Saturday, 30 September 2017 14:30

የኬንያ ም/ፕሬዚዳንት መኖሪያ ቤት ላይ ጥቃት በመፈፀም የተጠረጠረው ኢትዮጵያዊ ተከሰሰ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(6 votes)

   በኬንያ ምክትል ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ መኖሪያ ቤት ላይ “በመሣሪያ የታገዘ ጥቃት ፈፅሟል፣ የአልሸባብም አባል ነው” የተባለው ኢትዮጵያዊ ተጠርጣሪ፣ ተከሶ በናይሮቢ ፍ/ቤት መቅረቡን የሃገሪቱ ዋና  ዋና ጋዜጦች እየተቀባበሉ ዘግበውታል።
ኢትዮጵያዊው አሊ ኤልማ ዋሪዮ፤ ከትናንት በስቲያ ሃሙስ በናይሮቢ ፍ/ቤት የቀረበው ከ2 ወራት በፊት ሶጎኢ በተባለች የገጠር መንደር ውስጥ በሚገኘው የኬንያ ም/ፕሬዚዳንት መኖሪያ ቤት ላይ ጥቃት ፈፅሟል በሚል ጥርጣሬ ሲሆን በህገ ወጥ መንገድም የሃገሪቱን ድንበር ጥሶ በሞያሌ በኩል በመግባቱ ከወዲሁ የአንድ ወር እስራት ተፈርዶበታል ተብሏል፡፡
ወጣቱ ኢትዮጵያዊ፤ በኬንያ በተደጋጋሚ የሽብር ጥቃት የፈፀመው የአልሸባብ አባል ነው ተብሎ መጠርጠሩን የዘገበው ዴይሊኔሽን ጋዜጣ፤ ተከሣሹ በፍ/ቤት በሠጠው ቃል ግን ፈጽሞ የአልሸባብ አባል እንዳልሆነ መናገሩን ድርጊቱንም እንዳልፈፀመ ክዶ መከራከሩን ጠቁሟል፡፡
የኬንያ መንግስት አቃቤ ህግ በበኩሉ፤ በዋናነት ጥቃቱን ካቀነባበረውና 20 ሰአታትን በፈጀው የፖሊስና የጥቃት ፈፃሚዎች የተኩስ ልውውጥ ወቅት ከተገደለው መሃመድ ኢብራሂም መሃመድ ጋር የስልክ ንግግር ማድረጋቸውንና በጥቃቱ መሳተፉን የሚያረጋግጥ ማስረጃ አለኝ ብሏል፡፡ የሀገሪቱ ፀረ ሽብር ግብረ ሃይልም ወጣቱ ከአልሻባብ ጋር ግንኙነት እንዳለው ማስረጃ አለኝ ማለቱን ዴይል ኔሽን ዘግቧል፡፡
ኢትዮጵያዊው በተጠረጠረበት የሽብር ጥቃት መፈፀም ወንጀል ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘ፣ እስከ 30 ዓመት በሚደርስ እስራት የሚቀጣ ሲሆን ከትናንት በስቲያ ለፍ/ቤቱ ያቀረበው የዋስትና ጥያቄም ተቀባይነት አላገኘም ተብሏል፡፡
እ.ኤ.አ ሐምሌ 29 ቀን 2017 ዓ.ም በምክትል ፕሬዚዳንቱ መኖሪያ ቤት ላይ ጥቃቱ ከመፈፀሙ የተወሰኑ ሰዓታት በፊት ም/ፕሬዚዳንቱና ቤተሰቦቻቸው ለስራ ጉዳይ ከቤት ወጥተው ስለነበር በጥቃቱ ጉዳት እንዳልደረሰባቸው የተዘገበ  ሲሆን በፖሊሶች ላይ ግን ጉዳት ደርሷል ተብሏል፡፡
ጥቃቱን ለመቀልበስም የሀገሪቱ የፀረ ሽብር ግብረ ሃይል በሄሊኮፕተር የታገዘ ኦፕሬሽን ማካሄዱም ተዘግቧል፡፡  

Read 2865 times