Sunday, 17 September 2017 00:00

በርካቶችን ለሞት የዳረገው የኦሮሚያ - ሶማሌ ግጭት እስከ ትናንት አለመቆሙን መንግስት አስታውቋል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(24 votes)

በኦሮሚያ እና በሱማሌ ክልሎች መካከል የተፈጠረው ግጭት እንደቀድሞ የወሰን ጉዳይ እንዳልሆነ የተጠቆመ ሲሆን፣ ትክክለኛ መንስኤው እየተጣራ መሆኑን ያስታወቁት የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ፤ ግጭቱ እስከ ትናንት አርብ ድረስ በተለያዩ ቀበሌዎች መቀጠሉንና በርካቶች ተገድለው፣ ከ20 ሺህ በላይ ዜጎች መፈናቀላቸውን አስታውቀዋል፡፡
ለበርካታ ቀናት በቀጠለ ግጭት፤ የሠው ሕይወት ጠፍቷል፣ ንብረት ወድሟል፣ ዜጎች ተፈናቅለዋል ያሉት ሚኒስትሩ፤ ግጭቱ በቅርቡ እንዲገታ ይደረጋል፤ የሃይማኖት አባቶች፣ የሃገር ሽማግሌዎችም በመሃል ገብተው የማረጋጋት ስራ ይሠራሉ ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለ ማርያም ደሣለኝ፤ ከሁለቱ ክልል አመራሮች ጋር በግጭቱ ላይ በስልክ ውይይት ማድረጋቸውንና ግጭቱ እንዲቆም ማሣሠቢያ መስጠታቸውንም ሚኒስትሩ አስታውቀዋል፡፡
በአካባቢው ለግጭቱ መባባስና ለሠው ህይወት መጥፋት ምክንያት የሆኑ ለህግ እንዲቀርቡ ይደረጋል ያሉት ሚኒስትሩ፤ የመሳሪያ ትጥቅ የማስፈታት ስራም ይሰራል ብለዋል፡፡
የመከላከያ ሰራዊትና የፌደራል ፖሊስ በግጭቱ መሃል ገብቶ ለማረጋጋት ለምን ዘገየ ተብለው የተጠየቁት ሚኒስትሩ፤ ክልሎቹ ችግሮቹን በራሳቸው ይፈቱታል የሚል እምነት በመጣሉ ነው ብለዋል፡፡
በግጭቱ የሶማሊያ ሪፐብሊክ ኃይሎችና የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል መሳተፋቸው ተጣርቶ ህጋዊ እርምጃ ይወስዳል ብለዋል - ሚኒስትሩ፡፡ ግጭቱ በታጠቁ አካላት የታገዘ መሆኑን የጠቆሙት ሚኒስትሩ፤ እነዚህ የታጠቁ አካላት እነማን ናቸው የሚለው ግን እስካሁን ምላሽ አለማግኘቱንና በማጣራት ሂደቱ እንደሚታወቅ ተናግረዋል፡፡ ግጭቱ የህዝብ ለህዝብ አለመሆኑን ግን አስረግጠው በመግለፅ፡፡  ከዚሁ ጋር በተያያዘ የሁለቱ ክልሎች የመንግስት ኮሚኒኬሽን ኃላፊዎች ጉዳዩን አስመልክቶ በየሚዲያው የሚያስተላልፏቸው መግለጫዎች፣ ግጭቱን ሊያባብሱ የሚችሉ በመሆኑ ከእንግዲህ በኋላ ግጭት አባባሽ መግለጫዎችን ከመስጠት እንዲቆጠቡ ዶ/ር ነገሪ አሳስበዋል፡፡
የኮሚኒኬሽን ኃላፊዎቹ ከዚህ ድርጊታቸው የማይቆጠቡ ከሆነ፣ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድም ሚኒስትሩ ጠቁመው፤ በሁለቱም የሚገለፁ አሃዛዊ መረጃዎችንም ገና ያልተጣሩ መሆናቸውንና መንግስት ሁኔታውን አጣርቶ እንደሚገልፅ አስታውቀዋል፡፡
የሶማሌ ክልል ግጭቱን አስመልክቶ ለቪኦኤ በሰጠው መግለጫ፤ በአወዳይ ከተማ 50 ሠዎች መገደላቸውን ሲገልፅ፣ የኦሮሚያ ክልል በበኩሉ፤ በአወዳይ ከተማ 18 ሰዎች መገደላቸውን፣ ከነዚህ ውስጥ 12ቱ የሶማሌ ተወላጆች፣ ቀሪዎቹ የኦሮሞ ጃርሶ ጎሣ አባላት መሆናቸውን አስታውቋል፡፡
የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ቃል አቀባይ አቶ አዲሱ አረጋ ትናንት ምሽት ባሰራጩት መረጃ፤በሰሞኑ ግጭት ከተፈናቀሉት ከ22ሺ በላይ ዜጎች በተጨማሪ አጠቃላይ የድንበር ግጭቱ ከተከሰተበት ከ2009 ጀምሮ 416ሺ807 ዜጎች መፈናቀላቸውን አስታውቀዋል፡፡
በአወዳይ የደረሠውን ግጭት ተከትሎ፣ ከሶማሌ ክልል ከ21 ሺህ በላይ ዜጎች ተፈናቅለው በጭናቅሠን፣ ባቢሌና ሐረር ከተሞች ተጠልለው እንደሚገኙ የኦሮሚያ ክልል ቃል አቀባይ አቶ አዲሱ አረጋንና ምንጮቹን ጠቅሶ ቪኦኤ ዘግቧል፡፡
የሱማሌ ክልል የመንግስት ኮሚኒኬሽን ሃላፊ አቶ ኢንድሪስ አህመድ በበኩላቸው፤ “ሰዎች ከአካባቢው የተፈናቀሉት በግዴታ ሳይሆን በፍቃዳቸው ነው፤ ጥቃት አልተፈፀመባቸውም” ብለዋል፡፡ ምንጮች በበኩላቸው፤ የግዳጅ ማፈናቀል መፈፀሙንና በዜጎች ላይ ድብደባና እንግልት እንደደረሰባቸው ለመገናኛ ብዙኃን ተናግረዋል፡፡
የሱማሌ ክልል መንግስት ኮሚኒኬሽን ሃላፊ አቶ ኢንድሪስ አህመድ፤ በአወዳይ ከተማ የደረሰውን ግድያ ተከትሎ ባስተላለፉት መግለጫ፣ የኦሮሚያ ክልል መንግስትን “የአሸባሪነት አላማ አራማጅ” በሚል የፈረጀ ሲሆን የኦሮሚያ ክልል ቃል አቀባይ በበኩላቸው፤ ፍረጃውን አጣጥለው፣ ከአንድ ክልልን ከሚያስተዳድር አካል የማይጠበቅ ነው ብለዋል፡፡
የሶማሌ ክልል መንግስት ኮሚኒኬሽን ሃላፊ ለቪኦኤ በሰጡት መረጃ፤ በአስራ አንድ የሶማሌ ወረዳዎች፣ ማንነታቸው ባልታወቀ አካላት በተሠነዘሩ ጥቃቶች፣ ከሁለት መቶ አስራ ሶስት ሰዎች በላይ ህይወት ማለፉን አስታውቀዋል፡፡ ይሄን ተከትሎም የሶማሌ ክልላዊ መንግስት፣ ለ5 ቀናት የሚቆይ ብሄራዊ የሃዘን ቀናት በክልሉ ማወጁንም ለማወቅ ተችሏል፡፡
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ፣የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የግጭቱን መነሻና የደረሰውን ጉዳት የሚያጣራ ቡድን ከትላንት በስቲያ ሐሙስ ወደ አካባቢው መላኩንና ማጣራት መጀመሩን የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ደምሰው በንቲ ለአዲስ አድማስ አስታውቀዋል፡፡
ሰሞኑን የሁለቱ ክልሎች የመንግስት ኮሙኒኬሽን ኃላፊዎች በማህበራዊ ድረ-ገፆቻቸው የሚያሰፍሯቸው የእርስ በርስ ውንጀላዎች አስደንጋጭና ግጭቱን የሚያባብሱ መሆናቸውን አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ፡፡ ክልላዊ መንግስታቸውን ወክለው መልዕክት የሚለዋወጡ እንደማይመስሉና ኃላፊነት የጎደሏቸው እንደሆነም ተገልጿል፡፡ ከሁለቱም የኮሙኒኬሽን ኃላፊዎች ማህበራዊ ድረ-ገፅ ላይ የተገኘውን አንድ አንድ ፅሁፍ ለመታዘብ ያህል አቅርበንላችኋል፡፡ እንደወረደ (ኤዲት ሳናደርግ)
(የኢትዮ-ሶማሌ ክልል መንግስት ኮሚኒኬሽን ቢሮ)
የኢትዮ-ሶማሌ ህዝብና መንግስት፣ የሀገራችን የፌደራል ስርዓታችንን በመጠበቅ፣ የስርዓቱ ዘብ በመሆን መቆየቱ የሚታወቅ ነው፡፡ የክልላችን ህዝብና መንግስት በብዝሀነት ላይ የተመሰረተውን ልዩነት በማክበር፣ በመቻቻልና በመፈቃቀር፣ ለዘመናት ከብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በጋራና በጥሩ ጉርብትና አምኖና ተግሮ የሚኖር ጨዋ ህዝብ ነው፡፡ ታዲያ ሰሞኑን ክልላችን ከኦሮሞ ክልል ጋር በሚዋሰንበት አካባቢዎች፣ በክልሉ መንግስት የሚደገፍና በክልሉ በታጠቁ ሀይሎች፣ በክልሉ ፖሊስ፣ ሚሊሺያና የአሸባሪው የኦነግ ቄሮ አባላት በተደጋጋሚ ጥቃት ሲፈጽሙና ወረራ ሲያካሂዱ የቆዩ ሲሆን በዚህም የክልሉ መንግስትና የአሸባሪው ኦነግ አንድ አቋም በመያዝ፣ በግልጽ ጆሀር መሀመድና የኦሮሞ ክልል ኮሚኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አዲሱ አረጋ፣ ተመሳሳይ አቋም ያሳዩበትና አዲሱ አረጋም በግልጽ የኦነግ አባልነቱን ያረጋገጠ ሆኖ ተገኝቷል፡፡
ታዲያ ይህ መንገድ አልሳካ ብሎ ሲቀር፣ ፊቱን በክልሉ ነዋሪ በሆኑ የሶማሌ ተወላጆች ላይ የዘረኝነት ጭፍጨፋን የጀመረ ሲሆን በተለይ በአወዳይ ከተማ በትላንትናው እለት ከ50 በላይ የሆኑ ንጹህን ዜጎች ላይ በአሰቃቂ ሁኔታ እስከዛሬ ድረስ በሀገራችን ታይቶ በማይታወቅ መልኩ አካላታቸውን በመቆራረጥና በእሳት በማቃጠል፣ ህይወት የቀጠፉ ሲሆን ከ300 በላይ የሚሆኑ ደግሞ በመከላከያ ሰራዊት ሀይል ህይወታቸውን በማትረፍ፣ ወደ ሀረር እንዲገቡ ተደርጓል፡፡ በዛሬው እለትም 30 የሚሆኑ የዜጎች የተቆራረጠና የተቃጠለ ሬሳ የመጣ ሲሆን በነገው እለት (ፅሁፉ የወጣው ረቡዕ እለት ነበር) በክብር ግብአተ ግብራቸው ይፈጸማል፡፡
በአሁኑ ሰዓት የክልሉ መንግስት፣ የተቆጣውን የክልሉን ህዝብ በማረጋጋት፣ በክልሉ የሚገኙ የኦሮሞ ተወላጆችን በማሰባሰብ፣ ጉዳት እንዳይደርስባቸው ከለላ በማድረግ፣ ምግብና መኝታን በመስጠት፣ ህዝባዊነቱን፣ ሰላም ወዳድነቱንና ወገን አክባሪነቱን ያሳየ ሲሆን በተቃራኒው የኦሮሞ መንግስትና የፀጥታ ሀይሉ፣ በኦሮሞ ክልል ላይ ከ200 ዓመታት በላይ የኖሩ፣ ከክልሉ ማህበረሰብ ጋር በደም የተዛመዱ፣ የሶማሌ ተወላጆች ላይ የወሰደው እርምጃ፣ የክልሉን ህዝብና መንግስት በእጅጉ ያስቆጣ ሲሆን ይህንንም በሀገራችን ህግና ደንብ መሰረት፣ ጉዳት አድራሾቹ ለህግ ተጠያቂ የሚሆኑበትን መንገድ የክልሉ መንግስት አጥብቆ ይሰራል፡፡
የተከበራችሁ የክልሉ ነዋሪዎች፡- የሀገራችንን ብሎም የክልላችንን ሰላም ለማስጠበቅና ፈጣኑ ልማታችንን ለማስቀጠል፣ የተለመደው የክልሉ ባህልና ሀይማኖታዊ ስርአት የሆነውን ሌሎችን ያለመጉዳት ባህላችንን በማስቀጠል፣ “እነሱ ተሳስተዋል” ብለን እኛም ተሳስተን በኦሮሞ ተወላጅ ላይ ምንም እርምጃ እንዳትወስዱ እናሳስባለን፡፡
በመጨረሻም ለእነዚህ እጅግ ዘግናኝ በሆነ መንገድ ህይወታቸውን ላጡ ዜጎች ነፍስ ይማር እያልን፣ ለቤተሰቦቻቸው ደግሞ መጽናናትን እንመኛለን፡፡
(የኦሮሚያ መንግሥት ኮሚኒኬሽን ኃላፊ የሰጡት ምላሽ)
ይድረስ ለሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት፣ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ
የሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ፤ በኦሮሚያ እና በኢትዮጵያ ሶማሌ አዋሳኝ አካባቢዎች ሰሞኑን ከተከሰተው ችግር ጋር አያይዞ በትናንትናው (ረቡዕ) ዕለት በአማርኛ ቋንቋ መግለጫ አውጥቷል፡፡ የወጣው መግለጫ እጅግ በጣም አሳፋሪና ኃላፊነት በጎደለው መልኩ የቀረበ ነው። መግለጫው አሁን ያለውን ችግር ከማርገብ ይልቅ ወደ ሌላ አቅጣጫ ሊወስድ የሚችልና ሀገርን ከሚያስተዳድር ትልቅ የመንግስት መስሪያ ቤት ይሰጣል ተብሎ የማይጠበቅ አሳፋሪ መግለጫ ነው፡፡ የወጣው መግለጫ የሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ የተጣለበትን ህዝባዊና መንግስታዊ ኃላፊነት ከመሸከም አንጻር ያለበትን ደካማ ቁመናና ዝቅተኛ ደረጃ ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ነው፡፡
ከመግለጫው ስህተቶች መካከል፣ የሶማሌ ክልላዊ መንግስትን፣ የፌደራል ስርዓቱ ብቸኛ ዘብ እና ጠባቂ አድርጎ የማቅረቡ ጉዳይ ነው፡፡ በእኛ እምነት፣ አሁን ላለው ህብረ ብሔራዊ ፌደራላዊ ስርዐት፤ ሁሉም የኢትየጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች እኩል መስዋዕትነት የከፈሉበት የትግላቸው ውጤት ነው። ስለሆነም አሁን እየገነባን ላለነው ህብረ ብሔራዊ ፌደራላዊ ስርዓት ዘቦች ሁሉም የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ናቸው፡፡ የመግለጫው ሀሳብ በተጨባጭ ተግባር የሚገለፅ ቢሆን ኖሮ ደግሞ እሰየው ነበር፡፡ አንድ የፌዴራሊዝም ዘብ ነኝ የሚል መንግስት፤ በምን ስሌት ልዩ ሃይል አደራጅቶ፣ ሰላማዊ ዜጎች ላይ ጥቃት ይፈጽማል? ሰሞኑን በተፈጠረ ግጭት እንኳ ስንት ሰላማዊ ዜጎች በኦሮሞነታቸው ብቻ ቀዬአቸውን ጥለው እንዲሰደዱ እየተደረገ አይደለምን? ከዚህ አንጻር የሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ፣ የክልሉን መንግስት የፌደራሊዝም ዘብ ነኝ ብሎ ራሱን ማቅረቡ ከተግባሩ ጋር የሚሄድ አይደለም፡፡
በሁለተኛ ደረጃ የቢሮው መግለጫ፤ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልልን “የኦሮሞ ክልል” ብሎ ከህገ መንግስቱ ውጪ መሰየሙ ነው፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ “የኦሮሞ ክልል” የሚባል ክልል የለም፡፡ መግለጫው ይህን አጻጻፍ የተከተለው፣ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልልን “የኦሮሞዎች ብቻ” እንደሆነችና ሌሎች የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችን የማታቅፍ እንዲሁም አግላይ አስመስሎ፤ ማቅረብ የሞከረበት አደገኛ ተልዕኮ ያለው አጻጻፍ ነው፡፡ በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት እምነት፣ የኦሮሚያ ክልል የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ናት፡፡ ለዚህ ደግሞ የክልሉ፣ ስያሜ “የኦሮሞ ክልል” የማይሆንበት ምክንያት ሁሉም የኢትዮጵያ ህዝቦች በወንድማማችነትና በአንድነት በፍቅር የሚኖሩባት ክልል እንደሆነች ምስክር መጥራት አያስፈልገንም፡፡
ሶስተኛው መሰረታዊ ስህተት፤ የክልሉን መንግስት በአሸባሪነትና በኦነግነት መፈረጁ ነው፡፡ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት አመራሮች፤ በኢትዮጵያ አንድነትና በህዝቦች ወንድማማችነት ላይ የማያወላውል ጽኑ አቋም እንዳለን፣ መላ የኢትዮጵያ ህዝብ ምስክራችን ነው፡፡ ኦሮሚያ እና የኦሮሞ ህዝብ የኢትዮጵያ አንድነት ምሰሶዎች ናቸው፡፡ የክልሉ አመራሮችም ለፌደራላዊ ስርዓታችን ማበብና መጎልበት፣ የህዝቦች ወንድማማችነትና እኩል ተጠቃሚነት እንዲሰፍን ለማድረግ እየታገሉ፣ መስዋዕትነት እየከፈሉ ያሉ ውድ የኢትዮጵያ ህዝብ ልጆች እንጂ በአሸባሪነትና በኦነግነት የሚፈረጁ አይደሉም፡፡ መግለጫው ከዚህ አንጻር ኃላፊነት በጎደለው አግባብ የተጻፈና ወንጀልም ጭምር በመሆኑ፣ ህገ መንግስቱን ተከትለን በህጋዊና አስተዳደራዊ መንገድ የምንጠይቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡ ከዚህ ባለፈ የኦሮሞ ተወላጆችን እና የክልሉን አመራሮች በኦነግነት ሌብል በማድረግ፣ ለማሸማቀቅ መሞከር ከበርካታ አመታት በፊት ሲደረግ የነበረ፣ አሁን ግን ጊዜው ያለፈበት ተራ ሌብሊንግ መሆኑን ለመግለጽ እንወዳለን፡፡
የመግለጫው ሌላኛው ይዘት ግጭትን የሚያባብሱ አደገኛ ቃላትና በተጋነኑ ውሸቶች መሞላቱ ነው፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ሰሞኑን በተከሰተው የጸጥታ መደፍረስ ክቡር የሰዎች ህይወት አልፏል፡፡ በዚህ ረገድ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት፤ ኦሮሞም ይሁን ማንም ሰው መሞት የለበት ብሎ ያምናል፡፡ በሰሞኑ ሁኔታ ከሁለቱም ወገን ህይወታቸው ላለፉት ዜጎች የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን ይገልጻል፡፡ ከዚህም በላይ በንጹሃን ዜች ላይ የህይወት ማጥፋትና አካል የማጉደል ወንጀል የፈጸሙ ሰዎች ለህግ መቅረብ አለባቸው ብሎ ያምናል፡፡ ከዚህ በተረፈ ሰሞኑን ስለነበረው እውነታ ሀቁን ለህዝባችን መግለጹ አስፈላጊ ነው፡፡ መስከረም 1 ቀን 2010 ዓ.ም ከጉርሱም ወደ ሀረር እየተጓዙ ያሉ ሰላማዊ የኦሮሞ ተወላጆችን የሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የጸጥታ አካላት፣ ቦምባስ ከተማ ኬላ ላይ ይዘው ያስራሉ፡፡ እነዚህ ታሳሪዎች፣ በነጋታው በደረሰባቸው ድደባ መሞታቸው ተሰማ፡፡ ይህ ሰላማዊ ሰዎች ላይ የተፈጸመው ግድያ፤ የምስራቅ ሀረርጌ ነዋሪዎችን በማስቆጣቱ በምስራቅ ሀረርጌ ዞን አወዳይ፣ ደደር፣ ቆቦ እና መልካ ራፉ ከተሞች ያልተጠበቀ የህዝብ ቁጣና ሰልፍ አስከተለ፡፡ በተለይ አወዳይ የነበረወ ሰልፍ ወደ ግርግር ተሸጋገረ። በተፈጠረው ግርግርም የ18 ሰዎች ህይወት ሊያልፍ ችሏል፡፡ በዚህ ግርግር ውስጥ ህይወታቸውን ካጡ 18 ሰዎች፣ 12 የሶማሌ ተወላጅ ወንድሞች ሲሆኑ 6ቱ ደግሞ የጃርሶ ጎሳ ተወላጅ ኦሮሞዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች ድንበር ላይ እየተፈጸመ ካለው ጥቃት ጋር ምንም ተያያዥነት የሌላቸው፣ በላባቸው ሰርተው የሚያድሩ ሰላማዊ ዜጎች ናቸው፡፡ በዚያ ግርግር የእነዚህ ወንድሞችን ህይወት ማለፍ በእጅጉ አሳዝኖናል፡፡ በድርጊቱ ተሳትፎ አላቸው ተብለው የተጠረጠሩ ከ200 ሰዎች በላይ ደግሞ በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው ነው። እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ፣ የሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ፤ ይህን ጉዳይ ግጭትን በሚያባብሱ ስሜታዊ ቃላትና ውሸትን ጨምሮ አጋኖ ማቅረብ፣ ግጭቱን ከማባባስ ያለፈ ምንም ጠቀሜታ አይኖረውም፡፡
ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ ስንገልጽ እንደነበረው፣ የኢትዮጵያ ሶማሌና የኦሮሞ ህዝቦች ወንድማማች ህዝቦች ናቸው፡፡ በጋብቻና በደም የተሳሰሩ፣ ተመሳሳይ የአኗኗር ዘይቤ፣ ተመሳሳይ ስነ ልቦና ያላቸው ህዝቦች ናቸው፡፡ አሁን እየተከሰተ ያለው የሰላም መደፍረስ፣ የሁለቱ ህዝቦች ፍላጎት እንዳልሆነ ግልጽ ሊሆን ይገባል። ከዚህ ግጭት ጀርባ ያሉ አካላት ተጣርተው፣ ወደ ህግ እንደሚቀርቡና የስራቸውን ዋጋ እንደሚያገኙ ምንም ጥርጥር የለንም፡፡
ኢትዮጵያ ሶማሌ እና የኦሮሞ ህዝቦች ወንድማማችነት ለዘለአለም ይኑር!
መስከረም 4 ቀን 2010
ፊንፊኔ ኦሮሚያ


Read 11650 times