Print this page
Sunday, 17 September 2017 00:00

ኧረ ስማኝ ሀገሬ!

Written by  ከተሾመ ብርሃኑ ከማል
Rate this item
(7 votes)

 “ሁሉም ስልጣን ፈላጊ ሆነ፤ ወንበሯ ደግሞ አንዲት...” - የቀድሞው ፕ/ት
                
        ያገሬ ሕዝብ፣ ባለፈው ዓመት በሀገርም ሆነ በውጭ አገሮች የተከናወኑ በጎ ነገሮች እንዳሉ እርግጥ ነው። ኢትዮጵያ አለም አቀፍ ድጋፍ በማግኘቷም በጸጥታ ምክር ቤት፣ በዓለም ጤና ድርጀት፣ በአፍሪካ ህብረት ሁነኛ ተሳትፎ አድርጋለች። መንግሥት ሁለት ጊዜ መሠረታዊ የስልጣን ሹምሽር አካሂዷል። በዚህ ሹምሽር ነባር ታጋዮች ተገልለው፣ አገራቸውን ሊያገለግሉ ይችላሉ ተብለው የታመነባቸው ምሁራን ተተክተዋል። አገሪቱ  በፖለቲካ ስትናጥ መባጀቷና ለአንድ አመት ያህል በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሥር እንደነበረችም  እርግጥ ነው። ተቃዋሚዎች ሰፋፊ እርሻዎችን ያቃጠሉትና ፋብሪካዎችን ያወደሙትም ባለፈው ዓመት ነበር። በኢሬቻ በዓልም ብዙ የሰው ህይወት አልፏል፡፡ በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በሱማሊ፣ በአፋር የተከሰቱት ግጭቶችም በዝምታ የሚታለፉ አይደሉም። ሌሎችም ደስ የማይሉ ክስተቶች ነበሩ። በአንጻሩም በአዋሳ፣ በመቀሌ፣ በአዲስ አበባ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ተገንብተዋል።
በሙስና የተጠረጠሩ አንቱ የተባሉ የመንግሥት ባለሥልጣናትና ቱባ ባለሃብቶች በቁጥጥር ሥር የዋሉትም ባሳለፍነው ዓመት ነው፡፡ በሙስና በመጠየቅ ላይ የሚገኙት ባለስልጣኖች ጉዳይም፣ «ይህ እርምጃ የት ድረስ ይሄዳል፣ የት ላይስ ይቆማል? በሀብት የናጠጡ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጉዳይ ግን አይነኬ ነው የሚለው ሐሜትስ ተጣርቶ ይቀርባል? ወይስ እዚያ ላይ ሲደርስ ይቆም ይሆን?» ብዙ ያነጋገረ ጉዳይ ነው። እዚህ ላይ በጃንሆይ ዘመን የሆነው ትዝ አለኝ። ጉቦኞች ቢኖሩም ያዝኑ ነበር። ለምሳሌ አንድ አህያው የጠፋበት ሰው፣ አፈርሳታ እንዲጣራለት ወደ ወረዳ ባለሥልጣን ቤት ይሄዳል።  አቤቱታውን እያቀረበ አምስት ሽልንግ ይሰጣቸዋል። እርሳቸውም ገንዘቡን እያዩ፤ « ኧረ አድነኝ-ኧረ እግዚኦ! አንተ ለኔ ይህን የምትሰጠኝ አህያይቱ ስንት ልታወጣ ነው?›› ብለው አራት ሽልንግ መለሱለት። ለወንበር (ጉዳይ ማስፈጸሚያ) የሚከፈለውም ከ25 ሳንቲም እስከ 2 ብር ቢደርስ ነው። ይህም በበግ ለሚተመን መተያያ ወይም የወንበር 25 ሳንቲም ቢከፈል፣ ለግመል 2 ብር ይከፈላል እንደ ማለት ነው። ወይም «ተደብድቤያለሁና ፖሊስ፣ ደብዳቢዬን ጣቢያ ወስዶ ይጠይቅልኝ» ለማለት 25ሳንቲም ቢከፍል፣ ሀብቴን ቤት ሠርሥሮ ሰርቆብኛልና ተይዞ ይጠየቅልኝ ለማለት እስከ 10 ብር መደለያ ሊሰጥ ይችላል፡፡
ግን ጉቦኝነት እስከ ምን ድረስ? ሙሰኝነት እስከ ምን ድረስ? አድልዎ እስከ ምን ድረስ? ከአነስተኛው ባለስልጣን እስከ ቱጃሩና በተለያዩ ስሞች እስከ ሚዘርፈው ይደርሳል? ማንስ ተደፍሮ ማን ይቀራል? ወይስ የኢትዮጵያ ባለስልጣኖች ነገር ተከድኖ ይብሰል ተብሎ ይተዋል? ወይስ ሌብነቱ እንደ ብረት ሰንሰለት የተያያዘና የማይበጠስ በመሆኑ ምክንያት ምናኔ ያስገባል። ለማንኛውም ሕልም ተፈርቶ ሳይተኙ አያድሩም እንዲሉ፣ ከደረሰበት እስኪደርስ አማራጭ አይኖረውምና ነው።
ከዚህም ባሻገር አገሪቱ፣ ጦርነትም ሲሞከርባትና ‹›እሽም እምቧ» ሲባልባት ነው ዓመቱ የባጀው፡፡ የዚህ ጽሑፍ አውድም በዚህ ዙሪያ ይሸከረከራል።
እንደሚታወቀው፣ ሀገራችን በዓለም ተፈርታና ተከብራ ከመኖር ወርዳ፣ ተሸማቃ የኖረችው በተካሄደባት የረዥም ዘመናት የእርስ በእርስ ጦርነት ነው፡፡ የዛጉዌ ኩሻዊ ስርወ መንግሥት፣ የአክሱም ስርወ መንግሥትንና ስልጣኔን አጥፍቶ የራሱን ለመተካት፣ የሸዋ ሰለሞናዊ ስርወ መንግሥት የዛጉዌን ስርወ መንግሥትና ስልጣኔን ለማጥፋት፣ የሸዋ ስርወ መንግስትን ለመጣል የአዳል ሱልጧኔት፣ የአዳል ሱልጧኔትን ለመጣል የኦሮሞ ገዳዊ ስርዓት፣ የኦሮሞ ገዳዊ ስርዓትን ለመጣል ዘመነ መሳፍንት፣ ዘመነ መሳፍንትን ለማስወገድ አጼ ቴዎድሮስ፣ አጼ ቴዎድሮስን ለመጣል አጼ ዮሐንስ፣ አጼ ዮሐንስን ለመጣል አጼ ምኒልክ፣ ከአጼ ምኒልክ በኋላ አጼ እያሱ፣ እያሱን ለመጣል አጼ ኃይለስላሴ፣ አጼ ኃይለስላሴን ለመጣል ደርግ፣ ደርግን ለመጣል ኢህአዴግ፣ አሁን ደግሞ ኢህአዴግን ለመጣል ጦርነት በተለይም በዘረኝነት ላይ የተመሠረተ የጦርነት ነጋሪት እየተጎሰመ ነው። ዘወር ብለን ማስታወስ የሚኖርብን፣ በዚህ ሁሉ ዘመን እጅግ አሰቃቂ በሆነ ሁኔታ ሰዎች ተገድለዋል፡፡ የእንስሳ፣ የደን ወዘተ እልቂት ተፈጽሟል። የሀገር ሀብት ወድሟል።
ጦርነትን ለማያውቁና በቀጥታ ለማይሳተፉበት ቀላል ነው፡፡ ሌላውን ሁሉ ትተን በርካሽ ዋጋ የገዙትን በውድ ዋጋ በመሸጥ አትራፊ ለመሆን ለሚፈልጉ ደግሞ መልካም አጋጣሚ ነው፡፡ ተደብቀው የፖለቲካ ዓላማቸውን ለሚያራምዱም ጥሩ የሚሆን ሊመስላቸው ይችላል፡፡ በትርፍ ጊዜያቸው ለሚያራግቡ ደግሞ የሚጎዳቸውም ሆነ የሚጠቅማቸው ላይሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን ጦርነት ከተነሳ፤ የአክሱም ስልጣኔን፣ የዛጉዌ ስልጣኔን ያጠፋው ጦርነት፣ የጎንደርን፣ የሸዋንና የሌሎችን ስልጣኔ አይምርም፡፡ ትውልድ ያልቃል፡፡ በሚሊዮን  የሚቆጠሩ የጦርነት ማገዶ ይሆናሉ፡፡ ይህን በምሳሌ ለማረጋገጥ ሶሪያን፣ ኢራቅን፣ ወዘተ መጥራት አያስፈልገንም፤ የጦርነት ታሪካችን እራሱ ምስክር ነው፡፡
ለመሆኑ ችግራችን ምንድነው? ምን ይሁን? ምን ይደረግ? የችግሩ መንስኤ የአስተዳደር በደል ነው፡፡ ይህም የአስተዳደር በደል፣ መካሪም ዘካሪም፣ ተከራካሪም ሳይኖረኝ እኔ ብቻ ልግዛ ከሚል የአንድ ፈላጭ ቆራጭ አምባገነን ድርጅት የሚመነጭ ነው። ከዚህ ምንጭም እራስ ወዳድነት፣ ተጠራጣሪነት፣ ተንኮል፣ ጭካኔ፣ አስመሳይነት፣ ግፈኝነት ይንፎለፎላል። ይህ በተለያዩ ሀገሮች ታይቷል። ተረጋግጧልም። በሀገራችንም ለስልጣኔያችን መውደምና ለድህነት መንሰራፋት ዋነኛ ምክንያት ሆኖ ቆይቷልና አልሰራም፤ ወደፊትም አይሰራም፡፡
ፕሬዚደንት መንግሥቱ ኃይለማሪያም የዲሞክራሲ ጥያቄ ሲነሳባቸው፤ «ሁሉም ስልጣን ፈላጊ ሆነ ወንበሯ ደግሞ አንዲት...» ማለታቸው ይታወሳል። እንዳሉትም መቶ ተቀናቃኝ ቢኖር ተደራርቦ አይቀመጥባትም። ነገር ግን «ወንበሯን ደግሞ እኔ ተቀምጨባታለሁና አደብ ግዙ» ማለት መልስ ሊሆን አይችልም።  መፈንቅለ መንግሥቱን ሲያካሂዱ፣ «የሠራዊቱ ዓላማ፣ በሀገሪቱ ፍትሃዊ ስርዓት አስፍኖ ወደ ጦር ካምፑ መመለስ ነው።›› በማለት ለሕዝብ ቃል በገቡት መሠረት፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሕዝባዊ መንግሥት ማቋቋም ይገባቸው ነበር። ሳይሆን ቀረና ወንበሩ ላይ ተቀምጠው መኖር አማራቸው። ለነገሩ የግብጹ መሪ ጀማል ዓብዱናስርም፣ የኢራቁ መሪ ሳዳም ሑሴንም፣ የሊቢያው ቐዛፊም፣ ወዘተ በኃይል የያዙትን ስልጣን ያጡት በኃይል ነው። ሆኖም በስልጣን ላይ እያሉ የሸረቡት ሴራ፣ ዛሬም ሕዝብን ያተራምሳል፡፡ «አምባገነኖችን በኃይል አስወግደን ሕዝባዊ  ስርአት እንገነባለን» ያሉት ሁሉ አገራቸውን ወደ ምድራዊ ሲኦል ሲለውጧት እንጂ የተሻለ ዴሞክራሲያዊ አገር ሲገነቡ አልታዩም።
ተገቢ ጥያቄዎችን መጠየቅ ህገ መንግስታዊ መብት ነው፡፡ በሥልጣን ላይ ያለ መንግስት ደግሞ ተገቢውን መልስ መስጠት ሃላፊነቱ  ነው፡፡ እናም---- በዚች አገር እኩል የሆነ የእምነት ነጻነት አለ ወይ? በዚች አገር እኩል የሆነ ሐሳብን የመግለጽ ነጻነት አለ ወይ? በዚች አገር በሁሉም ክልሎች ፍትሐዊ አስተዳደር አለ ወይ? ወይስ በምናመጣው ልማት መብላት ከቻላችሁ መናገር ይቅርባችሁ እየተባለ ነው? እሱንም በግልጽ አማርኛ ቢነግሩን ይገባን ነበር፡፡ እስከዚያው ግን ህዝብ መጠየቁን አያቆምም። የሚሻለውና የሚያዋጣው ደግን ለህዝብ ፍላጎት መገዛት ብቻ ነው፡፡ ህዝብን ማድመጥ፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ታሪካዊ እርቅን ለማምጣት ከመጣር ይልቅ በሰበበ ብሔራዊ እርቅ በስልጣን ላይ ለመንጠላጠልና በተራቸው የአስተዳደር በደል ለመፈጸም ያሰፈሰፉ ቡድኖች መኖራቸውን እያስተዋልን ነው፡፡ ከሁሉም በላይ አስፈሪው ደግሞ ዘረኛ አመለካከታቸው ነው፡፡ የእነዚህ ቡድኖች ወደ ሥልጣን መምጣት የህዝቡን  የዲሞክራሲ ጥያቄ የሚያዘገይ እንጂ የሚመልስ አይሆንም፡፡ በዘረኝነት ላይ የተመሰረተው ጥላቻቸው፣ ከሁሉም የከፋ በሽታ ነው፡፡ መርዝ ነው፡፡  ኢትዮጵያዊ አንድነትንና ኢትዮጵያዊ ወንድማማችነትን አስረስቶ ዞንን፣ ወረዳን፣ ቀበሌን የሚለያይ የዘር ፖለቲካ አይናቸውን የጋረዳቸው ኃይሎች በመሆናቸው ለአገርም ሆነ  ለህዝብ አደገኛ ጠንቅ ናቸው፡፡ ስለዚህም ጦርነት አንዳንድ የዋሆች እንደሚገምቱት በቀላሉ አይመጣም እንጅ ቢመጣ ምህረት የለሽ ሊሆን እንደሚችል ለመገመት መቻል አለብን፡፡

Read 5192 times