Monday, 25 September 2017 12:51

ዋው የማዕድን ውሃ፣ለ60 ችግረኞች፣የገንዘብ ድጋፍ አደረገ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ከእያንዳንዱ ጠርሙስ ውሃ፣ 1ሣንቲም፣ ለችግረኞች ድጋፍ ይውላል

ዋው የማዕድን ውሃ ፋብሪካ ምርት ከጀመረበት ቀን አንስቶ ከሸጣቸው ከእያንዳንዱ ጠርሙስ የማዕድን ውሃ ላይ አንድ ሳንቲም፣ ጧሪና ደጋፊ ለሌላቸው አረጋውያንና ወላጆቻቸውን ላጡ ህፃናት ድጋፍ አደረገ፡፡ ድርጅቱ ያደረገው የገንዘብ ድጋፍ፤ ቀጣይነት ያለውና ቋሚ
መሆኑን የፋብሪካው ባለቤትና ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ጠንክር በቀለ ገልፀዋል፡፡ ሰሞኑን በጉራጌ ዞን ቸአ ወረዳ ውስጥ በሚገኘው
የፋብሪካው ቅፅር ግቢ በተከናወነ ሥነሥርዓት፣ድርጅቱ 60 ለሚሆኑ አረጋውያንና ችግረኛ ህፃናት የገንዘብ ድጋፍ አድርጓል፡፡ በአረጋውያኑና በህፃናቱ ስም በንብ ኢንተርናሽናል ባንክ በተከፈተ የቁጠባ ሂሳብ፣ ለእያንዳንዳቸው 1500 ብር ገቢ የተደረገላቸው ሲሆን ችግረኞቹን በዘላቂነት ለመደገፍ ድርጅቱ ቃል ገብቷል። ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ ባደረጉት ንግግርም፤የተደረገው የገንዘብ ድጋፍ፣ ድርጅቱ የገባውን ቃል
የሚያረጋግጥበትና ሃገራዊ ሃላፊነቱን በመወጣት ተግባራዊ እንቅስቃሴውን የሚያሳይበት ነው ብለዋል፡፡ ድጋፍ የተደረገላቸው አረጋውያንና ወላጅ
የሌላቸው ህፃናት በበኩላቸው፤ ባገኙት ድጋፍ ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸው ገልጸው፣ ድርጅቱ በቀጣይነት በሚያደርግላቸው ድጋፍ፣ ህይወታቸውን ለማስተካከል የሚችሉበትን ሥራ ለመስራት እንደሚጥሩ ተናግረዋል። በዕለቱ በፋብሪካው ቅጥር ግቢ ውስጥ የተገኙ በርካታ
የአካባቢው ተወላጅ ባለሃብቶችም፣ለችግርኛ ህፃናቱና አረጋውያኑ የተለያዩ ድጋፎችን አድርገዋል፡፡ በ”የካብዲ አግሮፕሮሰሲንግ” ኃ.የተ.የግ.ማ ሥር
የተቋቋመው ዋው የማዕድን ውሃ ፋብሪካ፤ ለአካባቢው ወጣቶች የሥራ ዕድል በመፍጠርና ሌሎች አገር አቀፍ ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞችን በማስገኘት ሰፊ እንቅስቃሴ እያደረገ እንደሚገኝ የገለፁት የፋብሪካው ባለቤት፤ ከዚህ ባሻገር ችግረኛ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን በቋሚነት ለመደገፍ ዕቅድ ነድፎ በስፋት እንደሚንቀሳቀስ ተናግረዋል፡፡ ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ካፒታል የተቋቋመው ድርጅቱ፤ በቀጣይ በወተትና የወተት ተዋፅኦ፣ በፍራፍሬ ጭማቂዎችና በሌሎች የምግብና የመጠጥ አግሮፕሮሰሲንግ ሥራዎች ላይ በስፋት እንደሚሰማራ አቶ ጠንክር ገልፀዋል፡፡

Read 2197 times