Sunday, 17 September 2017 00:00

የክልሎች የድንበር ግጭቶች ወዴት እያመሩ ነው?

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(33 votes)

  · “የድንበር ግጭት የፌደራል ሥርዓቱ ያመጣው አይደለም”
          · “በእነዚህ ችግሮች አገር ትበተናለች የሚል ስጋት የለኝም”

   የትግራይና አማራ ክልል በጠገዴ ጉዳይ ላይ የነበራቸው የድንበር ውዝግብ ከሰሞኑ መፈታቱ የተገለፀ ሲሆን በሌላ በኩል ከወራት በፊት በኦሮሚያና በኢትዮጵያ - ሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ ድንበር ላይ በተቀሰቀሰ ግጭት የሰዎች ህይወት ካለፈና ንብረት ከወደመ በኋላ የተረጋጋ ቢመስልም ሰሞኑን በድጋሚ በተቀሰቀሰው
የድንበር ግጭት የበርካቶች ህይወት ማለፉ ታውቋል፡፡ መንግስት ምን ያህል ሰዎች በግጭቱ እንደሞቱ ባይናገርም 600 ያህል ሰዎች ከቀዬአቸው መፈናቀላቸውን የጠቆመ ሲሆን በአሁኑ ወቅት የፌደራል መንግስት መከላከያ ሠራዊት ጣልቃ መግባቱ ተናግሯል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ የኦሮሚያ ክልል፤ በግጭቱ ላይ የኢትዮጵያ ሶማሌ ልዩ ፖሊስና የሶማሊያ ሪፐብሊክ ወታደሮች መሳተፋቸውን ሰሞኑን ገልጿል፡፡ የሁለቱ ክልሎች የድንበር ግጭት ተባብሶ እዚህ ደረጃ እስኪደርስ ለምን ተጠበቀ? የፌዴራል መንግስት መከላከያ ሠራዊት በፍጥነት ገብቶ የሰው ሞትንና ጥፋትን መከላከል አልነበረበትም? የፌደራል ስርአቱ እንዴት ሰላማዊ የችግር መፍቻ ዘዴ የለውም? ወደፊትስ መፍትሄው ምንድን ነው? በዚህ ሰበብ የሚፈጠረውን ቂምና ቁርሾ እንዴት ነው ማከም የሚቻለው? የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ፖለቲከኞችንና የህግ ባለሙያዎችን በጉዳዩ ዙሪያ አነጋግሮ አስተያታቸውንና የመፍትሄ ሃሳባቸውን እንደሚከተለው አጠናቅሮታል፡-

            
              የፌደራል ሥርአቱ የመበታተን አደጋ እንዳይገጥመው እሰጋለሁ”
                አቶ ቶሎሣ ተስፋዬ (ፖለቲከኛ)

     በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ አደገኛ እየሆኑ የመጡት ጉዳዮች፣ በአዋሳኝ ድንበሮች ላይ የሚፈጠሩ  የሚፈጠሩ ግጭቶች ነው፤ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልል አዋሳኝ ላይ የተፈጠሩ ግጭቶችን አሁን ላይ “አነስተኛ ግጭት ነው፣ የተለመደ አይነት ነው” ማለት አይቻልም፡፡ ድሮ በግጦሽና በውሃ ምክንያት ግጭቶች ነበሩ፤ ይሄ ግን ረዘም ላለ ጊዜ የተከሰተ ግጭት ነው፡፡ በተለይ በ1997 ዓ.ም በሁለቱ ክልሎች የድንበር ሪፈረንደም ተካሂዶ ችግሩ ተፈቶ ነበር፡፡ ውሳኔው በወቅቱ ተፈፃሚ ሳይደረግ በመቅረቱ ነው አሁን ወደ ጦርነት ደረጃ ያደገው፡፡ በኔ አመለካከት፣ ይሄ የፌደራል ስርአቱ የፈጠረው ችግር አይደለም፡፡ የፌደራል መንግስት የችግሮች አፈታት ዘዴ ጤናማ ያለመሆኑ ውጤት ነው፡፡ ለምሳሌ ሪፈረንደም ከተካሄደ በኋላ ድንበር በማካለል፣ ድጋሚ ችግር እንዳይፈጠር ማድረግ ይቻል ነበር፡፡ ችግሩ አሁን እንደሚታየው ተደጋግሞ የሚመጣ ከሆነ ደግሞ የፌደራል መንግስቱ ግጭቱን የማስቆምና መፍትሄ የማፈላለግ ኃላፊነት አለበት፡፡ የወሰንና የድንበር ችግር ሲያጋጥም፣ የማስማማቱን ተግባር ማከናወን ያለበት፣ የፌደራል መንግስቱ ነው፡፡ አጥፊዎችንም ለህግ የማቅረብ ስልጣን አለው - የፌደራሉ መንግስት፡፡ ክልሎች ደግሞ የተወሰነላቸው የድንበር ወሰን አላቸው፡፡ ያንን ድንበር በጊዜ አካልሎ፣ የማስተዳደርና የማልማት ኃላፊነት አለባቸው፡፡
ይሄን ኃላፊነታቸውን ባለመወጣታቸው ነው፣ አሁን ላይ የድንበር ውዝግቦች ተባብሰው የሚታዩት፡፡ የፌደራል መንግስቱ በድንበር አካባቢ የሚፈጠሩ ችግሮች፣ በአግባቡና በአፋጣኝ እንዲፈቱ ፍላጎት ባለማሳደሩና ቸልተኛ በመሆኑ ነው፣ አሁን ለገባንበት ችግር የተዳረግነው፡፡
በአማራ ክልልና በትግራይ፣ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልል፣ በደቡብ አካባቢም ያሉ የወሰንና የግዛት ይገባኛል ጥያቄዎች የሚነሱት፣ የፌደራል መንግስቱ የችግር አፈታት ደካማ በመሆኑ የተነሳ ነው፡፡ በትንሹ በግጦሽና በውሃ የተጀመረ ግጭት ነው የተባለ ጉዳይ ነው፣ በአሁኑ ወቅት ጦርነትን የፈጠረው፡፡ የታጠቀ ኃይል ነው በዘመናዊ መሳሪያ ጦርነት የከፈተው፡፡ የሚሞቱትም ንፁሃን ዜጎች ናቸው፡፡ ይሄ ነገር እየተባባሰ ከሄደ፣ ፌደራሊዝም ሥርዓቱ በቀጥታ ችግር ውስጥ ይገባል፡፡ በኦሮሚያና በሶማሌ ድንበር አካባቢ፣ በተፈጠረው ግጭት  ንፁሃን ሲሞቱ ህዝብ ለወገኑ ቆሞ፣ የመቆጣት ስሜት ሊያንፀባርቅ ይችላል፡፡ ይሄ ደሞ ዞሮ ዞሮ ዳፋው ለሀገር የሚተርፍ ነው፡፡
የፌደራል መንግስት፣ ከስር ከስር እየተከታተለ እንዲህ ሉ ችግሮችን በአጭሩ መቅጨት አለበት። ችግሩ በዚህ ከቀጠለና በቶሎ መቋጫ የማያገኝ ከሆነ፣ ፌደራሊዝሙ በቀጥታ አደጋ ውስጥ ገብቶ፣ ሀገሪቷ ወደ መበታተን አቅጣጫ ልትሄድ ትችላለች፡፡ ሁሉም “የራሴን ክልል አስተዳድራለሁ፣ ፌደራሊዝሙን አልፈልግም” ብሎ በኢትዮጵያዊነት ጥላ ሥር የቆየው ህዝብ ሊበታተን ይችላል ብዬ እፈራለሁ፡፡ በተለይ ኢትዮጵያዊነትና የኢትዮጵያ አንድነት፣ ጥያቄ ምልክት ውስጥ ሊገባ ይችላል የሚል ስጋት አለኝ፡፡
ለዚህ ችግር መፍትሄ የሚጀምረው፣ ለክልሎች ራሳቸውን በራሳቸው በነፃነት፣ ያለ ጣልቃ ገብነት የማስተዳደር መብት ከመስጠት ነው፡፡ የፌደራል መንግስቱ ጣልቃ መግባት በሚገባው ብቻ ጣልቃ እየገባ፣ ሌላውን ክልሎቹ በራሳቸው እንዲወጡት ሙሉ መብት መስጠት አንደኛው የመፍትሄ አቅጣጫ ነው፡፡ ባለስልጣን የመቀየርና ወደ ስልጣን የማምጣት ጉዳይ ላይ የፌደራል መንግስቱ ከጣልቃ ገብነት መቆጠብ አለበት፡፡ ሌላው ህዝበ ውሳኔዎችን ሳይውሉ ሳያድሩ መተግበር ያስፈልጋል፡፡ አለበለዚያ ይህ የፌደራል ስርአት የመበታተን አደጋ እንዳይገጥመው እሰጋለሁ፡፡  

---------------------

                         “የችግሩ ምንጮች ፖለቲከኞች እንጂ ህዝብ አይደለም”
                            አቶ ሙላቱ ገመቹ (ፖለቲከኛ)


    አሁን በክልሎች፣ በድንበር ይገባኛል ምክንያት የሚፈጠሩ ችግሮች፣ የፌደራል ስርአቱ ያመጣው ችግር ነው የሚል እምነት የለኝም። ችግሩን የፈጠረው በፌደራል ስርአቱ አያያዝና ወደ ተግባር በመለወጡ ሂደት ላይ ያለው ደካማ አፈፃፀም ነው። አንዳንዴ መንግስት አንድ ችግር ሲያጋጥመው፣ ለነገሮች ማስቀየሻም እንዲህ ያለውን አካሄድ ሆነ ብሎ ሊፈጥር ይችላል፡፡ በማልቴዥያን የኢኮኖሚክስ ንድፈ ሀሳብ፤ በተቻለ መጠን ህዝብ በአመራሩ እርካታ ካላገኘ እንዲሁ ዝም አይባልም፣ በጎን ችግር ይፈጠርለታል፤ በዚህም ወደ መንግስቱ ከሚጮህ ይልቅ ወደ ጎንዮሽ፣ እርስ በእርሱ እንዲጠያየቅ ይደረጋል፡፡ አሁን በኛ ሀገርም ይሄ ንድፈ ሀሳብ እየተተገበረ ይመስላል፡፡
ኦሮሚያ - ሶማሌ ፣ ትግራይ - አማራ የተፈጠሩት ችግሮች የዚህ ውጤት ይመስላሉ። ፌደራል መንግስት የራሱ መሬት አይኖረውም - በፌደራል ስርአት መሰረት፡፡ ክልሎችም የተሰመረ ድንበር ይኖራቸዋል፡፡ ስለዚህ ጠመንጃ መማዘዝን አይጋብዝም፡፡ በህግ በሰፈረ ወሰን ችግሩ በቀላሉ መፈታት ይቻላል፡፡ ትልቁ ችግር ግን ይሄ ህግ በተግባሩ ላይ ያለው ዳተኝነት ነው፡፡
የሶማሌና የኦሮሞ ህዝብ ፈፅሞ አይጋጭም፡፡ ችግሩ የሚመነጨው ከመንግስቱ አመራሮች ነው። ህዝብ በጉዳዩ የለበትም፡፡
እንዲህ ያሉ ግጭቶች ምናልባት ለመንግስት አካላት ይጠቅም ይሆናል፡፡ ህዝብ ግን መቼውንም ቢሆንም ሊራራቅ አይችልም፡፡ እኔ በእነዚህ ችግሮች ሀገር ትበተናለች የሚል ስጋት የለኝም። ህዝብ አይበታተንም፡፡ እንደሚታየው ሰላማዊ ዜጎችን እየገደሉ ያሉትና ወረራ የሚፈፅሙት የመንግስት ሚሊሺያዎች  እንጂ ህዝብ አይደለም። በዚህች አገር ለረዥም ዘመን የዘለቀው የብሔር ብሔረሰቦች ችግር አሁንም አለ፡፡ ለዚህ ጥያቄ መልስ መስጠት ያስፈልጋል፡፡ ትክክለኛ ፌደራሊዝም መስፈን አለበት፡፡ አሁን ያለው አላማውን ያላሳካ፣ በቅርፁም፣ በመልኩም ፌደራሊዝም ያልሆነ፣ የአንድ አካል ገዥነት መንፈስ የተጫነው ነው፡፡ ለዚህ ነው ይሄ ስርአት ለፌደራሊዝም አተገባበር አያመችም የሚባለው፡፡
ይህቺ ሀገር አንድነቷን ጠብቃ እንድትቀጥል ከተፈለገ፣ መንግስት የምርጫ ስርአቱን አዘምኖ፣ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር በማድረግ፣ “ችግሩን መፍታት እንችላለን” ለሚሉ እድሉን መስጠት አለበት፡፡ በሌላ በኩል አዲስ አስተሳሰብና አመለካከት ይዞ፣ ውይይት ማድረግም ያስፈልጋል፡፡   

--------------------

                          “የጠባብነት ችግር ያለው ህዝብ ጋ ሳይሆን መሪዎች ጋ ነው”
                               አቶ አስገደ ገ/ሥላሴ (ፖለቲከኛ)

     አሁን የሚታዩት ችግሮች፣ ያለአግባብ የተለጠጡ የብሔርተኝነት አስተሳሰቦች ውጤት ናቸው፡፡ የእነዚህ አስተሳሰቦች ምንጭ ደግሞ የህውኃት የትጥቅ ትግል አጀማመር ነው፡፡ በ1967 ዓ.ም ወደ ትጥቅ ትግል ስንወጣ፣ የብሔር ጭቆና፣ የፍትህ፣ የነፃነት፣ ህዝባዊ መንግስት የማስፈንን መርህ ለመከተል ነበር፡፡ ወዲያው ግን በወቅቱ የነበሩ የህወኃት መሪዎች አቅጣጫውን በመቀየር፣ “ትግሉ የትግራይ ነፃ ሪፐብሊክ ስርአትን ለማምጣት ነው” የሚል ፕሮግራም አመጡ፡፡
ፕሮግራሙ ግን በወቅቱ በታጋዮች ተቀባይነት አላገኘም፡፡ ይሄ ተደብቆ የቆየ አጀንዳ ነው፡፡ የያኔው ኢህዴን፣ የአሁኑ ብአዴን ደግሞ በሀገራዊው አንድነት ላይ ነበር የሚንቀሳቀሰው፤ “ቀይ ባህርና ኤርትራን ለማንም አሳልፈን አንሰጥም” የሚል አቋምም ነበረው፡፡
በኋላ ይሄን ሀሳቡን ህውኃት አፈረሰበት። በወቅቱ ይሄን የኤርትራና የቀይ ባህር አቋማችሁን ካልለወጣችሁና በብሄር ጉዳይ ካላመናችሁ፣ ፀባችን ከእናንተ ነው” ብሎ ነው ህውኃት ያስፈራራቸው። በዚህም ኢህዴን ውስጥ ከፍተኛ አለመግባባት ቢፈጠርም በኋላ ብአዴን ተቋቋመ፡፡ በአጠቃላይ የብሔርተኝነት አክራሪ አጀንዳዎች የመጡት ከዚህ መነሻ ነው፡፡ በኋላ የትግራይ ሪፐብሊክ ጉዳይም ቀርቶ፣ ፌደራሊዝሙ በቋንቋና በብሔር ሊሆን ችሏል፡፡
በዚህ መንገድ የመጣው ፌደራሊዝም ዛሬ ብዙ ፈተና ተጋርጦበታል፡፡ ብአዴንና ህወኃት ያመጡት ጠባብነት፣ መዘዙ አደገኛ መሆኑ እየታየ ነው፡፡ አስታውሳለሁ፤ በሽግግሩ ወቅት ሻለቃ አድማሴ እና ፕ/ር አስራት ወልደየስ የዚህ ፌደራሊዝም የኋላ ጠንቅ ታይቷቸው፣ የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት ሲታወጅ፣ ብዙ ትንቢት የሚመስል ነገር ተናግረዋል፡፡ ሰሚ አላገኙም እንጂ፡፡ አሁን ያ ችግር እየመጣ ያለ ይመስላል፡፡
እኔ ፌደራሊዝም ስርአትን ፈፅሞ አልቃወምም ነበር፤ ግን በቋንቋና በብሔር ብቻ መሆኑ ዋጋ እንደሚያስከፍለን አሁን ከሚታዩት ምልክቶች በመነሳት መገመት እችላለሁ፡፡ በአሁን ወቅት እኮ ዩኒቨርሲቲዎች እንኳ ሳይቀሩ በክልል የታጠሩ እየሆኑ ነው፡፡
የዩኒቨርሲቲ መምህራንና አስተዳደሮች በቋንቋና በብሔራቸው ነው እየተቀጠሩ ያሉት። የምርምር ማዕከላት ሳይቀሩ እንዲህ በጠባብነት ሲታጠሩ ማየት ያሳዝናል፡፡ ለዚህ ሁሉ ጠንቅ የሆነው ደግሞ የፌደራሊዝሙ ፍልስፍና ነው፡፡ ለምሳሌ ትግራይ ውስጥ እንኳ ብንመለከት፣ የድንበር ጉዳይ ወረዳ ከወረዳ፣ ዞን ከዞን እያጋጨ ነው፡፡ ታሪካዊ ስሞች ሲቀየሩ ይስተዋላል፡፡ በሌላውም ተመሳሳይ ችግር ነው ያለው፡፡
በተለይ ምሁራን ተመራምረው፣ አሁን ለተጋረጠብን የሀገራዊ አንድነት ችግር የመፍትሄ ሀሳብ ካላመጡ ሁኔታው አደገኛ ነው የሚሆነው። ትክክለኛ የፌደራሊዝም መስፈርት ተጠንቶ በተግባር ላይ እንዲውል ካልተደረገ፣ አሁን የተያዘው አቅጣጫ አደገኛ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት ዝም ብሎ በቃል ብቻ አይመጣም፡፡ ህዝብ ከህዝብ መገናኘትና መገማመድ አለበት፡፡ ቋንቋ ሚናው በመግባቢያነት ብቻ መወሰን አለበት፡፡
የጠባብነት ችግሩ ያለው ህዝቦች ጋ አይደለም፣ መሪዎቹ ጋ ነው፡፡ ይሄ መታወቅ አለበት፡፡ በዚህ ጉዳይ ህዝቡም መንቃት አለበት፡፡ ምሁራኖች በተለይ የታሪክና የፖለቲካ ሳይንስ ምሁራን፤ ሀገርን በማዳን ስራ ላይ በስፋት መግባት አለባቸው። ሚዲያዎችም በኢትዮጵያዊነት በአንድነት፣ በፌደራሊዝም ትርጉም ላይ ግንዛቤ መስጠት አለባቸው፡፡ በስመ ፌደራሊዝም የማይገባ መዋቅር የመዘርጋት ጉዳይ መቅረት አለበት፡፡ የኢህአዴግ መሪዎችም የህዝቡን ስነ ልቦናና ፍላጎት መጠበቅ አለባቸው፡፡ ይሄ ጉዳይ በቶሎ መቋጫ ማግኘት አለበት፡፡

------------------

                      “የኢትዮጵያ ህዝብ ጠላት የህግ የበላይነት ያለመኖር ነው”
                           አቶ ወንድሙ ኢብሳ (የህግ ባለሙያ)

      ችግሩ የፌደራል ስርአት በዚህች ሀገር የመተግበር ጉዳይ አይደለም፡፡ ዋናው ጉዳይ ትክክለኛ ስርአት መቅረፅና በቅንነት ህዝቦችን የመምራት ጉዳይ ነው። በርካታ ሀገሮች በፌደራል ስርአት ስር ነው ያሉት። ስለዚህ ስርአቱ ይሄን ችግር ፈጥሮታል ባይባልም አተገባበሩ ግን የችግሩ መንስኤ ሆኗል፡፡
ህገ መንግስቱ ችግሮች እንዳሉበት ሆኖ፣ ብዙ ችግሮቻችንን ለመወጣት የሚያስችለን ነበር፤ ነገር ግን አተገባበሩ ላይ ዳተኝነትና የቅንነት መጓደል ስላለ ግጭቶች ሊጠፉ አልቻሉም፡፡ የመንግስቱ ፖሊሲ ደግሞ ጎሰኝነትና ዘረኝነትን አክርሮ፣ በህዝቦች መካከል ግንብ የመገንባት ያህል መሆኑም አሁን ዋጋ እያስከፈለን ነው፡፡ ለምሳሌ የትምህርት ፖሊሲውን ብንወስድ፣ በየክልሉ ያለው ቋንቋን መሰረት ያደረገ ስርአት፣ አንዱ ለሌላው ክብር እንዳያሳይ የሚያደርግ መሆኑን እናስተውላለን፡፡ የኦሮሞ ልጆች ላለፉት 25 ዓመታት አማርኛ በቅጡ እየተማሩ አይደሉም፡፡ የሚጀምሩትም ከ5ኛ ክፍል ነው፡፡ ይሄ ከአክራሪነት ጋር የሚመጣ ነው፡፡ ይሄ ሁሉ ችግር ነው አሁን ያላግባባን፡፡
ባድመ ላይ የተካሄደው ጦርነት እኮ የትግራይ ብቻ አልነበረም፤ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ነበር። ኢህአዴግ ከዚህ የህዝብ ፍላጎት ትምህርት ወስዶ ራሱን የሚቀይርበትና የኢትዮጵያ አንድነት ላይ የሚሰራበት እድል ነበር፡፡ ዛሬ የሶማሌ ልዩ ኃይል፣ የኦሮሚያ ልዩ ኃይል፣ የአማራ ልዩ ኃይል … እየተባለ እንዴት ነው ሀገራዊ አንድነት ሊመጣ የሚችለው? የድንበር ጥያቄ የሚነሳው እኮ የእርስ በእርስ መተማመን ሲሸረሸር ነው፡፡ በህገ መንግስት የተደነገጉ ህጎች በተግባር አለመዋላቸው ሌላው የፌደራሊዝም ስርአቱ የገጠመው ፈተና ነው፡፡ መንግስት በተደጋጋሚ “የዚህች ሀገር ትልቁ ጠላት ድህነት ነው” ይላል እንጂ በኔ አረዳድ፣ የዚህች ሀገር ትልቁ ጠላት፣ የህግ የበላይነት ያለመስፈን ጉዳይ ነው፡፡ የወረዳና የዞን ሹማምንት ለህግ የበላይነት ተገዢ አለመሆናቸው ለግጭት ዳርጎናል፡፡
ሌላው አሁን ዘመን ተቀይሯል፡፡ እንደ ዘመኑ ነገሮች መስተካከል አለባቸው፡፡ የህዝብ ስነ ልቦና እየተጠና፣ በየጊዜው ሀገራዊ ፖሊሲዎችን ማሻሻልና ማስተካከል ያስፈልጋል፤ የዛሬ 25 ዓመት ላይ ተቸክሎ መቅረት ኢትዮጵያን አደጋ ላይ ይጥላታል። የማዕከላዊ ዲሞክራሲያዊነት ጉዳይ መታየትና መፈተሽ አለበት፡፡ አሁን ህገ መንግስቱ፣ አንድ ሶስተኛው ነው በተግባር እየዋለ ያለው፡፡ ይሄን ህገ መንግስት ሙሉ ለሙሉ ተግባር ላይ ማዋል ያስፈልጋል፡፡ መከላከያ ሰራዊቱ በግጭቶች መሃል በፍጥነት ጣልቃ ገብቶ ማረጋጋት አለበት፡፡ ከማንም በላይ ግን የህዝብ ስነ ልቦና መጠበቅ ያስፈልጋል። ተንኮል የተሞላበት የአመራር አካሄድ መቅረት አለበት፡፡

Read 8141 times