Saturday, 30 September 2017 14:29

የአፍሪካ የፋሽን ሳምንት ኤክስፖ ማክሰኞ ይከፈታል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

    የአፍሪካ ሶርሲንግና የፋሽን ሳምንት ኤክስፖ የፊታችን ማክሰኞ በሚሊኒየም አዳራሽ ይከፈታል። አዘጋጁ “ትሬድ ኤንድ ፌይርስ አፍሪካ ሊሚትድ” (TFEA) የተሰኘውና በምስራቅ አፍሪካ አካባቢ መሰል የንግድ ትርኢቶችን በማዘጋጀት የሚታወቀው አውሮፓዊ ድርጅት ከትላንት በስቲያ ረፋድ ላይ ቦሌ በሚገኘው ጎልደን ቱሊፕ ሆቴል፣ ኤክስፖውን አስመልክቶ በሰጠው መግለጫ፤ በዚህ የንግድ ትርኢትና ኮንፍረንሰ ላይ በጅምላና በችርቻሮ የቡቲክ ስራ የተሰማሩ ነጋዴዎችን ጨምሮ በጨርቃጨርቅና አልባሳት፣ በልዩ ልዩ የመስተንግዶ ሥራ የተሰማሩ፣ መዋቢያና መጫሚያ አምራችና አከፋፋዮች፣ በፋሽንና በዲዛይን ስራ የተሰማሩና ከ230 በላይ የዘርፉ አምራችና ላኪዎች እንደሚሳተፉ ተናግረዋል፡፡ እነዚህ የዘፍ ተዋናዮች፤ ኢትዮጵያውያን ጨምሮ ከ25 የዓለም አገራት ምርቶቻቸውን ይዘው እንደሚቀርቡም ተገልጿል፡፡
እንደ ኤግዚቢሽኑ አዘጋጆች ገለፃ፣ በአጠቃላይ በኤግዚቢሽኑ ላይ ከ3 ሺህ 500 በላይ ከዓለም ዙሪያ የሚመጡ ተሳታፊዎች ይጠበቃሉ፡፡ ከመስከረም 23-26 ቀን 2010 ዓ.ም በሚቆየው ከዚህ የንግድ ትርኢት ጎን ለጎን፣ የሶስት ቀናት ጉባኤ የሚካሄድ ሲሆን ጉባኤው በዋናነት በአሜሪካ የአፍሪካ ከቀረጥና ኮታ ነፃ የንግድ እድል (አጎዋ) ላይ፣ በዘርፉ ኢንቨስትመንትና ቀጣይነት ዙሪያ፣ በቢዝነስ አጋርነትና በሎጂስቲክና ፋሽን ዙሪያ በተያያዥ ጉዳዮች ላይ ከመንግስትና ከኢንዱስትሪው ተወክለው የሚገኙ የዓለም ኤክስፐርቶች የመፍትሄ ሀሳቦቻቸውን በጉባኤው አቅርበው፣ ውይይትና ውሳኔ እንደሚካሄድባቸው አዘጋጆቹ ገልፀዋል፡፡ ለአራት ቀናት የሚቆየውን ይህን የፋሽን ሳምንት ትርኢት፤ ሰዎች እንዲጎበኙትም ጥሪ አቅርበዋል፡፡  

Read 1219 times