Monday, 25 September 2017 11:56

“በኩሮቹ” - የማደጎና የጡት ልጆች

Written by  ዳኘው
Rate this item
(1 Vote)

የጥረታቸውና የድካማቸው ፍሬ፣ ለስኬት ያደረሳቸው በርካታ ዜጎች በሀገራችን ሞልተዋል፡፡ ለእነዚህ መሰል አርዓያ ዜጎች አክብሮቴ ይድረሳቸው። ትምህርትና ትጋት አንቱ ላሰኛቸው የሀገሬ ልጆችም - አሹ ብዬ ኩራቴን እገልፅላቸዋለሁ፡፡ እንደነዚህ ዓይነት ዜጎች፣ የሀገር ጌጥና ሞገስ ስለሆኑ ቢወደሱ አግባብ ነው፤ ቢሸለሙም አይበዛባቸውም፡፡ ምሳሌዎቻችን ስለሆኑም በየአደባባዩ “ነዎር” እየተሰኙ ቀዳሚው መንበር ቢሰጣቸውና፣ በማንኛውም ምስባክ፣ ፊት ለፊት ቆመው ቢጨበጨብላቸው፣ ከአድናቂዎቻቸው ጋር ለመቀላቀል ተሽቀዳድሜ ከወንበሬ መነሳቴ አይቀርም፡፡ የጦቢያ የአብራኳ ክፋይ ናቸዋ!!!
ደግሞ አሉ አንዳንዶች፤ የህሊናቸውን ልጓም አሽቀንጥረው በመጣል፣ ክብራቸው ነውራቸው፣ ሆዳቸው አምላካቸው የሆኑ የማደጎና የጡት ልጆች። ጥቅም ያለበትን ቦታ እያነፈነፉ፣ “እንዳያ ምንትስ” ሁሉም ለእኔ ባዮች፡፡ ቅዠታቸው ጥቅም፣ ስልታቸው ዘረፋ፣ ሩጫቸው “አብሉኝ” ብቻ የሆነ፡፡
እነዚህን መሰል የማደጎና የጡት ልጆች፣እንዳሁኑ ዘመን እንደ አሸን ፈልተው እንደማያውቁ የሦስት መንግሥታት የሕይወት ውጣ ውረድ ያሸበተውን ፀጉሬን ዋቢ አድርጌ መመስከር እችላለሁ፡፡ የአፋቸው ቅድ ሰፊነት፣ ለጥቅማቸው ያወሳሰቡት ኔት ወርክ ጥልፍልፍነት፣ የሚጓዙበት የረቀቀ ሰርጥ ዚግዛግነትን ላስተዋለ ሰው፣ አጃኢብ አሰኝቶ ያስደምማል፡፡
ማደጎዎቹና የጡት ልጆቹ፣ እንጀራቸውን መጋገር ተክነውበታል፡፡ ዘመን ከፍ ያደረጋቸውንና ከፍ ያለ ቦታ ላይ ፊጥ ያሉ የጡንቸኛ ሹሞችን ክንድ በመንተራስ አለዚያም በኢኮኖሚ አቅማቸው በደመና ላይ ካልተንሳፈፍኩ እያሉ የቆሙበትን ምድር የተጠየፉ የጡት አባቶቻቸውን ተገን አድርገው፣ ሁሉ በእጄ ሁሉ በደጄን ሲያዜሙ ማስተዋል፣ እንደምን ውስጥን ዘልቆ እንደሚጠዘጥዝ መረዳቱ አይከብድም፡፡
አንድ ሀገራዊ ጉዳይ ሊከወን ሲታሰብ ቀድመው ራዕዩን በብብታቸው ሥር አስገብተው፣ የጥቅሙም ሆነ የዘረፋው ተጋሪ ሊሆኑ፣ ተሽሞንሙነው አደባባይ ላይ ቀድመው የሚታዩት፣ እነዚያው የማደጎና የጡት ልጆች ናቸው፡፡ አይ ኩራት፣ አይ መጀነን፣ አይ የጩኸት ስልት፣ አይ መራቀቅ፡፡ “ባዶ በርሜል ከበሮ ይተካል” እንዲሉ፡፡ የሚሊኒዬሙ በዓል በተከበረበት ሰሞን፣ ኩነቶችን የማስተባበሩንና የማዳመቁን ኃላፊነት ቀድመው በአደባባይ የጨበጡት እነርሱ ነበሩ፡፡ አንድ ሀገራዊ ጉዳይ ሊከወን ሲታሰብም በብዙኃን መገናኛ የሚለፍፉት፣ በመድረክ ላይ የሚያሸረግዱት እኒሁ፣ “ህሊናቸውን የሳቱ” ጡጦ ተቀባዮች ናቸው፡፡
የአዲስ ዓመት ማብሰሪያው የእነርሱ አፍ ካልሆነ በስተቀር ጀምበሯ ባለችበት እንደምትቆም ለማሳመን መሞከራቸው አይቀርም፡፡ የአዳዲስ ሸቀጥ ማስታወቂያ በእነርሱ እስትንፋስ ካልተባረከ ተጠቃሚ እንደማያገኝም ያወራሉ፣ ያስወራሉ። የታላቁ ህዳሴ ግድብ ከታሰበለት ግብ ሊደርስ የሚችለው፣ የመብራት በረከቱም ፏ ብሎ የሚበራው፣ የእነርሱ አስተዋፅኦ ሲታከልበት ብቻ እንደሆነ አምነው ያሳመኑ ይመስላል፡፡ የኪነ ጥበቡ ሠፈር ቱማታ አመንጭዎችም፣ መፍትሄ አፍላቂዎችም እነርሱ ብቻ ናቸው፡፡ ፊልም ያለ እነርሱ፣ ቴሌቶን ያለ እነርሱ፣ የአስር ቀናት ሀገራዊ “የቀናት አከባበር ባለ ራዕዮች” እነርሱ፤ ሁሉ በእነርሱ፣ ለእነርሱ እና ከእነርሱ ከሆነ ሰነባብቷል፡፡ የማደጎና የጡት አባቶቻቸው ድጋፍ ሁሌም ከእነርሱ ጋር ስለሆነ ስጋት አይገባቸውም። ህሊናቸውንም ገንዘው ስለቀበሩት ሃይ ባይ የላቸውም፡፡ በእውነት የሀገር አደባባይ በእነዚህ መሰሉ “ሆድ አምላኩ ሲረክስ” ሃይ ባይ ይጥፋ ጎበዝ፡፡
ትልልቅ ራዕይ ያላቸው የወገን ፈርጦች በእነዚህ መሰል ስግብግቦች ተገፍተው ሲደፈጠጡ አደብ የሚያስገዛ ሹምና አስተዋይ አማካሪ፣ በሀገሪቱ የሥልጣን ወንበር ላይ ከቶውንም አልተቀመጠምን? ያሰኛል፡፡ ሕዝብ ፊት የነሳውን ያንን አዛውንት ቴሌቪዥናችንን፣ በስህተትም ይሁን በሀገራዊ መረጃ ጥማት ገና ብልጭ ስናደርግ፣ እንደ ጅብራ ተገትረው ሲያገሱ የምንመለከታቸው እነርሱው ናቸው፡፡ “ዋርካ በሌለበት እምቧጮ አድባር ይሆናል” እንዲሉ፣ ለሀገር ዋርካ ሊሆኑ የሚችሉትን ስልጡን ባለሙያዎች፣ አማካሪዎች፣ ተግባሪዎች በሙሉ በውድድር አሸንፈው ሳይሆን “የእንጀራ አባቶቻቸውን” ተከልለው፣ ንፁሃንን በመጥለፍ ከጨዋታው ሜዳ አስፈንጥረው ጥለው፣ መድረኩን በሙሉ ያንቧችሩበታል፡፡
ልብ በሉ፤ እነዚህ የማደጎና የጡት ልጆች፣ “አናውቅም” የሚሉት ምንም ነገር አይገኝም። የኪነ ጥበባት ጉዳዮች ተሟጋቾች፣ የትልልቅ ኩባንያ አፈ ጉባዔዎች፣ ለዓየር ንብረት ሙግት ሀገር ወክለው የሚሄዱ ጎምቱ የሀገሪቱን መሪዎች ሸኝዎች፣ የሙት ዓመት ዘካሪዎች፣ የአዲስ ዓመት አብሳሪዎች፣ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ጠበቆች፣ የቴሌቶን አጋፋሪዎች፣ የሬዲዮ ባለሟሎች፣ የክልል መስተዳድር ፕሮግራም አስፈፃሚዎች . . . ወገን ስንቱ ተዘርዝሮ ያልቃል፡፡ “ምኗን የተማመነች ምንትስ እንትኗን ውጭ ታሳድራለች” እንዲሉ፡፡
ከሁሉም እጅጉን የሚገርመው የረቀቀው ዘዴያቸውና ብልሃታቸው ነው፡፡ መጀመሪያ አንድ ሀገራዊ ጉዳይ ሲወጠን ወይንም እንደነዚህ ዓይነት ፕሮግራሞች ሊደረጉ ነው ማለትን በጭምጭምታም ሆነ በተባራሪ ወሬ ሲሰሙ፣ (ለነገሩ መረጃዎችና ሰነዶች በወኪሎቻቸው በኩል ቀድሞ እንደሚደርሳቸው ጥርጥር የለውም) ተሽቀዳድመው በመሄድ፣ “እኛ ይህ ሀገራዊ ጉዳይ፣ የራሳችን ጉዳይ ስለሆነ በትብብርና በነፃ መስራት እንችላለን” በማለት በጮማ አንደበታቸው፣ የሚያስጎመጅ መረቅ ያንጠባጥባሉ። ወደ ሥራው ውስጥ ከገቡ በኋላም የስራውን ወይንም የፕሮግራሙን ይዘት፣ ከውቅያኖስ ጥልቀት አመሳስለው፣ ከተራራ ግዝፈት አተልቀው በማሳበጥ፣ ለተፈፃሚነቱ “መጠነኛ ክፍያ” እንዲከፈላቸው፣ አዘጋጁን ክፍል ወጥረው ይይዛሉ። ከኋላና ከጎን ደጋፊ የጡት አበው ድጋፍ ስላላቸው፣ ጥያቄያቸው ከገመቱትና ካሰቡት እጥፍ ሆኖ፣ በዳረጎት መልክ ይከፈላቸዋል፡፡ ያውም የሠርተፊኬትና የዋንጫ ሽልማት ታክሎበት፡፡
መቼም “ሀገር ሲያረጅ መጭ ያበቅላል” ሆኖብን፣ እኒህን መሰል ይሉኝታ ቢሶች በየአደባባዩ እያቃረንም ቢሆን መመልከቱ የግድ ሆኖብናል፡፡ ምናልባትም ይህንን ጦማር ሲያነቡ፣ “የቀናተኞችና የምቀኞች ሃሜት ነው” ብለው፣ በጡሩንባ የታጀበውን ኡኡታቸውን ማሰማታቸው አይቀርም፡፡
እስቲ አንድ መሰረታዊ ጥያቄ እንጠይቃቸው? ለመሆኑ እስከ ዛሬ ያለ ዕውቀትና ያለ ጥናት በዋላችሁበትና ባንቧቸራችሁበት መስክ ላይ ምን ውጤት አስገኛችሁ? ለታሪክ ተመራማሪዎች፣ ለዘመን ኩነት መዝጋቢዎች፣ ፕሮግራምህን ካላዘጋጀንልህ ላላችሁት ክፍል፣ ለምርምርና ለመዘክር ተቋማት ምን ተሻጋሪ ቅርስ አስቀመጣችሁ? ነግ ተነገወዲያ ትውልድ ቢጠይቃችሁ፣ ይህ ነው የሚባል የተደራጀ መረጃችሁን እስቲ አሳዩን፡፡
ለሚመለከተው ክፍልም የቅን ዜጋ ጥያቄ እናቀርባለን። ምናለ ዓይናችሁን ገልጣችሁ ሌሎች በዕውቀትና በችሎታ የበረቱ ባለሙያዎችን ብታወዳድሩ፣ ብትቃኙ? ምናለ ትልልቅ ሀገራዊ ጉዳዮች ሲታሰቡ ጉዳዩ ለሳሙና በተሟሸ ድምፀት፣ ለሮቶ በተሳለ ስልት ብቻ እንዲተገበር ባትፈቅዱ? ለአዳም አባታችን፣ ፈጣሪ ከገነት ከመባረሩ በፊት እንደሰጠው ዓይነት የፈላጭ ቆራጭነት ሥልጣኑን፣ ከተወሰኑ ሰዎች ላይ ብትገድቡስ ምን አለበት፡፡ ምናለበት ሀገራዊም ሆኑ ክልላዊ ጉዳዮችና ኩነቶች ሲታሰቡ ዕውቀቱ፣ አቅሙና ህጋዊነቱ አለን ለሚሉ ባለሙያዎችና ተቋማት ሁሉ እንዲዳረሱ የውድድሩን ሜዳ ክፍት ብታደርጉ፡፡ እነዚያ የባህር ማዶ ሰዎች “Varity is a Spice of Life” እንዲሉ፣ ምናለበት ሌላ የተሻለ ድምፅና መልክ በሀገራዊ መድረኮች ላይ ብናስተውል?  “ጎበዝ እባካችሁ እየተስተዋለ!!!” አለ አሉ፤ ወለዬው ዘመዴ፡፡
የአዘጋጁ ማስታወሻ፡- ከላይ የቀረበው ጽሁፍ የሚያንጸባርቀው የጸሃፊውን የግል አመለካከት ብቻ ነው፡፡     

Read 1475 times Last modified on Monday, 25 September 2017 12:38