Monday, 18 September 2017 10:19

አንብሮ፣ ተቃርኖ እና አስተፃምሮ - የዕድገት ህግ

Written by  ብሩህ ዓለምነህ (በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህርና “የኢትዮጵያ ፍልስፍና” መፅሐፍ ደራሲ brooha3212@gmail.com)
Rate this item
(2 votes)

  በቅድመ ልደት በበሬ እናርስ ነበር፤ በድንጋይ ወፍጮም እንፈጭ ነበር፡፡ ቤታችንም ደሳሳ ጎጆ ነበር። ፈጣኑ መጓጓዣችንም አህያ፣ ፈረስና በቅሎ ነበሩ። መካከለኛው ዘመን ላይም የሥራ መሳሪያዎቻችን ላይ ምንም ዓይነት ማሻሻያ ሳይደረግባቸው ሞፈር፣ የዲንጋይ ወፍጮ፣ ደሳሳ ጎጆና የጋማ ከብቶች ሆነው ቀጠሉ። ትውልድ ይመጣል፣ ትውልድ ይሄዳል። ትውልድ ቢቀያየርም የሥራ መሳሪያዎቻችን ግን እንዳሉ ናቸው፡፡ ምን ሆነን ነው? ምንድን ነው አንድ ቦታ ቸንክሮ ያስቀረን?
15ኛው ክ/ዘ ላይ ግን ይሄንን ሁኔታ የሚያሻሽሉ፣ በእምነት ግን ትንሽ የተለዩ ደቂቀ እስጢፋኖሳውያን ተነሱ፡፡ እነዚህ የአባ እስጢፋ ተከታዮች፣ በውሃና በንፋስ የሚሰሩ ወፍጮዎችን፣ ተሽከርካሪ ሰረገላዎችን፣ ቅባት መጭመቂያና ውሃ መቅጃ መሳሪያዎችን ሰርተው ንጉሱን አስገረሙት፡፡ ህዝቡ ግን ከደቂቀ እስጢፋኖሳውያን እውቀትንና የእጅ ሙያን ከመቅሰም ይልቅ በእምነት መለየታቸው ይበልጥ አብከነከነው። ተብከንክኖም አልቀረም፤ አሳዶም ፈጃቸው እንጂ። በዚህም የእስጢፋኖሳውያን እውቀትና የእጅ ሙያ ለትውልድ ሳይተላለፍ ጠፍቶ ቀረ፡፡ ህዝቡም ወደ ቀደሙት የጥንት የሥራ መሳሪያዎቹ ተመለሰ - ሞፈር፣ የዲንጋይ ወፍጮ፣ ደሳሳ ጎጆና የጋማ ከብቶች፡፡
የብርሃን ጭላንጭሉን አጠፋንና ዳግም በድንቁርና ተቸነከርን፡፡ ዘመናት መጡ፤ ዘመናት ነጎዱ፡፡ የእኛ ነገር ግን ምንም ለውጥ የሚታይበት አልሆን አለ፡፡ የ17ኛው ክፍለ ዘመን ፈላስፋ ዘርዓያዕቆብ ሁኔታችን እጅግ ቢያስገርመው እንዲህ ብሎ ፃፈ፡-
ምንድን ነው ትውልዱ በቀደመው ነገር ላይ ብቻ ረግቶ የቀረው? ምንድን ነው እንዳይመራመር ያደረገው? ኑሯችንን በዕውቀት እንድናሳምረው እኮ የእግዚአብሔር ፍቃድ ነው፡፡
ወልደ ህይወትም ከዓመት ዓመት ምንም ዓይነት ለውጥ በማይታይበት ኑሯችን እጅግ ተበሳጭቶ፣ ዱላ ቀረሽ ስድብ ነው የፃፈብን፡-
የሥጋህንና የነፍስህን ንፅህናን ጠብቅ እንጂ ልብ እንደ ሌላቸው እንስሳዎች አትሁን፡፡ ቤትህን ሰፊና የበራ አድርገህ በብዙ ጥበብ አሰናዳው እንጂ እንደ ጅብ በጉድጓድ ውሥጥ አትኑር፡፡ እግዚአብሔር በሰጠህ መልካም ነገር ሁሉ ተደሰት፤ ምግብህንና ልብስህን፣ የቤትህንም ኑሮ ሁሉ በደምብ አሰናዳ፡፡ …ሥራን ትግል አታድርገው፤ ይልቅስ በስራህ ይበልጥ ትርፋማ እንድትሆንና ድካምህንም እንድትቀንስ ስራህ ላይ የተለያዩ ፈጠራዎችን ጨምርበት  እንጂ።
አልፎ አልፎም ቢሆን በየዘመኑ የመጡ እንደነዚህ ዓይነት ልሂቃን፤ እንዲህ ጠንከር ባለ ተግሳፅ፣ ኑሯችንንና የሥራ መሳሪያዎቻችንን እንድናሻሽል ቢነግሩንም እኛ ግን ወይ ፍንክች የአባ ቢላዋ ልጅ ሆነን ቀረን፡፡ ፕ/ር መስፍን ወልደ ማርያምም ሁኔታችን እንቆቅልሽ ቢሆንባቸው እንዲህ አሉ፡-
በተማሩበት መስክ ተሰማርተው ውጤት ያስገኙ ኢትዮጵያውያን እነማን ናቸው? መክሸፍ መከሻሸፍ በርትቶ ዘለቄታ ያለው ስራ መስራትና ለህዝቡ ዕውቀትንና ብልፅግናን፣ ለሀገሪቱም ኃይልን ማስገኘት ያልተቻለው ለምንድን ነው?  ጥሬ በወፍጮ በሰው ጉልበት መፍጨት፣ ጌሾ ቆሞ በሰው ኃይል በጉልበት መውቀጥ ስንት ምዕተ ዓመታት ፈጁ? ደሳሳ ጎጆ ውስጥ በመኖር ስንት ትውልዶች አለፉ? አህያ ስንነዳ ስንት ትውልድ ተፈራረቀ? ከበቅሎና ከፈረስ ፍጥነት ሳንወጣ ስንት ዘመናት አስቆጠርን?
የፕ/ሩ ቁጭት ጥንታዊ ስልጣኔን ያመነጨው የአያቶቻችን ዕውቀት ወዴት ደረሰ? እንዴትስ ዘመናዊ ማህበረሰብን መፍጠር ተሳነው? እንዴት የበሬ እርሻችን በትራክተር አልተተካም? እንዴት አህያ መንዳቱን በመኪና አልቀየርነውም? እንዴት በቅሎዎቻችንን በአውሮፕላን መተካት አቃተን? የሚል ነው፡፡
ባጠቃላይ ቁጭታችን፣ ከዘመናዊነት ክሽፈት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ፕ/ር መስፍን ከላይ የጠቀሷቸው ነገሮች በሙሉ የዘመናዊነት ቁሳዊ ፍሬዎች ናቸው። ዘመናዊነት ግን ከቁሳዊ መገለጫዎቹ በተጨማሪ ባህላዊ መገለጫዎችም አሉት፡፡ እንዲያውም የዘመናዊነት ቁሳዊ ፍሬዎችን የሚፈጥረው ባህላዊው መገለጫዎቹ ናቸው። በመሆኑም፣ የእኛ ማህበረሰብ የዘመናዊነት ቁሳዊ ፍሬዎችን መፍጠር ያልቻለው፣ የዘመናዊነቱ ባህላዊ መሰረት ስለሌለው ነው፡፡
ስለሆነም ትልቁ ቁጭታችን እንዴት ማሽኖችንና መኪኖችን፣ ድልድዮችንና ህንፃዎችን መስራት አቃተን የሚለው ሳይሆን፤ እነዚህን ነገሮች እንዳንሰራ ምንድነው ያፈዘዘን? ምንድነው የስራና የፈጠራ ክህሎታችንን የሰለበብን? የሚለው ነው። ምንድነው ለመለወጥና ለመሻሻል፣ ለዕድገትና ለብልፅግና ያለንን ተነሳሽነት የገደለብን? ምንድነው ለዕውቀትና ለአዲስ ነገር ያለንን ፍላጎት ያኮላሸብን? ምንድን ነው እንዳንለወጥና እንዳንሻሻል ሰቅዞ የያዘን? የሚለው ነው ዋናው ቁጭት፡፡ በመሆኑም ቁጭቱ ከባህል ጋር የተያያዘ ነው — እንዴት ፈጣሪዎችን፣ ለዕውቀት የሚተጉ ሰዎችን፣ ለለውጥና ለአዲስ ነገር ጉጉ የሆኑ ሰዎችን ባህላችን መፍጠር ተሳነው? ከመቼ ጀምሮ ነው ባህላችን እንደዚህ መካን የሆነው?
6ኛው ክ/ዘ ላይ ከቀይ ባህሩ ዓለማቀፍ የንግድና የባህል ግንኙነት ከተነጠልን በኋላ (ከአክሱም ሥልጣኔ መዳከም በኋላ)  ማህበረሰባችን ለቀጣዮቹ 1500 ዓመታት ምንም ዓይነት የተለዩ ሐሳቦች የማይስተናገዱበት፣ በአንድ ዓይነት አስተሳሰብና ልማድ ብቻ የሚታሽ ሆኗል። በዚህም ህዝቡ በአንድ ዓይነት ወግና ልማድ ብቻ እንዲሰለጥንበት ተደርጓል። ያን ጊዜ ነው የማህበረሰባችን የዕድገት ዕድሉ የተዘጋው፡፡ ምክንያቱም መንፈስ የሚበለፅገው፣ ህይወትም የሚለመልመው የተለያዩ ሐሳቦችና ባህሎች በሚንሸራሸሩበት “በህገ ተቃርኖ” (Dialectics) ነውና። የፍልስፍና ምሁሩ ዶ/ር እጓለ ገብረ ዮሐንስ ሄግልን በመጥቀስ እንዲህ ይላሉ፡-
ህሊናችን የሚሰራው ልክ እንደ ግድግዳ ሰዓት እንጥልጥል (እንደ ፔንዱለም) ከአንዱ ፅንሰ ሐሳብ ወደ ተቃራኒው በመመላለስ ነው፡፡ በሁለቱ ተቃራኒነት ህሊና የነገሩን ጠባይ ስለሚረዳ ከሦስተኛው አማካይ ቦታ ላይ ይደርሳል፡፡ ሦስተኛው ቦታ ላይ ግን የሁለቱ ሐሳቦች ተቃራኒነታቸው ቀርቶ ተፃማሪ ይሆናሉ፡፡ እነዚህም ሦስት የህሊና ተግባሮች አንብሮ (Thesis)፣ ተቃርኖ (Anti-thesis) እና አስተፃምሮ (Synthesis) ይባላሉ፡፡
ህሊና የሚያድገው በዚህ የሐሳብ ህግጋት መሰረት ነው፡፡ ተቋማት ጤናማ የሆነ አሰራርና የፋይናንስ ስርዓት የሚኖራቸው በዚህ የሐሳብ ህግጋት ሲመሩ ነው፤ መንግስት አምባገነን ከመሆን የሚጠበቀው በዚህ የሐሳብ ህግጋት መሰረት ሲዋቀር ነው፡፡ ባጠቃላይ ይህ ህይወት የሚያድግበትና የሚለመልምበት ህግ ነው፡፡
ወንድ አንብሮ ሲሆን ሴት ደግሞ ተቃርኖ ነች፤ ከወንድና ሴት የሚወለደው ልጅም የእነሱ አስተፃምሮ ነው፡፡
ውበት አንብሮ ሲሆን ወሲብ ደግሞ ተቃርኖ ነው፤ ፍቅር የሁለቱ መስተፃምር ነው፡፡
ሊጥ አንብሮ ሲሆን፣ እርሾ ደግሞ ተቃርኖ ነው፤ የሚያምር ዳቦ የሚሆነው የቦካው ሊጥ ደግሞ የሁለቱ መስተፃምር ነው፡፡
ሃይማኖት (እምነት) አንብሮ ሲሆን፣ ፍልስፍና (አመክንዮ) ተቃርኖ ነው፤ ዕውቀት ደግሞ የእነሱ መስተፃምር ነው፡፡
አክሱማዊነት አንብሮ ሲሆን፣ ላሊበላዊነት ደግሞ ተቃርኖ ነው፤ ኢትዮጵያውያን ባለንበት የምንረግጠው የሁለቱን መስተፃምር መፍጠር ስላቃተን ነው፡፡ ይሄንን መስተፃምር ለመፍጠር ጥረት ያደረጉት ዘርዓያዕቆብና ወልደ ህይወት ናቸው፡፡
እግዚአብሔር አንብሮ ሲሆን፣ ተፈጥሮ ደግሞ ተቃርኖ ነች፤ የሰው ልጅ (ንቃተ ህሊና) የሁለቱ መስተፃምር ነው፡፡
ብሕትውና አንብሮ ሲሆን ዓለማዊነት ደግሞ ተቃርኖ ነው፤ ዘርዓያዕቆባዊነት የእነሱ መስተፃምር ነው፡፡
ገንዘብ ያዥ አንብሮ ሲሆን፣ ሒሳብ ሹምና ኦዲተር ደግሞ የገንዘብ ያዥ ተቃርኖዎች ናቸው፤ ጤናማ የፋይናንስ አሰራር የእነሱ መስተፃምር ነው፡፡
ኮንትራክተር አንብሮ ሲሆን፣ ተቆጣጣሪው ድርጅት ደግሞ የኮንትራክተሩ ተቃርኖ ነው፤ ጥራት ያለው የኮንስትራክሽን ስራ የሁለቱ መስተፃምር ነው፡፡
ህግ አስፈፃሚው አንብሮ ሲሆን፣ ህግ ተርጓሚውና ነፃ ሚዲያ ደግሞ የህግ አስፈፃሚው ተቃርኖ ናቸው፤ ዲሞክራሲያዊ መንግስት (ፓርላማው) የሁለቱ መስተፃምር ነው፡፡
ገዥ ፓርቲ አንብሮ ሲሆን፣ ተቃዋሚዎች ደግሞ የገዥው ፓርቲ ተቃርኖ ናቸው፤ ዲሞክራሲያዊ ምርጫዎች የሁለቱን መስተፃምር ይፈጥራሉ፡፡
ጤናማ የማህበረሰብ እድገት የሚመሰረተው በዚህ የአንብሮ—ተቃርኖ—አስተፃምሮ የሐሳብ ህግጋት ሲመራ ነው፡፡ ለዚህም ነው ዶ/ር እጓለም፡- “ይህ የሐሳብ ህግጋት በብዙ የዕውቀት ክፍሎች ውስጥ ፍቱን ሆኖ ተገኝቷል፤” የሚሉት፡፡ ፈላስፋው ሄግልም ይሄንን የሐሳብ ህግጋት የሰውን ልጅ የስልጣኔ ጉዞና የንቃተ ህሊና እድገት ለማጥናት ተጠቅሞበታል፡፡ የሰው ልጅ ከአንዱ የእድገት ደረጃ ወደሚቀጥለው እንዲያድግ የሚያደርገው በአጋጣሚ ሳይሆን በዚህ የሐሳብ ህግጋት ስለሚመራ ነው፡፡
ሆኖም ግን፣ የሰው ልጅ ይሄንን የሐሳብ ህግጋት ስለማይረዳ፣ “ተቃርኖን” በማጥፋት ላይ የተመሰረተ ህይወት መስርቷል፡፡ ሃይማኖት ፍልስፍናን፣ ገዥው ፓርቲም ተቃዋሚዎችን ለማጥፋት ቀን ከሌሊት ሲደክሙ ይታያሉ፡፡ ኮንትራክተሩ ከተቆጣጣሪው ጋር አንድ ይሆኑና ሥራው ይበላሻል፡፡ ገንዘብ ያዥው ከሒሳብ ሹሙ ጋር ይመሳጠርና የድርጅቱ ሀብት ይባክናል፡፡
ህግ አስፈፃሚው ከህግ አውጭው ጋር ይቀላቀልና መንግስት ይነቅዛል፤ አምባገነንም ይሆናል። ሄግል፤ የአፍሪካ ሀገሮችን “ታሪክ የላቸውም” የሚላቸው ለዚህ ነው፤ አፍሪካውያን ታሪካቸው ውስጥ የሐሳብ ሽግግር የለም፤ ሁልጊዜ በአንድ ዓይነት ሐሳብ (በአንብሮ) ላይ ብቻ ነው ተቸንክረው የሚኖሩት፡፡ ለዚህም ነው ዲሞክራሲ ለባህላቸው ባዕድ ሆኖባቸው፣ እስከ ዛሬም ድረስ ከአምባገነንነትና ከደም አፋሳሽ ምርጫዎች መሻገር ያልቻሉት፡፡

Read 5289 times