Monday, 25 September 2017 12:39

ለስፖርተኞች “አዋርድ” ጀምረናል!…ግን ከዚያስ?

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

  በኢትዮጵያ የስፖርት ውድድሮች መካሄድ ከጀመሩ አንድ ክፍለ ዘመን ሊሞላቸው ነው፡፡ በተለይ እግር ኳስ ከ80 ዓመታት በላይ አትሌቲክስ እስከ 70 ዓመታት የዘለቀ ታሪክ ያላቸው ስፖርቶች ናቸው፡፡ በእግር ኳስ በአፍሪካ ደረጃ ከመስራችነት የተነሳው ታሪክ አሁን ኃላቀር ከሆኑ አገራት የሚሰለፍ ሆኗል፡፡ በአንፃሩ በአትሌቲክስ በዓለም ሻምፒዮናና እና በኦሎምፒክ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ማንፀባረቁን ቀጥሏል፡፡
በሁለቱ ስፖርቶች በአገር ውስጥ ያለው ትኩረት ከፍ ያለ ቢሆንም በየዓመቱ የላቀ ብቃት ላሳዩ እና ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ስፖርተኞች ልዩ ዓመታዊ የክብር ሽልማቶች የሚሰጡበት ሁኔታ ወቅቱን በጠበቀ ደረጃ ብዙ ሊለመድ አልቻለም፡፡ የክብር፤ የኮከብነት፤ የላቀ አስተዋፅኦ እና የህይወት ዘመን  ሽልማቶች በስፖርቱ ቀጣይ እድገት እና ህልውና አበይት መድረኮች ሊሆኑ መቻላቸው በሁሉም ባለድርሻ አካላት ተገቢው ትኩረት ተነፍጎት ቆይቷል፡፡ በተለያዩ ጊዜያት በፌደሬሽኖች፤ እንዲሁም በመንግስት ተቋማት እና በግለሰቦች የሽልማት ስነስርዓቶች በተለያዩ አጋጣሚዎች ለማካሄድ ተሞክሯል፡፡ ይሁንና እነዚህ የሽልማት  ስነስርዓቶች ከዓመት አመት እያደጉ፤ እየገዘፉና ተናፋቂ መድረኮች እየሆኑ እንደመሄድ እንደዘበት የሚቋረጡ፤ የሚቀዛቀዙ እና ወጥነት የጎደላቸው ሆነው ቆይተዋል። ለውጤታማ ስፖርተኞች ተገቢውን ክብር እየሰጡ ያሉት አልፎ አልፎ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ማግስት የሚሰጡት የገንዘብ ሽልማቶች ናቸው፡፡
በተለይ በአትሌቲክስ መስክ በሜዳልያ ድል ለሚደምቁ አትሌቶች በመንግስት በኩል አንዳንድ ጊዜ የክብር ኒሻኖችና የመሬት ስጦታዎች በሚወክሏቸው ክለቦችና  የውትድርና ተቋማት ልዩ ሽልማቶችና የክብር ማዕረጎች ተሰጥተዋል፡፡ ሁሉም ግን ወቅታቸውን ጠብቀውና በደማቅ ስነስርዓት እና ክብር ያለው ሽልማት ታጅበው የተካሄዱበት ዘመን የለም፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን ዓመታዊ የኮከብ ስፖርተኞች ምርጫዎች እና ሽልማቶች እየተለመዱ መጥተዋል፡፡ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን፤ በስፖርት ጋዜጠኞች እና በኦን ላይን ሚዲያዎች ዓመታዊ የኮከብ ተጨዋቾች የሽልማት ስነስርዓቶች በመከናወን ላይ ናቸው፡፡
ባለፈው እሁድ በሸራተን አዲስ ሆቴል ላሊበላ አዳራሽ የመጀመርያው የኢቢሲ የስፖርት ሽልማት በልዩ ስነስርዓት ተካሂዶ ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን መስራችነት እና አዘጋጅነት የተካሄደው የሽልማት ስነስርዓቱ ደረጃውን የጠበቀ ለማድረግ በተለያዩ ፈርቀዳጅ ሙከራዎች የተስተዋሉበት ነበር። ኢቢሲ የሽልማት ስነስርዓቱን ፤ ከእነ ምርጫ ሂደቱ አንስቶ እስከ መጨረሻው ምሽት ለማዘጋጀት ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት እንዳወጣ የሚገመት ሲሆን አሸናፊዎችን ለመምረጥ በኤስኤሜስ በተካሄደው የምርጫ ሂደት በይፋ ባይገለፅም ዳጎስ ያለ ገቢ እንዳገኘ ታውቋል፡፡  የሽልማት ስነስርዓቱ በሸራተን ላሊበላ አዳራሽ በተካሄደበት ምሽት ኢቢሲ በቀጥታ ስርጭቱ ከ25 እስከ 30 ሚሊዮን ተመልካች ነበረው፡፡
በአንፃሩ  ባለድርሻ አካላት የሆኑትን የስፖርት ፌደሬሽኖች ሙሉ እውቅና በማግኘትና በአጋርነት ያላሳተፈ፤ እንዲሁም በተገቢው መንገድ ብቃትን በሚለካ የማወዳደርያ መስፈርት እና የምርጭ ሂደት የታጀበ አለመሆኑ ለትችት አጋልጦታል፡፡
የሽልማት ስነስርዓቱ በኦርጅናል ስያሜ፤ በቋሚ የመካሄጃ ወቅት፤ በሁለት የሽልማት ዘርፎች ተደራጅቶ የተዘጋጀ ቢሆንም አሸናፊዎችን ለመመርጥ በተከተላቸው የማወዳደርያ መስፈርቶች፤ የእጩዎች አመራረጥ እና የውጤት አሰጣጥ ዙርያ በተከተለው አሰራር ሂደት የሚመለከታቸውን ባለድርሻ አካላት ሙሉ እውቅና አለማግኘቱ ሊኖረው የሚገባ ጥሩ ጅምሮን ያደበዘዘው ሆኗል፡፡  የሽልማት ስነስርዓቱ በታዳሚዎች ፤ በተጋባዥ የክብር እንግዶች ንግግሮች፣ በአለባበስ፤ በኢቢሲ የቀጥታ ስርጭት እና በመድረክ ክንውን፤ በማጀቢያና በመዝነኛ ሙዚቃዎች የታጀበት አቀራረብ ሌሎች ሁኔታዎች በየአቅጣጫው ደረጃውን በጠበቀ ሁኔታ መካሄዱን የሚያስገመገሙ ክስተቶችም አስተናግዷል፡፡ የመጀመርያዎቹ አሸናፊዎች፤ ሸላሚዎች እና ሽልማታቸው በዝርዝር መመልከትም ተገቢ ይሆናል፡፡ 2ኛው፤ 3ኛው፤ 4ኛው እያለ የሽልማት ስነስርዓቱ እንዲቀጥል በማሰብ  በሽልማት ስነስርዓቱ አጀማመር የታዘብናቸው ሁኔታዎች ይህ የስፖርት አድማስ መጣጥፍ ይዳስሳል፡፡

ኢቢሲ ስለ ሽልማት ስነስርዓቱ
በሀገራችን የተለያዩ ዓመታዊ ሽልማቶችን በተለይ በፊልምና ሙዚቃ ዘርፎች ማዘጋጀት እየተለመደ መምጣቱን የሚጠቅሰው በኢቢሲ ስለ ስፖርት ሽልማት የተብራራበት ፓምፍሌት፤ ከዚህ አንጻር የሀገራችን ሚድያዎች አስተዋጽኦ ሲመዘን በሌሎች አካላት የተዘጋጁ ሽልማቶችን ከመዘገብ ባሻገር የራሳቸውን ፕግራም በማዘጋጀት ሲያወዳድሩና እውቅና ሲሰጡ አለመስተዋሉን በማመልከት፤ ኢቢሲ ይህንን ክፍተት ግምት ውስጥ በማስገባት እንደ ብሄራዊ ሚድያነቱ የራሱን አሻራ ለማስቀመጥ መጀመሩን አስታውቋል፡፡ ስለሆነም ኢቢሲ ያዘጋጀውን የስፖርት ሽልማት “የኢቢሲ የአመቱ ምርጥ ስፖርተኛ ሽልማት /EBC Sport Award of the Year/” የሚል መጠሪያ እንደሰጠውና በየአመቱ በነሐሴ ወር የመጨረሻ ሳምንት ቅዳሜ ምሽት ላይ  የሚከናወን መሆኑን  አመልክቷል፡፡
የሽልማቱን አላማዎች ሲዘረዝርም ወጣት ስፖርተኞችን ማበረታታት፤ በተሸላሚ ስፖርተኞች ዘንድ መነቃቃትን በመፍጠር ሀገሪቱን ወክለው በአለም አቀፍ መድረክ ውጤታማ ለመሆን እንዲነሳሱ ማስቻል እንዲሁም የስፖርት ቤተሰቡ ለሀገር ውስጥ ስፖርት ያለው ግንዛቤ፣ ድጋፍና ተሳትፎ ከፍ እንዲል ለማድረግ መሆኑን ገልጿል፡፡ ዘንድሮ በሽልማቱ የመጀመርያ ስነስርዓት  በ2 /ሁለት/ የስፖርት ዓይነቶች እና በ4 /አራት/ ዋና ዋና ዘርፎች ሽልማት ለመስጠት በመወሰን መንቀሳቀሱን በመግለፅ፤  በአትሌቲክስ እና በእግር ኳስ የስፖርት ዓይነቶች በሁለቱም ፆታዎች በመከተሉት አራት ዘርፎች ሲሆን ምርጥ ወንድ የእግር ኳስ ተጫዋች፣ ምርጥ ሴት የእግር ኳስ ተጫዋች፣ ምርጥ ወንድ አትሌት እና  ምርጥ ሴት አትሌት ውድድሩ የሚካሄድባቸው ዘርፎች እንዲሆኑ አድርጓል፡፡
ለአራት ወራት የተካሄደው የሽልማት ስነስርዓቱ የምርጫ ሂደት ላይ ስለተከተላቸው የማወዳደሪያ መስፈርቶች ኢቢሲ በዝርዝር ሲያብራራ በምርጥ  የእግር ኳስ ተጫዋች ዘርፎች ለመወዳደር የሚቀርቡት ኢትዮጵያ ዜግነት ያላቸው፤  በውድድሩ ዘመኑ በሀገር ውስጥ ሊግ ማለትም በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ፣ በከፍተኛ ሊግ ወይም በብሔራዊ ሊግ፣ በሌሎች ሀገሮች ሊግ ወይም በብሔዊ ቡድን በመጫወት ላይ የሚገኙ እንዲሁም በዓመቱ በብቃት እና በስፖርታዊ ጨዋነት አርአያ የሆኑ ብሏል፡፡  በምርጥ  አትሌት ዘርፍ ለመወዳደደር የሚችሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ዜግነት ያላቸው በውድድር ዘመኑ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በሚያዘጋጃቸው እንዲሁም በኢንተርናሽናል ውድድሮች በግል ወይም ሀገርን በመወከል ውጤታማ መሆን የቻሉ እና በዓመቱ በብቃት እና በስፖታዊ ጨዋታነቱ አርዓያ የሆኑት መሆናቸው አሳውቋል፡፡
የእጩዎች አመራረጥና ውጤት አሰጣጥ ባለፈበት ወራት ሂደት  በሁለቱም ፆታዎች የቀረቡት ተወዳዳሪዎች ከላይ በቀረቡት መስፈርቶች ተመዝነው በእያንዳንዱ ዘርፍ 10 /አስር/ ዕጩዎች በባለሙያዎች ሰብሰብ  እንዲቀርቡ መደረጉን በየዘርፉ ከተወከሉት አስር እጩዎች በባለሙያዎች ዳኝነት የተመረጡ ሶስት ሶስት ስፖርተኞች የኤ ኤም ኤስ ኮድ ተሰጥቷቸው በህዝቡ ድምጽ እንዲሰጣቸው ተደርጓል፡፡ ከዚያም ከየዘርፉ በህዝቡና በባለሙያዎች ድምጽ የተለያዩ የመጨረሻዎቹ አራት ስፖርተኞች የኢቢሲ ስፖርት ሽልማት አሸናፊ ሆነዋል፡ አጠቃላይ ውጤቱ 70 ከመቶ የሚሆነው በባለሙያዎች ድምጽ የሚሸፈን ሲሆን ቀሪውን 30 ከመቶ ደግሞ በኤስ ኤም ኤስ ከህዝቡ የሚገኘው ድምጽ እንደሆነ ነው የተገለፀው፡፡
የስነስርዓቱ ታዳሚዎች፤ የክብር እንግዶች ንግግር፣ አመጣጥ ተሳትፎ እና አለባበስ
በሽልማት ስነስርዓቱ ላይ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት፤ በኢቢሲ አስተዳደር ቦታ ያሉ ሰዎች ፤ የሚዲያ ባለሙያዎች፤ የቀድሞ ዘመን ስፖርተኞች፣ ታዋቂ ደጋፊዎች ዝነኛ ሰዎች ሌሎች የስፖርት ታዳሚዎች ተገኝተዋል፡፡ በእለቱ የሸራተን አዲስ ላሊበላ አዳራሽ ከ500 በላይ እንግዶችን አስተናግዷል ለማለት ይቻላል፡፡
የ2016 የዓለም ኮከብ አትሌት፤ የኦሎምፒክ እና የዓለም ሻምፒዮን አልማዝ አያና ከባለቤቷ እና አሰልጣኟ ሶሬሳ ፊዳ ጋር፤ የ5ሺ ሜትር የዓለም ሻምፒዮኑ ሙክታር ኢድሪስ፤ በማራቶን የኦሎምፒክ የብር ሜዳልያ ያለው ታምራት ቶላ፤ እጩ የሴት እግር ኳስ ተጨዋቾች፤ እጩ የወንድ እግር ኳስ ተጨዋቾች የስነስርዓቱን ሰዓት ጠብቀው ከመገኘታቸውም በላይ ደረጃውን የጠበቀ አለባበስ ፈፅመው ተገኝተዋል፡፡ የቀድሞ የእግር ኳስ አሰልጣኝ አስራት ኃይሌ፤ የቀድሞ የብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ፤ የቀድሞ የእግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት ዮሃንስ ሳህሌ፤ የረጅም ርቀት አሰልጣኝ ሻምበል ቶሎሳ ቆቱ፤ የስታድዬም ትሪቡን አስተናባሪ አቶ ተሾመ …ሰዓታቸውን ጠብቀው ለስነስርዓቱ ከተገኙት ታዳሚዎች የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
መንግስት ለሽልማት ስነስርዓቱ ትኩረት መስጠቱን ለመገንዘብ የቻላል፡፡ በክብር እንግዳነት ከመጡት የመንግስት ባለስልጣናት የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ የሆኑት የተከበሩ  አቶ ያለው አባተ እና የኢቢሲ ዋና ስራ ኣስፈፃሚ አቶ ስዩም መኮንን የመክፈቻ ንግግሮች አድርገዋል፡፡ ይህም የሽልማት ስነስርዓቱ ሳይቋረጥ በየዓመቱ ሊቀጥል እንደሚችል የሚያመለክት ነው፡፡ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ የሆኑት የተከበሩ አቶ ያለው አባተ ሲሆኑ ኢበሲ የሽልማት ስነስርአቱን በባለቤትነት ማዘጋጀቱን አድንቀው፤ “ዓለም የውድድር ናት ጊዜው የውድድር ዋናው ሆኖ መገኝት ለዚህም ደግሞ እናንተ ተገኝታችኋል” በማለት ተናግረዋል። የኢቢሲ ዋና ስራ ኣስፈፃሚ አቶ ስዩም መኮንን በበኩላቸው ሲናገሩ ‹‹ስለ ሽልማት ስነ ኢቢሲ እንደ ሚዲያ ተቋም መስራት ያለበትን ነገር ማከናወኑን ጠቅሰው፤ ተቋማቸው መሰል የሽልማት ስነስርዓቶን ደረጃቸውን ጠብቀው እንዲካሄዱ ለማነቃቃት መነሳቱን በመግለፅ እንደ ብሄራዊ ሚዲያነት የራሱን አሻራ ለመጣል እንዳዘጋጀው አስታውቀዋል፡፡ በሌላ በኩል ከመንግስት ኮምንኬሽን ዋና ፀሀፊ ከዶ/ር ነገሬ ሌንጮና ከወጣቶች ስፖርት ሚኒስተር ርስቱ ይርዳው ለአራቱ ምርጥ ስፖርተኞች በነፍስ ወከፍ የተበረከተውን የ75ሺ ብር በማበርከት ያደረጓቸው ተሳትፎዎችም ይጠቀሳሉ፡፡
የቀጥታ ስርጭቱ፤ የመድረኩ መሪዎች፤ የማጀቢያና የመዝናኛ ሙዚቃዎችና ዘጋቢ ፊልሞቹ
የሽልማት ስነስርዓቱ በኢቢሲ የስፖርት ጋዜጠኞች ሰላማዊት ደጀኔና ሙሉጌታ ክፍሌ በመድረክ ላይ በቅንጅት በሰሩት የመድረክ አጋፋሪነት የተመራ ሲሆን ከቀጥታ የቴሌቭዥን ስርጭቱ ጋር የሚጣጣም መስተንግዶ ሊሰሩበት ችለዋል፡፡ የስነስርዓቱን የተለያዩ ሂደቶች በሚገልፁበት ወቅት እንዲሁም ንግግር የሚያቀርቡ የክብር እንግዶች፤ ለሸላሚነት የተመረጡ ታላቅ የስፖርት ሰዎችን እንዲሁም ተሸላሚ ስፖርተኞችን ወደ መድረክ በመጋበዝ ማራኪ መስተንግዶ የስፖርት ጋዜጠኞቹ ከመስራታቸውም በላይ በአዳራሹ በተሰቀሉ ስክሪኖች በኢቢሲ የተዘጋጁ ጣቢያው ከተለያዩ ስፖርቶች ጋር ያለውን የታሪክ ትስስር የጋዜጠኞችን አስተዋፅኦ የሚያሳዩ አጫጭር ዘጋቢ ፊልሞች፤ በእግር ኳስ እና በአትሌቲክስ የቀረቡ 12 የመጨረሻ እጩዎች ስላሳለፉት የውድድር ዘመን፤ ስለሽልማት ስነስርዓቱ መጀመር፤ ስለ ወደፊት እቅዳቸው ምላሽ የሚሰጡባቸውን አጫጭር ፊልሞች በማቅረብ እና በመምራት ተሳክቶላቸዋል፡፡
የሽልማት ስነስርዓቱን በማጀቢያ ሙዚቃ እና በልዩ የመድረክ ላይ የሙዚቃ ስራዎች ለማድመቅ መሞከሩ ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡ በተለይ በስነስርዓቱ የተለያዩ ሂደቶች እንደመግቢያ እንደመሸጋገርያ እንዲሁም እንደማጀቢያ ሆኖ ሲቀርብ የነበረው ሙዚቃ በኢቢሲ በኩል ሽልማቱ ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆን የተደረገውን ጥረት የሚያመልክት ነው፡፡ በሌላ በኩል የክብር እንግዶች ካሰሙት ንግግር በኋላ እና በእግር ኳስ እና በአትሌቲክስ ምርጥ ስፖርተኞች የሽልማት ሂደቶች ጣልቃ ጋሽ ኣበራ ሞላ (ስለሺ ደምሴ) በክራሩ በመታጀብ ያቀረባቸው ሙዚቃዎችም ለቀጥታ ስርጭቱ የሚያምር ድባብ ከሙዚቃ ዝግጅቶች ጋር በማስተሳሰር ለመፍጠር እንደሚቻል ማረጋገጫ ሆኗል፡፡   
በቀረቡት ዘጋቢ ፊልሞች ላይ  በተለይ የአሸናፊዎች ዝርዝር የህይወት  ታሪክ፣ በየፌደሬሽኖቹ መዝገብ እና ክትትል ያሉ ወቅታዊ ነባር መረጃዎች፤ አጠቃላይ አሃዛዊ መረጃ እና ሌሎች እውነታዎች ተሟልተው መቅረብ ነበረባቸው፡፡ እነዚህ ሙሉ መረጃዎች በፊልሞቹ ላይ ብዙም ባይካተቱም በስነስርዓቱ ለተገኙ ታዳሚዎች በተለያዩ ህትመቶች እንዲሁም በዜና ማሰረጫ መረቦች ለመላው ዓለም የሚሰራጩበት አሰራር መተግበር ነበረበት፡፡
በአትሌቲክስ የሽልማት ዘርፍ ላይ ስለእጩ ተወዳዳሪዎች በዘጋቢ እና ቃለምልልስ ታጅበው በተዘጋጁት ፊልሞች  ስለእጩዎች የቀረቡ መረጃዎች የተወሰነ ክፍተት አለባቸው፡፡ ሙሉ ሙሉ ያተኮሩት ባለፈው የውድድር ዘመን ላይ ብቻ መሆኑ ተገቢ አይደለም፡፡ በተለይ የአሸናፊ አትሌቶች ሙሉ የሩጫ ዘመን ታሪክ፤ ስኬት፤ ሪከርዶች፤ እና ዝርዝር የውጤት መረጃዎች በዘጋቢ ፊልሞች፤ በህትመቶች እና በመረጃ መረብ ማቅረቡ እንደሚያስፈልግ መታወቅ ነበረበት፡፡
በሁለቱ ፌደሬሽኖች ላይ ቅሬታ ተፈጥሯል
በሽልማት ስነስርዓቱ ላይ ከተገኙት አብዛኛዎቹ የኢቢሲ ሰራተኞችና የእግር ኳሱ ቤተሰብ ነው ለማለት ይቻላል፡፡ በአትሌቲክስ ዙርያ ብዙ የተሰበሰበ አልነበረም፡፡ በተለይ ከፍተኛ ክብርና ዝና ያላቸው ታዋቂ አትሌቶች አለመኖራቸው ያልተጠበቀ ነው፡፡ በተለይ የስፖርቱ ባለድርሻ አካላት ናቸው የሚባሉት የፌዴሬሽን ፕሬዝዳንቶች አለመገኘት ስነስርዓቱ ሊኖረው የሚገባውን ሞገስ አሳጥቶታል፡፡ የኢትየጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኃይሌ ገ/ሥላሴ፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ጁነዲን ባሻ፣ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዝዳንት ዶ/ር አሸብር ወ/ጊዮርጊስ ለእንግድነት ጥሪ ተደርጎላቸው ሳይገኙ ቀርተዋል፡፡
የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ኃይሌ ገብረስላሴ “የኢቢሲ የአመቱ ምርጥ ስፖርተኛ ሽልማት /EBC Sport Award of the Year/” ላይ ከሸለሚዎቹ አንዱ ይሆናል ተብሎ ቢጠበቅም ባለቀ ሰዓት ፕሮግራሙን እንደሰረዘ ለማወቅ ተችሏል፡፡ የሽልማት ስነስርዓቱ በተካሄደበት እለት የጎረቤት ለቅሶ ስላጋጠመው ነበር። በሽልማት ስነስርዓቱ አጠቃላይ ሂደት የአትሌቲክስ ፌደሬሽን ቅር መሰኘቱንና ማዘኑን ለስፖርት አድማስ የተናገረው ፕሬዝዳንቱ ኃይሌ ገብረስላሴ፤ የአንድ አገር ብሄራዊ ሚዲያ የዓመቱን ኮከቦች ለመምረጥ የሚችልበት አቅምና ብቃት የለውም›› በማለት ይወቅሳል፡፡ ‹‹እነደፌደሬሽን የአትሌቶች የውጤት ታሪክ፤ የዲሲፕሊን ሬከርድ፤ የውድድር ዘመን ተሳትፎ እና ውጤት ስፖርቱን በበላይነት በሚመራው አካል የሚገኝ መሆኑን ኢበሲ መገንዘብ ነበረበት፡፡ በምርጫ ማወዳደርያ መስፈርቶቹ ከዚያ በባለሙያዎች የመለኪያ አሰራሮች የጎላ ሚና መጫወት ሲገባን እድሉ አልተሰጠንም፡፡ ይህ ደግሞ ሽልማቱ ሊሰጠው የሚገባውን ክብር እና ተቀባይነት እንዲጎድል አድርጓል›› በማለት ኃይሌ ገብረስላሴ ለስፖርት አድማስ አስተያየት ሰጥቷል፡፡
 በተያያዘ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንትም ለሀ-20 ውድድር ከከተማ ውጭ ስለነበሩ ሊገኙ አልቻሉም።  በሽልማት ስነስርዓቱ ዙርያ ከስፖርት አድማስ ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ ጁነዲን፤ ተጨዋቾች በመሸለማቸው የምንደሰት ቢሆንም ኢቢሲ ገና ከጅምሩ እግር ኳስ ፌደሬሽኑን ሳያሳውቅና አስፈላጊውን ምክክር ሳያደርግ መስራቱ አሳዝኖናል ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን በበላይነት በሚመራው ስፖርት ዙርያ የሚካሄዱ ማናቸውም ሁኔታዎች ተገቢውን እውቅና ሊሰጣቸው ያስፈልጋል ያሉት ፕሬዝዳንቱ አቶ ጁነዲን ባሻ፤ ለኮከብ ተጨዋቾች የሽልማት ስነስርዓት ሲካሄድ ፌደሬሽኑ በምርጫ ማወዳደርያ መስፈርቶቹ፤ በሽልማት ዘርፎቹና በአጠቃላይ ሂደቱ ላይ ግንባር ቀደም አስተዋፅኦ ማረግ ነበረበት ብለው ኢቢሲ የሽልማት ስነስርዓቱ በሚካሄድበት አጠቃላይ ሁኔታ የጋራ መግባባት አለመፍጠሩ ከባድ ጥፋት ነው በማለት ተችተውታል። ኢቢሲ በሽልማት ምርጫው ላይ ባለሙያዎችን ያሳተፈበት መንገድ በፌደሬሽን በኩል መኖር ያለበትን ፈቃድ የጣሰ ሲሆን  በኤስ ኤም ኤስ ድምፅ በመሰብሰብ ገቢ ለማግኘት መንቀሳቀሱ ልክ እንዳልነበረም የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ ፕሬዝዳንት ተናግረዋል፡፡  በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዝዳንት ዶ/ር አሸብር  ወ/ጊዮርጊስ ግልፅ ባልሆነ  ምክንያት በሽልማት ስንስርዓቱ ላይ አልተገኙም፡፡
ታላላቆቹ የስፖርት አመራሮች  ምንም እንኳን ኢቢሲ የተሟላ ብቃት ሊኖረው በማይችል የሽልማት ስነስርዓት መንቀሳቀሱ ባያስደስታቸውም በብሄራዊ ደረጃ ይህን የመሰለ ለስፖርተኞች ክብር ለመስጠት ለመጀመርያ ጊዜ የተካሄደውን ሽልማት በማክበር ጥሪቸውን ተቀብለው በመገኘት ጅምር ጥረቶች እንዲጠናከሩ ማበረታታት ነበረባቸው፡፡  ከስፖርት አመራሮች ባሻገር የአትሌቶች ማህበር፤ የተለያዩ ስፖርቶች ማህበራ ተወካዮች፣ የተለያዩ ፌደሬሽኖች ስራ አስፈፃሚዎች፤ የቀድሞ እና የአሁን ዘመን እውቅ አትሌቶች እና ሌሎች የስፖርት ባለሙያዎች በብዛት መከሰታቸው አስፈላጊ ነበር፡፡
ኢቢሲ የኢትዮጵያ ስፖርት እንዲያድግ ሰፊ ሚና መጫወቱን ባመለከተበት የሽልማት ስነስርዓቱ ላይ የኢቢሲ ዋና  ስራ አስፈፃሚ አቶ ስዩም መኮንን የሽልማት ስነስርዓቱ በቋሚነት እንደሚካሄድና በየዓመቱ እያደገ እንደሚቀጥል የተናገሩ ቢሆንም በሁለቱ ፌደሬሽኖች ለተፈጠሩ ቅሬታዎች መፍትሄ ማፈላለግ አለባቸው። ኢቢሲ በሚቀጥሉት ዓመታት የስፖርቱ ባለድርሻ አካላትን በሚመለከታቸው ጉዳይ በማሳተፍ መስራት ተገቢ መሆኑን ሊገነዘብ ይገባል፡፡ በኮከብ ስፖርተኞች ዓመታዊ ሽልማቱም ብቃትን መለካት የሚችሉ ባለድርሻ አካላትን የሚያስፈልገውን ጥረት ሁሉ አድርጎ በአጋርነት በማሳተፍ መንቀሳቀስ ይኖርበታል፡፡  
የመጀመርያው አሸናፊዎች፤ ሸላሚዎች እና ሽልማታቸው
በሽልማት ስነስርዓቱ እለት በእግር ኳስ እና በአትሌቲክስ ስፖርት በሁለቱም ፆታዎች ለመጨረሻ እጩነት ከቀረቡት 12 እጩዎች መካከል 9 ስፖርተኞች በስፍራው ተገኝተዋል። የቀሩት በቱርክ ለሙከራ የተጓዘችው ሎዛ አበራ፤ ለቺካጎ ማራቶን አሜሪካ የምትገኘው ጥሩነሽ ዲባባ እንዲሁም ለምን በስነስርዓቱ እንዳልተገኘ በይፋ ያልገለፀው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንና የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ አጥቂ ሳላዲን ሰኢድ ነበሩ፡፡
የሽልማት ስነስርዓቱ በእግር ኳስ በሁለቱም ፆታዎች የቀረቡ እጩዎችን በማስቀደም የተጀመረ ሲሆን በኢቢሲ የአመቱ ምርጥ እግር ኳስ ተጫዋች ዘርፍ በሴቶች የመጨረሻ እጩዎች ሆነው የቀረቡት ሶስቱም ከደደቢት የእግር ኳስ ክለብ ነበር፡፡ ሶስቱም የደደቢት እግር ኳስ ክለብ በ2009 ዓዓም የውድድር ዘመን የፕሪሚዬር ሊግ እና የጥሎ ማለፍ ሁለት ዋንጫዎችን ሲያስመዘግብ ከፍተኛ ሚና ነበራቸው፡፡ የአመቱ የኢቢሲ ምርጥ ሴት እግር ኳስ ተጨዋች ሆና ያሸነፈችው የደደቢቷ አጥቂ ሎዛ አበራ ናት፡፡ የሎዛ አበራ አሸናፊነት ያወጀችውና ለአሸናፊዋ ሎዛ አበራ ሽልማቱን ያበረከተችው ደግሞ  በለጥሽ ገ/ማርያም ናት፡፡ ሎዛ ለሙከራ ጊዜ ሀገር ዉጭ በመሆኗ ሽልማቷን በወንድሟ በኩል የተቀበለች ሲሆን በ2009 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሜርሊግ በ33 ግቦች ኮከብ ግብ አግቢ ሆና እንድጨረሰች ይታወቃል፡፡
በኢቢሲ የአመቱ ምርጥ እግር ኳስ ተጫዋች ዘርፍ በሴቶች የመጨረሻ እጩዎች ሆነው የቀረቡት የቅዱስ ጊዮርጊሶቹ አጥቂው ሳላዲን ሰኢድ እና ተከላካዩ አስቻለው ታመነ እንዲሁም የደደቢቱ አጥቂ ጌታነህ ከበደ ነበሩ፡፡ የአመቱ የኢቢሲ ምርጥ ወንድ እግር ኳስ ተጨዋች ሆኖ ያሸነፈው የቅዱስ ጊዮርጊስ እና የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የመሃል ተከላካይ አስቻለው ታመነ ነው። አሸናፊነቱን በማወጅ ሽልማቱን ያበረከተው ደግሞ ቀድሞ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ተጨዋች የነበረው ንጉሴ ገብሬ ነው።
አስቻለው ታመነ ሽልማቱን ከተቀበለ በኋላ በሰጠው አስተያት ሌላኛውን እጩ ጌታነህ ከበደ እና የቀድሞ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ አመስግኖ  ሽልማቱ ስፖርተኛውን ያነሳሳል ሲል ተናግሯል፡፡ ጌታነህ ከበደ በበኩሉ “ስፖርት ገንዘብ የሚገኝበት ስራ ነው፡፡ ሽልማት ደግሞ ለስፖርተኛው ሞራል ይሰጣል። በምርጫው መላው የኢትዮጵያ ህዝብ መሳተፉ ያስደስታል ብሏል፡፡ በአመቱ የኢቢሲ ምርጥ አትሌት የሽልማት ዘርፍ በወንዶች ምድብ የመጨረሻ እጩ ሆነው የቀረቡት ሙክታር ኢድሪስ፤ ታምራት ቶላ ነበሩ፡፡ የአመቱ የኢቢሲ ምርጥ ወንድ አትሌት ሆኖ ያሸነፈው ሙክታ ኢድሪስ ሲሆን በአገር ኣቋራጭና በማራቶን ስኬታማ አትሌት የሆነችው መሰለች መልካሙ ነበረች፡፡ ሙክታር ኢድሪስ ሽልማቱን ከተቀበለ በኋላ ኢቢሲ ለኢትዮጵያ ስፖርት ለሚያደርገው አስተዋፅኦ ምስጋናውን ገልፆ ተመልካች በስፖርት መስመር ገብቶ  ድጋፍ እንዲያደርግ ማስቻሉን አድንቆታል፡፡ በአመቱ የኢቢሲ ምርጥ አትሌት የሽልማት ዘርፍ በሴቶች የመጨረሻ እጩ ሆኖ የቀረቡት አልማዝ አያና ሰንበሬ ተፈሪ እና ጥሩነሽ ዲባባ ነበሩ፡፡ አሸናፊ የሆነችው አልማዝ አያና ስትሆን አሸናፊነቷን በማወጅ ሽልማቱን ያበረከተው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የማራቶን ዋና አሰልጣኝ እና የቀድሞ አትሌት አበበ መኮንን ነበር፡፡
በእግር ኳስ እና በአትሌቲክስ የኢቢሲ አመቱ ምርጥ  በመሆን ያሸነፉት አራቱ ስፖርተኞች በመጀመርያ በመድረኩ ላይ  የተሸለሙት አናቱ ላይ የኮከብ ምልክት ያለበት ከክሪስታል የተሰራ ልዩ ዋንጫ ሲሆን ይህ ሽልማት ትኩረት ተደርጎበት ደረጃውን በጠበቀ ሁኔታ እንዲሰራ መደረጉን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ከክሪስታል ዋንጫዎቹ ባሻገር አራቱ ምርጥ ስፖርተኞች እያንዳንዳቸው 75 ሺህ ብር ሽልማት በክብር እንግዳነት ከመጡት ከመንግስት ኮምንኬሽን ዋና ፀሀፊ ከዶ/ር ነገሬ ሌንጮና ከወጣቶች ስፖርት ሚኒስተር ርስቱ ይርዳው እጅ ተቀብለዋል። የኢትዮጵያ ወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትር አቶ ርስቱ ይርዳው በሽልማት ስነስርዓቱ ማጠቃለያ ላይ ባሰሙት ንግግር “ኢቢሲ በአገራችን የውድድር መንፈስ እንዲጠናከር ማስቻሉን አድንቀው የሽልማት ስነስርዓቱ ትልቅ መነቃቃት እንደሚፈጥር አስገንዝበዋል፡፡
የፕሮሞሽን ማነስ፤ ሰዓት አለመከበር፤ የባለ ድርሻ አካላት አለመገኘት
ለመጀመርያ ጊዜ ለመካሄድ የበቃው የኢቢሲ የዓመቱ ምርጥ ስፖርተኞች የሽልማት ስነስርዓት የሚመለከታቸውን ባለድረሻ አካላት በሃላፊነት አሳትፎ በአጋርነት ሊሰራ አለመቻሉ ትልቁ ክፍተት ሲሆን የምርጫ መስፈርቶች የሚያሳምኑ እና በበቂ ሁኔታ ብቃትን ለመለካት የማያስችሉ በመሆናቸው፤ አሸናፊዎችን የሚለዩባቸው የምርጫው ውጤቶች በይፋ አለመገለፃቸው፤ በስነስርዓቱ ላይ በቀረቡት ዘጋቢ ፊልሞች ተገቢ መረጃዎች አለመሟላት ከዚያም የፕሮሞሽን ማነስ፤ ሰዓት አለመከበር፤ የባለ ድርሻ አካላት አለመገኘት ዋናዎቹ የስነስርዓቱን ድምቀት እና አጀማመር ያደበዘዙ ሁኔታዎች ናቸው፡፡  
በአጠቃላይ ግን የዓመቱ ምርጥና ኮከብ ስፖርተኞችን ደረጃውን በጠበቀ ስነስርዓት በተለይ ባለድርሻ አካላትን በጋራ መግባባት አሳትፎ እና በትክክለኛ መንገድ ብቃቶችን ለክቶ በማወዳደር መሸለም ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች ይኖሩታል፡፡ በየጊዜው የላቀ ውጤት ለሚያስመዘግቡ ስፖርተኞች ታላቅነት እውቅና የሚሰጥበት፤ የስፖርት ቤተሰቡ ለምርጥ እና ኮከብ ስፖርተኞች አድናቆቱን፤ ግምቱንና ድጋፉን በመስጠት ተሳትፎ ማድረግ የሚችልበት፤ የሚዲያ ተቋማት በተለይ የብሮድካስት ተቋማት ማራኪ ዝግጅት እና የቀጥታ ስርጭት በመስራት ገቢ የሚያገኙበት እና የስፖርት ቤተሰቡን የሚያዝናኑበት በመንግስት እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት እውቅና የሚያገኙበት እንዲሁም የስፖርትን መስክ ስፖንሰር የሚያደርጉ ኩባንያዎች ገፅታቸውን የሚገነቡበት መድረክ ይሆናል።  አዳዲስ እና ተተኪ አትሌቶች ተመክሮ የሚያገኙበት እና ወደፊት የተሻለ በመስራት ለመሸለም የሚጓጉበት፤ ተሸላሚ ስፖርተኞች የወከሉትን ክለብ፤ አገር እንዲሁም የስፖርት መስክ በማስተዋወቅ የሚሰሩበት እና በስፖርቱ ዓለም የሚኖራቸውን ዋጋ በሜዳ ውስጥም ከሜዳ ውጭ የሚያሳድጉበት እና የሚበረታቱበት ይሆናል፡፡ 

Read 1377 times