Saturday, 30 September 2017 14:32

ከ60 በላይ የጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ መምህራን “ከለላ ይሰጠን” አሉ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(11 votes)

“ለአቤቱታው ምላሽ ሰጥቻለሁ” ትምህርት ሚኒስቴር

   ከ60 በላይ የጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ  መምህራን፣ “የብሄር ጥቃት ሊፈፀምብን ይችላል” የሚል ስጋት እንዳደረባቸው በመግለፅ፣ የትምህርት ሚኒስቴር፣ መፍትሄ እንዲሰጣቸው አቤቱታ ያቀረቡ ሲሆን ትምህርት ሚኒስቴር በበኩሉ፤ ለመምህራኑ  ምላሽ ሰጥቻለሁ ብሏል፡፡
በኦሮሚያና በሶማሌ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች የተፈጠረውን ግጭት ተከትሎ፣ ከ140 ሺ በላይ ዜጎች ከቀዬአቸው መፈናቀላቸው የተገለፀ ሲሆን የዩኒቨርስቲው መምህራን፤ “ጥቃት ሊፈፀምብን ይችላል፤ ትምህርት ሚኒስቴር ከለላ ይስጠን” ብለዋል፡፡
በጉዳዩ ላይ ከአዲስ አድማስ ማብራሪያ የተጠየቁት የጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ አንድ የስራ ኃላፊ በሰጡት ምላሽ፤ በጅግጅጋ ከተማ የተፈጠረውን ችግር ተከትሎ፣ ዩኒቨርሲቲው ለሁሉም መምህራን ከለላ መስጠቱን ጠቁመው፤ አቤቱታ አቅራቢዎቹ፣ የደረሰባቸው አካላዊ ጥቃት እንደሌለ ተናግረዋል። ነገር ግን “ለደህንነታችን እንሰጋለን” በማለት ዩኒቨርሲቲውን ለሚያስተዳድረው የትምህርት ሚኒስቴር፣ አቤቱታ ማቅረባቸውን አስረድተዋል-ሃላፊው፡፡
በአሁን ወቅት የተረጋጋ ሁኔታ በመፈጠሩም መምህራኑ ወደ መደበኛ ስራቸው ይመለሳሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የስራ ኃላፊው አስታውቀዋል፡፡
የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ጥላዬ ጌቴ በበኩላቸው፤ አቤቱታው ከመምህራኑ ቀርቦላቸው እንደነበር ገልፀው፤ ውይይት ከተደረገ በኋላ ወደ መደበኛ ስራቸው እንዲመለሱ መስማማት ላይ መደረሱን አስታውቀዋል፡፡
“አሁን ያለው ችግር የብሄር አይደለም፤ ለወደፊትም አይኖርም” በሚል ውይይት አድርገው፣ መምህራኑ ወደ መደበኛ ስራቸው እንዲመለሱ መግባባት ላይ ተደርሷል ብለዋል-ሚኒስትሩ፡፡
“የክልሉ መንግስት፣ እንደ ማንኛውም የመንግስት ሰራተኞች፣ መብታቸውን ያስከብራል፤ በዚህ ላይም ውይይት አድርገናል” ብለዋል- ሚኒስትሩ ለአዲስ አድማስ፡፡
ከአቤቱታ አቅራቢዎቹ መካከል ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንድ መምህር በሰጡት አስተያየት፤ ከትምህርት ሚኒስቴር ያገኙት ምላሽ እንዳላረካቸው ጠቁመው፤ ቀጣይ እርምጃቸው የዝውውር ጥያቄ ማቅረብ እንደሆነ አስታውቀዋል። “የደህንነት ስሜት አይሰማንም” ያሉት  መምህሩ፤ መንግስት ደህንነታቸውን እንዲያስጠብቅላቸው ተማፅነዋል፡፡Read 9933 times