Saturday, 30 September 2017 14:35

በነገው የኢሬቻ በዓል ላይ ከ6 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ይታደማል ተብሎ ይጠበቃል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(31 votes)

መንግስት በምንም መልኩ እጁን አያስገባም ተብሏል

  የኦሮሞ ህዝብ የምስጋና በአል “ኢሬቻ”፣ በነገው እለት በቢሾፍቱ ሆራ አርሶዲ የሚከበር ሲሆን በበአሉ ላይ ከ6 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ይሳተፋል ተብሎ እንደሚጠበቅ፣ የበአሉ አስተባባሪ አባ ገዳ በየነ ሰንበቶ ለአዲስ አድማስ አስታውቀዋል፡፡
የኢሬቻ በዓል አከባበርን በተመለከተ አባ ገዳዎች ደንብ ማውጣታቸው የተገለፀ ሲሆን በዚህ ደንብ መሰረት፣ የመንግስት አካላት በበአሉ ላይ በምንም መንገድ ጣልቃ እንዳይገቡ ይከለከላሉ ተብሏል፡፡ የኦሮሚያ አባገዳዎች ህብረት ሰብሳቢ አባ ገዳ በየነ ሰንበቶ ለአዲስ አድማስ በሰጡት ማብራሪያ፤ አንድ የመንግስት ባለስልጣን በኦሮሞነቱ እንደ ማንኛውም የበአሉ አክባሪ መገኘት የሚችል ቢሆንም ምንም አይነት የፖለቲካ ንግግር ለማድረግ መድረክ አይሰጠውም ብለዋል፡፡ መድረኩን ሙሉ ለሙሉ የሚመሩት አባገዳዎች መሆናቸውን የጠቆሙት የፀጥታ ኃይሎችም ቢሆኑ የጦር መሳሪያ ይዘው በአካባቢው መገኘት አይችሉም ብለዋል፡፡
በበዓሉ ላይ የሚታደሙትን ከ6 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በደንብና ስርአት ለማስተናገድ በገዳ ስርአት “ፎሌ” ተብለው የሚታወቁ ከ600 በላይ ወጣቶች መመደባቸውን አስታውቀዋል - አባ ገዳ በየነ፡፡ ከኦሮሞ ህዝብ በተጨማሪ ሌሎች ኢትዮጵያውያን ይታደሙታል ተብሎ እንደሚጠበቅ የጠቆሙት አባገዳው፤ የበአሉ ስነ ስርአት የሚከበርበት ቦታም አደጋ አድራሽ እንዳይሆን መሬቱን የመደልደልና መንገዶችን የማስተካከል ስራ ተሰርቶ መጠናቀቁን አስታውቀዋል፡፡
ለበአሉ አስፈላጊው ሁሉ ስለተመቻቸ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በበአሉ ላይ እንዲታደም አባ ገዳ በየነ ሰንበቶ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ባለፈው ዓመት መስከረም 22 ቀን 2009 ዓ.ም በኢሬቻ በአል ላይ በተከሰተ መንግስት 55 ሰዎች መሞታቸውን መግለፁ የሚታወስ ሲሆን ዓለማቀፍ የሰብአዊ መብት ተቋማት በበኩላቸው፤ የአደጋው መንስኤና የደረሰው ጉዳት በአለማቀፍ መርማሪዎች እንዲጣራ በተደጋጋሚ መጠየቃቸው ይታወቃል፡፡ ባለፈው ሳምንት “ሂዩማን ራይትስዎች” ባወጣው መግለቻ፣ ዘንድሮ የሚከበረው የእሬቻ በዓል ላይ ምንም ዓይነት ግጭት እንዳይፈጠር የፀጥታ ሃይሎች ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ማሳሰቡ ይታወሳል፡፡


Read 6916 times