Saturday, 30 September 2017 15:07

‹‹…ከሰው ስ ህተት ከ ብረት ዝ ገት … ቢባልም…››

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ
Rate this item
(1 Vote)

በአለም አቀፍ ደረጃ በየአመቱ 43/ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች ጥንቃቄ በጎደለው የህክምና አገልግሎት አሰጣጥ ምክንያት ከጉዳት ላይ ይወድቃሉ፡፡
ባለፈው እትም የሕክምና ባለሙያዎችን የህግ ተጠያቂነት በሚመለከት ለንባብ ያልነው ተከታይ እንደሚኖረው ገልጸን ነበር፡፡ እነሆ ዛሬም አቶ አበበ አሳመረ የህግ ባለሙያና ጠበቃ እንዲሁም የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሕክምና ባለሙያዎች ማህበር የህግ አማካሪ የሰጡትን መብራሪያ እና አንዳንድ እውነታዎችን እናስነብባችሁዋለን፡፡
በአለም አቀፍ ደረጃ በየአመቱ 234/ሁለት መቶ ሰላሳ አራት ሚሊዮን የሚደርሱ የቀዶ ሕክምና አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን ከ25/ሀያ አምስት ቀዶ ሕክምናዎች አንዱ ድንገት በሚፈጠር የጤና ችግር ይቅር የማይባል እና በድንገት ወይንም በግድ የሚሰራ ነው፡፡ በታዳጊ አገሮች በሚደረጉ ቀዶ ሕክምናዎች ምክንያት ወደ 10/ከመቶ የሚሆን ሞት ይደርሳል፡፡ መረጃው እንደሚያሳየው በአጠቃላይ በአለም ደረጃ ለሕልፈት ምክንያት ከሚሆኑት የቀዶ ሕክምና አገልግሎቶች መካከል ወደ 50/ከመቶ የሚሆኑት ጥንቃቄ ቢደረግ ኖሮ ሊከላከሉት የሚቻል ሰዎችንም ለጉዳት የማይዳርጉ በሆኑ ነበር፡፡  
በአንዳንድ አገሮች ለማሳያነት ያህል የተጠቀሰው በህክምና አገልግሎት አሰጣጥ ስህተት ምክንያት በአመት የሚደርሱ የሞት ቁጥሮች የሚከተሉትን ይመስላል፡፡
በአሜሪካ 98‚000/ ዘጠና ስምንት ሺህ
በካናዳ 24‚000/ሀያ አራት ሺህ
በአውስትራሊያ 18‚000/አስራ ስምንት ሺህ ይሆናል፡፡
ምንጭ (Times India)
ባለፈው እትም አንስተን ያልተመለሱት ጥያቄዎች የሚከተሉት ናቸው፡፡
በሕክምና አሰጣጥ ረገድ ጥፋት የሚባለው ምንድነው?
የሚመዘንበት ደረጃስ አለ?
ማነው ጥፋት አለ ማለት የሚችለው?
አንድ ወጥ የሆነ ደረጃስ አለ? የሚሉት ናቸው፡፡
የህግ ባለሙያው አቶ አበበ አሳመረ የሚከተለውን ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በኢትዮጵያ የህክምና ባለሙያው ምናልባት ስህተት ፈጥሮአል ቢባል በአስተዳደር፣ በፍትሐ ብሔር እና በወንጀል ኃላፊነቶች ጥቅም ላይ የሚውሉ የጥፋት መመዘኛዎች ይለያያሉ፡፡ ለምሳሌም የወንጀል ሕጉ የቸልተኝነት ደረጃን ስለሚገልጽ ለወንጀል ኃላፊነት ይጠቀምበታል፡፡ ለፍትሐብሔር ኃላፊነት ጥፋት የሚባለው ነገር በግልጽ መመዘኛው ባይታወቅም ነገር ግን ማንኛውም ሰው ላደረሰው ጥፋት ኃላፊነት አለበት ስለሚል  ፍርድ ቤቶች ይህንን እየመዘኑ ጥፋት አለ ወይንስ የለም የሚለውን ያረጋግጣሉ፡፡ በዚህም መሰረት ኃላፊነት አለበት ወይንስ የለበትም ብለው ውሳኔ ይሰጣሉ፡፡ የአስተዳደር ኃላፊነት ጥፋት አለ ወይንስ የሚለውን ኮሚቴው አይቶ ይወስናል፡፡ እንግዲህ በዚህ ዙሪያ የአለምን የህክምና ማህበር ጨምሮ የሚታየው ክርክር አንድ ወጥ የሆነ የህክምና ስህተት የሚዳኝበት ደረጃ እንዲኖር ቢደረግ የሚል ነው፡፡  ይሄ ቢደረግ ጥሩ ነው ብለው የህግ ባለሙያዎች ይስማማሉ፡፡ በሶስቱም ደረጃዎች ተጠያቂ የሚሆን ባለሙያ አንድ ወጥ በሆነ አሰራር ጉዳዩ እንዲታይ የሚለው ነገር ብዙዎችን ያስማማል፡፡ ብለዋል አቶ አበበ፡፡
አቶ አበበ አክለውም በወንጀል የመጠየቅ ነገር አሁን አሁን እንዲያውም እየደበዘዘ ነው ፡፡ በእርግጥ በእኛ አገር አለ የለም ወይንም ተጠያቂነቱ ጨምሮአል ወይንም አልጨመረም ለማለት የሚያስችል መረጃ የለም፡፡ በሌሎች አገሮች ግን እየቀነሰ ነው፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ሰዎች የሚሰሩት ስህተት ሰብአዊ ነው። ማንም ፍጹም ስለሌለ ስህተት ምንጊዜም ስለማይጠፋ መሳሳትም ሰው ባላሰበው መንገድ የሚፈጽመው አንዱ ተግባሩ ነው ተብሎ ይታመናል፡፡ በአገ ራችንም አባባል ‹‹…ከሰው ስህተት ከብረት ዝገት አይጠፋም…›› ቢባልም  የህክምናው አገልግሎት ስህተት ወደ እውነታው ሲተረጎም ማንኛውም የህክምና ባለሙያ ማለት በሚያስችል ሁኔታ ሰውን ለመጉዳት ብሎ የሚያደርሰው ጥፋት የለም። እንደማለት ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ችግር የሚፈጠረውም የሰውን ሕይወት አድናለሁ ብሎ በሚሰራው ስራ ላይ በተለያዩ ምክንያቶች በሚፈጠሩ ጉድለቶች የተነሳ  ነው፡፡ በእርግጥ ይህ ማለት ግን አንዳንድ በቸል ተኝነት ወይንም በችኩልነት …ወዘተ … በመሳሰሉት ምክንያቶች ሰዎችን ለሕልፈት እንዲዳረጉ የሚያደርጉ ባለሙያዎች የሉም ማለትም አይቻልም፡፡ ስለዚህ አንዳንድ ስህተት በሚፈጠር ጊዜ ተጠያቂነቱ በፍትሐብሔር ደረጃ እንዲሆን የተፈለገበት አንዱ ምክንያት ከላይ የተጠቀሰው ሲሆን በዚህም ምክንያት ተጠያቂነትን በመሸሽ የህክምና ባለሙያዎች እጥረት እንዳያጋጥም ከሚል ነው። ለምሳሌም በአንድ ወቅት በአሜሪካ ሁለት ግዛቶች በጣም ተፈላጊ የሆኑ ባለሙያ ዎችን እስከማጣት ተደርሶ ነበር፡፡ ምንም እንኩዋን በጣም ጥቂት በሆኑ ባለሙያዎች በሚፈጠር ስህተት ምክንያት ሰዎች የሚጎዱ ቢሆንም እጅግ ብዙ ባለሙያዎች የሰፊውን ህዝብ  ሕይወት በመጠበቁ ረገድ እንዲሳተፉ ይፈለጋል፡፡ ስለሆነም የሙያው አገልግሎት ክብርም ሆነ ባለሙ ያው መጎዳት የለበትም የሚለው አስተሳሰብ አለም አቀፍ ነው፡፡
በአገራችን (ኢትዮጵያ) የተደረገ ጥናት ወይንም የሚታይ መረጃ ባይኖርም በሌሎች አገሮች ግን የሚታዩ እውነታዎች አሉ፡፡ ለምሳሌም በሕንድ የተመዘገበው የህክምና ስህተት በመድሀኒት አሰጣጥ፣ በሚወሰድ መድሀኒት መጠን አለመስተካከል፣ የአንዱን ታካሚ መድሀኒት ለሌላው በመስጠት፣ የመድሀኒት አወሳሰድ ጊዜን በትክክል ባለማሳወቅ፣ በቸልተኝነት፣ በቀዶ ሕክምና ጊዜ ሊሰጥ የሚገባውን ትኩረት በመንፈግ፣ የማደንዘዣ መድሀኒት መጠንና ጊዜ….ወዘተ በመሳሰሉት ምክንያቶች በታካሚው ላይ ችግር የሚፈጠር ሲሆን በእነዚህም ምክንያቶች የሚቀርቡ የፍትሕ ጥያቄዎች በግምት በአመት ወደ 5.2/ሚሊዮን እንደሚደርስ ይገመታል፡፡
ያለፈውን እትም ያነበቡ አድማጭ የሚከተለውን ገጠመኝ ልከውልናል፡፡
‹‹…ጊዜው ምናልባት ወደ 16 አመት ይሆነዋል፡፡ ልጅትዋ የባለቤቴ እህት ልጅ ናት፡፡ በጊዜው በግምት የ19/ አመት ልጅ ነች፡፡ አንድ ቀን በድንገት ከተኛችበት መነሳት ያቅታትና እርዳታ ትጠይቃለች፡፡ በቃ። መቀመጥ መነሳት ችግር ሆነ፡፡ ወለምታ… ቅጭት …ያልተባለ ነገር አልነበረም፡፡ በባህላዊው እና በእምነቱ መንገድ የተቻለው ሁሉ ተደረገ፡፡ አልተሳካም፡፡ ሲብስባት ወደሐኪም ቤት ተወሰደች፡፡ ከሐኪም ቤቱ የተገኙት መልሶች እና የሚታዘዙላት መድሀኒቶች የሚያስደንቁ ነበሩ፡፡ አንዱ ሐኪም በበረሐ አካባቢ ትኖር ነበር ወይ ይላል፡፡ ሌላው ጉበትዋ ላይ ምልክት አይቻለሁና ይህንን ኪኒን ትውሰድ እና ካልተሸላት መልሳችሁ አምጡ ይላል፡፡ ብቻ ጨጉዋራ… አንጀት… ጣፊያ….ያልተባለ ነገር የለም፡፡ ሕክምናውም አንድ ቦታ ሳይሆን ወደ ተለያዩ ቦታዎች ነበር የተወሰደችው፡፡ ሁሉም ቦታ የሚሰጡአት መድሀኒቶች ግን ተጨማሪ በሽታ ነበር የሆነባት። አንዱን ሐኪም በተለይም አልረሳውም፡፡ባለቤቴ ስለልጅትዋ ሕመም ሁኔታ ሊያስረዳው ሲሞከር ይህን ካወቅህማ ለምን መጣህ ይዘህ ወደቤትህ ሂድ ነበር ያለው፡፡ በስተመጨረሻው ግን ቤተሰቡ ሁሉ ተስፋ ቆረጠ፡፡ ስለዚህም የተደረሰበት ስምምነት …ከእንግ ዲህ ወዲህ ይህች ልጅ ወደሐኪም ቤት አትሄድም፡፡ በቃ። እግዚአብሔር ከማራት ይማራት፡፡ ካለበለዚያም ትሙት፡፡ የሚል ነበር፡፡ ሌላ አማራጭ ግን የተደረገው ወደጸበል መውሰድ ነበር፡፡ ልጅትዋ ከተኛችበት ቤተሰቡ ተሰብስቦ የጸበል እጣ በመውጣት ላይ እያለ አንዲት ቅርብ የሆነች ጎረቤት ልጅትዋን ልትጠይቅ መጣች። ሁኔታውን አስረዳናት፡፡ የእሱዋም መልስ እስቲ ለእኔ አንድ እድል ስጡኝና አንድ ሐኪምጋ ልውሰዳት አለች፡፡ አጎትየው አይ ሆንም፡፡ ምንሲደረግ ከዚህ በሁዋላ ሐኪም ያያታል አለ፡፡ እሱዋም ለመነች፡፡ ቤተሰቡም ጸበል መሄጃው ቀኑ እስኪቆረጥ…እንዲሁም የት እንደሆነ ቦታው እስኪታወቅ…ስንቁም እስኪዘጋጅ ድረስ ምን ቸገረህ ትውሰዳት ተባለ እና ተፈቀደላት፡፡ በሁዋላ እንደተነገረን ከሆነ ልጅት ሐኪሙ ዘንድ በሸክም ስትቀርብ አስቀድሞ ታሪክዋን ነበር የጠየቃት፡፡ የት እንደም ትኖር… ወድቃ ታውቅ እንደሆነ…ወይንም ከግኡዝ ነገር ጋር ተጋጭታ እንደነበር …ከሰው ተጣልታ ወይንም ተደባድባ እንደነበር ….ካጠና በሁዋላ መመርመሪያ አልጋው ላይ አስተኝቶ ሕመሙዋን አወቀ፡፡ ለካስ ልጅትዋ ታማ ከመተኛትዋ ሶስት ወር በፊት ወድቃለች፡፡ በምት ወድቅበት ጊዜም ጭራዋ ተመትቶ ስለነበር ውስጥ ውስጡን ሲታመም ቆይቶ ከባሰ ደረጃ ላይ ሲደርስ ነበር የጣላት፡፡ አንዴ ጨጉዋራ…ጣፊያ…አንጀት…ጉበት…ሲባል የነበረው በሽታ የጭራ በድንጋይ መመታት ሆነ፡፡ ይሄኛው ሐኪም ያዘዘውም መድሀኒት ገና በሶስተኛው ቀን ቁጭ እንድትል ከአልጋዋም ላይ በሸክም ሳይሆን እራስዋ እንድትነሳ እንድትቀመጥ አስቻላት፡፡ እናም ሐኪሞች ሁሉም አንድ አይደሉምና ከፍተኛ የሆነ ክትትል ያስፈልጋል ባይ ነኝ፡፡
(ጸጋ ቢልልኝ ከቦሌ ቡልቡላ)
 ይቀጥላል…

Read 1304 times