Sunday, 17 September 2017 00:00

መከፋፈል እንኳን ለወዳጅ ለጠላትም አይበጅ!

Written by 
Rate this item
(14 votes)

  ከዕለታት አንድ ቀን አንድ በህይወት ኑሮው ሁሉ ነገር ተሳክቶለት፣ ይለጉመው ፈረስ፣ ይጭነው አጋሠሥ ያለው እጅግ የናጠጠ ዲታ ሰው ነበረ፡፡ እጅግ ቆንጅዬ ሚስት የነበረችው ሲሆን፤ ከእሷ የተወለዱ የሚያማምሩ ልጆችም ነበሩት፡፡ ታዲያ ይህን ሰው ሁልጊዜ የሚከነክነው በአገሩ ውሸት እንጂ ዕውነት አለመኖሩ ነበር፡፡ ስለዚህ አንድ ቀን ማለዳ ተነስቶ ሚስቱን፤
“ሰማሽ ወይ የኔ ቆንጆ?” ይላታል፡፡
“አቤት የእኔ ጌታ?” ትላለች፡፡
“ኑሮዬ ደርጅቶ ሁሉ ነገር የተሟላልኝ ሰው ሆኜ ሳለ፣ አንድ ነገር ግን በጣም ይቆጨኛል”
“ምን?”
“ዕውነትን አለማግኘቴ”
“ዕውነት ነው ያልከኝ?”
“አዎን”
“እባክህ ዕውነት የሚባል ነገር ኖሮ አያውቅም”
“አለ እንጂ እኛ መፈለግ አቅቶን ነው”
“በዚያ የምታምን ከሆነ ቤት ቁጭ ብለህ መቆጨት ሳይሆን ወጥተህ መፈለግ ነው ያለብህ”
“ካልሺስ ዛሬ ማለዳ የተነሳሁት ዕውነትን ፍለጋ ለመዞር ነው”
“ይቅናህ፡፡ ስታገኛት ግን ለእኔ ልታሳየኝ ቃል ግባልኝ”
ሊያሳያት ቃል ገባና ንብረቱን ሁሉ አውርሷት መንገድ ጀመረ፡፡ ከዚያ በኋላ ዕውነትን ለማግኘት ከለማኝ ጀምሮ ይጠይቅ ጀመር፡፡ ተራሮች ላይ ወጥቶ ፈተሸ፡፡ ሸለቆዎች ውስጥ እየገባ በረበረ፡፡ ትናንሽ መንደሮችንና ከተሞችን አሰሰ፡፡ ባህሮችንና የባህር ዳርቻዎችን መረመረ፡፡ ጨለማና ብርሃንን አጤነ፡፡ የቆሸሹ ቦታዎችንና በአበባ የተሞሉ አትክልት ሥፍራዎችን ሁሉ እየገባ አጣራ፡፡ ቀናትንና ሌሊቶችን አጠና፡፡ ሳምንታትን፣ ወራትን እና ዓመታትን በደምብ አጤነ፡፡ ዕውነት አልተገኘችም፡፡
አንድ ቀን በተራራ ግርጌ ባለ አንድ ዋሻ ውስጥ ዕውነትን ተሸሽጋ እንደምትኖር ምልክት አየና ፈጥኖ ወደሷ ዘንድ ሄደ፡፡ ዕውነት አንዲት የጃጀች አሮጊት ናት፡፡ ብልህ ናት፡፡ አስተዋይ ናት፡፡ በመላ ድዷ ላይ የሚታየው አንድ ጥርስ ብቻ ነው- እሱም የወርቅ! ፀጉሯ ሽበት ብቻ ነው፡፡ እሱንም ሹሩባ ተሠርታዋለች። የፊቷ ቆዳ የደረቀና የተጨማደደ ብራና ይመስላል፡፡ አጥንቷ ላይ ተጣብቋል፡፡ ይህ ሁሉ እንዳለ ሆኖ፣ በዕድሜ ብዛት የአሞራ ኩምቢ የመሰለውን ጣቷን እያወናጨፈች መናገርን ታውቅበታለች፡፡ ድምጿ የሚያምር፣ የተቃና፣ ለስላሳና ጣፋጭ ናት፡፡ ሰውዬው “አዎ፤ ይቺ ዕውነት እራሷ ናት” አለ፡፡
ለማጣራትም፤
“ዕውን ዕውነት አንቺ ነሽን?” ሲል ጠየቃት
“አዎን ነኝ” አለች፡፡
አብሯት አንድ ዓመት በመቆየት የዕውነተን ትምህርት ሊቀስም ወሰነ፡፡
የምታስተምረውን ሁሉ ተማረ፡፡
ከአንድ ዓመት በኋላ ወደ ቤቱ ለመሄድ ተነሳ! እንዲህም አላት፡-
“የዕውቀት ዕመቤት ሆይ! እስከ ዛሬ ያለሽን ዕውነት ሁሉ አጎናፀፈሺኝ፡፡ ማወቅ ያለብኝንም አሳወቅሺኝ! ላደረግሺልኝ ውለታ ካሣ ይሆንሽ ዘንድ ምን ባደርግልሽ ደስ ይልሻል?”
ዕውነትም፤
“በየደረስክበት ስለ እኔ ተናገር!
አደራህን ወጣትና ቆንጅዬ ሴት
መሆኔን ሳትታክት አስረዳልኝ!”
አለችውና ወደ ጓደዋ ገባች፡፡
*  *  *
ኬንያውያን አዘውትረው የሚናገሩት አንድ አባባል አላቸው፡- “አካፋን አካፋ ነው እንጂ ትልቅ ማንኪያ ነው አትበል!”
ስለ ማንነታችን፣ ስለ ዲሞክራሲያዊና ኢ- ዲሞክራሲያዊ ግንኙነታችን፣ ስለ ፓርቲያችን፣ ስለ ሀገራችንና ስለ መከላከያ ኃይላችን፤ ስለ ሥልጣናችንና ስለ ልማታችን ስናስብ፤ የኬንያውያኑ አባባል እናስታውስ! ሚሥጥራዊነታችን ፍንትው ብሎ እየታየ ከእኛ በላይ ግልፅ የለም፤ አንበል፡፡ በራችንን ሁሉ ክርችም አድርገን ዘግተን ስናበቃ እንወያያለን፣ ሀቁን እንገመግማለን ብንል ተዓብዮ እንጂ ሌላ ሊሆን አይችልም፡፡ እያየን አላየንም፤ እየሰማን አልተሰማንም፤ እያጠፋን አላጠፋንም ማለት በባህሪያችን የሰረፀ ቢሆንም፤ ቀስ በቀስ እየቀረፍን መጣል ያለብን ታላቅ ችግር ነው፡፡ በቡድናዊ ስሜት ተወጥረን ዴሞክራሲያዊነታችንን እያበለፀግን ነው፤ ብንል፤ በጠብታ ውሃ ውስጥ ጉማሬ ዓይተናል፤ ማለት ይሆንብናል፡፡ ዓላማችን በሀቅ ላይ የተመሰረተ ከሆነ፤ ተስፋችን ይለመልማል፡፡ ሴረኛና ደባ-ሠራሽ አንሆንም!
ያንን ያሸተትን ዕለት ወደ ጥፋት ጎዳና ማምራታችን ነው፡፡ ስለ ሴራ ህንዳዊው ፈላስፋ ካውቲላ ይህንን ፅፏል፡-
  “በዓላሚ ቀስተኛ፤ የተሰደደ ቀስት
 ሁለት ዕድል አለው፤ መግደል ወይም መሳት፡፡
 ግን በስል ጭንቅላት፣ ሴራ ከተሳለ ህፃንም ይገላል፣
 እናት ሆድ ውስጥ ያለ!!”
ይሄ ግጥም ሴረኞችን የሚያጋልጥ ነው፡፡ በአግባቡ እንድንሰጋ ያደርገናል፡፡ አደገኛነቱን እያየን እንድንጠነቀቅ ያግዘናል፡፡ ዕቅዳችንን በወቅቱ እናብስል!! የሌሎችን አስተያየት እንቀበል፡፡ “ካፈርኩ አይመልሰኝ”ን እንተው! ግትርን እንዋጋ፡፡ አያሌ ጊዜ ስለ አንድነትና ስለ መከፋፈል ተናግረናል፡፡ የተቋም አንድነት፣ የቡድን ስብስብ አንድነት፣ የግምባር አንድነት፣ የፓርቲ አንድነት ወዘተ አስፈላጊነቱን አውስተናል። ሆኖም ተፈታታኝ ሁኔታዎች የተገነባውን ሲንዱት፣ የተደራጀውን ሲያፈርሱት፣ የተመቻቸውን ሲያውኩ አስተውለናል፡፡ መፍትሔ ተብለው የሚቀመጡትን መላዎችም ለመመርመር ሞክረናል፡፡ በአብዛኛው በእነ ሌኒን ዘመን እንደተነገረው ዓይነት “The party purges itself” (ፓርቲ ራሱን አፀዳ እንደማለት) ያለ መርህ ነው የሚቀርበው፡፡ ተቀናቃኞችን ማስወገድ ነው ዘዴው፡፡ የተወገዱ ወገኖች፣ ለአስወጋጆቹ ወገኖች በጭራሽ አይተኙላቸውም፡፡ ወድቀው መቃብር እስኪገቡ ጉድጓድ ሲምሱላቸው ይከርማሉ፡፡ ይህ ተደጋጋሚ ክብ-ሩጫ መቆሚያ የለው፡፡ አንዳንዴ ወደ ደም መፋሰስ ሊደርስም ይችላል፡፡ ያ እንግዲህ ክፉ ገፅታው መሆኑ ነው፡፡ ይህ ዕውነታ በሀገራችን በተደጋጋሚ ተከስቷል፡፡ አሰቃቂ ሂደት ነው፡፡ አገር ይሸረሽራል፣ የተማረውን ወገን ያኮሰምናል፣ ሞራል ያደቃል፡፡ ፈፅሞ ለአገር የሚጠቅም ሂደት አይደለም! የጠላት ወገን እንኳ አንጃ ከተፈጠረበት፣ አንድ የነበረው ጠላት ሁለት- ሦስት ሆኖ ቁጭ ይላል፡፡
የሁኔታውን ፅናንነት ያዩ የተገነዘቡ፣ ፀሐፍት፤ ቅራኔዎች የማይታረቅ ደረጃ ሳይደርሱ በፊት በተቻለ መፍትሔ መፍጠር ብልህነት ነው ይሉናል፡፡ ዋናው ቁም ነገር፤ “መከፋፈል እንኳን ለወዳጅ ለጠላትም አይበጅ” የሚለውን አባባል በውል ማጤን ነው! ወደ ውስጣችን እንመልከት፡፡ “ጠጣሩ እንዲላላ፣ የላላውን ወጥር” እንደተባለው ነው!

Read 4227 times