Monday, 25 September 2017 11:54

የህይወታችን ‘ኦልዲስ’ ፊልሞች…

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(7 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
እንግዲህ የአዲስ ዓመትም ሰሞንም አይደል… ወደ ኋላ ዘወር ብለን የመጣንበትን ማየታችን አይቀርም። ያው እንደውም ያለፈውን ዓመት ብቻ ሳይሆን ርቀን ሄደን፣ የህይወታችን ‘ኦልዲስ’ ምናምን ፊልሞች በአእምሯችን ማመላለሳችን አይቀርም፡፡ አለ አይደል…በተለይ “ሰው የመሆን ሰው የጠፋ ዕለት” በሚጠፋብን ጊዜ፣ “ትናንትም እንዲህ ነበር?” እንላለን፡፡ ብዙ ነገሮች እንደጠብቅናቸው ሳይሆኑ ሲቀሩብን፣ ሁሉም ነገር ‘ተራራ መውጣት ሳይሆን ቁልቁለት መንሸራተት’ በመሰለን ጊዜ የህይወታችን ‘ኦልዲስ’ ፊልሞች አሰሳ እንገባለን፡፡
ትናንት አይደለም መስማት አስበን የማናውቃቸውን ነገሮች ስንሰማ፣ ወደ ትናንት ሄደን፣ የህይወታችን ‘ኦልዲስ’ ፊልሞች እናስሳለን፡፡ ሦስትም፣ አራትም ሆናችሁ በሆነ ጉዳይ ስታወሩ፣ አገር ሰላም ብላችሁ የራሳችሁን አስተያየት ትሰጣላችሁ፡፡
ቢያንስ ቢያንስ በዚህ አይነት አንፈራረጅም ነበር፡፡
ገበያ ትወጡና ጥራጥሬውን ስትጠይቁ ዋጋው ሰማይ፣ ቅጠላ ቅጠሉን ስትጠይቁ ዋጋው ሰማይ…ይሄኔ ትናንት ትዝ ይላል፡፡ “ያኔ እኮ ቢያንስ፣ ቢያንስ ሀያ ኪሎም፣ አሥራ አምስት ኪሎም የቀበሌ ስንዴ አይጠፋም ነበር፣” እንላለን፡፡
“ስማ…ያቺ አሥራ አንደኛ ክፍል የነበረችውን ገርልፍሬንድ…ማን ነበር ስሟ…”
“ቄንጦ!”
“አመጣህልኝ..እሷ ልጅ የት ደረሰች፣ የሆነች የጨሰች! የጨሰች!…ቢመቻት እኮ አዲስ አበባን በዱቤ ሁሉ ልትሸጣት ትችል ነበር!”
“አሁን እሱ ቀርቶ… የሆነች ‘ሀይማኖተኛ ነኝ፣’ ትላላች አሉ፡፡”
“ምን! እኔ የምለው… እንዲህም ይቻላል እንዴ! እንደዛ ስታተረማምሰን ኖራ፣ እንደዛ “ከቤታችን እቃ እያሰረቀች ስታሸጠን ኖራ …ጭራሽ ሀይማኖተኛ!”
“ምን ያንሳታል …በማርክስና በሌኒን ይምል የነበረው ሁሉ ሀይማኖተኛ ሆኖ የለ እንዴ! ያውም ቅልጥ ያለ ሰባኪ!”
የምር ግን እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ሰዎች የህይወት አቅጣጫቸውን በየጊዜው በመሰላቸው መንገድ ያለ ፍሬቻ ወዲህ፣ ወዲያ ሊለውጡ ይችላሉ፡፡ ግን “የማኦን ያህል ክብር ልትሰጡኝ ይገባል…” አይነት ነገር ይል የነበረው፣ በአንድ ጊዜ “የመንግሥተ ሰማያት ቁልፍ ኦሪጅናሉ በእኔ እጅ ነው” አይነት ነገር ሲል ለ‘ትንታኔ’ ትንሽ ያስገቸግራል፡፡ (የሆነች ነገር ‘ብልጭ’ ባለች ቁጥር ሚዲያውን የሚሞሉት ‘ከት ኤንድ ፔስት’ ተንታኞች ሁሉ ምነው ይሄን አይነቱን ነገር የማይተነትኑልንሳ!)
“እንደውም አስታወስከኝ…ያ ፈተና ላይ ሁልጊዜ ሲኮርጅ ይያዝ የነበረው ክላስሜታችን…”
“አፍሮው…”
“አዎ፣ እሱ…ምን እንደሆነ ሰምተሀል?”
“ፖለቲከኛ…”
“አንተም ታውቃለህ?”
“እንዴት አላውቅም! ኒኦ ሊበራሊዝም፣ ምናምን ምናምኒዝም እያለ በየመድረኩ መከራችንን እያበላን እንዴት አላውቅም!”  
“ግን… ምናምኒዝም የሚለውን ነገር ሁሉ፣ ስሙን ብቻ ኮረጀና …ሲናገር እኮ ከመሀሉ ዘጠና ዘጠኝ ገጽ የጎደለው መቶ ገጽ መጽሐፍ የሚያነብ ነው የሚመስለው።”
የምር ግን…ዘንድሮ ግራ የሚገባን ነገር…አለ አይደል…ይሄ የፖለቲካ ‘ንቃተ ህሊናችንን ሊያዳብሩልን’ የሚሞክሩ አንዳንድ ሰዎች ነገር ነው፡፡ (‘አንዳንድ’ የሚለውን ቃል ያስገባነው ‘ጨዋ’ ለመባል ሊሆን ይችላል፡፡) ‘ምናምኒዝም፣ ምናምኒዝም’ ስለተባለ ብቻ የፖለቲካ መሪነት ሊቼንሳ ሊሆን አይችልም፡፡ ለነገሩ… አብዛኛው ሰዋችንም እንዲህ አይነት ነገሮችን “እህ…” ብሎ መስማት መተዉ ደግ ነው፡፡
እናማ… የሆነ ድሮ የምናውቀው ሰው ስም ተነስቶ፣ “እሱ ሰውዬ ምን ሆኖ ይሆን!”  ስንል፣ “የፖለቲካ ተንታኝ ሆኗል፣” ብንባል መገረም ትተናል፡፡
ታዲያላችሁ …ነገሮች አንዳንዴ ባላሰብነው መንገድ ሲሄዱብን፣ የህይወታችን ‘ኦልዲስ’ ፊልሞች እናስሳለን፡፡ ልጆች፣ በአደባባይ አጉል ስነ ምግባር ሲያሳዩ ስንመለከት፣ እኛ የጎረቤታችን ሴትዮ ትዝ ይሉናል፡፡ ትንሽ ነገር እንኳን ካዩብን፣ “እናቱ ምን ትለኝ ይሆን!” “አባቱ ይጣላኝ ይሆን!” ሳይሉ ጭናችሁ ስር ገብተው የሚመለዝጓችሁ ጎረቤት ትዝ ይሏችኋል፡፡ ፓስቴ ተደብቃችሁ ስትበሉ እጅ ከፍንጅ ይያዟችሁና፣ በጥሩ ቁንጥጫ ያነሷችኋል፡፡ እንባችሁን እየጠረጋችሁ ወደ ቤት…
“ምን ሆንክ?”
“እኚህ እትዬ እንትና ቆነጠጡኝ፡፡”
“ምን አድርገህ?”
“ፓ..ፓስቴ ስበላ…”
“ፓስቴ! እንደው ምነው ጀርባህን በሰበሩልኝ ኖሮ!”  ከቁንጥጫ ተርፎ የነበረው ጭን፣ አሁን ተራው ይደርሰዋል፡፡
በነገራችን ላይ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል… በፊት እኮ ልጅን መቆጣጠር የቤተሰብ ብቻ ሳይሆን የጎረቤትም፣ የመንደርም ሃላፊነት ነበር፡፡ የሆነ ነገር ከማድረግ በፊት ስጋቱ “እማዬ እንዳታየኝ!”  “አባዬ እንዳያየኝ!” ብቻ ሳይሆን “የሰፈር ሰው እንዳያየኝ!” የሚል ነገር ነበር፡፡ ዘንድሮ፣ አይደለም ሰፈረተኛ ግድግዳ የምንካፈለውን ጎረቤት እንኳን በማናውቅበት ዘመን…እንኳን የጎረቤት ልጅን፣ የራስን ልጅ መጥፎ ቀለበት መንገድ ላይ እንዳይገባ መከላከሉ አስቸጋሪ ሆኗል፡፡ ግሎባላይዜሽን ነዋ!
ይቺን ስሙኝማ…ሦስት ጥንዶች፣ የሆነ ሬስቱራንት ውስጥ እየተመገቡ ነው፡፡ አሜሪካዊው ለሚስቱ እንዲህ አላት…
“የእኔ ማር፣ እስቲ ማሩን አቀብይኝ፡፡” አቀበለችው።
እንግሊዛዊው ለሚስቱ እንዲህ አላት፡- “የእኔ ስኳር፣ እስቲ ስኳሩን አቀብይኝ፡፡” አቀበለችው፡፡
ሦስተኛው ባል ሚስቱን ምን ቢላት ጥሩ ነው፡- “አንቺ ደደብ፣ እስቲ ጥብስ አቀብይኝ!”
ይኸኛው ከየትኛው የዓለም ክፍል እንደሆነ ገና እየተጣራ ነው፡፡ ቂ…ቂ…ቂ…
እናላችሁ… ፊልም ታዩና ከአኒሜሽን መራቀቅ ይልቅ የትወና ጥበብ ስታጡበት፣ “ኢሮ!” ብላችሁ፣ የምታጨበጭቡለት ተዋናይ ስታጡበት ስለ ‘ኦልዲስ’ ፊልሞች ማሰብ ትጀምራላችሁ፡፡ ያ መቼም የማትረሱት የካውቦይ ፊልም!…‘ቴክሱ’ ስድስት በሚጎርስ ሽጉጥ፣ አንዴም ደግሞ ጥይት ሳያጎርስ አስራ ሰባት ‘ሬድ ኢንዲያን’ ሲረፈርፍ፣ እጃችሁ እንሶስላ ነው ምን የተቀባ እስኪመስል ያጨበጨባችሁበት! (ዘንድሮ ቢሆን “ይሄ እኮ ጄኖሳይድ ነው፣ እንዴት ታጨበጭባለህ!” እንባል ነበር!)
ደግሞ የሆነ ቦታ ጉዳይ ልታስፈጽሙ ትሄዱና፣ የሆነ ባለስልጣን ባህሪይ፣ ‘ያንን’ የቀበሌያችሁ ሊቀመንበር የነበረውን ሰው ያስታውሳችኋል፡፡ አለ አይደል… ‘ጓድ’ የሚለውን ቃል አብራችሁ ከስሙ ጋር ካልሰፋችሁለት፣ ዘወር ብሎ የማያያችሁና በሌጣው ስሙን ብትጠሩት ፍርድ ሸንጎ ሊያቀርባችሁ ምንም የማይቀረው ሰውዬ፡፡ (ይሄኔ ወይ ‘ቦተሊከኛ’ ወይ ሰባኪ ሆኖ ይሆናል!)   
እግረ መንገዴን…ይቺን ስሙኝማ፣ ልጆቹ ውድ ምግብ ቤት ይገባሉ፡፡ የቤቱን ውድ ምግብ ያዛሉ፡- “እባክህ፤ የዶሮ ሾርባና አሮስቶ አምጣልን”
አሳላፊው ከፍ ዝቅ አድርጎ አያቸውና፣ ምን ቢላቸው ጥሩ ነው…“ልትበሉት ነው ወይስ ፎቶውን ፌስቡክ ፕሮፋይል ፒክቸር ልታደርጉት!” አላቸውና አረፈው። (በፊት ፕሮፋይል ፒክቸር የሚባል ነገር ስላልነበር፣ አይደለም ዘቢብ ኬክ፣ ባቅላባ ቢታዘዝም እንዲህ ሞራል የሚነካ አስተያየት የሚሰጥ አሳላፊ አልነበረም፡፡)
ደሀና ሰንብቱልኝማ!
Read 3667 times