Saturday, 07 October 2017 14:31

ያም ሲያማ፣ ያም ሲያማ…

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(13 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ… ዘንድሮ “ሰው ጠፋ” እየተባባልን ነው። አለ አይደል… አይደለም አብሮ የሚሠሩትና አብሮ የሚኖሩት...አብሮ የሆድ የሆድን የሚያወሩት ሰው ማግኘት አስቸጋሪ እየሆነ ነው ይባላል፡፡ ምን ነካን! እንዴት ነው በጥቂት ዓመታት ውስጥ እዚህ የለየለት የጎሪጥ መተያየት ደረጃ የተደረሰው! እስከዚህ ጣራ የነካ ያለመተማመን ደረጃ ያደረሰን ምን እንደሆነ ባለሙያዎች አጥንተው የማይነግሩንሳ!
እናማ… “ዓይኔን ሰው አማረው፣ የሰው ያለህ የሰው፣” ለዘንድሮም የምትሠራ ነው የምትመስለው።
ትናንት ያለ ሀሳብ ስናወራው፣ ስንመካከረው፣ ስንከራከረው ከነበረው ሰው ጋር ዛሬ ትንሽዬዋን ነገር መነጋገር ምነው አቃተንሳ! በስንትና ስንት የአገር ጉዳይ ላይ የሆድ ሆዳችንን እንዳላወራን፣ ዛሬ በአርሴና ማንቼ ደጋፊነት “መቃብሬ ላይ እንዳትቆም!” አይነት መራራቅ ላይ ያደረሰን ምን ጉድ ቢመጣ ነው!
እናላችሁ…ዘንድሮ ከሰዎች ጋር ገለባ ገለባው እንኳን ማውራት አስቸጋሪ እየሆነ ነው፡፡ የምር ግን…ትንፍሽ ያላችኋት ትንሽዬዋ ነገር ተደማምራ፣ ተባዝታ ትሰራጭላችኋለች፡፡
“በቀደም መንገድ ላይ ትንሽ አደናቅፎኝ ነበር፣” ካላችሁ ነገርዬው በሰበር ዜናነት፣ “በአፍ ጢሙ ተደፍቶ ነበር!” ተብሎ ይነገርላችኋል፡፡
ከእሱ ጋር ቁጭ ብላችኋል፡፡ እናማ… ስለ ራሱ አንድ፣ ሁለት ነገር ጣል ያደርግና ስለ ራሳችሁ ይጠይቃችሁ ይጀምራል፡፡…
“መጠጥ ምናምን ትቀማምሳለህ?”
“ይሄን ያህል ባይሆንም በወር አንዴ፣ አንዳንዴም በወር ሁለቴ ለጨዋታ ያህል እቀማምሳለሁ፡፡”
“ጎበዝ ነህ፣ ራስህን ትጠብቃለህ፡፡ ቢራ ነው የምትወደው?” ይሄ ነገር ‘ኢንተሮጌሽን ምናምን ነው እንዴ!
“ለነገሩ ቢራ ላይ እንኳን እምብዛም ነኝ፡፡ ከጠጣሁ ሁለት መለኪያ ጂን ይሻለኛል…” ምናምን ትላላችሁ። አሁን ይሄ ለወሬነት ይበቃል! አዎ፣ ለአንዳንድ ሰዎች ከወሬም ለመክፈቻ ወሬነት ይበቃል…በነገራችሁት ሰው ዘጋቢነት፡፡
“አጅሬው ለካስ ድምጹን አጥፍቶ ነው የሚቀመቅመው!”
“አንተ የሰው ስም አታጥፋ! እሱ እንደዚህ አይነት ሰው አይደለም፡፡”
“ስነግረህ!…ሰውየዋ እንትኗን በምናምን ደፍና ነው ጂኗን የምትገለብጠው!”
“አንተ በምን አወቅህ?”
“ራሱ ነው የነገረኝ፡፡”
“ምን እሱ ራሱ ጂን እገለብጣለሁ አለህ?”
“እንደዛ ባይለኝም ጂን እወዳለሁ ያለኝ ራሱ ነው…”
ያም ሲያማ፣ ያም ሲያማ
ወገኔ ለእኔ ብለህ ስማ
ታዲያላችሁ…እንደዚህ፣ እንደዚህ እያለ ታሪኩ እየተቆረጠ፣ እየተቀጠለ…እየተቦጨቀ፣ እየተጣፈ… መጨረሻ ላይ በወር አንዴ ወይ ሁለቴ ጥቂት መለኪያ እቀምሳለሁ ያላችሁት… “ገንዘብ ሁሉ እያጠረው በዱቤ ጭምር ነው የሚጠጣው አሉ…” ምናምን ተብላችሁ ታርፉታላችሁ፡፡
የምር ግን…አለ አይደል…እናንተ ላይ በቀጥታ ባይደርስም ዙሪያችሁን ሌሎች ላይ የደረሰውን ስትሰሙ መከላከያ አጥራችሁን ማበጀት ትጀምራላችሁ፡፡
እናማ…አስቸጋሪ ነው፡፡ እንደ ቀልድ የሚነገሩ ነገሮች ዊግና አርቲፊሻል ዳሌ እየተጨመረላቸው ሽቅብም አግድምም የእውነተኛ መጠናቸው ብዙ እጥፍ ይሆናሉ፡፡
ታዲያላችሁ…እንበል የራሱን ጉርሻ ከማጣጣም የሰው ጉርሻ መቁጠር ከሚወድ ከሆነ ሰው ጋር አብራችሁ እየተመገባችሁ ነው፡፡ እንደ አጋጣሚ በሥራ ድካም የተነሳ ራባችሁ ባስ ስላለ የመጀመሪያዎቹን ሁለት፣ ሦስት ጉርሻዎች የኦሎምፒክ አሎሎ ታናሽ ወንድም አሳክላችሁ ትልኩና ወደ መደበኛው ጉርሻ ትገባላችሁ፡፡ (በነገራችን ላይ…መደበኛ ጉርሻ ብሎ ነገር ምንድነው! እኔ የምለው… ጉርሻን በመዳፍ ደገፍ አድርጎ መግፋት በምድርም በሰማይም የሚያስጠይቅ ነገር አለው እንዴ!) ሰውየው ትኩር ብሎ ሲያያችሁ ነገርዬው ይገባችኋል፡፡
“ይገርመሀል ጠዋት ጀምሬ ለደቂቃ እረፍት አላገኘሁም፡፡ በጣም ነበር የራበኝ፣” ትላላችሁ። ሳቅ ይልና ያልፋችኋል፡፡ የታሪኩ መጨረሻ ግን አይደለም፡፡
“አንቺ እሱ ሰውዬ፣ ሆዱ ውስጥ ባዶ የሆነ የእህል መጋዘን አለ እንዴ! ይንደዋል ነው የምልሽ!”
“እኔ ግን ስለ እሱ ስሰማ ምግብ ላይ በጣም ቁጥብ ነው ይሉታል፡፡”
“ኸረ እባክሽ፣ የእሱ እኮ መመገብ ሳይሆን አጨዳ በዪው፡፡ የቻይኖቹ ቡልዶዘር እንኳን እንደዛ አይዝቅም! እጁን ቤት አስቀመጦ አካፋውን ክንዱ ላይ ተክሎ የመጣ ነው የሚመስለው!”
“አንተ ሰውዬ አታጋን! ከየትም  ወሬ እየለቃቀምክ የሰው ስም አታጥፋ…”
“ቅዳሜ ምሳ አብረን ነው የበላነው እያልኩሽ እኮ ነው!”
እንዲህ እያለ ይቀጥላል፡፡
ያም ሲያማ፣ ያም ሲያማ
ወገኔ ለእኔ ብለህ ስማ
የምግብ ነገር ካነሳን አይቀር… ሰውየው የሆነ ምግብ ቤት በራፍ ላይ ይለምናል፡፡ ባለቤትየውም፤
“ይሄኔ ትንሽ እንጨት ብትፈልጥ ኖሮ  ለምግብ ገንዘብ ታገኝ ነበር፣” ሲለው የእኔ ቢጤው ምን ቢል ጥሩ ነው…
“መጀመሪያ የምግብ ዝርዝራችሁን ልየውና እፈልጣለሁ፡፡”
እናላችሁ…በዚች በገለባዋ፣ በገለባዋ ነገር እንኳን ወሬዎች የሚቀየሩት በዝግምታዊ ለውጥ ሳይሆን በቅጽበታዊ ለውጥ ነው፡፡ (ቂ…ቂ…ቂ…)  ስሙኝማ…ይሄን ነገር የሆነ ‘አዲስ ፍልስፍና’ ምናምን አድርጌ የሆነ ቡድን ላቋቁም መሰለኝ!
እናላችሁ…ዘንድሮ በመካከላችን ያለው ግንኙነት ነገር አስቸጋሪ ሆኗል፡፡ ባስ ሲልም በቦለቲካው አካባቢም፣ በቤተሰብ አካባቢም፣ በትዳር ግንኙነቶች አካባቢም… ያለው ነገር “የቻይኖቹ ቡልዶዘር እንኳን እንደዛ አይዝቅም!” አይነት ነው፡፡ ብዙ ጓደኝነት፣ ብዙ ትዳሮች ዝንቧን ዝሆን በማሳከል አይነት ወሬ ፈጠራና ማጋነን ፈርሰዋል፡፡
ስለ ባልና ሚስት ካወራን አይቀር ይቺን ስሙኝማ…ሰውየው ንብ ያነባል፡፡ ታዲያ አንድ ቀን ጓደኛው፣
“እንዴት ነው፣ ዘንድሮ ንቦችህ ብዙ ማር አልሰጡህም?” ይለዋል፡፡
“ዘንድሮስ አንዲት ብልቃጥ የምታክልም ማር አልሰጡኝም፡፡ ቢሆንም ደስተኛ ነኝ፡፡”
ጓደኝየው ግራ ይገባውና…“ማር ካልሰጡህ እንዴት ደስተኛ ትሆናለህ!” ሲል ይጠይቀዋል፡፡ ምን ብሎ ቢመልስ ጥሩ ነው…
“አማቴን ነድፈውልኛል፡፡”
ሴትዮዋ ወሬ ይወዳሉ፡፡ አንድ ቀን ሁለት ወንድ ልጆቻቸው በሆነ ጉዳይ ጭቅጭቅ ይጀምራሉ፡፡ እናትየው እዛው ነበሩ፡፡ ነገሩ እየከረረ ሲሄድ ታላቅየው ልጅ፣ “እማዬ እስቲ አንድ ጊዜ ውጪልንና እኔና እሱ የሆነ ምስጢር እናውራ፣” ይላቸዋል፡፡ እናትም ተነስተው በሩን ከፈቱና ሊወጡ ብለው ዘወር አሉና ምን ቢሉ ጥሩ ነው… “ልጆች ግን ጮክ ብላችሁ አውሩ፣” አሏቸውና አረፉ፡፡ ‘ዓመል አይለቅ’ የሚባለው እኮ እዚህ ላይ ነው፡፡
ያም ሲያማ፣ ያም ሲያማ
ወገኔ ለእኔ ብለህ ስማ
እንዲህም ሆኖ ግን…ተወደደም፣ ተጠላም ከሰው ጋር መኖር የግድ ነው፡፡ ዘንድሮ…አይደለም ለብቻ ተሠርቶ፣ በጋራ ተሠርቶም አልተቻለም፡፡ በዚህ መሀል ቀደም ብለን ያልናቸው ነገሮች ይኖራሉ፡፡ ያውም ዘንድሮ ዝም ብሎ በፊት እንደነበረው ተራ አሉባልታ ብቻ ሳይሆን መተማሚያ፣ መወነጃጀያ፣ ነገሮቻችን እየበዙ በሄዱበት ጊዜ፣ ሶሻል ሚዲያው ህይወታችንን እየተቆጣጠረ በሚመስልበት ጊዜ ‘ዝንቧን ዝሆን የማሳከል’ አባዜ ቶሎ የሚሻለን ነገር አይመስልም፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!


Read 4310 times