Saturday, 30 September 2017 15:04

በ44ኛው የበርሊን፤ በ40ኛው የቺካጎ፤ በ47ኛው የኒውዮርክ ማራቶኖችና በ10ኛው የማራቶኖች ሊግ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

በ44ኛው የበርሊን ማራቶን
44ኛው የበርሊን ማራቶን  ባለፈው ሳምንት በጀርመን ዋና ከተማ በሚገኙ ዋና ዋና ጎዳናዎች ላይ ሲካሄድ ከፍተኛ ትኩረት በመሳብ ነበር፡፡ ለ3 ዓመታት በኬንያዊው ዴኒስ ኬሚቶ ተይዞ የቆየው የዓለም ማራቶን ሪከርድ ሊሰበር እንደሚችል  በመጠበቁና በሌላ በኩል የማራቶን 42.195 ኪሎ ሜትር ርቀት በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ከ2 ሰዓት በታች እንደሚገባ በመገመቱ ነበር፡፡ በማራቶን ፈጣን ሰዓት ያስመዘገቡ የዓለማችን ምርጥ አትሌቶች፤ አሰልጣኞች፤ ማናጀሮች ፤ የስፖርት ሳይንቲስቶች እና ግዙፍ ኩባንያዎች በሁለቱ የማራቶን ስኬቶች ላይ የሚያደርጉትን ጥረት የተገበሩበት መድረክ ሆኖ አልፏል፡፡
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት የሆነው  ኃይሌ ገብረስላሴ  በ44ኛው የበርሊን ማራቶን ዋዜማ ላይ ለስፖርት አድማስ በሰጠው አስተያየት የዓለም ሪከርድ ሊሻሻል እንደሚችል ቢጠብቅም ማራቶንን ከ2 ሰዓት በታች ለመግባት የሚደረገው ሩጫ ፈር እየሳተ መምጣቱ እንደሚያሳስበው ተናግሯል፡፡ ኃይሌ በበርሊን ማራቶን ለአራት ተከታታይ ዓመታት በ2006፤ በ2007፤ በ2008 እና በ2009 እኤአ ላይ በማሸነፍ ከፍተኛውን የውጤት ታሪክ ያስመዘገበውና ለ2 ጊዜያት  የዓለም ማራቶን ሪከርዶችን በስፍራው እንዳስመዘገበ  ይታወቃል፡፡ የዓለማችን ግዙፍ የስፖርት ትጥቅ አምራች እንዲሁም የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች  የማራቶንን ተፈጥሯዊ ባህርይ በሚያሳጡ አጓጉል ሳይንሳዊ ምርምሮች፤ በቴክኖሎጂ የዳበሩ የስፖርት ትጥቆች እና ሌሎች ቁሳቁሶች ከ2 ሰዓት በታች ለመግባት የያዙት አቅጣጫ በጥርጣሬ እንደሚያየው  ኃይሌ ገብረስላሴ  ተናግሮ፤ በስፖርቱ ላይ ከ‹‹ዶፒንግ›› ያላነሰ አደጋ እየጋረጡ የመጡ ፕሮጀክቶች መሆናቸውን በማመልከት  የማራቶን ክብርና ተወዳጅነት የሚቀንሱ ምርምሮች እየበዙ መምጣታቸው አልቀበልም ብሏል ፡፡
በ44ኛው የበርሊን ማራቶን ላይ በተለይ በወንዶች ምድብ አዲስ የዓለም ክብረወሰን ሊመዘገብ እንደሚችል ተጠብቆ የነበረው ያለምክንያት አይደለም፡፡ የአምናው የበርሊን ማራቶን አሸናፊ ቀነኒሳ በቀለ  ፤ የኬንያዎቹ ምርጥ ማራቶኒስቶች የኦሎምፒክ ሻምፒዮኑ ኤሊውድ ኪፕቾጌ እንዲሁም  የቀድሞ የሪከርዱ ባለቤቶች ዊልሰን ኪፕሳንግ እና ፓትሪክ ማኩ በመሮጣቸው ነበር፡፡ እነዚህ ምርጥ ማራቶኒስቶች  በማራቶን ውድድር  ምርጥ ሰዓታቸው በአማካይ ከ2 ሰዓት ከ04 ደቂቃ በታች በመሆኑ ነው፡፡ ቀነኒሳ በቀለ ባለፈው ዓመት የበርሊንን ማራቶንን ሲያሸንፍ በ2 ሰዓት ከ03 ደቂቃዎች ከ03 ሰከንዶች በማስመዝገብ ለሪከርዱ በ6 ሰከንዶች ልዩነት እንደቀረበ የሚታወስ ነው፡፡ በ2017 የውድድር ዘመን ላይ በጣሊያን ሮም ማራቶንን ከ2 ሰዓት በታች ለመግባት በተደረገ ሙከራ ህጋዊ ሰዓት ሆኖ የማይፃፈውን 2፡00፡25 ያስመዘገበው ኤሊውድ ኪፕቾጌ በፈጣን ሰዓቱ  2 ፡03፡05፤ በ2013 እኤአ 2 ሰዓት ከ03 ደቂቃዎች ከ23 ሴኮንዶች  የዓለም ሪከርድ የወቅቱ ሆኖ ባስመዘገበው ፈጣን ሰዓቱ ዊልሰን ኪፕሳንግ እንዲሁም  በ2011 እኤአ በ2 ሰዓት ከ03 ደቂቃዎች ከ38 ሴኮንዶች  የዓለም ሪከርድ የወቅቱ ሆኖ ባስመዘገበው ፈጣን ሰዓቱ ፓትሪክ ማኩ  በበርሊን በመሮጣቸው ለሪከርዱ መሰበር የተሰጠውን ግምት አጠናክረውታል፡፡ አራቱ ምርጥ ማራቶኒስቶች በማራቶን የዓለማችንን ፈጣን ሰዓት ያስመዘገቡና የቀድሞ ሪከርድ ባለቤቶች፤ በመሆናቸው ብቻ ሳይሆን ማራቶን ከ2 ሰዓት በታች ለመግባት በተጧጧፉ የተለያዩ ፕሮጀክቶች በመስራታቸው  የማራቶን ውድድሩን የምንግዜም ምርጥ አሰኝቶታል፡፡
ከላይ በተዘረዘሩት የተለያዩ ምክንያቶች ፤ የዝግጅት ሁኔታዎች እና የፕሮጀክት እንቅስቃሴዎች 44ኛው የበርሊን ማራቶን በከፍተኛ ዓለም አቀፍ ትኩረት የተካሄደ ነበር፡፡ በወንዶች ምድብ ያሸነፈው ኬንያዊው ኤሊውድ ኪፕቾጌ ሆኗል፡፡በሩጫ ዘመኑ ከ9 ስምንት ማራቶኖችን ያሸነፈው ኤሊውድ ኪፕቾጌ ከውድድሩ በኋላ በሰጠው አስተያየት  በሩጫ ዘመኔ ፈታኝ ማራቶን ነበር፤ በጣም ከባድ ዝናብ እየወረደ በዛላይ መሮጫ ጎዳናው እያንሸራተተኝ ነው የሮጥኩት፤ በአይእምሮዬ ሪከርዱን እያሰብኩ ነበር፡፡ ግን በፈታኝ የአየር ሁኔታ ማሸነፌ አስደስቶኛል፡፡ በስፖርት ነገ ሌላ አዲስ ቀን ነው። ሪከርድ ሰዓት መሮጥ እንደምችል አውቃለሁ፡፡ ብሏል፡፡
በ2014 እኤአ ላይ በዓለም የግማሽ ማራቶን ሻምፒዮና ላይ የብር ሜዳልያ ያገኘው ጉዬ አዶላ በመጀመርያ የማራቶን ሩጫው በርሊን ላይ ሁለተኛ ደረጃ ሲጨርስ 2፡03፡46 የሆነ ጊዜ አስመዝግቦ የምንግዜም ምርጥ አጀማመር አሳይቷል፡፡ ጉዬ አዶላ ምርጥ የግማሽ ማራቶን ሯጭ ሲሆን እነ ኪፕቾጌ፤ ቀነኒሳ እና ኪፕሳንግ ለሪከርድ በተጠበቁበት ውድድር የክብረወሰን ብቃት ያለው አሯሯጥ ማሳየቱ አስደንቋል። ዋና አሰልጣኙ ገመዱ ደደደፎ የሚባል ሲሆን በ2017 የዱባይ ማራቶንን ያሸነፉት ታምራት ቶላ እና ዎርቅነሽ ደገፋ፤ በ2016 የቦስተን ማራቶንን ያሸነፉት ሃይሉ ለማ እና አፀደ ባይሳ እና የዱባይ ማራቶን ወጣቱ አሸናፊ ፀጋዬ መኮንንን በስሩ ማሰባሰቡን ዘገባዎች አመልክተዋል። በ2017 መግቢያ የዛይናሜን ማራቶንን ብምርጥ ሰዓት የሮጠው ሞሰንት ገረመው ደግሞ ሶስተኛ ደረጃ አግኝቷል፡፡ በጣም የተጠበቁት ቀነኒሳ በቀለ እና የቀድሞ የማራቶን ሪከርድ ባለቤት ዊልሰን ኪፕሳንግ ውድድሩን አቋርጠው ወጥተዋል፡፡
ከ44ኛው የበርሊን ማራቶን በኋላ ሌትስ ራን የተባለው ድረገፅ ባጠናቀረው ዘገባ 2017 ለቀነኒሳ ጥሩ አመት አይደለም በሚል የመግቢያ ሃሳብ ከሆላንዳዊው ማናጀር ጆስ ሄርማንስ ያደረጋቸውን ውይይቶች አቅርቧል፡፡ የበርሊን ማራቶን ላይ ቀነኒሳ በቀለ  ውድድሩን አቋርጦ ከወጣ ከ24 ሰዓታት በኋላ በበርሊኑ ኢንተርኮንትኔንታል ሆቴል ቁርስ ላይ ከጆስ ሄርማንስ ጋር ተገናኙ የሚለው የሌትስራን ዘጋቢ በሆቴሉ የነበሩ ሰዎች  በሙሉ ወጥተው ዙርያቸው ጭር ሲል ያደረጉትን ውይይት እንዲህ ታዝቦታል፡፡
ጆስ ሄርማንስ በወዳጅነት ስሜት ለቀነኒሳ ምክር ሲሰጡ  በማራቶን ስኬታማ ሆኖ የሩጫ ዘመኑን ለማጠናቀቅ ብዙ ማሻሻል ያለበትን ሁኔታዎችን በዝርዝር አንስተዋል፡፡ ቀነኒሳ ጠንካራ የስራ ዲስፕሊን እና ፕሮፌሽናሊዝም ከኬንያዊው ኢሊውድ ኪፕቾጌ መማር እንዳለበት አበክረው የመከሩት ጆስ ሄርማንስ፤ ማራቶን በበቂና የተሟላ ዝግጅት የሚሳተፉበት ውድድር መሆኑን በመግለፅ፤ ቀነኒሳ የማራቶን ሩጫውንና ቢዝነሱን በሚያስተዳድርበት ሁኔታ ላይ ጥያቄ እንደፈጠረባቸው ጠቅሰው፤ ከማራቶን ልምምዱ ባሻገር የሚያስተዳድራቸውን የተለያዩ ኢንቨስትመንቶች ዘወትር ማለዳ ከሚያደርገው ልምምድ በኋላ ጉብኝት በማድረግ እረፍት ማጣቱ መቀጠል የለበትም ብለዋል። እንደ ጆስ ሄርማንስ እምነት ቀነኒሳ በበርሊን ማራቶን ሳይሳካለት የቀረው ጉዳት ስለነበረው ሳይሆን ለማራቶን በሚያደርገው ዝግጅት በቂ ትኩረት ባለመስጠቱ፤ የሚያደርገው ጥረት እና ስራ በማነሱ ነው ብለዋል። ቀነኒሳ ወደ ማራቶን ከገባ በኋላ 8 ማራቶኖችን ሮጦ ያሸነፈው በ2 ብቻ ሲሆን በ3 ውድድሮች ለንደን፤ ዱባይና በርሊን ላይ አቋርጦ ወጥቷል፡፡
ሆላንዳዊው የግሎባል አትሌቲክስ ማናጀር ጆስ ሄርማንስ ቀነኒሳ በቀለ ወደፊት በማራቶን ስኬታማ ለመሆን እንደሚችል ብዙ እምነት እንዳላቸው የገለፀው ሌትስ ራን፤ ለማራቶን ሙሉ ጊዜውን ሰጥቶ በትክክል ካልሰራ እና ካልተወዳደረ የሩጫ ዘመኑን አላግባብ ለማቋረጥ ይገደዳል ብለው መስጋታቸውን አውስቷል። በዓለም አገር አቋራጭ ውድድሮች የተሳካለት ቀነኒሳ ይሄው ውድድር መጥፋቱ የተለየ ብቃቱን እያጠፋው መጥቷል የሚለው የሌትስ ራን ትንታኔ በማራቶን  የልምምድ ስራው ከጆስ ሄርማንስ ባሻገር፤ ከፊዚዮሎጂስቱ የስኮትላንድ ፕሮፌሰር ያኒስ ፒስታሊደስ እንዲሁም ከአሰልጣኞቹ ሬናቶ ካኖቫ እና መርሻ አስራት እየሰራ ቆይቷል፡፡
በ44ኛው የበርሊን ማራቶን ላይ በአስገራሚ ሁኔታ በአሜሪካው የስፖርት ትጥቅ አምራች ኩባንያ ናይኪ ስፖንሰር ስር ያሉት ቀነኒሳ እና ኪፕቾጌ ኤንኤን ራነኒንግ በሚል ፕሮጀክት ባንድ ማልያ የሚሮጡ ሲሆን ዊልሰን ኪፕሳንግ ደግሞ ከትጥቅ ስፖንሰሩ የጀርመኑ አዲዳስ ጋር በሚሰራበት ስፖንሰርሺፕ ተወዳድሯል፡፡ የበርሊን ማራቶንን ትኩረት እንዲስብ ካደረጉ ምክንያቶች አንዱ ይሄው የስፖርት ትጥቅ አምራች፤ ቴክኖሎጂ አቅራቢ ኩባንያዎች ትንቅንቅ ነበር፡፡ በናይኪ፤ በአዲዳስ እና በቮዳፎን ኩባንያዎች የማራቶን የዓለም ሪከርድ እንዲሰበር እና ከ2 ሰዓት በታች እንዲገባ የተያዘው ፍጥጫ በ100 ሚሊዮን ዶላሮች ወጭ የሚንቀሳቀስ ነው፡፡ ያለፉት 5 የዓለም ማራቶን ሪከርዶች በአዲዳስ ልዩ የመሮጫ ጫማዎች መመዝገባቸው የኃይል  ሚዛኑን ወደ ጀርመኑ ኩባንያ እንዲያጋድል ቢያደርገውም ናይኪ የዓለማችን ምርጥ እና ፕሮፌሽናል ሯጭ ከተባለው ኬንያዊው ዊልሰን ኪፕሳንግ ጋር በሚያንቀሳቅሰው ፕሮጀክት የዓለም አቀፍ ሚዲያዎችን ትኩረት በተሻለ እያገኘ መጥቷል፡፡ ኪፕቾጌ የበርሊን ማራቶንን በማሸነፉ ለናይኪ መልካም ገፅታ ሲፈጥርለት በእድሜው የገፋው ዊልሰን ኪፕሳንግ በአዲዳስ ልዩ የመሮጫ ጫማ ‹‹አዲ ዜሮ›› በ44ኛው የበርሊን ማራቶን ላይ ይመልሳል ተብሎ ቢጠበቅም አልተሳካለትም፡፡ በርሊን ላይ በሪዮ ኦሎምፒክ የማራቶን የወርቅ ሜዳልያ የወሰደው ኬንያዊው ኤሊውድ ኪፕቾጌ በናይኪ በልዩ ትዛዝ የተሰራለትን ‹‹ዙም ቫፕር ፍላይ››፤ ቀነኒሳ በቀለ በበኩሉ ከቮዳፎን ግሩፕ የቀረበለትን ልዩ አልባሳት እና የሩጫ መቆጣጠርያ ሰዓት በመታጠቅ ተሰልፈዋል፡፡
በ40ኛው የቺካጎ ማራቶን
40ኛው የባንክ ኦፍ አሜሪካ ቺካጎ ማራቶን ከሳምንት በኋላ የሚካሄድ ሲሆን የኢትዮጵያ ማራቶን ሪከርድን የያዘችው የዓለማችን የምንግዜም ምርጥ የረጅም ርቀት ሴት ሯጭ ጥሩነሽ ዲባባ 3ኛ የማራቶን ውድድሯን የምታደርግበት ነው፡፡ ከዓመት በፊት በ37ኛው የለንደን ማራቶን በሩጫ ዘመኗ ሁለተኛውን የማራቶን ውድድር ስትሳተፍ የ31 ዓመቷ ጥሩነሽ ዲባባ  በሁለተኛ ደረጃ ማጠናቀቋ የሚታወስ ሲሆን በወቅቱ ርቀቱን የሸፈነችበት 2፡17፡56 አዲስ የኢትዮጵያ ማራቶን ሪከርድ ሆኖ እንደተመዘገበ ይታወቃል፡፡
29  ትንንሽ ከተሞች እና  መንደሮች በማካለል በቺካጎ ከተማ የሚካሄደው ማራቶን 40000 ተሳታፊዎች የሚሮጡበት ሲሆን በየጎዳናዎቹ ከ1.7 ሚሊዮን በላይ ተመልካቾች ይኖሩታል፡፡ በ2016 የማራቶን ውድድሩ ለ39ኛ ጊዜ ሲካሄድ ለቺካጎ ከተማ ኢኮኖሚ ከ282 ሚሊዮን ዶላር በላይ ያስገኘ ሲሆን ባለፉት 4 ዓመታት ለከተማዋ ኢኮኖሚ ያበረከተው አስተዋፅኦ በ3 እጥፍ መጨመሩን ዘገባዎች አውስተዋል፡፡፡
በቺካጎ ማራቶን በሁለቱም ፆታዎች ለሚያሸንፉ አትሌቶች በነፍስ ወከፍ 100ሺ ዶላር የገንዘብ ሽልማ የሚበረከት ሲሆን በአጠቃላይ በየደረጃው ለሚገኝ ውጤትና ሌሎች ተያያዥ ውድድሮች ከ753ሺ ዶላር በላይ እንደቀረበና  የምርጥ ሰዓት እና ሪከርድ የቦነስ ክፍያ ደግሞ 420ሺ ዶላር እንደሆነ ተገልጿል፡፡ በቺካጎ ማራቶን በየጊዜው ፈጣን ሰዓቶች የተመዘገቡ ሲሆን በሁለቱም ፆታዎች 4 የዓለም ሪከርዶችም ተመዝግበውበታል። በወንዶች ምድብ ሁለት የዓለም ማራቶን ሪከርዶች የተመዘገቡት፤ በ1984 እኤአ ላይ በስቲቭ ጆንስ 2፡08፡05 እምሠንዲሁም በ1999 እኤአ በካሊድ ካኑቺ 2፡05፡42 ሲሆን በሴቶች ምድብ ደግሞ በ2001 ካተሪን ንድሬባ በ2፡18፡47 እንዲሁም በ2002 እኤአ ፓውላ ራድክሊፍ በ2፡17፡18 ያስመዘገቡአቸው ነው፡፡ የቦታውን ሪከርድ በወንዶች ምድብ ዴኒስ ኬሚቶ በ2013 እኤአ ላይ 2፡03፡45 እንዲሁም በሴቶች ምድብ 2002 እኤአ ላይ ፓውላ ራድክሊፍ በ2፡17፡18 ነው፡፡

በ47ኛው የኒውዮርክ ማራቶን
በ2017 ቲሲኤስ ኒዎርክ ሲቲ ማራቶን  በታሪክ ለ47ኛ ጊዜ 27 አገራትን የወከሉ 22 ኦሎምፒያኖች በማሳተፍ የሚካሄድ ሲሆን ከኢትዮጵያ ማራቶኒስቶች በወንዶች ምድብ የ22 ዓመቱ ለሚ ብርሃኑና የ27 ዓመቱ ሌሊሳ ዴሲሳ እንዲሁም በሴቶች ምድብ ትግስት ቱፋና ማሚቱ ደስካ የሚሳተፉ ይሆናል፡፡
በሁሉም የውድድር አይነቶች ለሽልማት የቀረበው ገንዘብ ከ825ሺ ዶላር በላይ ሲሆን  በዋናው ማራቶን በሁለቱም ፆታዎች ለሚያሸንፉ አትሌቶች በነፍስ ወከፍ 100ሺ ዶላር ይበረከታል፡፡
ለሚ ብርሃኑ በ2017 በዛይናሜን ፤ በ2016 እኤአ ላይ በቦስተን፤  በ2015 የዱባይ ማራቶን እንዲሁም በ2014 የዙሪክ ማራቶንን ያሸነፈ ሲሆን የግሉ ምርጥ ሰዓት 2፡04፡33 ያስመዘገበው በ2016 በዱባይ ማራቶን ነው፡፡ በሌላ በኩል ሌሊሳ ዴሲሳ ደግሞ ለሁለት ጊዜያት የቦስተን ማራቶንን ያሸነፈ ሲሆን ፈጣን ሰዓቱ በ2013 እኤአ ላይ በዱባይ ማራቶን በ2፡04፡45 ያስመዘገበው ነው፡፡ ሌሊሳ በኒውዮርክ ማራቶን ዘንድሮ የሚሳተፈው ለ3ኛ ጊዜ ሲሆን በ2014 እኤአ ላይ ሁለተኛ በ2015 እኤአ ላይ ሶስተኛ ደረጃ ነበረው፡፡
በሴቶች ምድብ ታሸንፋለች ተብሎ ከፍተኛ ግምት የተሰጣት ነዋሪነቷን በአሜሪካ ብሮንክስ ያደረገችው ትግስት ቱፋ ስትሆን፤ በ2015 እኤአ ላይ የለንደን ማራቶን ያሸነፈች ፤ በ2016 እኤአ ላይ ደግሞ በሁለተኛ ደረጃ ጨርሳለች፡፡ ዘንድሮ በኒውዮርክ ማራቶን የምትሳተፈው ለ3ኛ ጊዜ ሲሆን አስቀድሞ በ2015 3ኛ እና በ2013 8ኛ ደረጃ ነበሯት፡፡

በ10ኛው የማራቶን ሊግ    
የኢትዮጵያ ማራቶኒስቶች በ2017 እኤአ በመላው ዓለም በሚካሄዱ ትልልቅ የማራቶን ውድድሮች በሚያስመዘግቡት ውጤት እንደኬንያውያን እየተሳካላቸው አይደለም፡፡ Abbott World Marathon Majors series የሚል ስያሜ በተሰጠውና በሁለት የውድድር ዘመናት የሚካሄዱ 6 ግዙፍ እና እውቅ ማራቶኖችን በሚያቅፈው ማራቶኖች ሊግ ባለፉት የውድድር ዘመናት የተመዘገቡ ውጤቶች  የኬንያውያን ብልጫ ቀጥሏል፡፡  ባለፉት 9 የዎርልድ ማራቶን ሜጀር ሲሪዬስ የውድድር ዘመናት በከፍተኛ ውጤት የማራቶኖች ሊጉን በወንዶች ምድብ ካሸነፉት 9 አሸናፊዎች ስምንቱ ኬንያውያን ብቸኛው አሸናፊ ከኢትዮጵያ ፀጋዬ ከበደ ነው፡፡ በሴቶች ምድብ ደግሞ ከ9 የማራቶኖች ሊግ አሸናፊዎች 4 ኬንያዊ፤ 3 ጀርመናዊ ሲመዘገቡ ኢትዮጵያን አንዴ በማሸነፍ የወከለችው ጌጤ ዋሚ ብቻ ናት፡፡
በሁለት የውድድር ዘመናት የሚካሄዱ 6 ግዙፍ እና እውቅ ማራቶኖችን እንዲሁም የዓለም ሻምፒዮና  ውጤት በመደመር አሸናፊዎቹ በሚለዩበት የማራቶኖች ሊጉ በሁለቱም ፆታዎች ለሚያሸንፉ አትሌቶች በነፍስ ወከፍ 500ሺ ዶላር የገንዘብ ሽልማት እንደሚታሰብ ይታወቃል። ለማራቶኒስቶቹ የሚሰጠው ነጥብ በሁለቱ  የውድድር ዘመናት ከ6 ማራቶኖች በ4 የሚያስመዘግቡት ከፍተኛ ውጤት ተደማምሮ ሲሆን ለአንደኛ 25፤ ለሁለተኛ 16 ለሶስተኛ 9 ለአራተኛ 4  እንዲሁም ለአምስተኛ 1 ነጥብ በመስጠት ነው፡፡ 6ቱ ማራቶኖች ቶኪዮ ማራቶን፤ ቨርጂን መኒ ለንደን ማራቶን፤ ቢኤምደብሊው በርሊን ማራቶን፤ ባንክ ኦፍ አሜሪካ ቺካጎ ማራቶን እና ቲሲኤስ ኒውዮርክ ሲቲ ማራቶኖች ናቸው፡፡
በ2017 የማራቶኖች ሊግ የተጀመረው  ከ6 ወራት በፊት በለንደን ማራቶን  ሲሆን በለንደን ከ2 ወራት በፊት የተደረገው 16ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና፤ ባለፈው ሳምንት የተደረገው 44ኛው የበርሊን ማራቶን 3ኛው ውድድር ነበር፡፡  
ከ1 ሳምንት በኋላ 4ኛው የማራቶን ውድድር በቺካጎ የሚቀጥል ሲሆን፤ ከወር በኋላ የኒውዮርክ ማራቶን፤ ከዚያም 2018 ከገባ በኋላ በመጀመርያው ወር የሚካሄደው የቶኪዮ ማራቶን፤ በ3ኛው ወር የሚካሄደው የቦስተን ማራቶን፤ እንዲሁም በተመሳሳይ ወቅት የሚካሄዱት የለንደን ማራቶን አሸናፊዎች ይለዩበታል፡፡ለ10ኛ ጊዜ በሚካሄደው የማራቶኖች ሊግ  በሴቶች ምድብ የደረጃ ሰንጠረዡን የምትመራው የኬንያዋ አትሌት ሮዝ ቼሌሞ በ25 ነጥብ ሲሆን ማሪ ኪታኒ እንዲሁም ግላዲስ ቼሮኖ በተመሳሳይ 25 ነጥብ በሁለተኛ እና ሶስተኛ ደረጃ ይከተሏታል፡፡ ሌላዋ የኬንያ አትሌት ኤድና ኪፕላጋት፤ ኢትዮጵያዊያኑ ጥሩነሽ ዲባባ፤ ሩቲ አጋ በ16 ነጥብ 4ኛ፤ 5ኛ እና 6ኛ ደረጃ ላይ ሲመዘገቡ፤ አሰለፈች መርጊያ ከኢትዮጵያ ፤ ኤሚ ሃስቲንግ ከአሜሪካ ፤ ቫሌሪ አዬቢ ከኬንያ በእኩል 9 ነጥብ እስከ ዘጠነኛ ደረጃ እንዲሁም ቪቪያን ቼሮይት በ4 ነጥብ 10ኛ ደረጃ ላይ ናቸው፡፡
ለ10ኛ ጊዜ በሚካሄደው የማራቶኖች ሊግ  በወንዶች ምድብ የደረጃ ሰንጠረዡን የሚመራው የኬንያው ጄዮፈሪ ኪሪዊ በ25 ነጥብ ሲሆን ዳንኤል ዋንጅሩ እና ኤሊውድ ኪፕቾጌ በተመሳሳይ ነጥብ ሁለተኛ እና ሶስተኛ ደረጃ ላይ ናቸው፡፡ ቀነኒሳ በቀለ ፤ ታምራት ቶላ እና ጉዬ አዶላ ከኢትዮጵያ በእኩል 16 ነጥብ ከ4ኛ እስከ 6ኛ ደረጃ ሲይዙ አልፎንሴ ሲንቡ ከታንዛኒያ በ10 ነጥብ፤ ቤዳን ካሮኪ ከኬንያ  እንዲሁም ሞሰነት ገረመው ከኢትዮጵታ በእኩል 9 ነጥብ እና አቤል ኪሪዊ ከኬንያ በ4 ነጥብ እስከ 10ኛ ደረጃ ይቀመጣሉ፡፡

Read 1443 times