Monday, 25 September 2017 11:41

በዘንድሮ የኢሬቻ በዓል ግጭት እንዳይፈጠር ቅድመ - ጥንቃቄ ሊወሰድ ይገባል ተባለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

የፀጥታ ኃይሎች ከኃይል እርምጃ እንዲቆጠቡ ተጠየቀ
“ኬንያ፤ ኢትዮጵያውያን የፖለቲካ ስደተኞችን አሳልፋ እየሰጠች ነው” - (ሂዩማን ራይትስዎች)

      በዘንድሮ የኦሮሞ ህዝብ “የምስጋና በዓል” ኢሬቻ አከባበር ላይ የፀጥታ ኃይሎች ከማንኛውም የኃይል እርምጃ በመቆጠብ በዓሉ ያለግጭት እንዲያልፍ የበኩላቸውን እንዲወጡ ያሳሰበው “ሂውማን ራይትስ ዎች”፤ ባለፈው ዓመት በበዓሉ ላይ የደረሰ አደጋም በገለልተኛ ዓለማቀፍ መርማሪዎች እንዲጣራ ጠይቋል፡፡
ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋም ሰሞኑን ባወጣው መግለጫ፤ ባለፈው ዓመት የኢሬቻ በዓል ላይ በተፈጠረ ግጭት በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች መሞታቸውን አስታውሶ፤ በዘንድሮ በዓል ግጭቶች እንዳይፈጠሩ ከፀጥታ ሃይሎች ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲደረግ ተማፅኗል፡፡
የፀጥታ አካላት፤ የተባበሩት መንግስታት የፀጥታ ማስከበር ሥነ ስርአቶችን እንዲከተሉና አስለቃሽ ጭስ ሲጠቀሙም የቦታውን አመችነትና ጉዳት እንደማያደርስ አረጋግጠው ሊሆን እንደሚገባ ያሳሰበው ተቋሙ፤ በዚህ መንገድም ሊፈጠሩ የሚችል ጉዳት ለመቀነስ ከወዲሁ መዘጋጀት ያስፈልጋል ብሏል፡፡
ባለፈው ዓመት በበዓሉ ላይ የደረሰው አደጋ በዓለም አቀፍ ተቋማት እንዲመረመር ያቀረበውን ጥያቄ የኢትዮጵያ መንግስት ውድቅ እንዳደረገው ያስታወሰው ተቋሙ፤  መንግስት ጉዳዩን በድጋሚ እንዲያጤነው ጠይቋል፡፡
የዘንድሮ የኢሬቻ በዓል መስከረም 21 ቀን 2010 ዓ.ም በቢሾፍቱ ሆራ አርሰዲ እንደሚከበር የሚጠበቅ ሲሆን የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት፣ ባለፈው ዓመት በተፈጠረው አደጋ ለሞቱ ተጎጂዎች ሃውልትና መታሰቢያ ፓርክ መገንባቱ ይታወቃል፡፡
ሆኖም በዚህ ሃውልትና ፓርክ ላይ “በድንገት ህይወታቸው ላለፈ የተሰራ” የሚል ፅሁፍ መስፈሩን ተቃዋሚዎች አጥብቀው በመቃወም የክልሉ መንግስት ያሰራው ሃውልትና ፓርክ ተቀባይነት እንደሌለው በቅርቡ መግለፃቸው አይዘነጋም፡፡
በሌላ በኩል፤ ይኸው “ሂውማን ራይትስ ዎች” ባለፈው ሐሙስ መስከረም 11 ቀን 2010 ባወጣው መግለጫ፤ በፖለቲካ ምክንያት ከኢትዮጵያ ተሰደው በኬንያ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ደህንነት፣ የኬንያ መንግስት እያስጠበቀ አይደለም ሲል ወንጅሏል፡፡
የፖለቲካ ጥገኝነት ፈልገው በኬንያ የተጠለሉ ኢትዮጵያውያንን የኬንያ ፖሊሶች ለኢትዮጵያ መንግስት አሳልፈው እየሰጡ እንደሆነ በቂ ማስረጃ አለኝ ያለው ተቋሙ የስደተኞቹን ጉዳይ አስመልክቶ የኬንያ ፖሊስ ኮሚሽን ማብራሪያ እንዲሰጠው ደብዳቤ ቢልክም ምላሽ አለማግኘቱን አስታውቋል።
ከኬንያ በተጨማሪም በኡጋንዳ፣ በሱዳን፣ በጅቡቲና ሌሎች ሀገሮች የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የፖለቲካ ስደተኞችም የተለያዩ ማስፈራሪያዎችና ወከባዎች እንደሚደርስባቸው ያስታወቀው  ተቋሙ፤ የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ ኤጀንሲና ስደተኛ አስጠላይ ሀገራት፣ የኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ደህንነት እንዲያስጠብቁ በአፅንኦት ጠይቋል፡፡  

Read 3154 times