Saturday, 07 October 2017 14:51

የፈረስ ማህበር - ከኢንጂባራ እስከ ዘንገና ሀይቅ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ (አዊ ኢንጂባራ)
Rate this item
(3 votes)

 ዘንድሮ በዓለም ለ38ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ30ኛ ጊዜ የዓለም ቱሪዝም ቀን “ቱሪዝም ለዘላቂ ልማት” በሚል መሪ ቃል ተከብሯል፡፡
የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ባህልና ቱሪዝም ቢሮም መሪ ቃሉን ይዞ ሦስት ዞኖችን ለጉብኝት መርጦ እንቅስቃሴውን መስከረም 23 ቀን ጀምሯል፡፡
በቱሪስት መስህብ ሀብቱ ከፍተኛ የሆነው “ይህ ክልል፣ እስከዛሬ አልተጎበኙም፣ የመታየት እድል አልገጠማቸውም” በሚል የመረጣቸው ዞኖች፤ ምዕራብ ጎጃም ዞን የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን እና የሰሜን ጎንደር ዞን ናቸው፡፡
ጉብኝቱም የተጀመረው የምዕራብ ጎጃም ዞን ዋና ከተማ ከሆነችው ፍኖተ ሰላም በቅርብ ርቀት ላይ በምትገኘው የጨረቃ የተባለች ከተማ መሃል ላይ ከ1928 እስከ 1933 ዓ.ም በነበረው ሁለተኛው የጣሊያን ወረራ ወቅት የጠላትን ጦር በጀግንነት የፈጁት ደጃች ኃይለ እየሱስ ፍላቴ (አባ ሻውል) የመታሰቢያ ሃውልት በመጎብኘት ነው፡፡
የምዕራብ ጎጃም ዞን፣ እጅግ በርካታ መስህቦች ያሉት፣ የክልሉን 35 በመቶ ያህል የሚሸፍን ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ህዝብ  የሚኖርበት፣ የአባይ መፍለቂያ ሰከላ ወረዳን ያጠቃለለና የዞኑ የባህል አምባሳደር የሆነውን ዋሻራ የባህል ቡድን ያቀፈ ሲሆን በሁለተኛው የጣሊያን ወረራ ጊዜ በውጊያ ጠላትን ያርበደብዱ የነበሩት አባ ሻወል ሐውልት ለጉብኝት በቅተዋል፡፡
የምዕራብ ጎጃም ዞንን ሰፊ ታሪክ በቀጣይ በሰፊው የምንመለስበት ይሆናል፡፡
ባለፈው ሐሙስ ከተለያዩ የሚዲያ ተቋማት የተውጣጡ ጋዜጠኞች፣ የየወረዳውና የዞን የባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ ዶ/ር ሂሩት ካሳውና ሌሎች የጉብኝቱ ተሳታፊዎች በአዊ ብሄረሰብ ዞን ዋና ከተማ ወደሆነችው እንጅባራ ከተማ ተጉዘዋል። በዚህች ከተማ በሚገኘው ካርድ ሆቴል፤ የዞኑ የባህል ቡድን ባህላዊ ውዝዋዜና ጥዑመ ዜማ የተጀመረው ዝግጅት፣ በባህላዊ ምግብ ትውውቅና በፓናል ውይይት ቀጥሏል፡፡
በፓናል ውይይቱ ላይ በርካታ ርዕሰ ጉዳዮች የተነሱ ሲሆን በዞኑ እጅግ በርካታ የመስህብ ቦታዎች ቢኖሩም በአግባቡ ጥቅም ላይ አለመዋላቸው ተነግሯል፡፡ የአካባቢው ማህበረሰብም የቱሪስት መስህቦቹ እንዳይጎበኙ እንቅፋት የሆነባቸውን የመሰረተ ልማት ችግሮች ገልፀው፤ የክልሉ መንግስት እልባት እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡
የአማራ ብሔራዊ ክልላለዊ መንግስት ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ሂሩት ካሳው፣ በፓናል ውይይቱ ላይ ለጥያዌዎች ምላሽ የሰጡ ሲሆን በተለይ ዘንድሮ በአዊ ብሄረሰብ ዞን ሁለት የቱሪስት መስህቦች ላይ የልማት ስራ ተሰርቶ በአግባቡ ለማሳየት ፕሮጀክት መቅረፃቸውን ይናገራሉ፡፡
እነዚህ ሁለት መስህቦች የሰባት ቤት አገው ፈረሶች ማህበር እና የዘንገር ሃይቅ ናቸው፡፡ ለዛሬ የሰባት ቤት አገው የፈረሰኞች ማህበር አመሰራረትና ወደፊትም ምን እንደታሰበ እናስቃኛችሁ፡፡
የሰባት ቤት አገው የፈረሰኞች ማህበር፤ በጠላት ወረራ ጊዜ በ1933 ዓ.ም ከ18 እስከ 25 በሚሆኑ አባላት መመስረቱን የማህበሩ ሊቀ መንበር አቶ ጥላዬ አየነው ብዙነህ ይናገራሉ፡፡
ታሪካዊ አመጣጡም በጠላት ወረራ ጊዜ ጠላት ድል የተደረገው በፈረሰኛው ቅዱስ ጊዮርጊስ ታቦትና በፈረሰኛ ጦረኞች በመሆኑ፣ እሱን ታሳቢ በማድረግ፣ በ1933 ጥር 23 ቀን እንደተቋቋመ ነው የሚነገረው። ከ18 እስከ 23 በሚደርሱ አባላት የተመሰረተው ማህበሩ፤ የ78 ዓመት እድሜ ያስቆጠረ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ከ48 ሺህ በላይ አባላትን አፍርቷል። በየዓመቱ ጥር 25 እጅግ በደመቀ ሁኔታ የፈረስ ጉግስ ሽርጥ እና ግልቢያ ይካሄዳል፡፡
“የፈረስ ማዕበል እንጅባራ እስከ
ዘንግና ሃይቅ”
ምንም እንኳን በየዓመቱ በተለያዩ ወረዳዎች የፈረስ ማዕበል እየፈሰሰ፣ ቢከበርም ከትላንት በስቲያ ሃሙስ ዞኑ ለጉብኝት የተመረጠ በመሆኑ፣ ይኸው የፈረስ ትርኢት ለጎብኚዎች ቀርቧል፡፡ በትርኢቱ 650 ፈረሶች እንዲቀርብ ታዞ እንደነበር የሚገልጹት የማህበሩ ሊቀመንበር በትርኢቱ ላይ ግን 890 ፈረስና ፈረሰኛ በገዛ ፈቃዱ ተሳትፏል፡፡
ትርኢቱን የአዊ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን ዋና ከተማ እንጅባራ በ4 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከሚገኘው ዘንግና ሃይቅ ድረስ የፈረስ ግልቢያ ሲካሄድ እጅግ በጣም አይን የሚያፈዝና አጃኢብ የሚያሰኝ ነው፡፡ እንደ አቶ ጥላዬ ገለጻ ከሆነ፤ 890 ፈረሶች የመጡት ከባንጆ ወረዳ ብቻ እንደሆነና ሌሎች ወረዳዎች ፈረስ ይዘው ቢወጡ ቦታ እንደማይበቃ ያብራራሉ፡፡ በዞኑ ከወንድ ፈረስ ጋላቢዎች በተጨማሪ 7 እውቅ ሴት ፈረስ ጋላቢዎች የሚገኙ ሲሆን የሴቶቹን ቁጥር ለማብዛትና ተወዳዳሪ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ኃላፊው ይናገራሉ፡፡
በቀጣዩ ዓመት የአባላቱን ቁጥር 70 ሺህ ለማድረስ እየተሰራ እንደሆነም ተገልጿል፡፡
በፈረስ ትርኢቱ ላይ ከፈረስ ማስገርና የግልቢያ ፉክክሩ በተጨማሪ የፈረሶቹ ጌጣጌጥና የጋላቢዎቹ የተለያዩ ባህላዊ አልባሳት እጅግ ማራኪ ናቸው፡፡
አንድ የፈረስ ጋላቢ የማህበሩ አባል ለመሆን ምን ይጠበቅበታል?
አንድ የፈረስ ጋላቢ የሰባት ቤት አገው ፈረሰኞች ማህበር አባል ለመሆን፣ እድሜው ከ18 ዓመት በላይ መሆን ይጠበቅበታል፡፡
ከእድሜው ባሻገር በአካባቢው በባህሪው ምስጉን የሆነ፣ የተጠላን አስታራቂ፣ ከሌብነትና ከሌሎች አጉል ባህሪያት የፀዳ መሆን እንደሚጠበቅበት በእለቱ ያነጋገርናቸው የማህበሩ ሊቀመንበር ያብራሩ ሲሆን አባል ከመሆኑ በፊት ከሰዎች ጋር ግጭት የነበረው ከሆነ፣ ሽማግሌዎች ሰብስቦ እርቅ ማውረድና ሰላም መፍጠር ይኖርበታል፡፡
“ይህ የሚሆንበት ማህበሩ በጊዮርጊስ ስም የተቋቋመና ከአባቶቻችን በፍቅር የወረስነው ስለሆነ ፀብ ቂምና ጥላቻ የያዘ ሰው አይሳተፍበትም” ብለዋል - አቶ ጥላዬ፡፡
በሌላ በኩል አንድ ፈረሰኛ የማህበሩ አባል ለመሆን፣ ለፈረሱ ኮርቻ፣ ፉርጌሳ፣ ለኮ፣ ወዴላ፣ ውስጠ ምቹ እና ግላስ የተባሉ መሉ መሳሪያዎች ማሟላት ሲኖርበት፣ ለራሱ ደግሞ አለንጋ፣ ዘንግ ገምባሌ፣ ባት ተሁለት ሱሪ፣ ሳሪያን ኮት እና ጀበርና ማሟላት ይጠበቅበታል፡፡
እነዚህን ያሟላ ሁሉ የማህበሩ አባል መሆን እንደሚችል የሚገልጹት ሊቀ መመንበሩ፤ በዚህ ማህበር በፈረስ ግልቢያ በፌደራል ደረጃ ተወዳድረው በማሸነፍ፣ 3 ሜዳልያ የተሸለሙ አቶ አንዱአለም ሰውነት የተባሉ ግለሰብ፣ የማህበሩን ስም በማስጠራት ትልቅ ሚና ተጫውተዋል፡፡
አቶ አንዱዓለም ሰውነት ከትንት በስቲያ በተካሄደው የፈረስ ትርኢት ሰጋር ፈረሳቸው ላይ ተቀምጠው፣ አረንጓዴ ኮፍያቸውን ደረብ አድርገው፣ ፈረሳቸውን እየኮረኮሩ፣ የፈረሱን ሰልፍ ሲመሩት ተመልክተናል፡፡
ይህንን የፈረስ ትርኢት፤ ከዞኑ አልፎ በአገር አቀፍ ደረጃ ብሎም የዓለም ቅርስ ለማድረግ ከመንግስት ባለፈ የአካባቢው ተወላጅ የሆኑ ባለሀብቶች እንቅስቃሴ እያደረጉ እንደሚገኙ ለማወቅ ችለናል። ከነዚህም መካከል የአካባቢው ተወላጅ የሆኑት ባለሀብትና የቢአርሲ በጀት አስጎብኚ ድርጅት ባለቤት አቶ ቢሻው በላይ አንዱ ናቸው፡፡
አቶ ቢሻው ይህንን ረጅም እድሜ ያስቆጠረ የፈረስ ትርኢት፣ በአገር አቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅና የዓለም ቅርስ ሆኖ እንዲመዘገብ ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴ ለማድረግ፣ ከአገው ፈረሰኞች ማህበር፣ ከአዊ ማህበረሰብ ዞንና የአቶ ቢተው በላይ ቢአርሲ በጀት አስጎብኚ ድርጅት፣ በዘንገና ሃይቅ ላይ በተካሄደው የፈረስ ትርኢት መጠናቀቂያ ስርዓት ላይ የስምምነት ፊርማ ተፈጽሟል፡፡

Read 5703 times