Print this page
Monday, 25 September 2017 12:03

“ዓይነ ስውሩ እና ውሻው”

Written by  ዮፍታሄ ካሳ
Rate this item
(56 votes)

    ጓደኛዬ ሚናስ፣ እኔ በሰጠሁት ሀሳብ መነሻነት የፃፈው ልብ ወለድ እንደዚህ ከዝና ማማ ላይ ያወጣዋል ብዬ አልገመትኩም ነበር፡፡ ዐይኔ እያየ ዝነኛ ሆነ! ሚናስ “ባለቅኔ” ተባለ፡፡
እንደ ቀልድ ነበር ሀሳቡን የሰጠሁት፡፡ የማወራው ሳጣ የነገርኩትን ሀሳብ እሱ ሆዬ ቀልቦ፣ … በየሬዲዮ ጣቢያው የሚተረክ ዝነኛ ታሪክ ጽፎ ቁጭ አይልም? እየቆየ ሲሔድ ከነከነኝ፡፡ “ምነው ጽሁፉን እኔው በፃፍኩት” የሚል ሀሳብ ሸንቆጥ ያደርገኝ ጀመር፡፡ የሚናስ ዝና እየገነነ ሲሔድ ደሞ፣ “እንዴት የመነሻ ሀሳቡን እንደሰጠሁት አልገለፀም?” የሚል ሀሳብ ሰቅዞ ያዘኝ፡፡ በጽሁፉ ላይ ባይገልፅ እንኳ በሚሰጣቸው ቃለ - መጠይቆች ላይ፣ ሀሳቡን ያፈለቅሁት እኔ እንደሆንኩ መግለጽ ነበረበት፡፡ ዝናውን መካፈል ባለመቻሌ ተናደድኩ፡፡ የጽሁፍ ድርቅ ባጠቃው ዘመን፣ የሱ ታሪክ በጋዜጣ ታትሞ በሬዲዮ ለመተረክ በቃ፣ … ከአድማስ እስከ አድማስ፣ እንደ ሰንደቅ ዐላማ ከፍ ብሎ የሚታይ ሰው ሆነ - ሚናስ!
ሬዲዮ ስከፍት የሚናስ ልቦለድ ታሪክ እየተተረከ አገኛለሁ፣ ጋዜጦች ላይ ስለ ታሪኩ መዋቅር፣ ስለተከተለው ዘይቤ፣ ስለ ጭብጡ … ወዘተ … ትንተና ይፃፋል፡፡ ቅናት ውስጤን ገዘገዘው፡፡ ሮጬ የማላመልጠው ቅናት! ሀሳቡን እንዴት እንደሰጠሁት ሳስብ ሳቄ ይመጣል፡፡ ያን አይነት ቀሽም ሀሳብ ይዞ፣ ዝነኛ ታሪክ ለመፃፍ መብቃቱ አስደማሚ ነው፡፡ ሀሳቡን የሰጠሁበት አስገራሚ ሁኔታ አይረሳኝም፡፡
አንድ ቅዳሜ ከሰዓት፣ ከሚናስ ጋር ተገናኝተን እያወራን ነበር፡፡ ሚናስ ቅርጫት ውስጥ እንደተጣለ ኩታ፣ እጥፍ ኩርምት ብሎ ነው የተቀመጠው፡፡ የተቀዛቀዘ መንፈስ ውስጥ ነበር፡፡ መንፈሱ ይጋባል፡፡
“ሀገር እየታመሰች፣ ጩኸት በዝቶ፣ መንገዱ በወጣቶቻችን ደም ተሞልቶ፣ እናቶች ዐይን ላይ የእንባ ዘለላ እየታየ እንዴት መጻፍ ይቻላል?” አለ፤ ቅዝዝ ባለ ስሜት፡፡
ለነገሩ እሱ ብቻ ሳይሆን ዘመኑም የሚደብት ነገር ነበረው፡፡ 1969 ዓ.ም እንዲያልፍ እንዳልተመኘን፣ 1970 ዓ.ም ደግሞ የመአት ዐመት ሆኖ፣ ከምኔው በተገላገልነው እያልን ነበር፡፡ የፖለቲካ መጋጋል አይሎ፣ ወጣቶች እዚህና እዚያ ተደፍተው ሲታይ፣ እንኳን እኛ ጽሁፍን መተዳደሪያችን ያደረግን ሰዎች፣ ማንም ላይ ቢሆን ዘመኑ ቅዝቃዜውን የማጋባት ከፍተኛ ኃይል ነበረው፡፡ ቀይ ሽብርና ነጭ ሽብር በከተማው የፍርሀት ቋፈን ለቆ ነበር፡፡
“የኪነት ሰው እኮ ቆዳውን ገልብጦ የለበሰ ነው። ስሜተ - ስስ ነን፡፡ ሀገር እየተረበሸ ሙሾ እንጂ እዮሀ የሚል ዜማ ልናወጣ አንችልም!” እኔ ለተፈጠረው ነገር ሁሉ ተጠያቂ እንደሆንኩ ዓይነት ነበር ሚናስ እየጮኸ የሚያናግረኝ፡፡
እኔም መጻፍ አቅቶኝ ነበር፡፡ እሱም መጻፍ አቅቶታል። እንኳን አጽመ-ታሪክ አውጥተን፣ ጭብጥ አስልተን፣ መቼት ተልመን ልቦለድ ልንጽፍ፣ የትርጉም ሥራ እንኳን መስራት አቅቶን ነበር፡፡ በሀገሪቱ ከፍተኛ ስርጭት በነበራቸው የመንግሥት ጋዜጦች ላይ የኪነ ጥበብ አምድ ፀሐፊች ነበርን፡፡ መፃፍ አለመቻል አደጋ አለው፡፡ መጻፍ ስራችን ነው፡፡ ለመኖር የምንሰራው፡፡ ህሊናችን ግን እጃችንን ማዘዝ አቅቶት ተቸገርን፡፡
“መፃፍ አቅቶኛል፡፡ ሁለት ሳምንት ለጋዜጣው ጽሁፍ አልሰጠሁም፡፡ የፕሬስ መምሪያ ኃላፊው ጠርቶ ምን እንዳለኝ ታውቃህ?” ሚናስ ደሙ ተቆጥቶ፣ ስለ መምሪያ ኃላፊው ይነግረኝ ጀመር፡፡
“‹ከፀረ-አብዮተኞች ጋር አባሪ ተባባሪ ከሆንክ ግልፁን ንገረኝና ሥራህን ልቀቅ!› ብሎ አስፈራርቶ፤ አንድ ጽሁፍ በዚህ ሳምንት እንዳመጣ አስጠነቀቀኝ። ካላመጣሁ አብዮታዊነቴ ጥያቄ ውስጥ እንደሚገባ ነግሮኛል” ሚናስ ተጨንቆ ነበር፡፡
“አንድ የሆነ ነገር ጽፈህ ለምን አትሰጠውም?”
“ምን ልፃፍ?”
“በቃ የሆነ ነገር ፃፍ! ያለዚያ እነዚህን ሰዎች ታውቃቸዋለህ አይደል …”
ሁለታችንም ላይ ፍርሀት ነግሶብን ነበር፡፡ መፃፍ እንዳለብን እንጂ ምን እንደምንፅፍ አናውቅም፡፡
“ስለ ምን ልጻፍ? በዚህ ወቅት ስለ ፍርሃት ነው መጻፍ የምችለው፡፡ ስሜቴ ያ ነው፡፡ ስለ ምንም ነገር ልፅፍ አልቻልኩም! አንተ ደግሞ ዝም ብለህ ፃፍ ትላለህ!” በሰጠሁት አስተያየት ተናዶብኝ ነበር፡፡ ላረጋጋው የሆነ ነገር መናገር ፈለግሁ፡፡
“ዝም ብሎ አንድ ነገር! ለምሳሌ….” ምን ምሳሌ እንደምሰጠው ሳላውቅ ነበር፤ ለምሳሌ ብዬ የጀመርኩት። ሚናስ አፍጥጦ እያየኝ፣ የምለውን ይጠባበቃል፡፡
“ለምሳሌ … ለምሳሌ …” የምናገረው ነገር ጠፍቶብኝ፣ በአይኖቼ መቃበዝ ጀመርኩ፡፡
ሚናስ የምሰጠውን ምሳሌ እየጠበቀ ነበር፡፡
የተቀመጥነው መንገድ ዳር ካለ፣ ካፊቴሪያ በረንዳ ላይ ነው፡፡ አይኖቼ ከመንገዱ ባሻገር ቃበዙ፡፡ አንድ ነገር ቀልቤን ሳበው፡፡ አንድ ሽማግሌ ጎዳናውን እያቋረጡ ነበር። ዐይነ - ስውር ናቸው፡፡ ሰው ቀረብ ሲላቸው፣ ለእርጥባን እጃቸውን ይዘረጋሉ፡፡ የሚመራቸው ውሻቸው ነው፡፡ ከአንገቱ ላይ የታሰረውን ገመድ ይዘው ይከተሉታል፡፡
“እኮ ስለ ምን?” ሚናስ ትዕግስት ባጣ ሁኔታ ጠየቀኝ።
“ስለ አንድ ሽማግሌና ስለ አንድ ውሻ ለምን አትፅፍም?”
“ምን?!” አለ፤ ሚናስ ባለማመን፡፡
“ስለ አንድ ሽማግሌና ስለ ውሻ!” አስረግጬ ነገርኩት። ደግነቱ ጀርባውን ለመንገዱ ሰጥቶ ስለተቀመጠ አያያቸውም፡፡
“አብደሃል? ስለ አንድ ሽማግሌና ስለ ውሻ ምንድነው የምፅፈው?”
ዝም ብዬ ከአፌ ላይ ያመጣሁት እንደሆነ ጠርጥሯል። ትንሽ ንዴት ቢጤ ተሰማኝ፡፡
“ምን ነካህ ከምሬ እኮ ነው! ‹ሽማግሌው እና ባህሩ› የሚለውን የሄሚንግዌይ ዝነኛ ሥራ ታስታውሳለህ?”
አንገቱን በአዎንታ ነቀነቀ፡፡
“እኮ ስለ አንድ ሽማግሌና ስለ አንድ ውሻ … ምን?!”
“ለምሳሌ … ለምሳሌ …”
አፌ ተንተባተበ፡፡ ሚናስ “በል ተናገራት!” በሚል ስሜት አፍጦብኛል፡፡
“ለምሳሌ ሽማግሌው የሚመሩት በውሻቸው ነው ...”
“ምንም ሴራ የሌለው ታሪክ ነው!” ሚናስ በብሽቀት ጮኸብኝ፡፡ “በእንቶ ፈንቶ ወሬ፣ ጊዜዬን ታባክናለህ!” በብሽቀት አማረረ፡፡
“በቃ አንድ ታሪክ … ሽማግሌው በልጅነታቸው ያላቸውን ነገር ሁሉ አሟጠው፣ ለልጆቻቸውና ለዘመዶቻቸው ሰጥተዋል፡፡ በደከሙበት ጊዜ ግን እነዚያ ሲረዷቸው የነበሩ ቤተሰቦቻቸው፤ የራሳቸውን ኑሮ ይዘው፣ እሳቸውን ዞር ብሎ የሚያይ፣ የሚረዳ ጠፋ። ዐይኖቻቸው በእርጅና ደክሞ ማየት ተሳናቸው። ጉልበታቸው ዝሎ መራመድ አቃታቸው፡፡ የሚበሉት አጡ፡፡ መንገድ ወጥተው እርጥባን እንዳይለምኑ፣ ማን መርቶ ይውሰዳቸው፡፡ በቤታቸው ያሳደጉት ውሻ ብቻ ነበር የቀራቸው፡፡ እሱን መሪ አድርገው ወደ መንገድ ወጡ፡፡  ውሻቸው ደረሰላቸው፡፡” ምን እንደማወራ ጠፍቶብኝ፣ በግርታ ሚናስን አየሁት፡፡ አፍጥጦ እየሰማኝ ነበር፡፡
“ከዛስ?”
“ከዛማ ለጥቂት ጊዜ እንዲህ እንደቆዩ … ውሻው በማዘጋጃ ቤት ይገደልባቸዋል፡፡ አቤት ያን ቀን ያነቡት እንባ! ሽማግሌው እየዞሩ እርጥባን የሚለምኑበት ቦታ የሚያደርሳቸው ያጣሉ፡፡ ርሀብ ያጎሳቁላቸዋል፡፡ አንድ ቀን በተኙበት ያሸልባቸዋል …”
“የታሪኩ ጭብጥ ምንድንነው?” ሚናስ አቋረጠኝ
“የሰብአዊነት ተቃርኖ ነዋ፡፡ ሰብአዊ ስንል ሰዋዊ የሆነ መልካም ባህሪ ማለታችን ነው፡፡ አውሬነት ወይም ሳቬጅ ስንል ደሞ ከሰውነት የወጣ እንስሳዊነት ማለታችን ነው፡፡ ግን አስበው … በዚህ ውሻ ውስጥ የምናገኘውን መልካምነት፡፡ የጥሩ ምግባር ሚዛን ያደረግነው ሰብአዊነት፤ በሽማግሌው ዘመዶች አፈር ድሜ ሲገባ፣ ይኼ እንስሳ፣ ይኼ ውሻ ግን የጥሩነት መለኪያን ገለበጠው፡፡ …”
ሚናስ ጆሮውን አቁሞ እየሰማኝ ነበር፡፡ በማከብረው ጓደኛዬ ፊት አንሼ ላለመታየት፣ ጭብጡን ራሴን እስኪገርመኝ ድረስ አከረርኩት፡፡
“…ህብረተሰባችን ለውሻ ያለውን አመለካከት ታውቀዋለህ፡፡ ታማኝ አገልጋዩን ውሻን፣ በተገላቢጦሽ የስድቡ መገለጫ ነው የሚያደርገው፡፡ ‹እንደ ውሻ ጭራህን አትቁላ!›፣ ‹እንደ ውሻ አትጩህ› ይልሀል … ውሻን የአድር ባይነትና የከንቱ ጩኸት ተምሳሌት አድርጎት፡፡ ‹ቤተ ክርስቲያን የገባች ውሻ› ማለት የተደናበረች ማለት ነው፡፡ በሰው ልጆች ታሪክ እንደ ውሻ የተበደለ ፍጡር የለም! ለፈረስ ያዜምነውን ያህል፣ ለበሬ ያዜምነውን ያህል … ለውሻ ምን አድርገናል? በራችንን በጠበቀ፣ መንገድ በመራን፣ ባጫወተን … የሱን ውለታ ግን ከፍለን አልጨረስንም …” ሳላውቀው እንባ ተናንቆኝ ነበር፡፡
ሚናስ ከወንበሩ ተነሳ፡፡ አላናገረኝም፡፡ “የአብርሆት ቅጽበት” ይለዋል፤ እንዲህ ያለውን ጊዜ፡፡ መፃፍ አሰኝቶታል ማለት ነው፡፡ ያን ጊዜ ወረቀት ፍለጋ አይኖቹ ይቃብዛሉ፡፡ ያን ጊዜ ፀጥታ ፍለጋ ከሰው ተለይቶ ይሸመጥጣል፡፡ አእምሮው ውስጥ ያጋተው ሀሳብ ድንገት እንዳያፈተልክ የሰጋ ይመስል ሰው አያናግርም። አሁንም ተነስቶ ሹልክ አለ፡፡ ሀሳቡን ሊጽፈው እንደሆነ አውቄያለሁ፡፡ እየፈጠነ ሲሄድ ከኋላው አየሁት፡፡ ኩስስ ያለ፣ በሰው ዐይን የማይሞላ ነው ሚናስ፡፡ ሽማግሌውና ውሻውን አልፏቸው ሲሔድ እንኳ አላስተዋላቸውም ነበር፡፡
በሳምንቱ ቅዳሜ ጠዋት “ሽማግሌውና ውሻው” የሚል ድርሰት የፕሬስ መምሪያው በሚያሳትመው ጋዜጣ ላይ ታትሞ አየሁ፡፡ አንድ ሽማግሌ በውሻ እየተመሩ ሲሔዱም የሚያሳይ የካርቱን ስዕል አብሮት አለ፡፡ የነገርኩትን ታሪክ አሳድጎ፣ በተለመደው ግሩም የቋንቋ ክህሎቱ ጽፎታል፡፡ ገረመኝ! የዛ ቀን ማታ የፕሬስ መምሪያው በስልክ ተጨናነቀ፡፡ አንባቢዎች ጽሁፉን ወደውት ነበር፡፡ “ሚናስ! ሚናስ! ሚናስ!” የማይል አልነበረም፡፡
ሁሉ ነገር አልፎ፣ ሰኞ ወደ ሥራ ስንገባ፣ የፕሬስ መምሪያ ኃላፊው በሰራተኞች ፊት ጠርቶ አመሰገነው። እንዲህ ዓይነት ሥራ በቀጣይም እንዲሰራ አበረታቶ፣ የአብዮቱ ወገንተኛ መሆኑን አዳንቆ ነገረው፡፡
“ሽማግሌውን የገለጽክበት ሁኔታ በጣም አንጀት የሚበላ ነው! የሰራተኛው መደብ እንዲህ ጉልበቱ ተበዝብዞ፣ እንደ አሮጌ ቁና የትም እንዲጣል መደረጉ እንዳንገበገበህ በግልጽ ነው ያሳየኸው፡፡ ሽማግሌው በስተርጅናቸው መጦር ሲገባቸው፣ ዙሪያቸውን የከበቧቸው በዝባዦች፣ ሀብታቸውን መዝብረው ተሰወሩ፡፡ በመጨረሻም በውሻ እየተመሩ መለመን ያዙ…” የመምሪያ ኃላፊው በሽማግሌው ሁኔታ ተነክቶ ነው መሰለኝ፣ መሀረብ ከኪሱ አውጥቶ አይኑን አባበሰ፡፡
“…ካርል ማርክስ፤ ሰራተኛው የስልተ ምርቱ ባለቤት መሆን አለበት የመደብ ልዩነት ተቃርኖው በኃይልም መፈታት ይኖርበታል … ያለው እንዲህ አይነቱን የበዝባዦች ሴራ ለ.መ.ሰ.ባ.በ.ር ነው!” አለ - “ለመሰባበር” የሚለውን ቃል ረገጥ አድርጌ፡፡
ሚናስ ግራ ገብቶት፣ አይኑን ያቁለጨልጫል፡፡
“የፃፍከው የሀገራችንን የታሪክ ምፀት ነው፡፡ ይኼ ማስተርፒስ የሆነ ቅኔ፣ በጓዶች ዘንድም ተወዷል! ለዚህ ደሞ በኔና በመምሪያው ሰራተኞች ስም ምስጋና አቀርባለሁ” ብሎ ሲያጨበጭብ፣ እኛም ተቀብለን፣ ጨብ ጨብ ጨብ!!! አደረግን፡፡
ሚናስ፤ “ይኼ ሰውዬ ምንድነው የሚያወራው?” በሚል አስተያየት፣ የፕሬስ መምሪያ ኃላፊውን ሲያይ ቆየ። ግራ እንደገባው በግልፅ ያስታውቃል፡፡
የሚናስ ዝና በዚህ ብቻ አላቆመም፡፡ “ከመፃህፍት ዓለም” በተሰኘ የራዲዮ ፕሮግራም ላይ ሥራው ተተረከ። የኪነጥበብ ፕሮግራም ላይ ቀርቦ፣ ቃለ መጠይቅ ተደረገለት፡፡ በቃለ- መጠይቁ፤ “ንዑስ-ከበርቴውን ያሳየህበት መንገድ ይገርማል፤ ተከላሾችና ረድፈኞች ግን ጎልተው እንዲወጡ አላደረካቸውም…” ወዘተ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ቀረቡለት፡፡ ሚናስ ነገር ዓለሙ ዞረበት፡፡ ሥራውን አስመልክቶ፣ በሰራተኛ የውይይት ክበቦች ውይይት ተደረገበት፡፡ በቴሌቪዥን መስኮት፣ ሁለት የስነጽሁፍ ምሁራን ክርክር ሲያደርጉ የሚያሳይ ፕሮግራም ተላለፈ - በድርሰቱ ላይ፡፡
አንደኛው ፕሮፌሰር፤ ሽማግሌው የኢትዮጵያ ገባር ህዝብን እንደሚወክል፣ ውሻው ደሞ ለህዝቡ መሪነት የመጣውን አብዮት እንደሚያሳይ አብራሩ፡፡
“የሽማግሌው አይነስውርነትም ያለምክንያት የመጣ አይደለም! አንድም ህዝቡ መሪ አጥቶ መቆየቱን፣ በሌላ በኩል ደሞ መሀይምነት ጨለማ ውስጥ ይኖር እንደነበር ማሳያ ነው፡፡ በውሻው የተወከለው አብዮት ደርሶ፣ ህዝቡን ባይመራው፣ የዚህ ህዝብ መጨረሻ የት ነበር?” የምሰማውን ነገር ማመን አልቻልኩም፡፡ ሚናስ ነገር ዓለሙ ተደባልቆበት፣ እቤቱ ዘግቶ ተቀምጦ ነበር፡፡
“እነዚህ ሰዎች ስለ ምንድነው የሚያወሩት?” ይላል፤ ድምጹን ቅዝዝ አድርጎ-አተካሮውና ውዝግቡ ግራ እያጋባው፡፡
የከፍተኛው የኪነት-አስተባባሪ ሚናስን አናገረው። ጽሁፉን ወደ መድረክ ሥራ መቀየር እንደሚፈልጉ ገለጸለት፡፡ ሚናስ ከመስማማት ውጪ ምርጫ አልነበረውም፡፡ “የጭቁኖች ገድል” የሚል ርዕስ ሰጥተው፣ ቲያትር ሰሩበት፡፡ የሚናስ ዝና ሰማይ ነካ፡፡ ይኼኔ ከዝናው ልጋራ ባለመቻሌ ልደብቀው የማልችለው ንዴት ሰውነቴን ወረረኝ፡፡ “ቢያንስ ሀሳቡን እኔ እንደሰ
ጠሁት እንዴት አይናገርም?” ብ ተቆጣሁ ለራሴ፡፡
ንዴቱን ላባርር ወደ መጠጥ ቤት ሮጥኩ፡፡ ቢራ በአናት በአናቱ ጠጣሁ፡፡
ሁለት ሰዐት ደርሶ የመጠጥ ቤቷ ባለቤት፣ ቴሌቪዥን እንዲከፈት አዘዘች፡፡ ትንሽ ቆይቶ በከፍተኛው ኪነት የተሰራው “የጭቁኖች ገድል” ድራማ መቅረብ ጀመረ፡፡ ንዴቱ ከመጠጡ ጋር ተቀላቅሎ ጠብ ጠብ አለኝ፡፡ ቀጥታ ሚናስ ቤት ሄጄ ነገር ልፈልገው አሰኘኝ፡፡
አጭሩ ተውኔት ሲያልቅ፣ ለረጅም ዘመን የማውቀው የመጠጥ ቤቱ ደንበኛ፣ ሳቅ እያለ ወሬ ጀመረኝ፡ ፡
“አየህ ሲያገባላቸው!” አለኝ በሹክሹክታ
“ማንን?”
“ደርጉን!” ፈገግ እያለ፡፡
“እንዴት?”
“ውሻውን ማን እንደገደለው አስታውሰሀል? ማዘጋጃ ቤት! አይነስውሩን እየመራ ወደ ተሻለ ጊዜ ይወስዳቸው የነበረውን ውሻ፣ ማዘጋጃ ቤት ገደለው! የወጣቶቻችንን በየጎዳናው መጣል ነው ባለቅኔው ሊያሳየን የፈለገው፡፡ እነዚህ ሞኞች ግን ስለ ራሳቸው ጉድ እየነገራቸው መሆኑ አልገባቸውም!” አለ ሰውዬው፤ አንድ ታላቅ ምስጢር የተገለጠለት ያህል በኩራት ተኮፍሶ፡፡
በጣም ገረመኝ፡፡ “ኧረ አይደለም! ይኼ ራሳችሁ የምትሰጡት ትርጉም ነው!” ልለው ፈልጌ ነበር ግን አልቻልኩም፡፡ አናግሮ ሊያናግረኝ ይሆናል፡፡ ይኼ ህዝብ ቅኔ ሲፈልግ ነው የሚውለው? ከመንገድ ዳር ወርቅ ቢያገኝ እንኳ፣ ንቆ ነው የሚተወው፡፡ ወርቅ ተቆፍሮ ብቻ የሚገኝ ነው የሚመስለው፡፡
“ቢገባቸውማ ኖሮ … አንድ ቀንም ባላሳደሩት!” አለኝ፤ ሰውዬው በሹክሹክታ
ደነገጥኩ!
ቀስ ብዬ ወደ ውጪ ወጣሁ፡፡ ዙሪያ ገባዬን ተጠራጠርኩ፡፡ የእርምጃዬን ዳና በስጋት እያዳመጥኩ ወደ ሰፈር ሔድኩ፡፡ ከዛ በኋላ ሚናስን ላለማግኘት ጥረት አደርግ ጀመር፡፡
“አስገባላቸው! ወንድ ነው!” የሚል ሹክሹክታ፣ ከሌላ የመስሪያ ቤት ባልደረባዬም ሰማሁ በድጋሚ፡፡
ከሳምንት በኋላ አንድ ምሽት ላይ ሰፈር አካባቢ ስደርስ፣ የሚናስ ቤት በር ላይ አብዮት ጠባቂዎች ቆመዋል፡፡ ሚናስ ከቤቱ ሲወጣ አየሁት፡፡ እጆቹን ወደ ኋላ የፊጥኝ አስረውት ነበር፡፡ እየገፈተሩ ወደ መንገዱ አወጡት፡፡ ቀና ብሎ አየኝ፡፡ አይኖቹ ውስጥ ግራ መጋባት ይንፀባረቃል፡፡ ከዛ አንገቱን ደፍቶ ሄደ፡፡ ልከተለው አልቻልኩም፡፡
ይኼ ህዝብ፤ ስንቱን ምስኪን፣ ባለቅኔ እያደረገ፣ አስበልቶ ይሆን? ወደ ቤቴ ገብቼ በጊዜ ተኛሁ፡፡  



Read 5473 times