Saturday, 30 September 2017 14:42

ከእሾህ አጥር፣ የሰው አጥር ይጠነክራል! “ካብ ሐፁር እሾኽ፣ ሓፁር ሰብ ይፀንዕ”

Written by 
Rate this item
(13 votes)

   የላቲን አሜሪካው ጎሬላ መሪና አብዮታዊ ንድፈ - ሀሳብ ቀማሪ፣ ቼ ጉቬራ ዕውነተኛ ስሙ ኤርኔስቶ ጉቬራ ነው፡፡ የ1960ዎቹ አዲስ የግራ - ሥር - ነቀል ኃይሎች ጀግና ነው፡፡ በፊደል ካስትሮ በሚመራው የኩባ አብዮት ዋና ከሚባሉት ሰዎች አንዱ ነው፤ ቼ፡፡ ቼ ጉቬራ የአርጀንቲና ተወላጅ ይሁን እንጂ በየትም ሀገር ሄዶ፣ ትግል ለማገዝ ወደ ኋላ የማይል ዓለም - አቀፋዊ ታጋይ ነው፡፡ እንደ እሱ ዕምነት የላቲን አሜሪካን ድህነት፣ በሽታና ኢኮኖሚያዊም ሆነ ፖለቲካዊ ኢ-ፍትሃዊነት ለመላቀቅ፣ ብቸኛው መፍትሄ/መድሕን አብዮት ነው ብሎ ያምናል። የካስትሮ ዋንኛ አማካሪ የሆነ ሲሆን ካስትሮ ከኪውባው አምባገነንና ሙሰኛ መሪ ከፉልጄንቺዮ ባቲስታ ጋር ባደረገው የጎሬላ ውጊያ፤ ቼ ጉቬራ ቁልፍ ሚና ተጫውቷል፡፡ ቼ በኋላ የቦሊቪያን ወታደራዊ መንግስት ሲዋጋ ተገደለ፡፡ የተቀበረው ኪዩባ ውስጥ ነው።
ከላይ በተጠቀሰው የካስትሮና የቼ ጉቬራ ትግል ላይ በመመስረት፣ በወቅቱ ይጠቀስ የነበረ ቀልድ የሚመስል አንድ ታሪክ አለ፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን ቼ ጉቬራ፣ ካስትሮና አንድ ተራ ወታደር ኪውባ ውስጥ አምባገነኑን ወታደራዊ መሪ ባቲስታን እየተዋጉ ሳሉ አንድ ቃል ይገባባሉ፡፡
ካስትሮ ነው ነገሩን ያመጣው፡፡
“እንግዲህ” አለ ካስትሮ፤ “መቼም ሽምቅ ውጊያ ላይ ነንና ድንገት ጠላት እጅ ልንወድቅ እንችላለን፡፡ ጠላትም የሚሰጠን ቅጣት እኛ እሱ ላይ ባደረስንበት ጥቃት ያህል እንደሚሆን ጥርጥር የለውም”
ቼ፤ በጉዳዩ መስማማቱን ሲገልፅ፤
“ዕውነት ነው፤ ጠላታችን ብዙ ጉዳት ያደረሰበት ሰው ላይ የመጨረሻውን አሰቃቂ የቅጣት እርምጃ እንደሚወስድበት ከዓለም ታሪክ የተረዳነው ነገር ነው፡፡ አይመስልህም ወዳጄ?” አለው፤ ወደ ወታደሩ ዘወር ብሎ።
ወታደሩም፤
“የእኔም ዕምነት እንደዚያው ነው!” አለ፡፡
ቀጠለ ካስትሮ፤
“እንግዲያው ጓዶች እንዳንከዳዳ! ጠላት ላይ የጥቃት እርምጃ ስንወስድ አናወላውል፡፡ የማያዳግም ጥቃት እናድርስ!”
ቼ፤ “በትክክል! ወሳኝ ጥቃት ነው መሰንዘር ያለብን!” አለ፡፡
ወታደሩም፤
“በበኩሌ የተማርኩትን የጎሬላ ጥበብ ሁሉ ልጠቀም ቃል እገባለሁ!”
ካስትሮ፤
“እኔም ቃል እገባለሁ!”
ቼም፤
“እኔ ቅንጣት ጥርጣሬ የለኝም፤ ቃሌ ቃል ነው!” አለ፡፡ ሲዋጉ ከርመው የተባለው አልቀረም፣ ሶስቱም ጠላት እጅ ወደቁ! ይባላል! ቅጣታቸውም እንደየበደላቸው መጠን በቁማቸው መሬት መቀበር ሆነ፡፡
ያ ተራ ወታደር እስከ አንገቱ ድረስ መሬት ተቀብሯል፡፡ ካስትሮ ግን እጉልበቱ ድረስ ብቻ ነው መሬት የገባው፡፡
ይሄኔ ያ ወታደር፤
“ካስትሮ፤ የገባነው ቃል እንዲህ ነበር? ጠላት ላይ ምንም ጉዳት አላደረስክም ማለት’ኮ ነው አንተ?” አለው፡፡
ካስትሮም፤
“አይ፤ ቼ ጉቬራ ጭንቅላት ላይ አቁመውኝ እኮ ነው!” አለ፡፡ (I am just standing on the head of Che Guevara) ቼ ሙሉ ለሙሉ ከመሬት በታች ተቀብሯል ማለት ነው!
*            *            *
አንድም በቼ ጭንቅላት ነው እዚህ የደረስከው ማለት ነው፤ ነገሩ፡፡ ቼ ያልተገነዘበው፤ “የሰው ቤት የሰው ነው” የሚለውን አማርኛ ተረት ነው! ያም ሆኖ መኖሪያው ያልሆነ ኩባ፣ መቀበሪያው ሆነ! የእንቅስቃሴዎች ሁሉ መዘውር ዕምነትን መካድ፣ ማተብን መበጠስ፣ አድር - ባይነት፣ ፅናት፣ ቆራጥነት፣ አይበገሬነት ነበር፤ ነውም፡፡
ጠንካራ ሰው ጥንካሬን ለዘለዓለም ማቆየት አይችልም፡፡ ጉልበትን ወደ መብት፣ ታዛዥነትን ወደ ሥራ ግዴታ ካልለወጠ በስተቀር፤ ይላሉ ፀሐፍት፡፡
ቼ ማርክሲስት ነው፡፡ የ60ዎቹ ዘመን ኢትዮጵያውያንም ማርክሲስቶች ነበሩ፡፡ እስከ ዛሬም አባዜው ያልለቀቃቸው፤ ልክ ይሁኑም አይሁኑም፤ አሉ፡፡
“ማርክሲዝምን ማግኘት፤ ጫካ ውስጥ ካርታ እንደ ማግኘት ነው” የሚል ሰው ነበር፡፡ የዚያን ዘመኑ ማርክሲዝም የፖለቲከኝነት መገለጫ ነበር፡፡ በኢትዮጵያም እንደዚሁ የፖለቲካው መገለጫ የሶሻሊስቱ አካሄድ ሲሆን መጠንጠኛው ይኼው ማርክሲዝም ነበር፡፡ ዛሬ በገዢው ፓርቲም ሆነ በተቃዋሚ ጎራ የተሰለፉት ወገኖች የማርክሲዝም አቀንቃኞች ነበሩ፡፡ እስካሁን ያልለቀቃቸው አሉ ቢባል ስህተት አይሆንም፡፡
ቶማስ ፔይን፤ “አንድ ትክክለኛ ሰው፤ ዘውድ ካጠለቀ አጭበርባሪ ይልቅ ብዙ ከበሬታ ይገባዋል” ይለናል። ዘውድ ያጠለቀ እንግዲህ ባለስልጣን ሁሉ ማለት ነው፡፡ ሹመኛ ማለት ነው፡፡ ሊቀመንበር ማለት ነው፡፡ የማህበርም፣ የፓርቲም መሪ ነው፡፡ የቢሮ ኃላፊ ነው፡፡
ካስትሮ እንዲህ ይለናል፡-
“የሀገሪቱ የወደፊት ዕጣ፣ ለችግርቿም የሚሰጠው መፍትሔ በጥቂት ስግብግብ ነጋዴዎች ትከሻ ላይ አሊያም ከደርዘን የማይበልጡ፣ አየር-ማረጋጊያ በተገጠመለት ነፋሻ ቢሮ የተቀመጡ፣ ወሳኝ ሰዎች፤ ቀዝቃዛ የትርፍ ሂሳብ ስሌት ላይ የተመሠረተ ሆኖ ሊቀጥል አይችለም፡፡ … ችግራችን የሚፈታው አባቶቻችን ባወረሱን ኃይል፣ ታማኝነት/ለአገር መታመን፤ ጀግንነት… ራሳችንን አሳልፈን ከሰጠን ነው፡፡ “የኢንተርፕራይዞች ፍጹም ነፃነት”፣ “ካፒታላቸውን ለሚያፈሱ ኢንቨሰትሮች ዋስትና መስጠት”፣ “የአቅርቦትና ፍላጎት ሕግ” እያልን ያማሩ ቃላት በመደርደር አይደለም ችግራችን የሚፈታው! በሙስና የተዘፈቁ ተቋሞቻችንን ስናፀዳና በዘርፉ የተጨማለቁ ባለሥልጣናትን ስናስወግድ ነው! ትክክለኛ ያልሆኑ ህግጋትን ተቀብሎ የሚኖር፣ አገርን የሚጨፈልቅና የተወለደባትን አገር የሚበድል ሰው እያየ ዝም የሚል ግለሰብ፤ እሱ የተከበረ ሰው አይደለም፡፡… በዓለም ላይ የተወሰነ ብርሃን ያለውን ያህል፣ የተወሰነ የክብር ደረጃ መኖር አለበት፡፡ ክብረ-ቢስ የሆኑ ሰዎች በኖሩ ቁጥር፤ የብዙ ሰዎችን ክብር ይዘው የሚኖሩ ሌሎች ሰዎችም ይኖራሉ፡፡ እንደነዚህ ያሉ ሰዎች፤ የህዝቡን ነፃነት የሚሰርቁ ሰዎች ለማስወገድ በኃይል የሚነሱቱ ናቸው፡፡ ያም ማለት ክብርን ራሱን የሚዘርፉ ሰዎችን የሚቃወሙ ማለት ነው! በእንደዚህ ያሉ ሰዎች ልብ ውስጥ  በሺዎች የሚቆጠሩ ህዝቦች አሉ፡፡ የሰው ልጅ ክብር ታፍሮ ይኖራል!...” የሀገራችንን ነገር ከኩባ ጋር አነፃፅሮ ማየት እጅግ ጠቃሚ ነው፡፡
 ሼክስፒር በሎሬት ፀጋዬ ብዕር ውስጥ ይሄን ይለናል፡-
“ገንዘቤን የሰረቀ ሰው፣ ወሰደ እንበል ከንቱ ነገር
 ዋጋ አለው ግን ከንቱም ነው፣ የእኔም የእሱም የእሷም ነበር፤
ግና ስሜን የሰረቀኝ
የማያከብረውን ወስዶ፣ እኔን በግልፅ አደኸየኝ”
ጆን ሚልተን፤ “የፖለቲካ ሥልጣን ያለው ለንጉሦች ዘውድ መጫንም፣ ዘውድ መንጠቅም፣ ጨቋኞችን የመጣል ግዴታም ባለው ህዝብ እጅ ውስጥ ነው!” ይለናል፡፡ ችግሩ የሚከሰተው የተባለው ህዝብ ይሄንን ያላወቀ እንደሆነ ነው፡፡
እዚህ ላይ የካስትሮን “ታሪክ ነፃ ያደርገኛል” የሚለው የፍርድ ቤት መከላከያ ንግግር መጥቀስ ተገቢ ነው፡፡ “ህልመኛ ነው ብለው የሚያስቡ ካሉ የማርቲን ንግግር እጠቅሰላቸዋለሁ፡፡ “ዕውነተኛ ሰው ጥቅም ያለበትን ቦታ አይደለም የሚሻው፡፡ ይልቁንም ተግባር ያለበትን ቦታ እንጂ፡፡ ዕውነተኛ የተግባር ሰው ይሄ ነው- የዛሬ ህልሙ የነገ ህግ የሚሆን! ምክንያቱም፤ የታሪክን ሂደት ዞር ብሎ ለተመለከተና እንደ እሳት የሚንበለቦሉና በዘመናት ሰታቴ ድስት ውስጥ እየተፍለቀለቁ የደሙ ህዝቦችን ላየ፣ ነገ ሥራን በሚያከብሩ ሰዎች እጅ ውስጥ መሆኑን ይገነዘባል” ስለዚህ ዕውነተኛ ሰዎችን በዙሪያችን መያዝ ተገቢ ነው፡፡ የሰው ኃይል፣ የተደራጀ የሰው ኃይል፣ ራሱን የሚያውቅ የሰው ኃይል ማፍራት ዋና ነገር ነው፡፡ “ከእሾህ አጥር፣ የሰው አጥር ይጠነክራል” የሚለው የትግርኛ ተረት የሚነግረን ይሄንኑ ነው፡፡

Read 7128 times