Monday, 18 September 2017 10:56

በዓለም ስፖርት ላይ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(4 votes)

  የቢሊዬነሮች መጨመር፤ የ5ቱ ታላላቅ ሊጎች ትርፋማነት የስፖርተኞች ደሞዝና ገቢ

      ከ322 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሃብት ግምት ያላቸው 63 ቢሊየነሮች
በመላው ዓለም የሚካሄዱ ፕሮፌሽናል የስፖርት ውድድሮች ባለፉት 10 ዓመታት በከፍተኛ ደረጃ የገቢ ዕድገት እያሳዩ ናቸው፡፡ በሁለገብ የሚዲያ መብት ፤ በስፖንሰርሺፕ እና በተለያዩ የንግድ እንቅስቃሴዎች የሚንቀሳቀሰው መዋዕለንዋይ እየገዘፈ መምጣቱ ዋናው ምክንያት  ሊሆን ይችላል፡፡ በተለይ ደግሞ በሁሉም ክፍለ አህጉራት በሚከናወኑ የስፖርት ውድድሮች ዙርያ ከቴሌቪዥን የስርጭት መብት በተያያዘ የሚገኘው ገቢ በየዓመቱ መጨመሩ የሚጠቀስ ነው ፡፡ Neilsen Sports የተባለ ዓለም አቀፍ ተቋም የዓለም ስፖርት የንግድ አቅጣጫዎች በሚል ርእስ ይፋ ባደረገው ሪፖርት ከስፖንሰርሺፕ እና ከተለያዩ ንግዶች ጋር በተያያዘ እስከ 62 ቢሊዮን ዶላር እንዲሁም ከሁለገብ የሚዲያ መብት ጋር በተገናኘ እስከ 45 ቢሊዮን ዶላር ወጭ ተድርጎ በዓለም የስፖርት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡
በሌላ በኩል ታዋቂው የቢዝነስ መፅሔት Forbes ፎርብስ ጥናት አድርጎ ይፋ ባወጣው ሪፖርቱ በዓለም ስፖርት በአሁኑ ወቅት ቢያንስ 1 የስፖርት ክለብ ወይም ቡድን በባለቤትነት የያዙ 63 ቢሊዬነሮች ተመዝግበዋል። በ78 የስፖርት ቡድኖችና ክለቦች ከፍተኛ የባለቤትነት ድርሻ ያላቸው እነዚህ 63 ቢሊዬነሮች አጠቃላይ የሃብታቸው ድምር ግምት ከ322 ቢሊዮን ዶላር በላይ ነው፡፡  በተለያዩ የስፖርት ቡድኖች እና ክለቦች  የአክሲዮን ድርሻ ያላቸው 128 ቢሊዬነሮች የተመዘገቡ  ሲሆን 47 የሚገኙት በ40 የእግር ኳስ ክለቦች የባለቤትነት ድርሻ በመያዝ ነው። በተጨማሪም በዓለም ዙሪያ ከ1 ቢሊዮን ዶላር በላይ የዋጋ ግምት ያላቸው የተለያዩ የስፖርት ቡድኖችና ክለቦች ብዛት ከ81 በላይ እንደደረሰ ታውቋል። በስፖርቱ ኢንቨስት ካደረጉ የዓለም ቢሊየነሮች ከፍተኛውን የብዛት ድርሻ የያዙት በአሜሪካ የሚካሄዱ እግር ኳስ ውጭ በሆኑ የስፖርት ውድድሮች ላይ ኢንቨስት ያደረጉት ሲሆኑ በአሜሪካ የቅርጫት ኳስ የቤዝቦል እና ፉትቦል ሊግ 40 ያህሉ በመገኘታቸው ነው።
በፎርብስ መፅሄት የጥናት ውጤት መሰረት በዓለም የፕሮፌሽናል ስፖርቶች እንቅስቃሴ በከፍተኛ የባለቤትነት ድርሻ ኢንቨስት ያደረጉ ቢሊየነሮች ብዛት እየጨመረ የሚገኘው የግሎባላይዜሽን ተፅእኖ ወሳኝ እየሆነ በመምጣቱ፤ የተለያዩ የስፖርት ምርቶች እና ቁሳቁሶች ሽያጭ እያደገ በመሆኑ፤ የቴሌቭዥን ስርጭት ለብራንዶች እድገት ከፍተኛ እገዛ ማድረጉና ሌሎችም መጠነ ሰፊ የገቢ ምንጮች በመፈጠራቸው ነው። ቢሊዬነሮቹ በተጨዋቾች ግዢ ተፅእኖ በመፍጠር፤ በአሰልጣኞች የስራ ዋስትና ላይ አደጋ በመጣል አሻራቸውን እያሳረፉ ናቸው፡፡

በአምስቱ የአውሮፓ ታላላቅ ሊጎች
በየዓመቱ ከቴሌቭዥን የስርጭት መብት 7.85 ቢሊዮን ዶላር፤ በስፖንሰርሺፕ እና ሌሎች የንግድ ገቢዎች 5.47 ቢሊዮን ዶላር፤ በስታድዬም ገቢ 2.62 ቢሊዮን ገቢ
KPMG ኬፒኤምጂ እና Delieotte ዴልዮቴ ባለፈው የ2016/17 የውድድር ዘመን ላይ በሰሩት ሪፖርት እንደተመለከተው ከሆነ በዓለም የስፖርት ገበያ ከፍተኛው መዋዕለንዋይ እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው በአውሮፓ እግር ኳስ ላይ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በአውሮፓ 5 ታላላቅ ሊጎች የሚንቀሳቀሱ፤ የቢሊዬነሮች ኢንቨስትመንት የሚፈስባቸውና በየዓመቱ ከፍተኛ ገቢ እና ትርፍ የሚያስመዘግቡ 32 ትልልቅ ክለቦች የዋጋ ግምታቸው 39.15 ቢሊየን ዶላር በላይ እንደሚገመት የሁለቱ ተቋማት ሪፖርቶች ያመለክታሉ፡፡ በዴሊዮቴ አማካኝነት በተዘጋጀው የ2017 የአውሮፓ እግር ኳስ ዓመታዊ የክለሳ ሪፖርት ላይ እንደተጠቆመው የአውሮፓ እግር ኳስ ገበያ በየዓመቱ ከ29.75 ቢሊዮን ዶላር በላይ እየተንቀሳቀሰ ሲሆን  እስከ 20ኛ ደረጃ የተሰጣቸው ክለቦች ከ145.5 ሚሊዮን እስከ 820 ሚሊዮን ዶላር ገቢ በየዓመቱ እያስመዘገቡ ናቸው። የአውሮፓ እግር ኳስ ገበያ በገቢው እድገት በማሳየት እየተጠናከረ የሚገኘው ከቴሌቭዥን የስርጭት መብት ጋር የተያያዘ እንደሆነ ዴሊዮቴ በሪፖርቱ ሲያመለክት፤ አምስቱ የአውሮፓ ታላላቅ ሊጎች ባለፈው የውድድር ዘመን ገቢ ካደረጉት 29.3 ቢሊዮን ዶላር ግማሹን እንደሚሸፍን በመጥቀስ ነው፡፡ በተለይ ባለፉት ሁለት የውድድር ዘመናት የአምስቱ የአውሮፓ ታላላቅ ሊጎች ገቢ እየጨመረ ሲሆን ይህ ሁኔታም ለሚቀጥሉት 3 የውድድር ዘመናት የሚቀጥል ይሆናል፡፡ የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ 5.83 ቢሊዮን ዶላር፤ የጀርመን ቦንደስ ሊጋ 3.213 ቢሊዮን ዶላር፤ የስፔን ፕሪሚዬራ ሊጋ 2.86 ቢሊዮን ዶላር፤ የጣሊያን ሴሪኤ 2.26 ቢሊዮን ዶላር እንዲሁም የፈረንሳይ ሊግ1 1.79 ቢሊዮን ዶላር ባለፈው የውድድር ዘመን ገቢ አድርገዋል፡፡ በአምስቱ የአውሮፓ ታላላቅ ሊጎች በየዓመቱ ከቴሌቭዥን የስርጭት መብት 7.85 ቢሊዮን ዶላር፤ በስፖንሰርሺፕ እና ሌሎች የንግድ ገቢዎች 5.47 ቢሊዮን ዶላር፤ በስታድዬም ገቢ 2.62 ቢሊዮን ገቢ እንደሚሆን የዴሊዮቴ ሪፖርት አመልክቷል፡፡

የስፖርተኞች ደሞዝ
በዓለም ዙርያ በዓመት ከ18.3 ቢሊዮን ዶላር በላይ
በ5ቱ የአውሮፓ ታላላቅ ሊጎች በዓመት 9.76 ቢሊዮን ዶላር በላይ
በዓለም አቀፍ ደረጃ በስፖርት መስክ በተለያዩ የስፖርት አይነቶችና ውድድሮች ለስፖርተኞች የሚከፍለው ዓመታዊ ደሞዝ ከ18.3 ቢሊዮን ዶላር በላይ መሆኑን ያመለከተው ‹‹ግሎባል ስፖርት ሳለሪ ሰርቬይ›› የተባለ  ሰነድ ነው፡፡  ለሰባተኛ ጊዜ በስፖርት ኢንተለጀንስ አማካኝነት በተዘጋጀው GSSS 2016 ሰነድ በዓለም ዙሪያ የሚንቀሳቀሱ የስፖርት ቡድኖች፣ ክለቦች በሚወዳደሩባቸው ስፖርተኞች እና የቋሚ ቡድን ዓመታዊ እና አማካይ ክፍያዎች በማስላት የተዘጋጀ ነው።
በዓለም ዙሪያ በ13 አገራት የሚገኙ 333 የስፖርት ቡድኖችና ክለቦች፤ 17 የሊግ  ውድድሮች፣ 7 የስፖርት ዓይነቶች እንዲሁም 9,776 ስፖርተኞች ላይ የደሞዝ ስሌቱ እንደተሰራ ለማወቅ ተችሏል፡፡ በመላው ዓለም ዙሪያ በሚካሄዱት የስፖርት እንቅስቃሴዎች በዓመት 18.3 ቢሊዮን ዶላር ለደሞዝ ክፍያ ወጭ እንደሚሆን በግሎባል ስፖርት ሳለሪስ ሰርቬይ ሲመለከት ከፍተኛውን የደሞዝ ወጭ በማውጣት የአውሮፓ እግር ኳስ ቀዳሚ ሲሆን በተለይ በዓመት ከ9.76 ቢሊዮን ዶላር በላይ ለደሞዝ ወጭ የሚያደርጉት አምስቱ የአውሮፓ ታላላቅ ሊጎች የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
በGSSS 2016 ሪፖርት መሰረት በ5ቱ የአውሮፓ ታላላቅ ሊጎች የሚወዳደሩ ክለቦች ቋሚ የቡድን ስብስብ እና የአንድ ቋሚ ተሰላፊ ተጨዋች አማካይ ዓመታዊ ደሞዝ ከዚህ ቀጥሎ እንደቀረበው ነው፡፡
የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ
ዓመታዊ ደሞዝ - 1.7 ቢሊዮን ዶላር
ያንድ ተጫዋች አማካይ ዓመታዊ ደሞዝ  - 3.22 ሚሊዮን
 የስፔን ፕሪሜራ ሊጋ
ዓመታዊ ደሞዝ -806.5 ሚሊዮን ዶላር
ያንድ ተጫዋች አማካይ ዓመታዊ ደሞዝ  - 1.64 ዶላር
የጣሊያን ሴሪ አ
ዓመታዊ ደሞዝ -791.01 ሚሊዮን ዶላር
ያንድ ተጫዋች አማካይ ዓመታዊ ደሞዝ  - 1.46 ሚሊዮን ዶላር
የጀርመን ቦንደስ ሊጋ
ዓመታዊ ደሞዝ -715.13 ሚሊዮን ዶላር
ያንድ ተጫዋች አማካይ ዓመታዊ ደሞዝ  - 1.37 ሚሊዮን ዶላር
የፈረንሳይ ሊግ 1
ዓመታዊ ደሞዝ -525.1 ሚሊዮን ዶላር
ያንድ ተጫዋች አማካይ ዓመታዊ ደሞዝ  - 961.64 ሺ  ዶላር

በዓመታዊ ገቢ እና ክፍያ እግር ኳስ ተጨዋቾች እየመጠቁ ናቸው
ክርስትያኖ ሮናልዶ በ93 ሚሊዮን ዶላር የዓለምን ስፖርት ይመራል
በዓመታዊ ገቢ እና ክፍያ የዓለም ስፖርትን በአንደኝነት የሚመራው የእግር ኳስ የወቅቱ ኮከብ ተጫዋች የሆነው ፖርቱጋላዊው ክርስቲያኖ ሮናልዶ  በ93 ሚሊየን ዶላር ዓመታዊ ገቢው መሆኑን ያስታወቀው ፎርብስ መፅሄት ነው፡፡ ባለፉት 15 ዓመታት በተመሳሳይ የደረጃ ሰንጠረዥ በመሪነቱ ስፍራ ላይ ይፈራረቁ የነበሩት ዕውቁ የጎልፍ ስፖርተኛ ታይገር ውድስ እና እውቁ ቦክሰኛ ሜዬሜልር ነበሩ፡፡ በ2017 ግን ይህን ሁኔታ ክርስትያኖ ሮናልዶ የቀየረው በሚጫወትበት ሪያል ማድሪድ ክለብ በደሞዝ እና በተለያዩ ቦነሶች በ12 ወራት ውስጥ 58 ሚሊዮን ዶላር እንዲሁም ከተለያዩ ስፖንሰሮች እና የንግድ ስራዎች 35 ሚሊዮን ዶላር በማግኘቱ ነው፡፡
በፎርብስ መፅሄት በከፍተኛ ዓመታዊ ገቢያቸው ከ1-100 ደረጃ የተመዘገቡ የዓለማችን ታላላቅ  ስፖርተኞች በ12 ወራት ውስጥ ከ3.11 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ማስመዝገባቸው ተጠቅሶ፤ 100 ዎቹ በዓለም ስፖርት ከፍተኛ ገቢ ያላቸው ስፖርተኞች አማካይ እድሜያቸው 31 ዓመት እንደሆነና 21 የተለያዩ አገራት ዜግነት እንዳላቸው ተመልክቷል፡፡
በዓመታዊ ገቢያቸው እስከ 100ኛ ደረጃ ከተጠቀሱት የዓለማችን ስፖርተኞች ከ11 የተለያዩ ስፖርቶች የተሰባሰቡ ከአሜሪካፉትቦል  15፣ ከእግር ኳስ 9፣ ከሜዳ ቴኒስ  9፣ ከሞተር ስፖርት 5፣ ከጎልፍ ስፖርት 5፣ ከቦክስ ስፖርት 2፣ ከክሪኬት 2 እንዲሁም ከአትሌቲክስ 1 ናቸው፡፡ በዚሁ የደረጃ ዝርዝር የጎልፍ እና የሜዳ ቴኒስ ስፖርተኞች በማስታወቂያ እና የስፖንሰርሺፕ ገቢያቸው ከሁሉም የተሻለ ድርሻ ስላላቸው እንዲሁም ብዙዎቹ የአሜሪካፉትቦል፤ ቅርጫት ኳስ እና ቤዝቦል ስፖርተኞች በዓመት በአማካይ 30 ሚሊዮን ዶላር ማስገባታቸው በብዛት እንዲካተቱ አድርጓቸዋል፡፡ በነገራችን ላይ ከአትሌቲክስ ስፖርት በብቸኝነት የተካተተ ስፖርተኛ ዩሴን ቦልት መሆኑ የሚያስገርም  ሲሆን በ34.2 ሚሊዮን ዶላር ዓመታዊ ገቢና ክፍያ 23ኛ ደረጃ ላይ ነው፡፡

በከፍተኛ ዓመታዊ ገቢ እና ክፍያ
ክርስቲያኖ ሮናልዶ - እግር ኳስ - 93 ሚ. ዶላር
ሊብሮን ጀምስ - ቅርጫት ኳስ - 86.2
ሊዮኔል ሜሲ - እግር ኳስ - 80
ሮጀር ፌደረር - ሜዳ ቴኒስ -64
ኬቨን ዱራንት - ቅርጫት ኳስ - 60.6
አንድሪው ለክ - የአሜሪካ ኳስ - 50
ስቴፈን ኩሪ - ቅርጫት ኳስ - 7,47.3
ጀምስ ሃርዱን - ቅርጫት ኳስ - 46.6
ልዊስ ሃሚልተን - ሞተር ስፖርት - 46

በዓለም እግር ኳስ የክረምት ዝውውር ገበያ 4.7 ቢሊዮን ዶላር ወጭ ሆኗል  
ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ፌደሬሽኖች ማህበር ፊፋ ሰሞኑን በድረገፁ ባሰፈረው ሪፖርት በ2017 እኤአ በዓለም እግር ኳስ ለ3 ወራት በቆየው የዝውውር ገበያ ከ7590 ተጨዋቾች ጋር በተያያዘ 4.7 ቢሊዮን ዶላር ወጭ ሆኗል፡፡ በአምስቱ  የአውሮፓ ሊጎች በክረምት የዝውውር ገበያ ከ3.67 ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጭ መሆኑን የጠቀሰው ፊፋ ይህ የወጭ መጠን ከአጠቃላይ ገበያ 77.9 በመቶ ድርሻ እንደሚወስድ አስታውቋል። ከዚህ በታች የቀረበው በአውሮፓ አምስት ታላላቅ ሊጎች የሚገኙ 10 ክለቦች በክረምቱ የዝውውር ገበያ ወጭ ያደረጉት ነው፡፡
ኤሲ ሚላን -203.03 ሚሊዮን ዶላር
ማንቸስተር ሲቲ - 179.45
ማን. ዩናትድ - 137.55
ኤቨርተን - 119.21
ሪያል ማድሪድ - 102.18
ባየርሙኒክ - 99.56
ቼልሲ - 90.39
ሮማ - 86.46
አርሰናል - 69.040

Read 3206 times