራዊ ኑሮ ጉዳዮች ያልተረበሸ የስራ ቀኔ ይህን ይመስላል። በእርግጥ በየመሃሉ ቤቴ ውስጥ በተሰናዱት የዘቢብ፣ የቴምር፣ የሱፍ ፍሬ፣ የኦቾሎኒና የመሳሰሉት ጣቢያዎች ቆም እያልኩ ነዳጅ እሞላለሁ!
“ኀሠሣ”ን ስትተረጉሚ ከእናት ድርሰቱ (Mine to Win) ወጣ ለማለት አልሞከርሽም ?
ከላይ እንዳልኩት ‘traditore’ ላለመሆን የተቻለኝን ያህል ሞክሬያለሁ። እናት ድርሰቱ የተጻፈበት ዘመን መንፈስ (Zeitgest)፣ የተገለጸው የአኗኗር ሁኔታ፣ የአነጋገር ዘዬ፣ የአመለካከት አጥናፍ እንዳለ ወደ አማርኛ ቢመለስ፣ ትርጉሙ የመጣፈጥ እድሉ ይጨምራል። ደግሞ ይዘቱ ውስጥ የሚገኘው ቅኔ ነው፣ ትምህርት ነው፣ ኢትዮጵያዊ ጥበብና ፍልስፍና ነው፤ ሕግጋትና ማፈንገጦች ናቸው። ለምን ወጣ ብዬ ለመሄድ እሞክራለሁ? ለዛውን ማሳጣት ይሆናል።
የዘመኑን (19ኛ ክ/ዘመን) የንግግር ዘዬ ለማምጣት እንዴት ተሳካልሽ ?
ያደረግኩት ዝግጅት የተጠቀምኩትን ስልት ይገልጻል ብዬ አስባለሁ። በመጀመሪያ የሥነጽሁፍና የታሪክ ምሁር በሆነ ውድ ጓደኛዬ ትጋት፣ ለዚህ ስራ ዝግጅት ላነባቸው የሚገባኝ መጻሕፍት ዝርዝር ወጣ። እኔም የራሴን አከልኩበት። ከዚህ በኋላ ዝርዝሩ ላይ ያሉትን መጻሕፍት አሰባሰብኩ። መጻሕፍቱ በአብዛኛው በ19ኛው ክ/ዘመን ጀምሮ እስካሁን ድረስ የነበሩ/ያሉ ሊቃውንት፣ መምህራን፣ ዲያቆናት፣ ጸሐፌ ዜና መዋዕሎች፣ ደራሲዎች የጻፏቸው፣ ወይም ስለእነሱ የተጻፉ ናቸው። አንዳንዶቹ እኔ ራሴ ቤት ውስጥ ነበሩኝ፣ ሌሎች በግዢ፣ በውሰት ወይም ከበይነ መረብ በማውረድ (ለምሳሌ: የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ክ መጻሕፍት) የተገኙ ናቸው።
ቀን ቀን መሰረታዊ የትርጉም ስራውን እየሰራሁ፣ ማታ ማታ እነዚህን መጻሕፍት ማንበብ ጀመርኩ። እያነበብኩም ሊጠቅሙኝ የሚችሉ ቃላትን በማስታወሻ  እየሰበሰብኩ፣ የራሴን ትንሽዬ ሙዳየ ቃላት አዘጋጀሁ። በእርግጥ ከዚህ በፊት የቤተሰብ አባላት ሲነጋገሩ በምሰማበት ወቅት፣ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ወቅት፣ በንባብ ወቅት፣ ካገኘኋቸው ቃላት በትውስታዬ የተገኙትን ሁሉ በረቂቁ ውስጥ ተጠቅሜባቸዋለሁ። በመቀጠል ረቂቁን የማበልጸግ የመጀመሪያ ዙር ስራ ስሰራ ያጠራቀምኳቸውን ቃላት እንደ ሁኔታው ቦታ ቦታ አገኘሁላቸው። ከገጠር የኑሮ ዘይቤና ከቤተ ክርስቲያን ስርዓት ጋር የተያያዙ ብዙ ቃላትን እናቴ ጠቁማኛለች። በአቅራቢያችን ከሚገኘው ሰዓሊተ ምህረት ቤ/ክ የነበሩ ካህን አገናኝታኝ በቃለ መጠይቅ ብዙ መረጃ ሰጥተውኛል። በዚህ ጊዜ በብዛት ያገኘኋቸው መጻሕፍት የተጻፉት በሸዋ ልሂቃን እንደመሆኑ የረቂቁ አማርኛ የሸዋ አማርኛ ያመዘነበት ይመስለኛል። ጥንታዊዎቹን መዛግብተ ቃላትና ተጨማሪ መጻሕፍትን በመጠቀም በበኩሌ የተቻለኝን ያህል የጎጃምን ዘዬ ለማምጣት ከሰራሁ በኋላ የቀረውን አርታኢዎች እንዲያዩት ተውኩላቸው። ያጎደልኩትን ሞሉልኝ፣ ያጣመምኩትን አቀኑልኝ።
ገና የእንግሊዘኛውን መጽሐፍ ማንበብ ስጀምርና ታሪኩ በ19ኛው ክ/ዘመን አጋማሽ አካባቢ እንደሚያጠነጥን ስረዳ፣ የተገለጸልኝ ነገር የሚተረጎምበት አማርኛ የገጠር አማርኛ ብቻ ሳይሆን፣ የድሮ የገጠር አማርኛ መሆን እንዳለበትም ጭምር ነው። በዘመን ሂደት ቃላትም ጡረታ ይወጣሉና የተገኘው የገጠር አማርኛ ብቻ በቂ ላይሆን ይችላል፤ የቆየ መሆን አለበት፣ አሁን እምብዛም የማንሰማው፣የማንናገረው። ስለዚህ ‘ወደፊት’ ሳይሆን ‘ግፋኝ’ ጊዜውን የበለጠ ያሳያል …  ቅድመ አያቴም፣ አያቴም ለምሳሌ “ተነስተሽ የማትሄጅ?” ሲሉ ሰምቼ አላውቅም። “ተነስተሽ እማትሄጅ?” ግን ይሉ ነበር። አርታኢዎችም በዚህ መንገድ የመጻፉን ሃሳብ አቅርበው ተቀብዬዋለሁ።
መጽሐፉ ውስጥ የምናገኛቸው እንደ ዐወቀ፣ አባ እና  ሠረገላ  ብርሃን ያሉ ሌሎች አውራ ገጸባሕሪያት ደግሞ፣ እንደው ሁሉም አንዳይነትና ልሙጥ እንዳይሆኑ ትንሽ የአነጋገር ልዩነት ቀለም ልቀባባቸው ሞክሬያለሁ። መቼም መቶ በመቶ ተሳክቷል ብዬ አፌን ሞልቼ ባልናገርም፣ አማርኛ እንዳሁኑ ሳይሆን፣ ከሞላ ጎደል በግዕዝ ፊደላት በሚጻፍበት ጊዜ ቃላቱ የሚጻፉበትን መንገድ ለመከተል ስለመረጥኩ ነው፤ ትርጉሙ ጊዜውን እንዲመስል። እንዳልኩት ታሪኩ የሚተረክልን በአንደኛ መደብ፣ በዋናው ገጸባሕሪ በተዋነይ ነው፤ ተዋነይ ደግሞ ሐዲስን ጠንቅቆ፣ ጸሐፌ ዜና መዋዕል ለመሆን የታጨ ሊቅ ነው። አማርኛውን ዛሬ እኛ እንደምንጽፈው እያቀላቀለ ወይም የግዕዝን ድምጾች ባስወገደ መንገድ ይጽፈዋል ተብሎ መቼም አይጠበቅም ብዬ በማሰብ ነው።
የቻልኩትንም ያህል ዋና ዋናዎቹን መዛግብተ ቃላት በመመልከት ለቅሜ ለመጠቀም ጥረት አድርጌያለሁ። ከላይ እንዳልኩት ለጊዜውና ለቦታው እውነተኛ (authentic) በሆኑ ቃላት ነገሮችን ለመግለጽ መሞከሬ እንዳለ ሆኖ፣ አንዳንድ ቃላት በጣም ዘመናዊ (modern) ወይም ዘመነኛ (contemporary) ሲመስሉኝ ቆየት ያለውን አቻቸውን ለመፈለግ ሞክሬያለሁ። አንዳንዴ አሁን ባለንበት ጊዜ እስኪሰለቹ ድረስ የምንጠቀማቸውን ቃላት በደራሲዋ ሕይወት ምክር የቀየርኳቸው ይኖራሉ፤ ለምሳሌ፡- ታዳሚው፣ ታዳሚያንን የሚለውን ትተን፣ ‘እድምተኛው’ን መጠቀም መረጥን።
ከሕይወት ተፈራ ጋር እንዴት ነበር የምትሰሩት?
ትርጉሙን ጨርሼ ነው የሰጠኋት። ያው የመጀመሪያው ምእራፍ የተወዳደርኩበት ነው። ሌሎቹን ጨርሼ፣ በተደጋጋሚ አንብቤና አርሜ ሙሉውን ነው የሰጠኋት። የስራው ሂደት እጅግ አስደሳች ነበር። ሕይወት ተፈራ በጣም አስተዋይ ናት፤ የረሳሁት መስመር ወይም በተሳሳተ መልኩ ተረድቼው የተረጎምኩት መስመር አያመልጣትም፤ የራሷን መጽሐፍ በልቧ ታውቀዋለች። በመሆኑም ረቂቁን አንድ ሶስቴ ኦዲት አድርጌዋለው፤ የጠፉ አናቅጽና  መስመሮች እንዳሉ ቆጠራ።
ያልመሰላት ጉዳይ ላይ በግልጽ ታዋየኛለች፣ ታደምጠኛለች። ወይ አሳምናታለሁ፣ ወይ ታሳምነኛለች። የመጨረሻ ውሳኔ የእሷ ቢሆንም፣ ብዙ ጉዳዮች ላይ እስከ መጨረሻ  ድረስ እንከራከር ነበር። ስለዚህ ራሴን ለመግለጽና ለማስረዳት ምንም ገደብ አላበጀችብኝም። አንዳንዴ እንዴት አድርጌ ሳዋራት እንደነበር ቤት ገብቼ  ሳስበው፣ እንደ እኩያዋ እንዳዋራት ያስቻለኝን ድባብ እንደምን እንደፈጠረችው ይደንቀኛል። የትርጉሙን የመጀመሪያውን ረቂቅ አንብባ በመደሰቷ የራሷን መጽሐፍ “ለካ እንዲህ ቆንጆ መጽሐፍ ነበርን’ዴ?” ያለችኝ ዕለት፣ እኔም እጅግ ደስ ተሰኝቼበታለሁ።
መጽሐፉን አሁን መለስ ብለሽ ስታይው፣ ትርጉምሽ ላይ ማስተካከል የምትፈልጊው ይኖር  ይሆን?
አንዳንድ አሁንም መስተካከል የሚችሉ ነገሮች አይጠፉም። ያው ለረጅም ጊዜ ከእጅህ ሳታወጣ ልታስተካክለው፣ ልታሰማምረው የምትችል ይመስልሃል። ግን የሆነ ቦታ ይህ ሂደት መቋረጥ አለበትና ነው እርማት ማድረግን የምታቆመው። በመሆኑም ትርጉሙን ያነበቡ እንዲሁም የገመገሙ ሰዎች አስተያየታቸውን ሲሰጡ፣ ባለማወቅ፣ በእንዝህላልነት ወይም በተሳሳተ ምክር ምክንያት የተፈጠሩ መስተካከል የሚችሉ ነገሮች ታይተውኛል። ከነዚህ ውጪ ምንም ማከልም ሆነ  ማንሳት አልፈልግም።
በሁለተኛው እትም ላይ ያስተካከልነው የተወሰኑ የፊደል ግድፈቶችን፣ እና አንድን ቃል በተለያዩ ሆሄዎች በመጻፍ የተሰሩ ስህተቶችን ነው። በተጨማሪ፣ ኀሠሣ ላይ የእንግሊዘኛው ርእስ (Mine to Win) ሳይካተት ነበርና የታተመው፣ እንግሊዘኛው መውጣቱን ያላወቁ ሰዎች የየትኛው መጽሐፏ ትርጉም እንደሆነ ጥያቄ ስላበዙ፣ ይህንንም አንድ ላይ አርመናል። እንዲህ አይነት ትናንሽ እርማቶች ናቸው እንጂ ይዘቱ ላይ የተደረገ ለውጥ የለም።
ከትርጉም ሥራዎች ውጭ  የራስሽ ወጥ ድርሰቶች የሉሽም ?
በአሁኑ ሰዓት አቋርጬው የነበረ አንድ ረቂቅ የረጅም ልብወለድ ስራ እጄ ላይ አለ። በቅርቡ እመለስበትና እጨርሰዋለሁ ብዬ አስባለሁ። ያለፈው አርባ አመት የፖለቲካ ታሪካችን በሁለት ትውልድ ደጋግሞ የሚበጠብጠው ቤተሰብ ታሪክ ነው ባጭሩ።
የትርጉም ሥራና ድርሰት ምንና ምን ናቸው ?
ከአሰራር ልማድ (routine) አንጻር ልዩነት የለውም። ከክህሎት አንጻር ግን አሁን ጀማሪ ተርጓሚ አይደለሁም፤ ግን ጀማሪ ደራሲ ነኝ፤ ሙልጭ ያልኩ አማተር። ስልቴን ገና እያፈላለግኩት ነው። ኀሠሣ ስልት ላይ ነኝ ማለት ይቻላል።
የሚቀጥለው ሥራሽ ምን ላይ የሚያተኩር ነው?
ወጥ ስራን በተመለከተ፣ ከላይ በአጭሩ አስቀምጬዋለሁ። ትርጉምን በተመለከተ፣ በአሁኑ ሰዓት በቅርብ ጊዜ ገበያ ላይ ውሎ ተወዳጅነት ያተረፈውን የዮርዳኖስ አልማዝ ሰይፉን “መንገደኛ” ወደ እንግሊዘኛ እየመለስኩ እገኛለሁ። ሌሎችም ልተረጉማቸው የምፈልጋቸው  መጻሕፍት አይጠፉም።




Read 4222 times