Saturday, 07 April 2012 09:28

የሦስት ዓመቱ ሕፃን የፎቶ አውደርዕይ ያቀርባል ጊነስ ላይ እንዲመዘገብ ይፈልጋል

Written by  መልካሙ ተክሌ (melkamutekele@gmail.com)
Rate this item
(0 votes)

በተወለደ ገና በስድስት ወሩ የካሜራና ሞባይል ስልክ መነካካት የጀመረው የሦስት ዓመቱ ሕፃን ኤልያታ ዳንኤል ያነሳቸውን ፎቶግራፎች በአውደርእይ ሊያሳይ ነው፡፡ አባቱ አቶ ዳንኤል ተፈራ እና እናቱ ወይዘሮ አይዳ ሰሎሞን መርሃግብሩን ከሚያዘጋጀው ትራፓ ካፒታል ጋር በመሆን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ ሕፃን ኤልያታ ያነሳቸው 450 የታዋቂ ሰዎች የተፈጥሮ አካባቢዎች እና ሌሎች ፎቶግራፎች በአውደርእዩ ለእይታ እንደሚቀርቡ ጠቁመው፤ ሕፃን ፎቶግራፈሩ የዓለም የድንቃድንቅ ታሪኮች መዝገብ በሆነው “ጊነስ ቡክ ኦፍ ወርልድ ሪከርድስ” ለማስመዝገብ ጥረት እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡ በመጪው የአፍሪካ ህብረት መሪዎች ጉባኤ ላይ በዕድሜ አነስተኛው ፎቶግራፈር እንዲሆን ከመንግስት ኮሙኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ቀና ምላሽ እያገኙ እንደሆነም ወላጆቹ ተናግረዋል፡፡ ሕፃን ኤልያታ ሞባይል ስልክ እና ካሜራ በመጠቀም በተከታታይ ፎቶግራፎች ሲያነሳ እንደነበር ማየት ችለናል፡፡

የትራፓ ካፒታል ባለቤት አቶ ናትናኤል ጋሻው በዚሁ ወቅት “ሕፃናት ብዙ የተደበቀ ችሎታ ቢኖራቸውም የማስተዋወቅ ልምዱ ስለሌለን ለሕዝብ ይፋ አልሆኑም፣ በዚህ መቀጠል የለብንም” በማለት ሕፃናት ችሎታቸውን እንዲያሳዩ ተማጽኗል፡፡ የሕፃኑ ወላጆች በበኩላቸው ልጃቸው እነሱ ካነሱት ፎቶ የተሻለ ፎቶ እያነሳ መሆኑን መስክረዋል፡፡

 

 

Read 1615 times Last modified on Saturday, 07 April 2012 09:29