Monday, 18 September 2017 10:17

የክስታኔ - ጉራጌ እህትማማቾች ስብስብ ምን እየሰራ ነው?

Written by 
Rate this item
(2 votes)

   ከቤተ ጉራጌ ህዝብ አንዱ የክስታኔ ጉራጌ ነው፡፡ የክስታኔ ጉራጌ የበርካታ ባህላዊ እሴቶች ባለቤትም ነው፡፡ ከባህላዊ እሴቶቹ መካከል ደግሞ አንዱ የደንጌሳት በዓል አከባበር ስርአት ነው፡፡ ይህ እጅግ ጥልቅ ባህላዊ ይዘት ያለውን በዓል በሰፊው ለማስተዋወቅ ሰፊ አላማ ይዞ የሚንቀሳቀሰው በክስታኔ - ጉራጌ ህዝብ የልማት ማህበር ስር የሚገኘው የክስታኔ - ጉራጌ እህትማማቾች ስብስብ ይህን የደንጌሳት ዝግጅት መስከረም 11 በአዲስ አበባ አየር ጤና አካባቢ በሚገኘው አንተለህ ሁለገብ
አዳራሽ ያካሂዳል፡፡ የዚህ ማህበር ሊቀ መንበር የሆኑት ወ/ሮ አስራቴነሽ ከበደ ከአዲስ አድማስ ጋዜጣ ጋር የአፍታ ቆይታ አድርገዋል፡፡

     ስብስቡ እንዴት ተመሰረተ?
የክስታኔ ጉራጌ እህትማማቶች ስብስቡን የመሰረትነው አስር ሆነን ነው፡፡ አሁን ላይ የአባላት ቁጥር ተበራክቷል፡፡ ማህበሩ በጠቅላላው አሁን 220 አባላት አሉት፡፡ ይህ የሴቶች ስብስብ ለጊዜው ተደራጅቶ ያለው በክስታኔ - ጉራጌ ህዝብ የልማት ማህበር ስር ነው፡፡ ለወደፊት ግን ራሱን ችሎ ፈቃድ አውጥቶ ይንቀሳቀሳል፡፡
አላማዎቹ ምንድን ናቸው?
በዋናነት አላማው የክስታኔ - ጉራጌ ሴቶች በክፉም በደጉም ለመጠያየቅ እንዲረዳቸው ነው። በክስታኔ ሴቶች ዙሪያ በገጠርም ሆነ በከተማ በርካታ ስራዎችን በመስራት አቅማቸውን ማጎልበት አንደኛው አላማ ነው፡፡ አንዳንድ መሰረታዊ የሆኑ ችግሮቻቸውን ለመቅረፍ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ቀርፆ የመስራት አላማ አለው፡፡ አሁን ላይ በየወሩ ተገናኝተን ስለማህበራችን ከመምከር ባለፈ በክስታኔ ጉራጌ ሴቶች አካባቢ የሚከበሩ አንዳንድ ባህላዊ ይዘት ያላቸው ክንውኖች የማስተዋወቅ ስራ እንሰራለን፡፡
ከሰራችኋቸው የማስተዋወቅ ስራዎች ጥቂት ቢጠቅሱልን …
ከዛሬ ሁለት ዓመት በፊት በ2008 መስከረም 11 የደንጌሳት በአል አዘጋጅተን ማህበረሰቡን ይበልጥ የሚያቀራርብ መርሃ - ግብር በደመቀ ሁኔታ አካሄደናል፡፡ በዚያ መንፈስ ቀጥለን በ2009 ለማድረግ አቅደን የነበረ ቢሆንም በአንዳንድ ሁኔታዎች ዝግጅቱን ለማካሄድ አመቺ ስላልነበረ ልናሳካው አልቻልንም፡፡ ዘንድሮ ግን በ2010 በተመሳሳይ ዝግጅቱን እናቀርባለን፡፡ ፕሮግራሙን የምናቀርበው አየር ጤና በሚገኘው በአንተነህ ሁለገብ አዳራሽ መስከረም 11 ቀን ይካሄዳል፡፡
የዝግጅቱ ይዘት ምንድን ነው?
የዝግጅቱ ይዘት ደንጌሳት ባህልን ለማያውቁት ለማሳወቅ፣ ለተተኪው ትውልድ ባህሉን ለማውረስ ነው፡፡ ምንግዜም የክስታኔ-ጉራጌባህል መለያና መገለጫ የሆኑትን እሴቶች መድረክ አመቻችቶ ለማንፀባረቅ የምናደርገው የማህበራችን አላማ አካል ነው ይህ ዝግጅት። ሌላው ማህበረሰብም የክስታኔ ህዝብን ባህል በሚገባ እንዲገነዘብ ማስቻልም ሌላው የዚህ ዝግጅት አላማ ነው፡፡
የወደፊት እቅዳችሁ ምንድን ነው?
ለወደፊት አሁን ካለውም በሰፋ ሁኔታ በርካታ ህዝብ የሚያሳትፍ ቀለመ ብዙ ዝግጅት በዚሁ በክስታኔ - ጉራጌ ሴቶች ህይወት ዙሪያ ሰፋ አድርገን ለማከናወን እቅድ አለን፡፡ ለጊዜው በዋናው ማህበር ስር ነው ይሄን የምንሰራው፡፡ ዋነኛው እቅዳችንም የክስታኔ ጉራጌ ሴቶችን የማንቃት፣ አቅም የመገንባትና በከተማም ሆነ በገጠር ባሉ የክስታኔ - ጉራጌ ሴቶች ላይ ተጨባጭ የኑሮ ለውጥ የማምጣት ስራ እንሰራን። በቀጣይ ዓመት የጉራጌ ዞን እንዲሁም የሀገሪቱ አንዱ የቱሪዝም መስህብ በሆነው በጢያ ትክል ድንጋይ አካባቢ ሰፊ ፌስቲቫል ለማዘጋጀት አቅደን እየተንቀሳቀስን ነው፡፡

Read 1417 times