Print this page
Sunday, 17 September 2017 00:00

‘ማለፍ ክልክል ነው’

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(7 votes)

  እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ… ይኸው እንግዲህ ‘አዲሱ ዓመት’ ገባ አይደል! ያው ለሌላ መጠሪያ ስለማያመች ‘አዲሱ’ ዓመት ገባ እንላለን፡፡ ሀሳብ አለን…ለወደፊቱ ‘አዲስ’ የሚለው ቃል ‘ተከታዩ’ በሚል ይተካልን፡፡፡
“እንኳን ለተከታዩ ዓመት አደረሰህ”
አሪፍ አይደል! ልክ ነዋ…‘አዲስ’ የምንለው ነገር ሁሉ የሆነ ‘ዘ ሴም ኦልድ ስቶሪ’ ነገር እየሆነብን ተቸግረናላ! በእሁድ ዿግሜ 5 ቀን፣ 2009 እና በሰኞ መስከረም 1 ቀን፣  2010 መካከል ያለው ልዩነት ቢኖር…
“መስከረምን ምን እየበላሁ እወጣት ይሆን?” የሚል ስጋታችን ነው፡፡
እርግብ እንኳን “እስቲ ከእኔና ከአንቺ ክብደት ማን እንደሚበልጥ እንወራረድ!” የምትባል አይነት ዶሮ፤ “ለእርሶ ስል አምስት ከሀምሳ ውሰዷት…” የሚባልበት ዘመን እንዴት ‘አዲስ’ ሊሆን ይችላል!  የከብት ሀኪም “ችግሩ ማልኒዩትሪሽን ነው፣” የሚለው በግ፤ “ከአራት ሺህ አይቀንስም፣” የሚባልበት ዘመን እንዴት አዲስ ሊሆን ይችላል!
እግረ መንገዴን…ሌላ ጊዜ በቴሌቪዥን ‘ጥያቄዎች ሲቀርቡ’ በቀጥታ ስርጭት አሳትፉና!
“እሱን ነገር እኛም እንወዳለን፡፡ ምራቃችንን ውጠን ጨርሰን ድርቀት እንዳያጠቃን በዓመትም በሦስት ዓመትም የምንከፍለው ብድር የምንወስድበት የሥጋ ፈንድ ይቋቋምልን፣” እንል ነበራ!
በነገራችን ላይ፣ እግረ መንገድ… ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… ይሄ ካሜራ ፊት በተቀረበ ቁጥር ተሞክሮ ምናምን የሚሉት ‘ጥያቄ’ አንድ በሉንማ …..
“ምን ተሞክሮ አለዎት?”
“ተሞክሮ ማለት…”
“ማለት መቼም ቢሆን የማይረሱት፣ አስደሳች ወይም አሳዛኝ ነገር…፡፡”
“በእርግጥ በርካታ ፈገግ የሚያደርጉና የሚያስደንቁ ነገሮች ገጥመውኛል”
“ለምሳሌ አንድ ሁለቱን ቢጠቅሱልኝ…”
“ለምሳሌ አንድ ጊዜ በዓል ነበር፡፡ በግ ገዝቼ ስመጣ ገመድ ተበጠሰብኝ!”
“እና አመለጠዎት!”
“እሱማ ገመዱን  አጥብቄ ያዝኩበት”
እና ይሄ ነው ስንት ህዝብ የሚከታተለው ሚዲያ ላይ የሚቀርብ ትውስታ! ይሄ ነው ‘ሜሞሪ’ የሚባለው ነገር! ገመድ የበጠሰ በግም፣ ሰፈር ለሰፈር ተሯሩጣ የተያዘች ዶሮም ‘የዛሬው ቀን በታሪክ ውስጥ’ ምናምን መዝገብ ውስጥ ገቡ ማለት ነው! የዛሬ ሀያ ምናምን ዓመት ገመድ ሊበጥስ ስለነበረ በግ አሁንም የሚያስታውስ ሰው ወይ የማስታወስ ችሎታው የተለየ ነው፣ ወይም በታሪክ ውስጥ ለመጨረሻ ጊዜ ገዝቷት የነበረች በግ ያቺ ነች፡፡ ቂ…ቂ…ቂ…
እና እባካችሁ የምታስተላልፉትን ነገር እየመረጣችሁ አድርጉልንማ! (ጥሩ ነገሮች የሚያቀርቡት እንዳሉ ሆነው፣) ተመልካች በጣም፣ እጅግ በጣም እርቆ መሄዱን ማወቁ አሪፍ ነው። አሀ…በልዩ ፕሮግራም ሰበብ ልዩ ራስ ምታት አትስጡና!
ስሙኝማ…እንግዲህ  ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… የዘንድሮው በዓል አንድ ያሳየው ነገር ቢኖር ባለንና (ቂ…ቂ..ቂ…) በሌለን መሀል ያለው ልዩነት ምን ያህል እንደሰፋ ነው፡፡ እኛ ሀምሳ አራት በጎች ስንደባብስ ውለን ሀምሳ አምስተኛው ላይ መቶ ብር ለማስቀነስ መቶ ደቂቃ ስንዳረቅ ሌላው ከመኪና ሳይወርድ.. “እሱን፣ ዳለቻውን ሙክት ጫነው፣” ብሎ መቶ ሰከንድ ሳይሞላ ግዢውን ይፈጽማል፡፡ በስንቱ እንጎምጅ!
እኔ የምለው… ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…የኑሮ ልዩነታችን መስፋት ‘ልንሄድባቸው የምንችለባቸውን’ (ወይም ‘ልንሄድባቸው የሚፈቀዱልንን’) ቦታዎች እያጠበበን ነው፡፡ ከተወሰኑ ወራት በፊት አንድ ወዳጃችን ከውጪ የመጣ እቃ ሊቀበል የሰው ቤት ፍለጋ አንድ መንደር ይሄዳል፡፡ መንደሩ አባኮራን ሰፈር፣ ጠብመንጃ ያዥ ሰፈር ምናምን ሳይሆን ‘የሀበሻ ስም የሚጠየፍ’ አይነት መንደር ነው፡፡ እናም ጥበቃው የሚጀምረው ከመንደሩ መግቢያ ነው፡፡
“ገና መንደሩን ከገባሁ ጀምሮ የጥበቃ ሠራተኞቹ ግልምጫ ሰርስሮ የሚገድለኝ ነው የመሰለኝ!” ነው ያለው ወዳጃችን፡፡ “የሰሜን ኮሪያ የኑክሌር ጣቢያም እንዲህ የሚጠበቅ አይመስለኝም፡፡”
እናላችሁ…አዲስ አበባ እንዲሀ እየሆነች ነው። እንደ ቤቨርሊ ሂልስ በሚመሳስሉ መንደሮች ያሉ ጥበቃዎች፣ ግልምጫ ከማሳመሙ የተነሳ “አንደኛውን በዱላ ቢያንቆራጥጠኝ ይሻለኝ ነበር!” የሚያስብሉ ናቸው፡፡
“በዚህ በኩል ማለፍ ክልክል ነው፡፡”
 “እሱን ሂድና ከፈለግህ ለማኦ፣ ከፈለግህ ለቼ ጉቬራ ንገር፡፡”
“እና ምን እያልከኝ ነው?”
“እንደውም በበራፎቻችን በኩል የሚያልፍ ሰው የኮቴ ይከፍላል፡፡” አለቀ፣ ደቀቀ ይሏችኋል ይሄኔ ነው፡፡
ስሙኝማ…ሰው ፍለጋ እንዲሀ አይነት መንደር ሲኬድ ምልክቱን ምናመኑን ሁሉ በስልክ መጨረስ ነው፤ ልክ ነዋ… “እባክህ ወንድም፤ የአቶ ጎንጤን ቤት ታሳያኛለህ??” የሚሉት እግረኛ ማግኘት አስቸጋሪ ነዋ!
የምር ግን፣ እንግዲህ ጨዋታም አይደል… ልምድ እኮ አስቸጋሪ ነው፡፡ እንዲህ አይነት መንደር ሄደን ድንገት መንገድ ላይ ሰው ስናገኝ፣ “የአቶ አደፍርስ ቤት የት ነው?” ብለን ብንጠይቅ…አለ አይደል… ሰዎቹ ሊደነግጡ ይችላሉ፡፡ ለማብረራትም “አቶ አደፍርስ፣ የቀዮ አባት፣” ስንል ጭራሽ ሆረር ፈልም ያዩ ያህል የጨው አምድ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ልምድ አስቸጋሪ ነው..
እናማ…አዲስ አበባ እንዲህ ሆናለች፡፡ እኛ ተራዎቹ የማናልፋቸው፣ በግልጽ ያልተሰመሩ መስመሮች በየቦታው እየበዙ ነው፡፡ ረጃጅም ግምቦችና የኤሌትሪክ ሽቦዎች እየበዙ ነው፡፡ አይደለም መኖሪያ መንደሮች፣ መዝናኛ ቦታዎች ሲገባ እንኳን ደስ የማይሉ፣ የርህሩህ እናትና የጨካኝ እንጀራ እናት ነገሮች ይፈጠራሉ፡፡
ምን ይመስልሀል ብትሉኝ --- ወደፊት በእንደዚህ አይነት መንደሮች ማለፍ ለእኛ ለ‘ሰፊዎቹ’ የሆነ የአገር ውስጥ ቱሪዝም ምናምን ነገር ሊሆን ይችላል፡፡ ችግሩ ግንብና ጂ ፕላስ ምናምኖችን እያደነቅን ስንሄድ ሌሊት ዲጂኖ ይዘን ለመምጣት ፕላን እያነሳን ሊመስልብን ይችላል፡፡
“እዚህ ምን ትሠራለህ?”
“ም…ምንም፡፡”
“እየተንጠራራህ የሰው ግቢ እያየህ ምንም ትለኛለህ! ለፖሊስ ሳልሰጥህ ምን እየሠራህ ነው?”
“እንዲሁ ዘወር፣ ዘወር እያልኩ ቤቶቹን እያደነቅሁ ነው፡፡”
“አጅሬው! አሁን ዘወር፣ ዘወር ብለህ ታደንቃለህ፤ ሌሊት ትመጣና ደግሞ ቀን ስታደንቅ የዋልከውን ስትቆፍር ታድራለህ፡፡”
“ኽረ እንደሱ አይደለም! እኔ…”
“ጀርባህን ሳልጎምድልህ ጥፋ ከዚህ!”
እንደውም፣ ሀሳብ አለን፡፡ እነኚህ የአቶ መህመት አይነት ቤቶች የተደረደሩባቸው መንደሮች ለእኛ ለ‘ሰፊዎቹ’ እንደ ቱሪስት መዳረሻ ይሁኑልንማ! የምንከፍለው ገንዘብ ብናጣ አትክልቶቹን ውሀ በማጠጣትና የግቢዎቹን አስፋልቶች በዱቄት ሳሙና በማጠብ እንክሳለን፡፡
በነገራችን ላይ… በፊት የአማሪካን ወዳጆቻችን የሰው መኪና ተደግፈው፣ የሰው ህንጻ ስር ሆነውም…
“በካሽ የገዛኋት መኪና…”
“የምሠራበት ድርጅት ህንጻ…”
ምናምን እያሉ ፎቶዎች ይልኩልን ነበር፡፡ እዚቹ አዲስ አበባ ውስጥ “የላስቬጋስ ትልቁ ናይትክለብ በር ላይ ሆኜ፣” ምናምን የሚያሰኙ ነገሮች ሞልተዋል፡፡
በዘነጡ መንደሮች ውስጥ በመቶ ሀምሳ ብር ጫማችን ጎርደድ እያልን ስናልፍ፣ በግልምጫ የማንሳቀቅበትን ዘመን ያምጣልንማ! “በሁለት ሺህ ዶላር አምስት ወር ስዝናና ከርሜ እመለሳለሁ፣” ብሎ ነገር የፊልም ጸሃፊዎቻችንም አይጠቀሙበትም፡፡ ለጥቆማ ያህል ነው።
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 2933 times