Monday, 25 September 2017 11:58

ኢህአዴግ ፈጠርኳት የሚለን “ኢትዮጵያ” የታለች?

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(30 votes)

· “የቴዲ አፍሮ ኢትዮጵያ”?-- “የዶ/ር ነጋሶ ኢትዮጵያ”?---”የደርግ ኢትዮጵያ”???
· መንግስትን፤ “ኢትዮጵያዊነታችንን” መልስልን ----ብለን ብንከሰውስ ?

  አያችሁልኝ … “የከፍታ ዘመን” በምኞት ብቻ እንደማይመጣ! አዲሱ ዓመት ገና ከመጥባቱ ከወደ ኦሮሚያና የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል የሰማናው ድንበር ተኮር ግጭት ያሳፍራል፡፡ የሚያሳፍረው ከወትሮው በተለየ በክልሎቹ ታጣቂ ሃይሎች ድጋፍ፣ የተጫረና የተቀጣጠለ “እሳት” መሆኑ ነው፡፡ (አማጺ ኃይል ወይም ተቃዋሚ ፓርቲ ቢሆን የአባት ነበር!) እንዴ ከጎረቤት አገር ጋር ጦርነት የገጠምን እኮ ነው የመሰለው - ወይም የሁለቱ ክልሎቹ የመንግስት ቃል አቀባዮች ያስመሰሉት።
 ኢህአዴግ መራሹ መንግስት፤በውጭ የሚገኙ ዳያስፖራ ኢትዮጵያውያንን፣ በማህበራዊ ሚዲያ ህዝብን ወደ ግጭት እንዲገባ እየገፋፉ ነው ብሎ በተደጋጋሚ ሲወነጅል ሰምተናል፡፡ (በኒውዮርክ ስብሰባ ጭምር ለዓለም መንግስታት አቤት ብሏል!)  ሰሞኑን ግን በሚያስገርም ሁኔታ ማህበራዊ ሚዲያውን ለእርስ በእርስ ግጭት የተጠቀመው ራሱ ኢህአዴግ ነው፡፡(መንግስት አማን አይደለም ልበል?)
በድንበር ግጭቱ ሰበብ በርካቶች ለሞት መዳረጋቸው ሳያንስ ብዙ ሺዎች ከመኖሪያ ቀዬአቸው መፈናቀላቸው በእጅጉ ያሳዝናል፡፡ ይሄ የሆነው ደግሞ ከ25 ዓመት የፌዴራሊዝም ሥርዓት ተሞክሮ በኋላ መሆኑ ግርም ድንቅ ይላል!! ከኛ አልፎ በቅርቡ የተረጋጋ መንግስት ለመመስረት ቀና ደፋ ለምትለው ሶማሊያ በሞዴልነት የቀረበው የፌደራሊዝም ሥርዓታችን፤ከሩብ ክፍለ ዘመን በኋላም ለድንበር ግጭቶች  መፍትሄ አልባ መሆኑ ወይም መሆናችን እርግማን ነው፡፡ የኋላቀርነት ማህተም እንጂ የሥልጣኔ አርማ አይደለም፡፡  በኪሳራ የተሞላ እንጂ አንዳችም ትርፍ የለውም፡፡
ኪሳራው ደግሞ የኢትዮጵያ ሶማሌ ወይም የኦሮሚያ ክልል ብቻ አይደለም፡፡ ኪሳራው  የኢህአዴግ ብቻም አይደለም፡፡ የመላ ኢትዮጵያውያን ኪሳራ ነው፡፡ የአገር ኪሳራ!! ይሄ ደግሞ አዲስ ዓመት መባቻ ላይ በየዋህነት የተመኘነውን “የከፍታ ዘመን” በአፍጢሙ ይደፋዋል፡፡  
አንድ ጥያቄ አለኝ፡፡ (ለጊዜው ነው እንጂ ጥያቄዎቼስ ሺ ናቸው!!) እናላችሁ ---- የኢህአዴግ የሥልጣን እኩያ ከሆነው የፌደራሊዝም ሥርአታችን ምን አተረፍን? (ሃቀኛ ጥያቄ እንጂ ስላቅ አይደለም!) እውነት “በልዩነት ውስጥ አንድነት” ተፈጥሯል? (ማስረጃው ምንድን ነው?) በእርግጥስ “ልዩነታችን ውበታችን” ሆኗል? የአገራችን ብሔር ብሔረሰቦች፣ በራሳቸው ጉዳይ ራሳቸው መወሰን ችለዋል? በየክልሎቹ የዜጎች መብትና ነጻነት ሰፍኗል? በመላው አገሪቱ የህግ የበላይነት ተረጋግጧል? (እንዴት ብሎ?) ለፌደራል ሥርዓቱ ውጤታማነት ቁልፍ ሚና የሚጫወተው “ዲሞክራሲ” በቅጡ ተገንብቷል? (ከየት መጥቶ?) ህዝቦች በወደዱትና በመረጡት መንግስት እየተመሩ ነው ወይስ በሚወዳቸውና በመረጣቸው መንግስት? (የሚወደን ብናገኝማ መታደል ነው!) ባለፉት 25 ዓመታት በብሄርና በጎሳ ታፍነን፣ በመንደርና በጎጥ ታጥረን ----- ምን አተረፍን? ምንስ አጎደልን? (የምን ትርፍ?)
አይገርምም---- ይሄን ሁሉ ጥያቄ ደርድሬም ገና ብዙ-- ብዙ ይቀረኛል፡፡ (የ25 ዓመት ውዝፍ እኮ ነው!) ውድ አንባቢዎቼን እንዳላሰለች ግን (እንደ ኢህአዴግ ካድሬ!) ለጊዜውም ቢሆን ጥያቄዎቼን ላሳርፋቸው። በእነዚህ ሁሉ ጥያቄዎች መሃል ግን እኔም እናንተም (ኢህአዴግም ጭምር!) የምናውቀው አንድ የጋራ እውነት አለን፡፡ ብሄራዊ እውነት፡፡ የማይበጀን ቀፋፊ እውነት። ግን ደግሞ የማንክደው፣ ያፈጠጠ እውነት፡፡ ምን መሰላችሁ?  “ኢትዮጵያዊነት”ን አጥተነዋል፡፡ ተዘርፈን ወይም ተነጥቀን አይደለም፡፡ ራሳችን ጦርነት ከፍተንበት ነው፡፡ (በኢህአዴግ አዝማችነት!) ጎሳና ብሔር ላይ የሙጥኝ ብለን (ጥቅምና ጉዳቱን ሳናሰላ!) ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት “ኢትዮጵያዊነት”ን በእጅጉ  ሸርሽረነዋል፡፡ “ኢትዮጵያዊ አንድነት” ላይ እንደ ባላንጣ ዘምተንበታል፡፡ (በራሱ ላይ የዘመተ ታሪካዊ ህዝብ ነን!!)
 ክፋቱ ደግሞ፣ ኢትዮጵያዊነት ላይ መዝመታችን መዘዙ መጥፎ ነው፡፡ ብሔር ብሔር ብለን “ኢትዮጵያዊነትን” ፊት መንሳታችን ለፈተና ዳርጎናል፤ ለማንወጣው መከራ። ኢህአዴግ ሁሌም ሳይሰራ ለነገ የሚያሳድራቸው የቤት ሥራዎች (በመልካም አስተዳደር ችግር፣ በቸልተኝነት፣ በፖለቲካ ቁማር፣ በጥበብ ማነስ ወዘተ…ወዘተ) ውሎ አድሮ ዋጋ እያስከፈለን መሆኑን ደጋግመን አይተነዋል - በጠራራ ፀሃይ!! (ያውም በዜጎች ውድ ህይወት!)
ለምሳሌ የአዲስ አበባና ኦሮሚያ ዙሪያ ማስተርፕላን… የማታ ማታ ውድቅ መደረጉ ላይቀር … ለብዙዎች ህይወት መጥፋት ሰበብ ሆኗል (በካድሬ አድርባይነትና በትንቢት ወይም በትዕቢት!) ቀጣይ ግጭትና ተጨማሪ የዜጎች ሞትንም አስከትሏል፡፡ በተለያዩ ክልሎች ዕድሜ ዘመናቸውን ከኖሩበት ቀዬ (አንዳንዴ “ደን መነጠሩ” እየተባለ ሁሉ!) ሲፈናቀሉ፤ ድርጊቱን በፈፀሙት ላይ የማያዳግም እርምጃ በመውሰድ፣ ተፈናቃዮቹን ወደ ቀዬአቸው መመለስና ማቋቋም ሲገባ! በቸልታ  ታልፏል…ዛሬ ግን እጅግ ውድ ዋጋ…!  አስከፍሎናል!!
የኢትዮጵያ ሶማሌና የኦሮሚያ ክልል አዋሳኝ  ግጭትን ተከትሎ በርካቶች ሲሞቱ … ከ140 ሺ ገደማ ዜጎች በላይ ተፈናቅለዋል ተብሏል፡፡ (ሳኡዲ እንኳን ህጋዊ ላልሆኑ ስደተኛ ኢትዮጵያውያን፣ ስንቴ ነው ምህረት ያደረገችው?) በቅርቡ በጣልያን ሮም ከተማ፣ ፖሊስ ከሽብር ጋር የተያያዘ ተልዕኮውን ሲወጣ፣ ወደ 800 ገደማ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ከመኖሪያቸው ተፈናቀሉ፣ ተብሎ ቡራ ከረዩ ሲባል ነበር-ያውም በሰው አገር፡፡ (በስደት!)
በድንበር ግጭቱ ከ2009 እስካሁን ድረስ ግማሽ ሚሊዮን ያህል ዜጎች መፈናቀላቸውን ሰምተናል፡፡ (“የኑሮ ሳይሆን የመፈናቀል ዓመት” እኮ ነው!) ይሄ ደሞ የሆነው በስደት… በሰው አገር አይደለም፡፡ በገዛ አገራቸው ነው፣ በገዛ አገራችን፡፡ (በኢትዮጵያ!!) …ኢህአዴግ እንደ ጭራቅ በሚፈራት የነገስታቱም ሆነ የደርግ “ኢትዮጵያ”፤በአንድ ዓመት ግማሽ ሚሊዮን ህዝብ ተፈናቅሏል? ከኢህአዴግ በፊት በምናውቃት “ኢትዮጵያ” (“ጠቅላይ አግላይ” ይሏታል!?) በብሄር ተቧድነን፣ የጎጥ አጥር ሰርተን፣ በቋንቋ አድመን፣ (አማራ፣ ትግሬ፣ ጉራጌ፣ ኦሮሞ፣ ሲዳማ…ወዘተ እያልን፣ ጦር ተማዘን ነበር?) በነገራችን ላይ ከመጀመሪያው የሶማሌና ኦሮሚያ ክልሎች የድንበር ግጭት አንስቶ የምንሰማው መረጃ ሁሉ የተዛባ ነበር፡፡ የኦሮሚያ ኮሙኒኬሽን ቢሮ፤ ጥቃት ፈፃሚዎቹ ታጣቂ የሶማሌ ሚሊሻ እንደሆኑ ሲጠቁም፣ የሶማሌ ክልል በበኩሉ፤ የሚባለውን ሃይል ወይም ቡድን ጨርሶ እንደማያውቀው ይገልፅ ነበር፡፡ (የመንግስት መረጃ የማይታመንበት ዘመን ላይ ደርሰናል!) ዜጎች ከሞቱና ንብረት ከወደመ በኋላ … ሚያዚያ ወር ላይ የሁለቱ ክልላዊ መንግስታት ፕሬዚዳንቶች፤ የድንበር ግጭቱን በሰላም ለመፍታት ተስማሙ፣ ተባለና-- (የቀድሞ የፌደራልና አርብቶ አደሮች ጉዳይ ሚ/ር የነበሩትን አቶ ካሣ ተክለብርሃንን ጨምሮ ተቃቅፈው የተነሱት ፎቶ ተሰራጨ፡፡) “ደስ ይበላችሁ --- ደስ ብሎናል” በሚል ስሜት!
ግን መተቃቀፉና መሳሳቁ የውሸት (የይምሰል) መሆኑን ያወቅነው … ግጭቱ ተመልሶ ሲመጣ ነው፡፡ ያውም የኢትዮ - ኤርትራ የድንበር ግጭትን መስሎ (ኧረ ከዚያም ይብሳል!) እናላችሁ … ኢህአዴግ “በአምሳሌ ፈጠርኳት” የሚለንን አገር …አፉን ሞልቶ ስሟን ለመጥራት እንኳ አይደፍርም፡፡ ይቺ ፌደራሊዝም የተባለ ውድ ካባ ተገዝቶላት የተጀቦነችው የኢህአዴግ “ኢትዮጵያ”፤ … በ25 ዓመት የጉዞ ሃዲድ፣ ከአንድነት ይልቅ ልዩነታቸው የሚቀድምባቸው የብሄር ነጻ አውጭዎች (አማራ .. ትግሬ … ጉራጌ…ኦሮሞ… ቤኒሻንጉል---ወዘተ)፣ ቀበሌና ጎሳ ዜግነት የሆነላቸው ወገኖች--- በብዛት አፍርታለች። በጎጆዋ እየኖሩ እናትነቷን የሚክዱ ብዙ “ዘረኞችን” ፈጥራለች (እንኳን ደስ አለህ - ኢህአዴግ!!)
ኢህአዴግ እና አንዳንድ “ጽንፈኛ” ብሔር ተኮር - ጎሳ ተኮር - ዘር ተኮር ፖለቲከኞች … (ምሁራንንም ያካትታል!)የኢትዮጵያዊነት ጉዳይ ሲነሳባቸው ክፉኛ ይደነግጡና … “የትኛዋን ኢትዮጵያ ነው የምናወራው?”፣ “መቼና በማን የተፈጠረችውን?” የሚል ቅድመ መደራደሪያ ያቀርባሉ። ነገር ፍለጋ ነው፡፡ “የምኒልክ ኢትዮጵያ” (???) …”የአፄ ቴዎድሮስ ኢትዮጵያ” (??) … “የደርግ ኢትዮጵያ” (??) “የኢህአዴግ ኢትዮጵያ” (?????) … ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ “የቴዲ አፍሮ ኢትዮጵያ” (??) “የዶ/ር ነጋሶ ኢትዮጵያ” (??) “የፌስቡኳ ኢትዮጵያ” (????) (“የኢቢሲ ኢትዮጵያ”) (????) ”የዳያስፖራ ኢትዮጵያ” (??) አሁንም ዕድሜ ለኢህአዴግ … ብዙ ባለቤትና ብዙ ፈጣሪ ያላት ኢትዮጵያን አዋልዶናል፡፡ ልክ አሁን እንደፈሉት የቲቪ ቻነናሎች (በሪሞት እንደምንቀያይራቸው!)፤ ይኼ ሁሉ “የኢሕአዴግ ነፍሴ” የእጅ ሥራ ውጤት ነው፡፡ ለ25 ዓመታት አንድነትን የተጠየፈ አውራ ፓርቲ፣ ጳጉሜን ሳይጠመቅ፣ ንስሐውን ሳያወርድ፣ መስከረም ባተ፤ደግሞ “የኢትዮጵያ ቀን” ይላል? “የከፍታ ዘመን” ይላል? (የቱዋ ኢትዮጵያ? የምን ከፍታ?)
በዚህ የስጋትና የውጥረት … በዚህ የተቃውሞና የእምቢተኝነት … በዚህ የጥላቻና የክፋት … በዚህ የግጭትና የእልቂት .. በዚህ የመከፋፈልና የመበታተን ---- በዚህ የምስቅልቅልና የውዥንብር… ክፉ ጊዜ ... ላይ ሆነን፣ እስቲ ኢህአዴግ ላፍታ ---- ወደ ውስጡ ይመልከት … እስቲ ፈጠርኳት የሚላትን ኢትዮጵያ በቅጡ ይያት … ምን ትመስላለች? (አለች እንዴ?)
እንደ አውራው ፓርቲማ … የኢትዮጵያ ዕድሜ… ከግንቦት 20 1983 ዓ.ም ጀምሮ ቢቆጠር ደስታውን አይችለውም - የ25 ዓመት  ኮረዳ “ኢትዮጵያ” ብትሆንለት፣ ስለቴ ሰመረ ይል ነበር፡፡ የኋላ ዘመን የሌላት  አገር … የ100 ዓመትም ሆነ የ3 ሺ ዘመን ታሪክ ባለቤት ያልሆነች … የእሱ ብቻ “ኢትዮጵያ” ብትሆን በደስታ ጮቤ ይረግጥ ነበር፡፡ (ታሪክ የማይወደው ለዚህ ነው!)
የኢህአዴግ ራዕይና ህልም እኮ የጦቢያ ታሪክ ብቸኛ ደራሲ መሆን ነበር! (አልተሳካም) ለዚህ ነው የቀድሞ የኢትዮጵያ ታሪክ ደራሲያንን (መሪዎቿን) የማይወዳቸው --- እነ ምኒልክን፣እነ ቴዎድሮስን፣እነ ጃንሆይን? ወዘተ!-- (ደራሲነቱን ይጋሩታላ!) እሱ ደግሞ እንኳን የድሮ መሪዎች፣ ወደፊት የሚመጣም--- ደራሲነቱን እንዲጋራው አይፈልግም፡፡ ብቸኛ “የኢትዮጵያ ፈጣሪ” መሆን ነው ፍላጎቱ! (አገር ደሞ ለብቻ አትፈጠርም!) በዚህ መሃል --- እኛ ደግሞ መንግስት፣”ኢትዮጵያዊነታችንን ይመልስልን” ብለን ብንከሰውስ?
መልካም ደመራ! መልካም መስቀል!

Read 10619 times