Monday, 18 September 2017 10:38

ጉስቁልናችንን ማን ሰረቀን? ስቃያችን ለምን መከነ?

Written by  ያዕቆብ ብርሃኑ
Rate this item
(5 votes)

 የአማርኛ ስነ-ጽሑፍን በቅርቡ የተቀላቀለ የአጻጻፍ ይት ባህሉ የሚመስጠኝ አንድ ደራሲ አለ፡፡ በብዕር ስሙ ኦታምፑል ቶይ ባላል፡፡ ‹የሲሳዬ ልጆች፣ ኬክሮስና ኬንትሮስ› የተሰኘ መጽሐፉን ሳነብ፣ ገጽ 104 ላይ በገፀ ባህሪያቱ ምልልስ አማካኝነት የሚደንቅ ሐሳብ አስፍሮ አየሁ፡፡ እንዲህ ይነበባል፡፡-
‹‹የቻይናውያን ውርደት ኮንፊሸስና ላኦዙን፣ የራሺያውያን ስቃይ ፑሽኪንና ዶስቶየቭስኪን፣ የደቾች ሰቆቃ ቫንጎን፣ችና የደቡብ አፍሪካውያን ወዮታጋንዲንና ማንዴላን፣ የጥቁር አሜሪካውያን ህማም የጃዝ ሙዚቃን ሲወልድ፣ ምነው የሃበሻ ረኃብና ድኅነት፣ ውርደትና ሐፍረት እንዲህ (“መከነ?››  የሲሳዬ ልጆች፣ ኬክሮስና ኬንትሮስ” ገፅ 104
እንዴት የሚደንቅ እይታ ነው! በዓለም ላይ ከአይሁዳውያን ቀጥሎ እጅግ የበዛ ስደት፣  ረሃብ፣  ግዞት፣ ቸነፈር፣ ጦርነት… የተጋፈጡ ህዝቦች ብንኖር እኛው ነን፡፡  ኢትዮጵያውያን ለሺህ ዓመታት የተሸከምነው ጭቆና፣ ጫንቃችን ያጎበጠው ምንዱብ ህዝቦች፣ በአንድ ክርስቶስ ስም በተሳሉሁለት መንታ ሰይፎች እንካስላንትያ የተቃመስንና ይህን ታሪክ በደማችን የጻፍን፣ ‹ስዩመ እግዚያብሔራዊ› ሺህ ፈላጭ ቆራጭ ነገስታትን ያገለገልን፣ ከሺንብራ ኩሬ እስከ አድዋ የሞትን የተጋደልን፣ ለጭቃ ሹም ያደገደግን፣ ለምስለኔ ያገለደምን ህዝቦች… እኛው ነን… እኛው፡፡
በእርግጥ ‹በራሳችን› ፊደል እንጽፋለን፡፡ ፊደል አለን፡፡ ሆኖም ዛሬም ሚሊዮናት ወገኖቻችን መሀይማን ሆነው እናያለን፡፡ በዓመት በአማካይ አስር ገጽ የማያነቡ፣ በዓለም አቀፍ የሐሳብ ገበያ ምንም ሐቲት ያላዋጡ የተናቁ ሕዝቦች ነን፡፡ ሙዚቃን በኖታ በመጻፍ የመጀመሪያዎቹ ሆነን ሳለን ሙዚቃ የማይገባቸው ዘላኖች ተብለን እንሰደባለን፡፡ ለአክሱም ሐውልትና ለላሊበላ ውቅር አቢያተ ክርስቲያናት፣ ዛሬም ከሺህ ዓመታት በኋላ በዓድ ነን፡፡ እነዚህን እጹብ ድንቅ የኪነ-ሕንፃ ጥበባት ያቆምን እኛ፣ የምንኖረው ዛሬም በደሳሳ ጎጆ ውስጥ ነው፡፡
እናስ ጉስቁልናችንን ማን ሰረቀው? ስቃያችን ለምን መከነ? ኦታምፑልቶ ለዚህም ተከታይ ጥያቄ የተጠቀሰው ገፅ ላይ መልስ አለው፡፡
‹‹የራሳችንን ሸክም እንኳን ለብቻችን ለመሸከም ስለማንፈቅድ ነው፡፡ …ታዲያ የሁላችንንም ቀንበር ተሸክሞ አርነት የሚያወጣን መሲህ ከወዴት ይምጣ? የእያንዳንዳችንን የሰቆቃ ዝቃጭ ጨልጦ፣ ትንሳዔያችንን ያውጅ ዘንድ ማንን እንጠብቅ? እስራዔላውያንን ከግብፅ ባርነት ያወጣው ማህበርና እድር ነበር? አይደለም፡፡ አረባውያንን ከድንቁርናና ከጣኦት አምልኮ የታደገው ማህበርና እድር ነበር? አይደለም፡፡  አንድ ሰው ነው፡፡  አንድ ሰው ብቻ … በፈሪነታችን፣ በሽሽታችን፣ በግለ እምነት አልባነታችን፣ …ፍጹም ድህነትን የመሰለ ሀብት፣ ፍጹም ውርደትን የመሰለ ክብር፣ [እንዴት] እንዲሁ ባክኖ፣ ፍጹም ከንቱ ሆኖ ይቅር?...››   
ጭቆና ለአንድ ዓይነት የሕይወት ለዛ ግኝት፣ የኪነት ፈጠራ፣ የጀግንነት ሙያ፣ የጋራ ተጋድሎ መነሻ ነጥብ መሆኑ እሙን ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን ግን ከዚህ ሁሉ ስቃያችን፣ መታረዛችን፣ መገለላችን፣ ለዓለም ሁሉ በተለፈፈ መራባችን…ቀለም አጥቅሰን የሚወክለን አንድ ዓይነት ምስል መፍጠር አልቻልንም፡፡ ስንኝ ቋጥረን ዜማ አልብሰን ለመዝፈን መውተፍተፋችን ባይቀርምዛሬም ዓለም ሁሉ የሚያውቀን በረሃብ ተምሳሌነታችን ብቻ ሆኗል፡፡የእልፍ አዕላፍት እንስቶቻችን እንባ፣ የጭሰኞችን ሁሉ ዋይታ የሚውጥ የሚያሰርግ የደደረ ሰብዕናችን ከየት መጣ? እናስ ጉስቁልናችንን ማን ሰረቀን? ስቃያችን ለምን መከነ?
የአሜሪካ የእርስ በእርስ ጦርነት እንደ አብርሃም ሊንከን ያለ የማይናወጥ ብልህ መሪን ፈጠረ፡፡ የህንዳውያን ጭቆና የምዕተ ዓመቱን ታላቅ ሰብዕና ጋንዲን አስገኘ፡፡ የአፓርታይድ አሰቃቂ አገዛዝ ለእኛ እንኳን የተውሶ ጀግናችን የሆኑትን ኔልሰን ማንዴላን አጎላ፡፡ የአየርላንዳውያን በእንግሊዞች በኃይል መወረር ለጆርጅ በርናንድ ሾው ዓይነት ጠቢባን መነሻ ቁጭትን እንደሰጠ ይታመናል፡፡ የእኛ ለሺህ ዓመታት የተለጠጠ ስፍር ቁጥር የለሽ መጫረስ እንዴት አንድ ዓይነት የሕይወት ለዛ፣ አንድ ጀግና መፍጠር ተሳነው? የእኛ ፍጂት የእሪያዎች ነበር እንዴ? ከሆቺሚኒ እስከ ቼጉቤራ …ጭቆና ጀግኖችን ይፈጥራል፡፡ እኛ ጋ ሲመጣ ይህ እንዴት ሊሰራ አልቻለም?
መገለልና መናቅን ያክል ቁጭት፣ መራብንና በሰንደቃላማችን መለመንን ያክል ውርደት፣ መሰደድን ያክል ግዙፍ ሐፍረት ተከናንበን እንዴት አንድ ጋንዲን፣ አንድ ማንዴላን፣ አንድ ፑሽኪንን፣ መፍጠር ተሳነን? የጋራ ስቃይን ያክል ውድ ሀብት ይዘን እንዴት በህብረት የምንዘምረው አንድ መዝሙ ር አጣን? እውነትስ የእኛ የሺህ ዓመታት ስቃይ፣ ጭቆና፣ ጉስቁልና፣ ረሃብ፣ እጦት፣ ቸነፈር... የሆነ ዓይነት ንጥር ግኝት፣ ጀግንነት፣ ጥበብ መፍጠር ለምን ተሳነው? ለምን? ጥበብም ሆነ ታላላቅ ሰዎች የሚፈጠሩት ይህን በመሰለው ተቃርኖ ውስጥ አልነበረምን? ስቃያችንን ማን ሰረቀን? እና ለምንከዚህ የስቃይ ሀብታችን ወርቁን ማውጣት ተሳነን? ለምን? እናስ ጉስቁልናችን ለምን መከነ? ስቃያችንን ማን ሰረቀን?  

Read 1982 times